ቤተ ክርስቲያንን ጠብቋት
ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም.
አባ ዘሚካኤል
ቅድሚያ ለቤተ ክርስቲያን እንቁም! ምን እንደምትልም እንጠብቃት (እንስማት)!
“ወይእዜኒ ዕቀቡ ርእሰክሙ ዘሎቱ ሤመክሙ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳተ ከመ ትርአዩ ቤተ ክርስቲያኑ ለክርስቶስ እንተ አጥረያ በደሙ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” (የሐዋ.20፥28)፡፡
ፓትርያርክ ለመሾም:-
- ሁሉም ድርሻው እስከምን እንደሆነ ይወቅ!
- የሲመቱ ሂደት ምንም ይሁን ምን የተዋሕዶ ምእመናንን ሊከፋፍል በሚችል መንገድ ለሚሠሩ በር አንክፈት!
- አንድነታችን የበለጠ እንዲጸና እንጸልይ!
ወይእዜኒ ዕቀቡ ርእሰክሙ፡ ’አሁንም ራሳችሁን ጠብቁ’ የግእዙ ትርጓሜ ሲል’፣ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ’ለራሳችሁ ተጠንቀቁ’ ይላል፡፡
ቅዱስ ሉቃስ እንደጻፈው፣ የቅዱስ ጳውሎስን የማስጠንቀቂያ ምክር በጊዜው የመንጋው ጠባቂ ለሆኑት አባቶች መጀመሪያ “ራሳችሁን ጠብቁ’ ነው ያላቸው፡፡ በመሆኑም ይህን የቅዱስ ጳውሎስ ምክር የተረዱ አባቶቻችን ከሁሉ በፊት ራሳቸውን በመልካም መንገድ ማቆምን ቅድሚያ ሰጥተዋል፡፡ በመሆኑም ራሳቸውን ከእምነት ለመለየት ከሚፈታተኗቸው:-በሥጋዊ ድካም ከሚመጡ ይሁን በሌሎች ውጫዊ ምክንያቶች ከሚነሡ እኩያት አሳቦችና ተግባራት ራሳቸውን ጠብቀው ይኖራሉ። ከሌላ ስለሚመጣው ፈተና ምክንያት ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል ”ወአነ አአምር ከመ ይመጽኡ እምድህሬየ ተኩላት መሰጥ እለ ኢይምህክዋ ለመርዔት፤ ከኔ በኋላ ለምእመናን የማያዝኑ ሰውን እየነጣጠቁ ወደ ገሃነም የሚያወርዱ ሐሰተኞች መምህራን እንዲነሡ አውቃለሁ” (ማቴ፣ 7: 15) ይላል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ዋናው ነገር ሐሰተኛ መምህራን ሊያሳስቱ የሚሞክሩት ምእመናንን ብቻ አይደለም ታላላቆችንም ነው እንጂ፤ ከዚህ በፊት ከታየው ልምድ ለቤተ ክርስቲያን የጠቀሙ በመምሰል አባቶችን ወደ አላሰቡት ስህተት የሚጥሉ አሉ፣ ሰይጣን እንኳን ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ሊፈታተን ቀርቦ የለምን? ከላይ በተመሳሳይ ”ከኔ በኋላ ለምእመናን የማያዝኑ ሰውን እየነጣጠቁ ወደ ገሃነም የሚያወርዱ ሐሰተኞች መምህራን እንዲነሡ አውቃለሁ” ተብሏልና፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳ ነገር ለምሳሌ፣ መከፋፈል እንዲፈጠር ሊያደርግ የሚችል ምክንያት እንዳይገኝ በየግል መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ቀጥሎም ጳጳሳትን በቡድን ማለትም ሲኖዶሱን ’ራሳችሁን ጠብቁ’ ማለት በመካከል የሚፈጠር አለመግባባት እና ሌላም ምክንያት እንዳይለያያችሁ ቀድማችሁ ጥንቃቄ አድርጉ ሲል ነው፡፡ በመከፋፈል ለሰይጣንና ለሠራዊቱ የተከፈተ በር፣ ከተከፈተ በኋላ እንኳን መልሶ ለመዝጋት ይቅርና የበሩን መዝጊያውን ለማግኘት የሚቸግር ይሆናል፡፡ ካለፈው የመከፋፈል ልምድ እንደ ተረዳነው፣ በሁለት መከፈል ሳይበቃ መዘዙ ወደ ብዙ ትንሽ ክፍፍል ጭምር ማምራቱን መዳኘትና መግታት ወደ ማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ ይህ ሁኔታ ወደፊት ምን ሊሆን እንደሚችል አምላክ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በጸሎት እንጠይቀው፡፡
“ወኵሎ መራዕየ፣ ምእመናንን ሁሉ ጠብቁ፡፡ ዘሎቱ ሤመክሙ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳተ፣ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳት አድርጎ የሾማችሁ እናንት ዕቀቡ ጠብቁ” ብሎአል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሹመት ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ማንም ሰው ደግም ይሥራ ክፉ፣ የሚሾመው ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡” ከመ ትርአዩ ቤተ ክርስቲያኑ ለክርስቶስ እንተ አጥረያ በደሙ፣ በወርቀ ደሙ የዋጃትን የምእመናንን አንድነት ትጠብቋት ዘንድ የሾማችሁ፡፡” አባቶች የሚጠብቁት የእግዚአብሔር መንጋ የሆኑትን ምእመናንን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ስንል የምእመናን አንድነት በመሆኑ፣ ከአባቶች ጠብቆት ውስጥ ምእመናንን ከመከፋፈል፣ ከኑፋቄ፣ ወዘተ በሽታ መከላከል ዋናው ተግባር ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ምእመናን በሀገር ውስጥ ሲኖዶስ፣ በውጭ እና ከዚህም ከዚያም የሌለ በሚል ተከፋፍለን በመለያየት ተውጠን ከርመናል፡፡ እግዚአብሔር ሲኖዶሱን” ወኵሎ መራዕየ፣ ምእመናን ሁሉ ጠብቁ” በማለቱ ሁሉም ምእመናን ከመሰናከል የሚድኑበት፣ ከፋፋዮች ምክንያት የሚያጡበት፣ መናፍቃን የሚያፍሩበት፣ አንድነትን የሚያመጣ ቁርጥ ውሳኔ የሚሻበት ወቅት ነውና መንጋው በመከፋፈል ከመጥፋት አባቶች እንዲታደጉት ጊዜው ግድ ይላል፡፡
የመንጋው ጠባቂዎች የተባሉት ቅዱስ ሲኖዶስ በዋናነት ሲሆን ከሊቃነ ጳጳሳት ቀጥሎ በቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች በተዋረድም ሀገረ ስብከት፣ ወረዳ ቤተ ክህነትና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉትን ሲሆን፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር መንጋ የተባሉት መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ምእመናንን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ ከነዚህም ዋና ውሳኔ ሰጭው የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ የፓትርያርኩ፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት መሪው መንፈስ ቅዱስ የሆነ ዐቢይ ጉባኤና የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት ነው፡፡ በማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወሰነው ውሳኔ የመጨረሻ ውሳኔ ይሆናል፡፡ ፓትርያርኩ ተጠሪነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ሊለውጡ አይችሉም፡፡ፓትርያርኩንም መርጦ የሚሾመው ይኸው ጉባኤ ነውና፡፡ ሁሉም ክርስቲያን በእኩል መረዳት ያለበት የሲኖዶስ አባላት ሲመረጡ እንደ ሕግ እግዚአብሔር መሆኑንና እግዚአብሔር ሳይፈቅድ ጳጳስ መሆን እንደማይቻል ነው፡፡ ሁለተኛም የተሰጣቸው ሓላፊነት ከእግዚአብሔር እንደመሆኑና የዘወትርም ሥራቸው በመሆኑ፣ ሁልጊዜም መንጋውን በመጠበቅ ለቤተ ክርስቲያን ስጋት የሆነውን ጉዳዮች በመለየት ጥንቃቄ ያደርጋሉ ብለን ማመን ይኖርብናል፡፡
እኛ ምእመናንም ደግሞ ማሰብ ያለብን አይነተኛ ነገር አለ፣ ይህም ለመንጋው ጠባቂዎች በትክክል ታዛዣቸው ነን? በጎቻቸው ነን ወይ? ብለን እራሳችንን መመርመር አለብን፡፡ ለንባብ የበቃ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንኳን እንደሚታየው ትኩረት ሳይሰጠው ከመታለፉ አልፎ እንደውም ማጣጣል ሲደረግበት ነው የሚስተዋለው፡፡ በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ አባቶቻችንን እንድንጠራጠር የሚያደርጉንን ወሬዎችን በመስማት ወሳኞቹ እኛ ሳንሆን አስቀድመን መሆን አለበት ብለን ወስነን ቅዱስ ሲኖዶስ ከሚወስነው ጋር እንዳንጋጭ ከወዲሁ፣
-
ከማን መስማት እንዲገባን መመርመር የለብንም ይሆን?
-
አስቀድመን ለመወሰንስ እኛ ማን ነን?
-
የቅዱስ ሲኖዶስ ከሳሽ መሆን ይጠቅመን ይሆን?
-
የቅዱስ ሲኖዶስ መሪ መንፈስ ቅዱስ ነው ካልን መንፈስ ቅዱስ አይጠብቃቸውምን?
-
ቤተ ክርስቲያን የሾመቻቸው ሊቃውንት ከሃምሳ በላይ ሊቃነ ጳጳሳት አንድ ላይ ሆነው መክረው የሚወስኑት ውሳኔ ሳንቀበል በአንድ ሚዲያ ላይ አሰማምሮ ወይም አጣጥሎ በተጻፈ ጽሑፍ የምንረበሽ እና የምንፈተን ከሆን ስህተቱ የማን ይሆን?
-
መረጃዎችን ማወቅ ጥሩ ሲሆን፣ ነገር ግን ከእምነት አንጻር የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ የማጣጣል ሁኔታ የመልካም ይሆን?
የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ማንሣትና ቀድሞ ሰው ካለው ልምድ እንዲሁም ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጻር መጪውን ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ጋር መቆም እንዴት ይኖርብን ይሆን? ብለን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም እስከ አሁን ከተለያዩ ጽሑፎች እንዳነበብነው፣ ከተለያዩ አስተያቶች እንደ ሰማነው፣ በጣም የሚገርመው መቼም፣ ምንም ሊጣጣሙ የማይችሉ አሳቦች ከተለያዩ ጽንፈኞች ሲቀርቡ ተስተውለዋል፡፡ ለምሳሌ፣ ባንድ ወገን መጀመሪያ እርቁ ይቅደም በሚል በሚገባ መረጃ አሳማኝ ነገር ሲቀርብልን በሌላ ወገን የእርቁ አካላት የተባሉ ጨርሶ የእርቅ አሳብ እንዳልተነሣ ሁሉ እንደገና ለእርቁ መፈጸም እንቅፋት ይሆናል ተብሎ የሚገመት ሁኔታ አደረጉ ወይም ለአዲስ መለያየት መንገድ ይከፍታል የሚያሰኝ መረጃ ተቀናብሮ የቀረበ ስናይ እንዴት ይሆን ይህ አሳብ የሚታረቀው? መቼ ይሆን እርቁ የሚፈጸመው? የሚል ጥያቄ እንድናነሣ ሁላችንንም ግድ አይለን ይሆን? በዚህ የተዘበራረቀ ሁኔታ አባቶችስ የምርጫውን ጉዳዩ እስከ መቼ ሊያቆዩት ይችሉ ይሆን? በዚህ ሁኔታ ላይ ባለድርሻ አካላት ሳያምኑበትና በወቅቱ ለቤተ ክርስቲያን ይጠቅማታል ብለው ባልወሰኑት የኛ ማጉረምረም ምን ጽድቅ ይፈጽም ይሆን? ሁል ጊዜም ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳት አባላቶቿ ከአባቶች መንፈሳዊ እልባትና ከቅዱሳት መንፈሳውያን መጻሕፍት ምክር ይልቅ በዓለማውያን ፍልስፍና ስንደገፍ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ”እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም። ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም። እንዲያስተምረው የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው? እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን” (1 ቆሮ 2: 13-16) ይለናል።
ሌላው ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ይጠቅማል ያሉትን ከምርጫው ጋር የተያያዙ የተለያዩ አሳቦች ሲያቀርቡ ተስተውለዋል፡፡ ግብአቱ መልካም ነው፣ በተለይ ሚዲያዎችን የሚከታተሉ ምእመናን፣ የሚጻፉ አሳቦችን ሁሉ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በላይ በማድረግ የማየቱን ጉዳይ ነው፡፡ መረዳት ያለብን ፍሬ አሳብ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሚዲያ እንደተጻፈ ሊያውቁም ላያውቁም ይችላሉ፣ በግድም የማወቅ ግዴታ የለባቸውም፡፡ ብፁዓን አበው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሥራቸውን መሥራት አለባቸው እንጂ ተቀባይነትን ለማግኘት ሁል ጊዜ ወደ ሚዲያ መቅረብ አለባቸው አንልም፡፡ በየሚዲያዎች ሁሉም እንደፈቃዱ የጻፈውን ሁሉ ለማስፈጸም ደፋ ቀና ማለት አለባቸውም ልንል አይገባም፡፡ ከማንም ይልቅ በቤተ ክርስቲያን ሕግና ጊዜውን በዋጀ ውሳኔ ቤተ ክርስቲያንን መምራት ስላለባቸው ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ፡፡ በአባቶች ውሳኔ ማንም ጣልቃ መግባት የለበትም፡፡ የሚወሰነውን ሁሉ በእውነት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በአግባቡ መቀበል ይኖርብናል፡፡ ሁሉም እንዲህ ቢያረግ ማለትም ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ቢገዛ ቤተ ክርስቲያን አንድነትዋ ይጠበቃል፣ መለያየት አይኖርም፣ አንድነታችን ይጸናል፣ ከፋፋይ ያፍራል፣ ይልቁንም ሰይጣን ይመታል፣ በመስቀሉ እውነተኛ ፍቅር ይቀጠቀጣል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የሚለየንን ሰይጣን ይቀጥቅጥልን!!!
በመሆኑም ቅዱስ ሉቃስ” ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሯቸው (የሐዋ. ሥራ.4፥32)” እንዲል፤ በአንድ ሲኖዶስ ውሳኔ ማዘዝና መታዘዝ ስንተዳደር ነው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚከበረው፡፡ ይህ ሲሆን ነው ፍቅርና አንድነት የሚመጣው እንጂ በየቦታው ለራሳችን እንደ ራሳችን አሳብ መምህር ካቆምን እንናገራለን እንጂ በሕይወታችን ዘመን እርቅና አንድነትን ሳናያት ልናልፍ እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር በሕይወታችን ዘመን የቤተ ክርስቲያንን አንድነቷን ያሳየን!!! ሳናይ አይውሰደን ብለን መመኘትና መጸለይ ይገባናል፡፡
ባጠቃላይም የአሁኑ ወቅታዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ፣ የፓትርያርክ ምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም እንደሚለው፣ በዓለም ያሉ የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ሁሉ በጉዳዩ ያገባቸዋል፤ (ይህንን ስንል ተመሳስለው የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች በመምሰል የኑፋቄና የጸብ መንገድ ሁል ጊዜ የሚምሱትን ሳይጨምር መሆኑን መገንዘብ ያሻል)፡፡ ነገር ግን በፓትርያርክ ምርጫ እያንዳንዱ ሰው ድርሻው እስከምንድነው? የዚህ ጥያቄ ምክንያት፣ ምእመናን በተለይ በውጭ አገር ያሉ የተለያየ ሚድያ ስለሚከታተሉ፤ ሚዲያዎቹ በአንድ በኩል የቤተ ክርስቲያኗን ጥቅም የሚፈልጉ ሲሆኑ፣ ሌሎቹ የፖለቲካ፣ የተሐድሶ ወዘተ ዓላማና ጥቅም ያላቸው ከወዲሁ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት የራሳቸውን ግምት በመስጠት ምእመናንን የሚያንጽ ወይም የሚረብሽ አሳብ ስለሚበትኑ፤ ከዚህ የተነሣ አንዳንድ ግለሰቦች በራሳቸው ፓትርያርክ የመረጡ ያህል እከሌ ይሁን እስከ ማለት የደረሱ አሉ፡፡ በመሆኑም ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አንጻር የፓትርያርክ ምርጫ ሥርዓትን በመረዳት:-
- ሁሉም ድርሻው እስከምን እንደሆነ ይወቅ!
- የሲመቱ ሂደት ምንም ይሁን ምን የተዋሕዶ ምእመናንን ሊከፋፍል በሚችል መንገድ ለሚሠሩ በር አንክፈት!
- አንድነታችን የበለጠ እንዲጸና እንጸልይ!
- በተለያየ ቤተ ክርስቲያንን በማይወክሉ ሚዲያዎች የሚቀርቡ ነገሮች ሁሉ እንደ ቤተ ክርስቲያን ውሳኔ ሊታዩ አይችሉምና በጥንቃቄ መረጃዎችን እንይ
- ምእመናንን ሊከፋፍል የሚችሉ ወሬዎች እየተለቀቁ ስለሆነ በጥንቃቄ እንከታተል
- ሚዲያዎችም ጥንቃቄ ቢያደርጉ በጎ ሚያሰኝ ነው፣ ምእመናንን በመከፋፈል የሚገኝ ጽድቅ የለምና፡፡
- እግዚአብሔር ከፈቀደው በቀር ማንም ሊመረጥ አይችልምና ከወዲሁ ተረብሸን የወደፊቱ ክርስትናችን ፍቅር የጎደለው እንዳይሆን እንጠንቀቅ
- ሊመርጡ /ሊወስኑ/ ለሚችሉ ባላደራዎች ፈንታውን እንስጥ እንጂ በማንወስነው ጉዳይ አስቀድመን አንፈርጅ
- ይልቁንም ሁሉን ማድረግ ለሚቻለው እግዚአብሔር አደራ እንስጥ፡፡
በዚህ በቃ ይበለን! ከዚህ በላይ በመከፋፈልና በመለያት እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት አያሳየን!!!
ወስብሐት ለእግዚአበሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመሰቀሉ ክቡር አሜን!!!