ቃለ ዓዋዲ
ጥቅምት 13 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዲ/ን ኅሩይ ባየ
ቃለ ዓዋዲ ቀጥተኛ ትርጉሙ “የአዋጅ ነጋሪ ቃል” ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ የአዋጅ ነጋሪ ቃል ብሎ የተነበየለት መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ነበር፡፡ /ኢሳ.40፥1፵፥፩/ ከጌታችን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዊ ልደት ስድስት ወራትን ቀድሞ የተወለደው ቅዱስ ዮሐንስ ጥርጊያውን እያስተካከለ ሰዎችን ለንስሐ እየጠራ ለአማናዊው በግዕ ለኢየሱስ ክርስቶስ አዘጋጅቷቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብም /ቃለ ዓዋዲ/ ሦስቱ ጾታ ምእመናንን/ ካህናት፣ ወንዶች እና ሴቶች/ በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን እየተመሩ ሕይወታቸውን እንዲጠብቁ ስለሚያውጅ ቃለ ዓዋዲ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ቃለ ዓዋዲ የተባለው መጽሐፍ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያለውን አስተዳደራዊ መዋቅር ያካተተ የሕግ መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህም ብቻ ሳይወሰን ከምእመናን ጀምሮ እስከ ካህናት ድረስ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መብትና ግዴታ በውሉ የሚያስገነዝብ መመሪያም ነው፡፡
ቃለ ዓዋዲ ቤተ ክርስቲያናችን የምትመራበት የሕግ መጽሐፍ ነው ሲባል፤ ቃለ ዓዋዲ ከመኖሩ በፊት ቤተ ክርስቲያን በምን ትተዳደር ነበር? የሚል ጥያቄ ያስነሣ ይሆናል፡፡ ይህንን ጥያቄ የምንመልሰው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ለረዥም ዘመን በሓላፊነት አገልግለው በሞተ ሥጋ የተለዩንን የአባ አበራ በቀለን የአንድ ወቅት ቃለ ምልልስ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አባ አበራ በቀለ እንዳሉት “ቃለ ዓዋዲ ከመፈጠሩ በፊት ቤተ ክርስቲያናችን ትመራበት የነበረ አስተዳደራዊ መዋቅር አላት ከኒቂያ ጉባኤ በፊትም ቢሆን የአስተዳደር ሥርዓት ነበራት፡፡ ከሁሉ በፊት ግን እንደ ሕግ ሆኖ የሚመራት ዋናው የሕግጋት ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ እርሱም የሃይማኖትና የሥነ ምግባርን ሕግ የያዘ ነው፡፡ በብሉይም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ዘመን አባቶቻችን በዚህ ሲገለገሉ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይመሰክራል ወደ ሀገራችንም ስንመጣ ፍትሐ ነገሥቱ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ መንግሥት ከአብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ ንግሥ ጀምሮ እስከ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ድረስ አንድነት ነበራቸው፡፡ ቤተ መንግሥት ወደ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ይገባ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ወደ መንግሥት አስተዳደር ትገባ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ፍትሐ ነገሥቱ በሁለቱም ወገኖች ሲሠራበት ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በዓፄ ኀይለ ሥላሴ ጊዜ አዳዲስ ሕጎች ሲወጡ ፍትሐ ብሔሩና ወንጀለኛ መቅጫው ሲወጣ የፍትሐ ነገሥቱ አሠራር እየቀዘቀዘ በአዲስ እየተተካ ሄደ፡፡ እንደሚታወቀው ፍትሐ ነገሥት ሁለት ክፍል አለው እርሱም፡-
- ፍትሕ መንፈሳዊና
- ፍትሕ ሥጋዊ በመባል ይታወቃል፡፡
ፍትሕ መንፈሳዊ አሁንም በቤተ ክርስቲያን ተጠብቆ እየተሠራበት ነው፡፡ የሥጋዊ አስተዳደሩ ደግሞ በቤተ መንግሥት በኩል በሌላ አዋጅ ተተክቷል፡፡”
በዓለመ መላእክት፣ በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት፣ መላእክትና ሰዎች እግዚአብሔርን ያመልኩበት የነበረ ሥርዓት አለ፡፡ በዘመነ አበው፣ በዘመነ መሳፍንት፣ በዘመነ ነገሥት፣ በዘመነ ነቢያትና በዘመነ ሐዲስም ይህ ሥርዓት የጸና ነው፡፡ የሥርዓት አስፈላጊነት በመጽሐፍ ቅዱስ ተደጋግሞ የተቀመጠ በመሆኑ አሁንም ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና ለማኅበረ ምእመናን ሥርዓት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያለ ሥርዓት፣ ያለ ሕግ፣ ያለ ደንብ፣ ያለ መዋቅር የምትሠራው ምንም ዓይነት አገልግሎትና ድርጊት የለም፡፡ ሊቀ ጉባኤ እንዳሉት የሕግ ሁሉ ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ፍትሐ ነገሥቱም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጎ በፍትሕ መንፈሳዊና በፍትሕ ሥጋዊ ተጣምሮ አገልግሎቱን ሲሰጥ ከቆየ በኋላ ፍትሕ ሥጋዊ ወደ መንግሥት አስተዳደር ተጠቃልሏል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ራሷን ችላ የምትመራበት ሕግ እንዲጸድቅላት በጠየቀችው መሠረት ከምእመናን ምጣኔ ሀብታዊ ጋር በተገናዘበ መልኩ ሁሉንም የሚያሳትፍ መዋቅር በሁለተኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመነ ፕትርክና የመጀመሪያው ቃለ ዓዋዲ ጥቅምት 14/፲፬ ቀን 1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም ታተመ፡፡ ቃለ ዓዋዲው ከመውጣቱ በፊት ረቂቁ ለፓርላማ ቀርቦ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ ለምእመናን እንዲደርስ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ተዘጋጅቶ በነጋሪት ጋዜጣ መልክ ወጣ፡፡ ይህ ቃለ ዓዋዲ ከ1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም እስከ 1970/፲፱፻፸ ዓ.ም ለአምስት ዓመታት ያህል እንዳገለገለ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ አያይዘው ገልጠዋል፡፡
የቃለ ዓዋዲው ተቀዳሚ ዓላማ
ሀ. ቅድስት፣ ከሁሉ በላይ ሐዋርያዊትና አንዲት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን መጠበቅና አገልግሎቷም የተሟላ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህን ሓላፊነት የሚወጡት ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ድረስ የሚገኙት የሥራ ሓላፊዎች ናቸው፡፡
ለ. የካህናት የኑሮ ደረጃ የተሻለ ሆኖ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በትጋት እንዲወጡ ማድረግ፡፡
ሐ. የምእመናን ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እንዲጨምር እና ያሉትንም በምግባር በሃይማኖት ማጽናት፤ በመንፈሳዊ ዕውቀት እንዲበለጽጉ ማገዝ፤ ሁኔታዎችንም ማመቻቸት፡፡
መ. የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እንዲሻሻል የገቢ ምንጮችና ልማቶች ተበራክተው በገንዘብ አቅም የጎለበተች ቤተ ክርስቲያን ሆና ከተረጂነት እንድትላቀቅ ማድረግ ነው፡፡
እነዚህን ዓላማዎች ግቡ አድርጎ የተመሠረተው ቃለ ዓዋዲ አፈጻጸሙ እንዲሳካ ከምእመናን ጀምሮ ሥልጣነ ክህነት እስካላቸው አገልጋዮች ድረስ የሠመረ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ምእመናን ስለ ቃለ ዓዋዲ ያላቸው ግንዛቤ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዞ ምቹ መሆን የካህናት ድርሻ ብቻ የተሟላ አያደርገውም፡፡ የምእመናንም ድርሻ ከፍተኛውን ድርሻ መያዝ አለበት፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ለተወሰኑ አካላት ብቻ የማንተወው በመሆኑ የእነሱና የእነሱ ሓላፊነት ብቻ እንደሆነ ማሰብ የለብንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሦስቱም ጾታ ምእመናን ናትና ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡
ቃለ ዓዋዲ ተደንግጎ ጸድቆ ሰበካ ጉባኤ ተቋቁሞ በሥራ ላይ ውሎ አሁን ካለበት ደረጃ ለመድረስ በርካታ ፈተናዎችን አልፏል፡፡ በ1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶችን በመጥራት የመጀመሪያውን የቃለ ዓዋዲ ረቂቅ ለውይይት አቅርበዋል፡፡ ቅዱስነታቸው በሸዋ ሀገረ ስብከት በዐሥራ አንድ አውራጃዎች እየተዘዋወሩ ስለ ቃለ ዓዋዲ ለካህናትና ለምእመናን ማብራሪያ በመስጠት አዲሱን እቅድ አስተዋውቀዋል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ ልኡካንን መድበው በየአህጉረ ስብከት እየተዘዋወሩ እንዲያስተምሩ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሆኖም ካህናቱና ምእመናኑ ተወካዮችን መርጠው ሰበካ ጉባኤና ቃለ ዓዋዲ የሚባል በባህላችን የማይታወቅ አዲስ አሠራር መጣብን ብለው ለንጉሠ ነገሥቱ /ኀይለ ሥላሴ/ አቤቱታ እስከማቅረብ ደርሰው ነበር፡፡
ይህንና የመሳሰሉትን ችግሮች ተሻግሮ በአገልግሎት ላይ የሚገኘው ቃለ ዓዋዲ ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ ከወጣበት ከ1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም ጀምሮ ለ5/፭ ዓመታት አገልግሎ በ1970/፲፱፻፸ ዓ.ም የተለያዩ ማሻሻያዎች ታክለውበት ለሁለተኛ ጊዜ ታትሟል ከ1970/፲፱፻፸ ዓ.ም እስከ 1991/፲፱፻፺፩ ዓ.ም መግቢያ ድረስ ለሃያ አንድ ዓመታት ያገለገለው ቃለ ዓዋዲ ዳግመኛ ተሻሽሎ ለሦስተኛ ጊዜ በ1991/፲፱፻፺፩ ዓ.ም ታትሟል፡፡
ጥቅምት 7-11/፯‐፲፩ ቀን 2004/፳፻፬ ዓ.ም 30/፴ኛው መደበኛ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ የኢሉባቡርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ አሳሳቢነት ቃለ ዓዋዲው ለአራተኛ ጊዜ እንዲሻሻል አሳብ አቅርበዋል፡፡ ምልዓተ ጉባኤውም ቃለ ዓዋዲው ተሻሽሎ እንዲወጣ በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል፡፡ የጉባኤው የውሳኔ አሳብ የሚፈጸመው በቅዱስ ሲኖዶስ ይሁንታ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ የጉባኤውን የውሳኔ አሳብ እንዲመለከተው ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡
በ1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣው ቃለ ዓዋዲ በ1970/፲፱፻፸ ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣበት ምክንያት በተለይ በ1966/፲፱፻፷፮ ዓ.ም በሀገራችን የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረቷን መንግሥት በውርስ ሲወስደው የገቢ ምንጮች ደረቁ፡፡ የኮሚኒስቱ ፓሊሲ ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የማይመችም ነበር፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎች በመንግሥት ተወረሱ፡፡ በመጀመሪያው ቃለ ዓዋዲ ስለ መሬት ርስትና ስለ ቤት ኪራይ የሚናገር አንቀጽ ነበረው፡፡ ይህ ድንጋጌ ለደርግ መንግሥት ጥቅም አላስገኘለትም፡፡ ስለዚህ ተስፋፍቶና ተሻሸሎ እንዲታተም ግድ በመሆኑ በ1970/፲፱፻፸ ዓ.ም በሚያዝያ ወር ተሻሽሎ ወጣ፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ በ1991/፲፱፻፺፩ ተሻሽሎ እንዲታተም ያስፈለገበት ምክንያት ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ካህናትና ዲያቆናት ለመሆን የበቁ አገልጋዮች በዘፈቀደ ሳይሆን በደብሩ አስተዳዳሪ ተመስክሮላቸው የትምህርት ደረጃቸው ታይቶ ክህነቱን እንዲቀበሉ፣ ወጣት ዲያቆናት ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት እየገቡ እንዲማሩና ካህናቱም የሰንበት ትምህርት ቤቶች መርሐ ግብርን ከሚያስተምሯቸው በተጨማሪ በጸሎት ጀምረው በጸሎት እንዲዘጉ፣ የቤተ ክህነት አገልጋዮች ዕድሜ ጣራ 60/፷ ዓመት እንዲሆን፣ ከደመወዛቸውም ከመቶ እጅ የተወሰነ እንዲከፍሉ፣ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ፣ ሥራ አስኪያጅ ሥልጣንና ተግባር የወረዳው ቤተ ክህነት ሊቀ ካህናት ሥልጣንና ተግባር እያለ በመጠኑ የተገለጸውን ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና ከቅዱስ ፓትርያርኩ የሚጠበቀውን ሥልጣንና ተግባር በስፋት አብራርቶ ለማስቀመጥ ታስቦ ነው፡፡
በ2004/፳፻፬ ዓ.ም 30/፴ኛው መደበኛ አጠቃላይ ዓመታዊ ጉባኤ ሲካሄድ ለአራተኛ ጊዜ እንዲሻሻል ያስፈለገው በቃለ ዓዋዲው እየታየ ያለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ክፍተት ነው፡፡ ለምሳሌ ቤተ ክርስቲያን በቋሚ ሠራተኛነት ቀጥራ ከምታሠራቸው ሠራተኞች መካከል ጥቂቶቹ ገንዘብ ሲያጎድሉ በቤተ ክህነት ሒሳብ መርማሪዎች ኦዲት ተደርገው ባለዕዳ መሆናቸው ሊረጋገጥ ይችላል፡፡ ዕዳቸውን መክፈል ያልቻሉትን ሕገ ወጥ ሠራተኞች በፍርድ ቤት ለመክሰስ አግባብ ባለው የሕግ አካል ቢጠየቁም የቤተ ክህነት ሒሳብ መርማሪዎች የሒሳቡን ሥራ ለማከናወን ሕጋዊ ዕውቅና የላቸውም? የሚል መከራከሪያ በማንሣት ጉዳያቸው በፍጥነት እንዳይታይና እልባት እንዳይሰጠው ይከራከራሉ፡፡ በቃለ ዓዋዲው ሕገ ደንብ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ ባሉት መዋቅሮች የሒሳብ በጀት ክፍል ስላለ በዚህ ክፍል ሒሳቡ እንዲመረመር ያዛል፡፡
በመሆኑም ቃለ ዓዋዲ የሒሳብ ጉዳዮችንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተነተነበት አንቀጹ ለፍትሕ መንፈሳዊና ለፍትህ ሥጋዊ በማያሻማ ሐተታ ቢብራራ አግባብ ባለው የሕግ አካል ለመክሰስም ሆነ ለመጠየቅ ያስችላል፡፡
የቃለ ዓዋዲ ሕገ ደንብ ለምእመናን ለካህናትና ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ያለው ጠቀሚታ የጎላ ነው፡፡ በሥርዓተ ተክሊል በቅዱስ ቁርባን የተጋቡ ባለትዳሮች ቢጋጩ ወደ ፍርድ ቤት ከሚሔዱ ይልቅ በፍትሕ መንፈሳዊ ቢዳኙ ምንኛ ደስ ይላል፡፡ ካህናትም የቃለ ዓዋዲውን ሕገ ደንብ ጠብቀውና አስጠብቀው ዐሥራት በኩራቱን ሰብስበው ራሳቸውንና ቤተ ክርስቲያንን ወደ ተሻለ እድገት ቢያሸጋግሩበት መልካም ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የተቃና እንዲሆን እንደ ቃለ ዓዋዲው ድንጋጌ ሓላፊነትን መወጣት ከተቻለ ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ካለባት አስተዳደራዊ ችግር መላቀቅ ትችላለች፡፡
ባለፈው ዓመት ቃለ ዐዋዲው እንዲሻሻል የቀረበው አሳብ መክኖ እንዳይቀር ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ሕገ ቤተ ክርስቲያኖቻችን ከተሻሻለ መዋቅሮቻችን ከተጠናከሩ አገልጋዮችም በሞያቸው በሓላፊነትና በተጠያቂነት መሥራት የሚችሉት የደንባችን አጥር ሲጠብቅ ነው፡፡
ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይተካል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሁሉም ለሁሉም ናት፡፡ ማንም ቢመጣ ማንም ቢሄድ ቤተ ክርስቲያን ሁሉን ታሳልፋለች፤ እሷ ግን አታልፍም፡፡ እኛ ብናልፍ ሥራችን ሕያው ምስክር ሆኖ እንዲኖር በሕጋችን መሻሻል ላይ በደንብ እንምከርበት፣ በሚገባ እናስብበት፣ በብስለት እንወያይበት፡፡ በምክክራችን ጊዜ ባለሞያዎችን እናሳትፍ፤ ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን አዲስና ብሩህ ተስፋ ዛሬን እንሥራበት፡፡
“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመበት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” /ሐዋ.20፥28/፳፥፳፰
እግዚአብሔር አምላካችን ቤተ ክርስቲያናችንን ከጥፋት ይጠብቅልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል