በሁሉም አኅጉረ ስብከት ብልጫ ያለው ሀገረ ስብከት ተሸለመ
ጥቅምት 9 ቀን 2006 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ውስጥ ካሏት 50 አኅጉረ ስብከት በልዩ ልዩ መመዘኛዎች በ2005 ዓ.ም. የሥራ ብልጫ ያሳየው የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት አንደኛ ተብሎ ተሸለመ፡፡ በ32ው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከየአኅጉረ ስብከቱ የቀረቡትን ሪፖርቶች ገምግሞ ተሸላሚውን የለየው ለዚሁ ተግባር በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ ቤት የተቋቋመው ኮሚቴ ነው፡፡ ኮሚቴው ከሽልማቱ በፊት ባቀረበው ሰፋ ያለ ማብራሪያ እንደገለጸው፤ የየምድቡንም ሆነ የአሸናፊዎች አሸናፊ የሆነውን ሀገረ ስብከት ለመለየት አስር የሚሆኑ መመዘኛዎችን አውጥቷል፡፡ እነሱም በቤተ ክርስቲያኗ መልካም አስተዳደር ለማስፈን፤ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ፤ሰበካ ጉባኤን፤ አብነትና ዘመናዊ ት/ቤቶችን ለማጠናከር፤ ገዳማትና ቅርሳ ቅርስን ለመጠበቅና ለማስተዋወቅ፤ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን ለማጠናከር፤ በራስ አገዝ ልማት ራስን ለማጠናከር፤ ገንዘብንና ንብረትን ለመጠበቅ፤ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን ለማቋቋም እና ቅዱሳት መጻሕፍትን ከማእከል ወስዶ ለማከፋፈል የተደረጉ ጥረቶች የሚሉ ናቸው፡፡
በእነዚህ መመዘኛዎች ሃምሳውንም አኅጉረ ስብከት ለ11 ከከፈለ በኋላ በየምድቡ ያሸነፉትን አኅጉረ ስብከት በመለየት ፤ከእያንዳንዱ ምድብ ያሸነፉት አኅጉረ ስብከት ተወዳድረው የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የአሸናፊዎች አሸናፊ ሆኖ ተሸልሟል፡፡ ሽልማቱም ኮምፒዩተር ሲሆን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና ዋና ሥራ አስኪያጅ በጉባኤው ፊት ከቅዱስ ፓትርያርኩ እጅ ተቀብለዋል፡፡
በዓመቱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ባስገባው ፐርሰንት ብልጫ በማሳየት ልዩ ተሸላሚ ሆኗል፡፡