ቅዱሱን መስቀል ቀብሮ ማስቀረት ቤተ ክርስቲያንንም ማዳከም አይቻልም
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉ ሰዎች ዘንድ ስንፍና ነውና፤ ለምንድነው ለእኛ ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው›› በማለት የተናገረው መስቀል እና ቤተ ክርስቲያን ለሚያምኑ ሰዎች ተጋድሎው የክብር መገለጫ ሲሆን ለማያምኑት ግን ሞኝነት መስሎ ስለሚታያቸው ነው። ሐዋርያው ይህን ቃል የተናገረው እምነት ለሌላቸው ሰዎች መከራ መቀበል የአላዋቂነት፣ የሞኝነት እና የየዋህነት ምልክት እንጂ የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ መስሎ ስለማይታያቸው ነው። ምሥጢሩ የገባቸውማ ጌታ ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው በማለት ሲጸልዩላቸው ዓይናቸው ተከፍቶላቸው ዘለዓለማዊውን መንግሥት ሲመለከቱ ቀድመው ወደ ሰማዕትነት ይገቡ ነበር። (፩ኛ.ቆሮ.፩፥፲፰)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ሙት ማስነሣቱ፣ ድውይ መፈወሱ፣ ዕውር ማብራቱ፣ አንካሳ ማርታቱ ያስቀናቸው አይሁድ አፈር ቢያለብሱትምስጥ የሚበላው፣ቆሻሻ ቢጭኑበት ተቀብሮ የሚቀር መስሏቸው ነበር። ከ፫፻ ዓመታት በላይ ቅዱስ መስቀሉን ቀብረው የጣሉበት ቆሻሻ ትልቅ ተራራ ቢያክልም ቅዱሱን መስቀል ቀብሮ ለማስቀረት ግን አልተቻለውም። የጌታችን መስቀል ለጊዜውም ቢሆን ተቀብሮ በመጥፋቱ ክርስቲያኖች ከድኅነት ተከልክለው ሊቀሩ ነው ብላ መንፈሳዊ ተሐውኮ የደረሰባት ንግሥት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ አረጋውያንን ጠይቃ መስቀሉ የተቀበረበትን በተረዳችው መሠረት ቆሻሻውን አስቆፍራ ከተቀበረበት ስታስወጣው የተቀበረበት ቦታ መዓዛው የሚያውድ ከመሆኑ በተጨማሪ ወዲያው ተአምራት በማሳየቱ ለማሳሳቻ አብረው ከተቀበሩት ሁለት መስቀሎች በቀላሉ ሊለይ ችሏል።
በዘመናችንም የተነሡ አፅራረ ቤተክርስቲያን ዓላማቸው እንዲህ ነው፤ሃይማኖታቸውም ይህ ነው የማይባሉ የክርስቶስን መስቀል በመቅበር ክርስትናን ማጥፋት የሚቻል የሚመስላቸው ወገኖች ያልተረዱት ጉዳይ ዛሬም ገቢረ ተአምራት ከመፈጸም እናስቆመዋለን ብለው በከንቱ ይደክማሉ። መስቀሉን አቃጥለን እናጠፋዋለን፣ ሰባብረን እንጥለዋለን በማለት በከንቱ ቢደክሙም በፍቅር ስቦ የማምጣት ተአምሩን እየገለጠ፣ በክህደት የጸኑትን ደግሞ እንዳይነሡ አድርጎ ሰባብሮ እየጣላቸው ከዘመናችን ደርሷል፤ ወደ ፊትም በዚሁ ይቀጥላል። በመስቀሉ የሚፈጸመው ተአምር የሚሠሩትን እያጠፋባቸው፣ የሚያደርጉትን እያሳጣቸው እንደ አበደ ውሻ የሚቅበዘበዙትም ብዙዎች ናቸው።
ይህንንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጬጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት «አብያተክርስቲያናትን እየተዳፈሩ እና እያቃጠሉ፣ እየዘረፉ እና እየገደሉ፣ ሰላምን እና አንድነትን፣ ፍቅር እና ልማትን ማምጣት ስለማይቻል እንዲህ ዓይነቱ አጉል አስተሳሰብ እና ድፍረት በእግዚአብሔር እና በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ እየተፈጸመ ያለ ክፉ እና አጥፊ ድርጊት መሆኑ ታውቆ በአስቸኳይ መቆም አለበት። በዚህ ዙሪያ በሚሆነው ነገር ሁሉ በጭራሽ መግባባት አይኖርም» በማለት የተናገሩት ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ እና መፍትሔ የሚሰጥ አካል በመጥፋቱ ነው። በቤተ ክርስቲያን ላይ ተደጋጋሚ ጥፋት በመፈጸም መስቀሉን ማየት የማይፈልጉ አካላት ቤተ ክርስቲያንን እንደማያጠፏት፣ መስቀሉን መሰወር እንደማይችሉ እንዲያውም ለማጥፋት የሚሞክሩ ወገኖች ራሳቸው እንደሚጠፉ ስለምታውቅ ሁል ጊዜ «የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው» እያለች ትጸልይላቸዋለች። ሊያጠፏት የተነሡት ለራሳቸው ይብስባቸዋል እንጂ እሷ እንደማትጎዳ የታወቀ የተረዳ ነውና።
አፄ ዳዊት ቅዱስ መስቀሉን ካላካችሁልኝ የዐባይን ውኃ አስቆመዋለሁ ሲላቸው፣ ግብፃውያን ለራሳቸው ሊያደርጉት እየፈለጉ ሳይወዱ በግድ እንዲሰጡን ተገደዱ፣ ቅዱስ መስቀሉም ኢትዮጵያን ሦስት ጊዜ ዞሮ የባረከ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ቅዱስ መስቀሉን ጋሻቸው እንደሆነ በማመን «ይሳለሙታል እንጂ አያቃጥሉትም፤ የአክብሮት ስግደት ይሰግዱለታል እንጂ አይረግጡትም፤ ያከብሩታል እንጂ አያዋርዱትም ምክንያቱም በመስቀሉ ክብራቸውን እና ድኅነታቸውን እንዳገኙ አሳምረው ያውቃሉና» ተብሎ የተመሰከረልን በአባቶቻችን ብቻ ሳይሆን በምዕራባውያን ታሪክ ጸሐፊዎችም ጭምር ነው። መስቀሉን በመሳለም ፈንታ ለማቃጠል፣ ሊሰግዱለት ሲገባቸው ሊረግጡት፣ሊያከብሩት ሲገባ ለማዋረድ የሞከሩ ወገኖች ትዕቢታቸው ተኖ፣ ኩራታቸው ጠፍቶ ‹‹የምትፈልጉትን ግማደ መስቀል ወስዳችሁ ሕይወታችን የሆነውን ዓባይን ልቀቁልን›› ብለው ዓፄ ዳዊትን እንደ ተማጠኑት መረዳት ከውድቀት ይታደጋል። የዘመናችን የመስቀል እና የቤተ ክርስቲያን ጠላቶችም ከግብፆች በመማር ራሳቸውን ከጥፋት መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ «ኢትዮጵያውያን መሪዎች እና ልሂቃን ከኀምሳ ዓመታት ላላነሱ ዘመናት ከእግዚአብሔር ርቀዋል። ከመስቀሉ ሥር ጠፍተዋል፤ ይህ ዓይነቱ አመለካከት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ማያስኬድ በግልፅ እየታየ ነው። ከእንግዲህ ወዲህ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ እንደ ቀደምት አባቶቻችን ከቤተ ክርስቲያን አጸድ እና ከመስቀሉ ሥር ተገኙ ቅድስት ቤተክርስቲያን እጇን ዘርግታ ለማቀፍ የምትጣራው የጎደለንን ፍቅር እና ሰላም፣ አንድነት እና እኩልነት፣ ፍትሕ እና ወንድማማችነት በመስቀሉ ተትረፍርፎ ስለምናገኝ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሰይጣን የብርሃን መልአክ እየመሰለ እንደ ሚገለጥ ሁሉ ባዕድ የጫናቸውን የሐሰት ታሪክ ከላያቸው አራግፈው እንዲጥሉ ኃይል ጽንዕ ትሆናቸዋለች። መስቀል የሚያስተምረን ከሁሉ ጋር ተግባብቶ በፍቅር መኖርን፣ ከሁሉም ጋር ተረዳድቶ፣ ተከባብሮ እየሠሩ መኖርን ነው። ስለዚህ በመስቀሉ ሃይማኖታችንን ልንሰብክ፣ አገራዊ እና ወገናዊ ፍቅርንም ልንግለጥበት ይገባል። ትላንት በሌላ መንገድ መጥተው ያልተሳካላቸውን ዛሬ ደግሞ የእኛን ሥጋ ለብሰው በእኛ ሰው አድረው እኛን በእኛ ሊያታግሉን፣ እኛን በእኛ ሊያጣሉን፣እኛን በእኛ ሊያጋድሉን እየሞከሩ በመሆኑ የእኛዎቹ የዋሃን አትሳሳቱ» በማለት ብፁዕ አቡነ አብርሃም ያስተማሩትን ትምህርት በመገንዘብና ልብ በመግዛት የባዕድ ዓላማ አስፈጻሚዎች ላለመሆን መጠንቀቅ ይገባል ብለን እናምናለን።
የመስቀሉ ጠላቶች መካሪ መስለው የያዝነውን ሊያስጥሉን፣ለእነሱ የሌላቸው በእኛ እጅ በመገኘቱ በቅናት ስለተቃጠሉ የቀበሮ ባሕታዊ ምክራቸውን ስለአወቅንባቸው እነሱ ከሚጠሉት በላይ የመስቀሉ ጠላቶችን ከመሰሎቻችን አሠልጥነው እያሰማሩብን መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ሰይጣን የብርሃን መልአክ እየመሰለ፣ የበቃ አባት መስሎ እየተገለጠ በበረሃ በተጋድሎ ላይ ወደ ሚገኙ አባቶች ሔዶ ለማሳሳት ከሚሞክርባቸው ዘዴዎች አንዱ በመስቀል እንዳያማቱቡ ወዳጅ መስሎ በመምከር ቢሆንም ከአነጋገሩ ማን እንደሆነ ስለሚያውቁት በስመ አብ ብለው ሲያማትቡ እንደ ጢስ ተኖ ይጠፋል። ከእኛ የሚጠበቀውም እንደ አባቶቻችን ከአነጋገሩ እና ከድርጊቱ ልናውቅበት ይገባል።
አገራችን ዳሯ እሳት መሐሏ ገነት ሆና በቅዱስ መስቀሉ እና በቅዱሳኑ ጸሎት ተጠብቃ እንድትኖር ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ከምስር ባመጣው ጊዜ ኢትዮጵያን ሦስት ጊዜ ዞሮ ስለባረካት ደፍሮ የሚገባ የለም። ወዳጅ መስሎ ገብቶ ለማጥፋት ቢሞክርም እጁ ተሳስሮ፣ ዓላማው ተሰናክሎበት ይመለሳል እንጂ አይሳካለትም። ባዕድ የጫናቸውን ተሸክመው፣እያጠፉ መሆናቸውን ለማየት ዓይነ ልቡናቸው ታውሮ የአገራቸውን ታሪክ ለማጥፋት የተሰለፉ አካላት ቢኖሩም በመውጊያው ብረት ላይ ለመቆም በመሞከራቸው ይጎዳሉ እንጂ ኃይላችን፣ መድኃኒታችን፣ ጋሻችን፣ የነፍሳችን መዳኛ የሆነውን መስቀል እንደ ማያስጥሉን መረዳት ይገባል። የእግዚአብሔር ሥራ የሚያስደንቀን በዚህ መከራ እና ፈተና በበዛበት ዘመን ተለያይቶ የነበረው ምእመን አንድ ወደ መሆን፣ ግዴለሽ የነበረው ታሪኩን እና ሃይማኖቱን አውቆ ዘብ ወደ መቆም መሸጋገሩ ነው። ይህ ደግሞ ‹‹ምስማር እና ክርስቲያን ሲመቱት ይጠብቃል›› የሚለውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንድንረዳ ያደርገናል።
ክርስቲያኖች መስቀል መድኃኒታችን መሆኑን የምንመሰክረው የማያምኑበት በግድ እንዲያምኑበት እያስገደድን አለመሆኑን መረዳት ይገባል። ክርስቲያኖች በማስተማር እንጂ በማስገደድ የእምነታችን ተከታይ እንዲሆኑ እንደማናደርግ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ አንብቦ መረዳት ይቻላል። ይህም ሲባል እኛ በሌሎች ጣልቃ እንደማንገባ ሁሉ ሌሎችም በእኛ እምነት ጣልቃ እንዲገቡብን አንፈቅድም።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ በመንግሥት ተወስዶ የነበረውን የደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ «ከዛሬ ጀምሮ መሬቱ የቤተ ክርስቲያኑ ይሆናል፤የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ በመውሰድ ከእንግዲህ እግዚአብሔር ጋር አንጣላም» በማለት የተናገሩትን ማሰብ ተገቢ መሆኑን እናስታውሳለን። ምክትል ከንቲባው እንዲህ ብለው የተናገሩት ከእግዚአብሔር ጋር የተጣሉ፣ ቤተ ክርስቲያንን ለመገዳደር ሞክረው የነበሩ እና በቤተ ክርስቲያን ላይ ቁማር ለመቆመር የተነሡ አካላት የደረሰባቸውን በማየታቸው እንደ ሆነ እናምናለን።
የአዲስ አበባ ከተማ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬም የመስቀል በዓል በመስቀል አደባባይ ሲከበር «የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሁላችንም እናት ናት። በቤቷ ተምረን አድገናል፤ አንደበታችንን፣ ቋንቋችንን፣ አሳባችችንን ሁሉ ገርታ ከዚህ ያደረሰችን እና ያስተማረችን ቤተ ክርስቲያን ናት። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስታዝን ኢትዮጵያም አብራ ታዝናለች፤ በአገራችን በተለያዩ ክፍሎች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በከተማ አስተዳደራችን ስም ሆነን መልክ እንዲይዝ፣ እንዲቆም ለጥፋት የተሰለፉትን እና መጥፎ ነገር የሚያስቡትን ሁሉ ከልባቸው እንዲሆኑ መልእክት እናስተላልፋለን። ይህንም የምንለው ቤተ ክርስቲያን የአገርን ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህል፣ የወጣቶችን ሥነ ምግባር ጠብቃ ስለኖረች፤ አሁንም ታሪክ እየሠራች በመሆኗ ነው። በየዓመቱ የምንመለከተው የበዓል ትርኢት በሰንበት ተማሪዎች፣ በወጣቶች፣ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሚቀርበው ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እየሠራች፣ ሰዎች ከሌላ ዓለም መጥተው እንዲያዩን እያደረገች መሆኗን የሚያስረዳ ነው። ስለዚህ ይችን ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ክብር ልንሰጣት ይገባል» ብለዋል። መስቀል የልዩነት እና የጥል ሳይሆን የእርቅ ምልክት በመሆኑ በቤተ ክርስቲያን ላይ እጃቸውን ያነሡ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ እንደሚኖርባቸውም አባቶቻችን እያሳሰቡ መሆኑን ተረድተን የሚያዝዙንን ለመፈጸም፣ የነገሩንን ለመስማት በቅንነት ከተነሣን እግዚአብሔር አምላካችን መከራውን ወደ ደስታ ሊቀይርልን የታመነ ነው።
የመስቀል በዓል በ፳፻፲፪ ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ በሰላም መከበሩ የታየ እና የታወቀ ቢሆንም በደብረ ዘይት ከተማ ግን እነ እገሌ ከለከሉ በሚል ሰበብ መንግሥት ባለበት አገር ሕገ ወጦች በፈጠሩት ሁካታ ሳይከበር ቀርቷል። ይህ ኦርቶዶክሳውያንን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያሳዘነ፣ ነገር በሌሎች ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ላለመፈጸሙ ዋስትና እንዳይኖራቸው ያደረገ ተግባር በመሆኑ መንግሥት ችግሩን በመፍታት በዓሉ እንዲከበር ማድረግ ነበረበት። በጸሎት ተጀምሮ በጸሎት የሚጠናቀቀውን እና ሰላምን የሚያመጣውን በዓለ መስቀል መከልከል ሆን ብሎ ክርስቲያኖችን በማስቆጣት ለጥፋት እንዲነሣሱ ለማድረግ ካልታሰበ በቀር በአገራችን አንዱ ከልካይ ሌላው ፈቃድ ጠያቂ መሆን እንደ ማይኖርበት የታወቀ ነው።
ወደ ፊትም ቢሆን ክርስቲያኖች በተለመደው ትውፊታችን በዓላትን ለማክበር የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። አጥፊዎች ከሚፈልጉት ጥፋት እና ብጥብጥ እየራቅን የመስቀሉን ተቃዋሚዎች በእምነት ድል እናደርጋለን። የመስቀሉ ታሪክ የሚያስተምረንም ተቀበረ ሲባል እየወጣ፣ ጠፋ ሲባል እየተገኘ፣ ተሰወረ ሲባል እየተገለጠ ተአምር ሲፈጽም መኖሩን ነው። ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ «የመስቀልን በዓል ስናከብር የእግዚአብሔር ሥራ ተቀብሮ የማይቀር መሆኑን እንገነዘባለን። ለአገራችሁ፣ ለትዳራችሁ፣ ለቤተ ክርስቲያናችሁ፣ ለመሥሪያ ቤታችሁ የታመናችሁ ሁኑ። ልትጠሉ ትችላላችሁ፤ ያለ ስማችሁ ስም ብትሰጡም አትጠፉም። የንግሥት ዕሌኒ ሕይወት የሚያስተምረው ይህንን ነው። የተሰበሰብነውም ይህን እንድናውቅ ነው።
ጥፋተኛ ያልሆነን ሰው ባሕር አታሰጥመውም፤አንበሶች አይበሉትም፤ እሳት አያቃጥለውም። የእግዚአብሔር ቃል ታስሮ ባይቀርም ሊያስሩት የሞከሩ ብዙ ናቸው። እውነት፣ ወንጌል፣ታሪክ ስለ ማይታሰር ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ደርሳለች። ወደ ፊትም ትኖራለች። በሁሉም የአገራችን ክፍል የምትገኙ አገርን የምትመሩ፣ ሕዝብን የምታገለግሉ አካላት በቤተ ክርስቲያን ላይ እየሆነ ያለው ሁሉ ሊገዳችሁ ይገባል። የዚች ቤተ ክርስቲያን መሪዎች አባቶች ቢሆኑም መንግሥትም አገር ጠባቂ ነውና በሆነው ነገር ሊያስብበት ይገባል። እኔ ተጠያቂ አይደለሁም ሊል አይችልም» በማለት ያስተማሩት ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ ነው። ትምህርታቸው በአንድ በኩል ምእመናንን ሲያጽናና በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥትን የሚያሳስብ ነው።
መንግሥትም ሕዝብም እየተረዳዳ ሰላም የሚገኝበትን ተግባር ካልፈጸምን በንግግር ብቻ እውነተኛውን ሰላም ማግኘት አንችልም። በሌላ በኩል ደግሞ በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት በቤተክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለው ጥፋት እልባት እንዳልተሰጠው የዐሥሩ ማኅበራት ኅብረት ጥቅምት ፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ‹‹ከመስቀል በዓል ጋር በተያያዘ የፌደራል ፖሊስ በሰጠው መግለጫ ምክንያት የታሰሩ ኦርቶዶክሳውያን እንዲፈቱ ተደርጓል፡፡ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋርም በተደረገው ውይይት በመስቀል በዓል አከባበር ላይ በአንዳንድ የጸጥታ ኃይሎች እና ሕገ ወጥ ቡድኖች ምክንያት የተፈጠረውን ችግር ከክልሎች የፖሊስ ኮሚሽነሮች ጋር በመገምገም የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እና አስፈላጊውን ርምት ለመውሰድ ከስምምነት ላይ ተደርሷል›› ብሏል፡፡
በመቀጠልም በክልሎች ደረጃ የተደረጉ ውይይቶችን አፈጻጸም በቅርበት ለመከታተል እና በቀጣይም ችግሮች እንዳይፈጠሩ በቅንጅት ለመሥራት ከመንግሥት እና ከየአህጉረ ስብከት የተውጣጡ አካላት ያሉበት የጋራ ኮሚቴ በየዞኖቹ ተቋቁመው በክልሎቹ በተቋቋሙት የጋራ ኮሚቴዎች አስተባባሪነት፣ በየዞኖቹ በመንግሥት እና በቤተክርስቲያን ተወካዮች መካከል ውይይቶች መካሔድ ጀምረዋል። በአንዳንድ ዞኖች የትግበራ ዕቅድ አውጥተው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሕዝበ ክርስቲያኑ በየዞኖቹ የተቋቋሙ ኮሚቴዎች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፍ፣ መረጃዎችን እንዲሰጥ እና ተገቢውን ድጋፍ በመስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ፡- የፌደራል ፖሊስ የመስቀል በዓልን አስመልክቶ በዋዜማው ዕለት የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እና መግለጫውን ተከትሎ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ቀለማት የተዋቡ አልባሳትን በለበሱ ምእመናን ላይ ፖሊስ ይፈጽመው የነበረው የማንገላታት እና የማመናጨቅ ተግባር አግባብነት የሌለው በመሆኑ ሊታረም ይገባል፡፡ መግለጫው ምእመናን ወደ ደመራ በዓሉ እንዳይወጡ፣ የወጡትም በስጋት እንዲያሳልፉ ከማድረጉም በላይ በአንዳንድ አካባቢዎች በዓሉ በሰላም እንዳይከበር እና ሁከት እንዲፈጠር ያደረገ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የፌደራል ፖሊስ ቃል በገባው መሠረት ገምግሞ አስፈላጊውን ርምት እንዲወስድ እንጠይቃለን፡፡
የመስቀል በዓል በታላቅ ድምቀት የሚከበር የዐደባባይ አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ በዓል ሆኖ ሳለ በአንዳንድ አካባቢዎች ሕዝበ ክርስቲያኑን ለግጭት በሚያነሣሣ መልኩ በጸጥታ አካላት አላስፈላጊ ርምጃዎች ሲወሰዱ ተስተውሏል፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ ድርጊቶች ወደ አልተፈለገ ግጭት የሚያመሩ እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊትም የአገር ገጽታን የሚያበላሹ ከመሆናቸውም በላይ በሕዝበ ክርስቲያኑ ትዕግሥት እና ማስተዋል ታክሎበት እንጂ የከፉ ችግሮች እንዲፈጠሩ የሚጋብዙ ስለነበሩ በአስቸኳይ ርምት እንዲደረግባቸው እንላለን፡፡
በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ከመስቀል በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ በዝምታ ሊታለፉ የማይችሉ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ በደብረ ዘይት ከተማ የመስቀል ደመራ በዓል ላይ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የለበሳችሁት ልብስ የሰንደቅ ዓላማ ቀለም አለበት አውልቁ መባላቸው፣ በዚሁም ምክንያት የመስቀል ደመራ በዓል ሳይከበር መቅረቱን እና ደመራው ሌሊት በሕገ ወጥ ቡድኖች መቃጠሉ፤ በጅማ ከተማ ለመስቀል ደመራ በዓል የወጡ ምእመናን መደብደባቸው፣ በሻምቡ ከተማ በዓሉ ሊከበርበት ከነበረው መስቀል ዐደባባይ ውጭ ሌላ ቦታ አክብሩ ተብለው መከልከላቸው ቤተክርስቲያናችንን በእጅጉ ያሳዘኑ ታሪካዊ ስሕተቶች ናቸው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ምእመናን በዓሉን በሰላም እንዳያክብሩ ክልከላዎችን ያደረጉ፣ በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ድብደባ የፈጸሙ እና ምእመናንን እና አስተባባሪዎችን በማሰር ለእንግልት መዳረጋቸው በዓሉን ሳይከበር እንዲቀር በማድረጋቸው ፍጹም የጥፋት ድርጊት በመሆኑ አስፈላጊው ርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡
በተጨማሪም ከግሸን ደብረ ከርቤ ክብረ በዓል የሚመለሱ ምእመናን በየመንገዱ በተደራጁ ወጣቶች እብሪት የተሞላበት የጥቃት ተግባር ተፈጽሞባቸዋል። የክልሉ መንግሥትም ይህንን ነውረኛ ድርጊት በዝምታ በመመልከት መንግሠታዊ ሚናውን ሳይወጣ ቀርቷል፡፡ አሁንም በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ሃይማኖታዊ ጫናዎችና እንግልቶች ቀጥለዋል፡፡ የቤተክርስቲያን ይዞታዎችን መውረር፣ መጋፋት እንዲሁም ቤተክርስቲያንን እና የኦርቶዶክሳውያን ቤቶች እና ሱቆች ማፍረስ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ መንግሥት በእነዚህ ሕገ ወጥ ድርጊት ፈጻሚዎች ላይ ርምጃ አለ መውሰዱ ጥፋቱ እንዲባባስ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የክልሉ መንግሥት ይህን እያደረጉ ባሉ ቡድኖች እና የመንግሥት አካላት ላይ አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስድ፣ እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮችም በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ እንጠይቃለን” በማለት እየደረሰ ያለውን ጉዳት በማያሻማ ቃል ገልጦታል። ይህም መስቀሉን እና ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት እንቅልፍ የሌላቸው አካላት እያደረሱ ያለውን ጥፋት ያሳየናል። ጥፋቱ በሐሰተኛ ትርክት የተደገፈ፣በፕሮፓጋንዳ የታጀበ መሆኑንም በአንዳንድ ሚዲያዎች እና ግለሰቦች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ጸያፍ እና ከፋፋይ የሐሰት ትርክቶች፣ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ የማጉደፍ እና የማጣጣል ድርጊቶች እንዲሁም ቤተክርስቲያንን ባልዋለችበት በማዋል የከበረ ስሟን በሐሰት የማጥፋት ዘመቻዎችን እያወገዝን በሕግ ለመጠየቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ላይ እንገኛለን” በማለት በመግለጫው አስገንዝቧል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!!!
ምንጭ፤ ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ፳፯ኛ ዓመት ጥቅምት ፳፻፲፪ ዓ.ም.