በአተ ክረምት

ሰኔ ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በዛሬው ዝግጅታችን ስለ ዘመነ ክረምት መግባት፣ ሰኔ ፳፮ ቀን (በዕለተ ሰንበት) ስለሚነበቡ ምንባባትና ስለሚዘመረው መዝሙር የሚያስረዳ አጭር ጽሑፍ እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀርበናል፤

*ክረምት* ከረመ፣ ከረመ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም የዝናም፣ የአዝርዕት፣ የአረም ጊዜ፤ እንደዚሁም ዕፅዋት፣ አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር በአረንጓዴ ዕፀዋትና በልምላሜ የምታሸበርቅበት ወቅት ማለት ነው፡፡ በአተ ክረምት ስንልም የክረምት መግቢያ ማለታችን ነው፡፡ ይኸውም ከዚህ በኋላ ዘመነ ክረምት መጀመሩን ያመለክታል፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ከሰኔ ፳፭ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ ዘመነ ክረምት ይባላል፡፡ ዘመነ ክረምት ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት፤ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን (ምግብን) ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይና የሚያሳውቅ ዘመን ነው፡፡

በዚህ ወቅት የውኃ ባሕርይ ይሰለጥናል፤ በመኾኑም ውኃ አፈርን ያጥባል፤ እሳትን ያጠፋል፡፡ ኾኖም ግን በብሩህነቱ ከእሳት፤ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፤ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ከሦስቱ ባሕርያት ጋር ይኖራል፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ወቅት በዕለተ ሰንበት (ሰኔ ፳፮ ቀን) የሚከተለው የቅዱስ ያሬድ መዝሙር ይዘመራል፤

ደምፀ እገሪሁ ለዝናም

ሶበ ይዘንም ዝናም ይጸግቡ ርኁባን

ደምፀ እገሪሁ ለዝናም

ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌሥሑ ነዳያን

ደምፀ እገሪሁ ለዝናም

ወሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ

ደምፀ እገሪሁ ለዝናም

ደምፀ እገሪሁ ለዝናም

ይህ መዝሙር ወቅቱ የክረምት መግቢያ መኾኑንና የዝናምን መምጣት የሚያበሥር ሲኾን፣ በተጨማሪም ዝናም በሚዘንብበት ጊዜ የሚበቅለውን እህልና የምንጮችን መብዛት ተስፋ በማድረግ የተራቡ እንደሚጠግቡ፤ የተጠሙም እንደሚረኩ የሚያትት ምሥጢር ይዟል፡፡ እንደዚሁም ጊዜ ለበጋ፣ ጊዜ ለክረምት የሚሰጥ አምላክ ለሰው ልጅ ማረፊያ ትኾን ዘንድ ዕለተ ሰንበትን መፍጠሩንም ያስረዳል፡፡

በዚህ ሳምንት በዕለተ ሰንበት በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ምንባባትም የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው፤

፩ኛ ቆሮንቶስ ፲፭፥፴፫-፶፩

ፍሬ ዐሳቡ፡- አዝርዕት በስብሰው እንደሚበቅሉ ኹሉ የሰው ልጅም ከሞተ በኋላ ከሞት እንደሚነሣ፤ ሲነሣም እግዚአብሔር እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን እንደሚከፍለው፤ እንደዚሁም የሰው ልጅ ሞቱንና የሚያገኘውን ሰማያዊ ዋጋ በማሰብ ከኀጢአት መለየት እንደሚገባው ያስረዳል፡፡

ያዕቆብ ፭፥፲፮-ፍጻሜ

ፍሬ ዐሳቡ፡- ነቢዩ ኤልያስ በጸሎት ዝናም እንዳይዘንምና እንደገና እንዲጥል ማድረጉን በመተረክ እኛም እምነቱ ካለን በጸሎት ኹሉን ማድረግ እንደሚቻለን ይናገራል፡፡

ግብረ ሐዋርያት ፳፯፥፲፩-፳፩

ፍሬ ዐሳቡ፡- ቅዱስ ጳውሎስና ተከታዮቹ መርከባቸው በማዕበል ክፉኛ መናወጧንና በእግዚአብሔር ኃይል መዳናቸውን፤ በባሕሩ ውስጥም በጨለማ ለብዙ ጊዜ መቆየታቸውን በማውሳት ይህ ወቅት (ዘመነ ክረምት) የውኃና የነፋስ ኃይል የሚያልበት ጊዜ መኾኑን ያስተምራል፡፡

ምስባክ፡- መዝሙር ፻፵፮፥፰

ኃይለ ቃሉ፡- *ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር ዘያበቍል ሣዕረ ውስተ አድባር*

ፍሬ ዐሳቡ፡- እግዚአብሔር ሰማዩን በደመና የሚሸፍን፤ ዝናምንም (ክረምትን) ለምድር (ለሰው ልጅ) የሚያዘጋጅ፤ እንደዚሁም በተራሮች ላይ ሣርን (ዕፀዋትን) የሚያበቅል አምላክ መኾኑን ያስገነዝባል፡፡

ወንጌል፡- ሉቃስ ፰፥፩-፳፪

ፍሬ ዐሳቡ፡- ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃለ እግዚአብሔርን በዘርዕ፣ የምእመናንን ልቡና (የመረዳት ዓቅም) ደግሞ በመንገድ፣ በዓለት፣ በእሾኽና በመልካም መሬት በመመሰል ቃሉን ሰምተው በሚለወጡትና በሚጠፉት መካከል ስላለው ልዩነት ማስተማሩን ያስረዳል፡፡

ቅዳሴው፡- ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ ሲኾን ይህ ቅዳሴ ስለ ዝናም፣ ደመና፣ መብረቅ፣ ባሕርና መሰል ፍጥረታት ዑደት፤ እንደዚሁም እግዚአብሔር ዓለማትን በጥበቡ ፈጥሮ የሚገዛና የሚመግብ አምላክ መኾኑን ስለሚያብራራ በዘመነ ክረምት ይቀደሳል፡፡

በአጭሩ ሰኔ ፳፮ ቀን በሚከበረው ዕለተ ሰንበት በቤተ ክርስቲያን ከአዝርዕት፣ ከዝናም፣ ከልምላሜ፣ ከውኃ ሙላትና ከባሕር ሞገድ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ትምህርቶች ከሰው ልጅ ሕይወትና ከምግባሩ እንደዚሁም በምድር ከሚያጋጥሙት ፈተናዎች ጋር እየተነጻጸሩ ይቀርባሉ፡፡

በአጠቃላይ ከሕይወታችን ጋር አያይዘን ስንመለከተው ዘመነ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ሲኾን፣ ገበሬ በክረምት ብርዱንና ዝናሙን ሳይሰቀቅ ለሥራ ይሰማራል፤ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሣል፡፡ ይህም ምእመናን በሰማያዊው ዓለም የምናገኘውን ተድላና ደስታ በማሰብ በምድር ቆይታችን ወቅት የሚደርስብንን ልዩ ልዩ መከራ በትዕግሥት ማሳለፍ እንደሚገባን ያስገነዝባል፡፡

ዘመነ ክረምት ዕፀዋቱ በስብሰው ከበቀሉ፣ ካበቡና ካፈሩ በኋላ የሚጠቅሙት በጎተራ እንደሚሰበሰቡ፤ እንክርዳዶቹ ደግሞ በእሳት እንደሚቃጠሉ ኹሉ እኛም ተወልደን፣ አድገን፣ ዘራችንን ተክተን እንደምንኖር፤ ዕድሜያችን ሲያበቃም እንደምንሞት፤ ሞተንም እንደምንነሣና መልካም ሥራ ከሠራን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደምንገባ፤ በኀጢአት ከኖርን ደግሞ በገሃነመ እሳት እንደምንጣል የምንማርበት ወቅት ነው፡፡

በመኾኑም ሰይጣን በሚያዘንበው የኀጢአት ማዕበል እንዳንወሰድና በኋላም በጥልቁ የእሳት ባሕር እንዳንጣል ኹላችንም ቅዱሳት መጻሕፍትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጁልንን የቃለ እግዚአብሔር ዘር በየልቡናችን በመጻፍ እንደየዓቅማችን አብበን፣ ያማረ ፍሬ አፍርተን መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ይህንን እንድናደርግም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትና የቅዱሳኑ ኹሉ ተራዳኢነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡