በጅማ ሀገረ ስብከት በምእመናን ላይ በደረሰው ጉዳት ማኅበረ ቅዱሳን አዝኗል

ሰኔ ፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዝግጅት ክፍሉ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በጅማ ሀገረ ስብከት የም ልዩ ወረዳ ቁንቢ ቀበሌ ሰኔ ፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በምእመናን ላይ በደረሰው ጉዳት በእጅጉ ማዘኑን ገለጸ፡፡

አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ‹‹ስለ ኹኔታው የሚደረገው የማጣራት ሥራ እንደ ተጠበቀ እና ወደፊት የሚገለጽ ኾኖ፣ አጥቂዎቹ በወገኖቻችን ላይ ያደረሱት ጉዳት በእጅጉ የሚያሳዝን፤ ሊወገዝ የሚገባው ድርጊትም ነው፡፡ ይህንን ድርጊት የፈጸሙት ሰዎች አካሔዳቸው በየትኛውም የእምነት መሥፈርት፣ ይልቁንም በክርስትና አስተምህሮ ከመንፈሳዊ እምነትና ዓላማው ውጪ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዋና ጸሐፊው አያይዘውም ‹‹ክርስትና የመስቀል ጉዞ እንደ መኾኑ ብዙ ፈተና አለው፡፡ እምነታችን እስከ ዛሬ ድረስ የቆየውም በደማቸው ሰማዕት ኾነው ባለፉ አበውና እማት ተጋድሎ ነው፡፡ በመኾኑም ምእመናን ይህንን ተረድተው በጉዳዩ መደናገጥ የለባቸውም፡፡ ማኅበራችንም በተደጋጋሚ ጉዳት እየደረሰበት ያለውን የጅማ ሀገረ ስብከት ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ጋር በመተባበር እና መመሪያቸውንም በመቀበል በተቻለው ኹሉ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ወደፊትም ድጋፉን ይቀጥላል›› ብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ፣ የኢሉባቡርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ በምእመናን ላይ በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን ገልጸው፣ ከሀገረ ስብከቱ፣ ከእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት፣ ከፌዴራልና ከክልሉ መንግሥት በተመረጡ አባላት የተዋቀረ ኰሚቴ ጉዳዩን እያጣራ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ የኰሚቴውን የምርመራ ውጤትም በሀገረ ስብከታቸው በኩል ለሕዝበ ክርስቲያኑና ለዝግጅት ክፍላችን ይፋ እንደሚያደርጉ ብፁዕነታቸው አስታውቀዋል፡፡

በአጥቂዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት እኅትማማች ምእመናት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሕክምና ርዳታ እየተደረገላቸው ሲኾን፣ በትናንትናው ዕለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመኾን በሆስፒታሉ ተገኝተው ጉዳት የደረሰባቸውን ምእመናትና ቤተሰቦቻቸውን ማጽናናታቸው ይታወሳል፡፡