በእንተ ዕለተ ስቅለት
በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል
ሚያዚያ ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
ጨረቃ ደም ሆነች፤ ፀሐይም ጨለመ
ከዋክብት ረገፉ፤ ሐኪሙ ታመመ
ልዑል ተዋረደ፤ ጌታ ሎሌ ሆነ
ፈጣሪ ሠራው ፍጡሩ በየነ
ያችን ብላቴና እንደምን ላጽናናት?
አንድ ልጇን አጥታ ዛሬ ኀዘን ላይ ናት
እንደምን ላባብላት እንዴት ትረጋጋ
ችንካር የልጇን እጅ ኀዘን ልቧን ወጋ
ይምጡ እስኪ ጥሯቸው በሰማያት ያሉ
ሚካኤል ገብርኤል መላእክት በሙሉ
አንዲት እህታቸው አንድ ልጇን አጥታ
ታለቅሳለችና ከእግሩ ሥር ተደፍታ
በኢያሪኮ መንገድ ጽድቅን ያረቀቀ
ዛሬ በግፈኞች እጅ ላይ ወደቀ
፳፭ ጊዜ ዱላ አረፈበት፤ አፍንጫው ነሰረ
የዓለሙ መዓዛ፣ የደስታችን ዕጣን፣ ሽታው ደም ነበረ
ያችን ብላቴና፤ እንደምን ላጽናናት?
አንድ ልጇን አጥታ ዛሬ ኀዘን ላይ ናት
በጎች ሆነን ሳለ እርሱ ግን እረኛ
ተክቶን ሊታረድ በግ ሊሆን ስለኛ
፵ ጊዜ ጡጫ ቢመታም ሳይናገር ባ’ፉ
ጨክነው ፍጡራን ፈጣሪ ላይ ተፉ
፳፪ ጊዜ በጅንፎ ደረቱን
፳፪ ጊዜ በአለንጋ ልቡን
ክቡራን እጆቹ ንዑዳን እግሮቹ ፷፭ ጊዜ
ተመቱ ተላጡ ሆኑ እንደ አዋዜ
በካህናት አለቃ ታስሮ ተወሰደ ከሐና ቀያፋ
ከአፉ ምራቅ አልቆ ሲወድቅ ደም ተፋ
ግርፋቱን አይተው እንዳያሳዝናቸው ልባቸው እንዳይራራ
አንዱ እየገረፈ ሌሎች በገበጣ ሲረሱ ቆጠራ
ያለ ልማዳቸው ብዙ ተገረፈ
አንዱ ተገራፊ ለሺህ ገራፊዎች በቃቸው ተረፈ
ያችን ብላቴና እንደምን ላጽናናት?
አንድ ልጇን አጥታ ዛሬ ኀዘን ላይ ናት
ልቡን በአዴራ በታላላቅ ችንካር
ደረቱን በሮዳስ ቀኝ እጁን በሳዶር
እግሮቹን በዳናት ግራ እጁን በአላዶር
ሆኖ ባየች ጊዜ ልጇ ተሰቅሎባት
ያችን ብላቴና ምን ብዬ ላጽናናት?
አንድ ልጇን አጥታ ድንግል ኀዘን ላይ ናት
ብርሃንን የፈጠረ ዓይኖቹን ሸፈኑ
ያንን ርኅሩኁን ፊት ሊመቱ ጨከኑ
እንደ ተቸገረ የሚያዝንለት እንዳጣ
እንደ ተናቀ በሁሉም እንደ ሚቀጣ
እንደ ምስኪን ድሀ ቀን እንደ ራቀው ሰው
ምድርን ያስጌጣት አጣሳ ይለብሰው?
ንገረኝ ጌታዬ በእጅህ ከፈጠርከው
ማንን ልብስ ነሳህ፣ ማንን አራቆትከው?
ይህን ጊዜ እናቱን ምን ብዬ ላጽናናት?
የደስታ ምንጭ ሆና ኀዘንተኛ እኮ ናት፡፡
እንደ ቀማ ወንበዴ ዱር እንዳለ ሽፍታ
ሀገር እንዳጠፋ ተሰቀለ ጌታ
እንደ ትንቢቱ ቃል እንደ ተነገረ
ረዳት እንደ ሌለው ሆነ ተቸገረ
ባየነውም ጊዜ አላከበርነውም
እንወደውም ዘንድ ደም ግባት የለውም
እኛ ስንመታው እርሱ ታገሠልን
እኛው ስናደማው ደምን ለበሰልን
ልብን የሚጠግን ልቡ ላይ ወጋነው
በችንካር ቸንክረን፤ በዋንጫ ቀዳነው
አቤቱ አምላኬ ታማኙ መድኅኔ
እሺ ብለህ የሞትክ ለሰቀልኩህ እኔ
ስለ ኃይል ትርጉም፤ በብርታት ስጠብቅ
አንተ በትሕትና መጣህ ልታሳውቅ
ስሕተት በሞላበት የኃይል ግንዛቤ
ትዕቢት በገነባው እንዳይገኝ ልቤ
አቤት የአንተ ፍቅር፣ አቤት የአንተ ነገር
በዚያች ጭንቅ ሰዓት ስለ ሠቃዮችህ መዳን ታስብ ነበር
ያ ስደት የኔ ነው፤ የኔ ነው ሰንበሩ
ጩኽትህም ጩኽቴ፣ የኔ ነው ችንካሩ
በደሌን ቻልክልኝ፤ ሆነህ በኔ ቦታ
ሞትህ ሞቴ ነበር መድኃኒቴ ጌታ
ልኖር ተወልጄ ሞት ስላሸነፈኝ፣ ልጄ በርታ እያልከኝ
አንተ ልትሞት መጥተህ ማሸነፊያ ሆንከኝ
ግን!
ያችን የኀዘን እናት
ያችን ብላቴና ምን ብዬ ላጽናናት
ድንግል ስለ ልጇ ዛሬ ኀዘን ላይ ናት፡፡