ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ ምን ይላሉ?
ታኅሣሥ 12 ቀን 2005 ዓ.ም.
- “በቤተ ክርስቲያን ነጻነት ያለበት አመራር ሊኖር ይገባል”
ዲ/ን ቴዎድሮስ ጌታቸው
በደብረ ገነት ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል
ከሐመረ ብርሃን ሰንበት ት/ቤት
የቅዱስ አባታችን ዕረፍት ምክንያት በማድረግ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ፓትርያርክ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ እንደ እኔ አመለካከት የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ለማስጠበቅ ዕርቁን አስቀድሞ መካሔድ ያስፈልጋል፡፡ ምርጫውም መፈጸም ያለበት ከዕርቁ በኋላ ቢሆን ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ምርጫውን በማስመልከት በተለይ በዚህ ዘመን እርስ በእርስ የሚጣረሱ ወሬዎች እየወጡ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባለን ሰዎች፣ በካህናቱም ዘንድ እየተወራ፣ እየታየም ያለው “እገሌ ይመረጥልን፤ ምርጫው ከእገሌ አይ ወጣም” በማለት አላስፈላጊ የቲፎዞ ነገር ነው፡፡ ብፁዓን አባቶቻችን የፓትርያርክ ምርጫውን ተረጋግተው ማካሔድ አለባቸው፡፡ አንዳንዶች ምርጫው በጎጥ፣ በጎሣ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን፤ በቡድን የሚንቀሳቀሱ አሉ ይባላል፡፡ ይህ ክርስቲያናዊ ነው ብዬ አላምንም፡፡ አባቶቻችን እነዚህን እኩይ ሤራ የሚያራምዱትን ሰዎች በንቃት ሊከታተሏቸውና ሤራቸውንም ከምንጩ ሊያደርቁት ይገባል፡፡ እግዚአብሔር የፈቀደው፣ መንፈስ ቅዱስ ያዘጋጀውን ሰው ለመመረጥ ተረጋግቶ ሁኔታዎችን ማጤን የሚያስፈልግበት ወቅት በመሆኑ፤ አባቶቻችን በዚህ ላይ ጥንቃቄ ሊያ ደርጉ ይገባል እላለሁ፡፡ ከዛ ይልቅ ለቤተ ክርስቲያን የሚበጃት ማነው? የሚለውን ነው መመልከት ያለብን፡፡ የዘር ጉዳይ በካህናቱ ብቻ ሳይሆን ወደ አንዳንድ ምእመናንም ወርዶ ይታያል፡፡ ብፁዓን አባቶች እነዚህ አላስፈላጊ ግፊት ከሚያደርጉ ሰዎች ሊጠነቀቁ፣ ምእመ ናንም ከዚህ ዓይነት ድርጊት ሊቆጠቡ ይገባል፡፡
ምርጫው የተሳካ ይሆን ዘንድም ጳጳሳቱ፣ ሊቃውንቱ፣ ካህናቱና ምእመናኑ በአንድነት ጸሎት ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የሚበጃትን አባት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንዲያዘጋጅልን ቅድሚያ ጸሎት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችም ከአባቶች እግር ሥር ሆነን የጸሎቱ ተካፋይ በመሆን እግዚአብሔር ጥሩ አባት እንዲሰጠን ተግተን መጸለይ አለብን፡፡
ፓትርያርኩ ከተመረጡ በኋላ በቤተ ክርስቲያን የሚጠብቃቸው ተግዳሮቶች በእኔ ዕይታ የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያኗን አስተዳደር የሚመለከት ነው፡፡ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ድረስ ያለው አስተዳደሯን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ከሚታዩት አስተዳደራዊ ችግሮች የተነሣ፤ የተለያዩ በደሎች እየተፈጸሙ ነው፡፡ ምእመናንም ይህን በመመልከት ከቤተ ክርስቲያን እየራቁ ያሉ፣ ጥቂት አይደሉም፡፡ ‹‹ተሐድሶዎች›› በስውር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴም ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡ ሌላው በቤተ ክርስቲያኗ ሥር ሰዶ የሚታየው የጎጥና የጎሳ ችግር ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን የሚሾመው መስፈርቱ ዕውቀቱ፣ በመንፈሳዊ ሕይወቱ እንጂ ከየትኛው ዘር የመጣ ነው የሚለው መቅደም የለበትም፡፡ ስለዚህ ተመራጩ ፓትርያርክ እነዚህን ሥር የሰደዱ ጉዳዮች የማስተካከል ትልቅ ሓላፊነት ይጠብቃቸዋል፡፡
ሌላው ቃለ ዓዋዲው በሥራ እንዲተረጐም መሥራት ያለባቸው ይመስለኛል፤ በአሁኑ ወቅት በቤተ ክርስቲያን ከቃለ ዓዋዲው ውጭ የሚሠሩ ሥራዎች እየበዙ መጥተዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን አምባገነናዊ አሠራር መወገድ አለበት፡፡ አምባገነናዊ አሠራር ጥሩ ሙያ ያላቸውን፣ ለቤተ ክርስቲያን የሚያስቡ ቅን አገልጋዮችን ያርቃል፡፡ ተመራጩ ፓትርያርክም ሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ ለተዘረዘሩት ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት፤ ቤተ ክርስቲያን ነጻነት ያለበት አመራር እንዲኖራት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በሰንበት ትምህርት ቤት የተሰባሰብንም ወጣቶች የቤተ ክርስቲያናችንን ወቅታዊ ጉዳይ እየተወያየን ነው፡፡ ዘመኑ የቴክኖሎጂ በመሆኑ አብዛኛዎቹ ወጣቶች ስለ ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ በዚህም ምንማድረግ አለብን? የሚለው መወያያችን ሆኗል፡፡ የውይይታችን ጭብጥም እግዚአብሔር ጥሩ አባት እንዲሰጠን ከመመኘት አንጻር በመሆኑ በግልም፣ በጉባኤም ጸሎት እያደረግን ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም በሐመር መጽሔት ይህን መድረክ ከፍቶ ወጣቶች፣ ምእመናን፣ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ቅን የሚያስቡ ሁሉ አስተያየት እንድንሰጥ በማድረጉ በጣም እናመሰግናለን፡፡ ወደፊትም በዚሁ ይቀጥል እላለሁ፡፡
-
“በተፈጠረው ክፍተት ክፉዎች እየተጠቀሙበት ስለሆነ ዕርቁ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ”
ዘሪሁን መንግሥቱ
በመንበረ መንግሥት /ግቢ/ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም
ከዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት
ቤተ ክርስቲያናችን ፓትርያርክ እንዴት መመረጥ እንዳለበት ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን የሚያውቀው መመሪያ ሊኖራት ይገባል፡፡ ሰዎች በዘር፣ በጐጥ፣ በአካባቢ ፓትርያርክ ለማስመረጥ ጥረት እንደሚያደርጉ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም አይደለም፡፡ ሐዋርያትን የመረጣቸው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም የሚመሩ አባቶች የሚመርጥ እግዚአብሔር ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ገጥሟት የማያውቀው ፈተና በዘመናችን ተከስቷል፡፡ ከምርጫው በፊት ዕርቁ መፈጸም አለበት፡፡ እንዲያውም ዕርቁ ዘግይቷል ነው የምለው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አሐቲ ሆና ልጆቿ በአመለካከት የተነሣ ተከፋፍለው “እኔ እገሌን ነው የምከተለው” የማለት አስተሳሰብ ተፈጥሯል፡፡ አባቶቻችን በአሁኑ ወቅት አንድ መሆን አለባቸው፡፡ ሐዋርያት በይሁዳ ምትክ ማትያስን ሲመርጡት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው እንጂ ተከፋፍለው አልነበረም፡፡
ቤተ ክርስቲያንን ለመታደግ በሁለቱም በኩል አባቶች ወደ አንድ መምጣት አለባቸው፡፡ እዚህ ላይ መታየት ያለበት እስከ ዛሬ ዕርቅ ባለመፈጸሙ ምክንያት ጵጵስና የማይገባቸው ሰዎች ጵጵስና እንዲያገኙ ሆነዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከመመሪያዋ፣ ከቃለ ዓዋዲዋ ከምትመራበት ሕግና ሥርዐት ውጪ እንድትመራ አድርገዋል፡፡ ይህ ክፍተት በመፈጠሩ የእኛን እምነት የማያምኑ ነገር ግን አማኝ መስለው ምእመናንን የሚያሳስቱ የተለያየ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች ተጠቅመውበታል፡፡
በምርጫው ላይ ትልቁ ድርሻ የጳጳሳቱ ነው፡፡ አባቶቻችን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ማድረግ የሚገባቸው ብዬ የማስበው ምርጫው እንደ ሐዋርያት መሆን አለበት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያዘው መሠረት ተተኪው ፓትርያርክ እንዲመረጥ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለባቸው፡፡ ሊቃውንት አባቶችም በፓትርያርክ ምርጫ ላይ የራሳቸው የሆነ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ሲገጥማት በችግሯ ጊዜ ሊሆን የሚገባውን ከመግለጽ ዝም ብለው በኋላ “እንዲህ አደረጉት፣ እኛ እኮ እንዲህ ብለን ነበር” ከማለት ይልቅ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን መደረግ እንዳለበት ለምእመናኑ ግልጽ የሆነ ነገር ማስረዳት፣ ውዥንብሮችን ማጽዳት፣ ፓትርያርክ ለመምረጥ ከሕዝቡ ምን ይጠበቃል? የሚለውን ማስተማር አለባቸው፡፡ ይህን መሥራት ከሊቃውንቱ በተጓዳኝ ከሊቃነ ጳጳሳቱም ይጠበቃል፡፡ ካህናቱም “እገሌ ስለሚጠቅመኝ ይሾምልኝ፤ ነገ ዕድገት ይሰጠኛል” ብለው ለመሾም፣ ለመሸለም፤ የተለየ ነገር ለማግኘት ብለው ሳይሆን፤ በትክክለኛው ሥርዐት እንዲመረጥ እገዛ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለንስሐ ልጆቻቸው በአገልግሎት ለሚያገኟቸው በርካታ ምእመናን ከአሉባልታ በጸዳ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዐት ለምእመናን የመንገር ሓላፊነት አለባቸው፡፡
ሰንበት ትምህርት ቤት በርካታ ወጣቶችን የያዘ ተቋም በመሆኑ፤ ወጣቱ ከምንም በላይ በፓትርያርክ ምርጫው ሂደት ላይ በንቃት እየተከታተለ ይገኛል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤት ያሉ ወጣቶች ከሊቃውንቱ እግር ሥር ቁጭ ብሎ በመማር ከአባቶች የወረደውን መመሪያ ብዥታ ባልፈጠረ መልኩ ምእመናን የሚያውቁበትን መንገድ ማመቻቸት፤ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ለምእመናን ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት ሂደት ላይ ሙያዊ እገዛ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
ፓትርያርኩ ከተመረጡ በኋላ በመጀመሪያ የሚጠብቃቸው ሥራ ቤተ ክርስቲያኒቱን አንድ ማድረግነው፡፡ ሌላው መረጃን በተመለከተ ዛሬ የተለያዩ ወሬዎች እየተናፈሱ ነው፡፡ “እገሌ እንዲህ ነው፤ እገሌ እንዲህ ስለሆነ ነው…” የሚሉ ወሬዎችን ምእመናኑ ከማይመለከታቸው አካላት መረጃ እየሰሙ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ቤተ ክርስቲያንን የማያውቀው ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲጽፍ ይታያል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ስም ለማጉደፍና አባቶቻችን የሌሉበትን ስም እየሰጡ ለማጥፋት የሚጥሩ አካላት አሉ፡፡ ከዚያ ጐንም የተሰለፉ ምእመናንም አሉ፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን አደረጃጀቷ ምን እንደሚመስል፣ ምእመናኖቿ ምን ዓይነት አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው፣ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት ተቋሞቹ እንዴት መደራጀት አለባቸው፤ ገዳማቶቿ እንዴት ቴክኖሎጂውን በመጠቀም መገናኘት አለባቸው? የሚሉ ጉዳዮች መልስ ከሚመረጡት አባት ይጠበቃል፡፡
ሲኖዶሱም ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ውሳኔዎችን ከሥር ከሥር እየተከታተለ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በእያንዳንዱ ሥራ አባቶች እታች እየወረዱ ማስፈጸም ላይጠበቅባቸው ይችላል፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ቀጥሎ አህጉረ ስብከቶች በተዋረድ የሚያስፈጽሙበትና ክትትል የሚደረጉበትን መንገድ ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ተመራጩ ፓትርያርክ ይህን ትልቅ ሓላፊነት ለመወጣት በመጀመሪያ ያልተሠሩ ሥራዎችን መለየት፣ ቤተ ክርስቲያኗን ተጭነው ያሉ በዘልማድ የተቀመጡ አሠራሮችን ነቅሰው ማውጣት አለባቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቢሮክራሲውን ማስወገድ፣ አስተዳደራዊ ቦታዎች በተማሩ እና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው አርአያ በሚሆኑ ሰዎች መተካት አለባቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ባስተማረቻቸው ልጆቿ ነው መተዳደር ያለበት እንጂ፤ እንደ ፓርላማ ኮታ “ከእገሌ ብሔር መቅረት የለበትም” በሚል ስሜት ቤተ ክርስቲያን መመራት የለባትም፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ወቅት በየገዳማቱ፣ በየአድባራቱ የሚሾሙ በትክክል ተምረው ነው ወይ? የሚለውም መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
ሰንበት ት/ቤቶች በፓትርያርክ ምርጫው ላይ “የእኛ ሱታፌ ምንድን ነው?” በማለት እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን መወያየት፣ የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረብ ከሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ይጠበቃል፡፡
-
“ ‘እነ እገሌ ይመረጡልን’ የሚሉ ቡድኖችን ቅዱስ ሲኖዶስ ማዳመጥ የለበትም”
ወጣት አንተነህ ዐወቀ
በደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል
ከእግዚአብሔር ምስሌነ ሰንበት ት/ቤት
ምርጫው ከመደረጉ በፊት፤ መቅደም ያለበት ዕርቁ ነው፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ለሦስት ተከፍላለች፡፡ እዚህ ባለው ሲኖዶስ የምትመራ ቤተ ክርስቲያን፣ ውጭ ባለው ሲኖዶስ የሚመራና እንዲሁም ገለልተኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተብሎ የሚታወቅ አለ፡፡ በዚህ ወቅት እነዚህ ሦስት ወገኖች ወደ አንድ መምጣት አለባቸው፡፡
ቤተ ክርስቲያን መለያየት የለባትም፤ የቤተ ክርስቲያን አንድነት ለሀገር አንድነት ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ለምሳሌ፡- የኒቂያ ጉባኤ ስንመለከት፤ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የአርዮስ ክህደት ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን፤ ለሀገርም ችግር ይፈጥራል ብሎ በማሰቡ አባቶች ተሰባስበው ችግሩን እንዲፈቱ ያደረገበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ አሁንም በውጭና በሀገር ውስጥ ባሉት አባቶች መካከል የተፈጠረው ችግር ሰላማዊ በሆነ ነገር መፈታት አለበት፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንድ ስትሆን ነው በአንድነት መሥራት የሚቻለው፡፡ ስለዚህ ዕርቁ ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡
ለፓትርያርክ ምርጫው የጳጳሳቱ፣ የካህናቱ፣ የሊቃውንቱ፣ የሰንበት ት/ቤት አባላት፣ የምእመናኑ፣ የምሁራኑ ቤተ ክርስቲያኗ ጥሩ መሪ እንዲኖራት፣ ምእመናንን በአግባቡ መምራት እንድትችል የድርሻችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ወጣቱ ስለ ቤተ ክርስቲያን ዕለት ዕለት መረጃ የሚያገኝበት ቤተ ክርስቲያን ምን መሆን አለባት? የቀድሞ አባቶች ያሳለፉት ነገር ምንድን ነው? አሁንስ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን ያሳያል? ወደፊትስ ምን መሆን አለበት? የሚለው ነገር በደንብ እየተረዳን ያለንበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ለቤተ ክርስቲያን ይበጃል፣ ይጠቅማል የሚለውን እንደየ ችሎታችን፣ እንደየ ዕውቀታችን፣ እንደየ አቅማችን ማድረግ የሚጠበቅብንን ነገር ሁሉ ማድረግ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡
በሰንበት ትምህርት ቤት እርስ በእርስም ቢሆን ስለ ፓትርያርክ ምርጫ እንወያያለን፡፡ ዛሬ ወጣቱ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ላይ በርካታ መረጃዎች በኢንተርኔት፣ በፌስ ቡክ፣ በተለያዩ ብሎጐች ያገኛል፡፡ ትናንት በነበሩ አባቶች ምን ተሠራ? ዛሬስ ያሉት ምን እየሠሩ ነው? የሚለውን እየተመለከትን ነው፡፡ ትናንት በቤተ ክርስቲያን ላይ ተፈጥሮ የነበረው ችግር ነገ እንዳይቀጥል የድርሻችንን አስተዋጽኦ እንዴት ማበርከት እንዳለብን ሁሌም በተገናኘን ቁጥር እናወራለን፡፡ ምናልባትም ይህ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ራእይ ይዛ ለአገልግሎት የምትነሣበት ጊዜ ሊሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ፈቅዶና ወዶ አሁን የታሰበው ምርጫ ወደ ግቡ ደርሶ በጆሮአችን የምንሰማበት ደረጃ ከደረሰን ትልቅ ለውጥ ይኖራል፤ ከበፊቱም የተሻለ ነገር አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ ወጣቱ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ በአትኩሮት እንዲከታተል ያደረገው የሚሰማቸው፣ የሚያያቸው፣ እየተደረጉ ያሉ ትንሽም ቢሆን ፍንጭ የሚሰጡ ነገሮች ስላሉ ነው፡፡
ፓትርያርኩም ከተመረጡ በኋላ ብዙ ከሚጠብቃቸው ሥራዎች ዋና ዋናዎቹ፡- በመጀመሪያ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ችግር ሆነው ያሉ ነገሮችን ለመቅረፍ መነሣት አለባቸው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ፈተና ሆኖ ያለው የዘረኝነትና የገንዘብ ጉዳይ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ክህነት በዘር ነበር፤ የሌዊ ወገን የሆነ ነበር የሚያገኘው፡፡ በሐዲስ ኪዳን ግን ክርስቶስ ራሱ ሊቅ ካህናት ሆኖ ያለ ዘር ሁሉም ለዚህ አገልግሎት የታጨና ብቁ ሆኖ የቀረበውን ቤተ ክርስቲያን በምትሰጠው መስፈርት የሚያሟላ ከሆነ ይሾማል፡፡ ስለዚህ ተመራጩ ፓትርያርክ ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ የዘረኝነት መንፈስ ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ዘመን መነኩሴው የመነኮሰው ከየት ነው? የት ነው የተማረው? ምንኩስናውን የሰጠው ማነው? የሚለውን ሊመለከቱ ይገባል፡፡ እነዚህ ነገሮች ዛሬ ካልጠሩ፣ ነገ እነዚህ መነኮሳት ናቸው አድገው የጵጵስናን ማዕረግ የሚያገኙት፡፡ ስለዚህ ምንጩና መነሻው ያልታወቀ መነኩሴ ነገ የጵጵስናውን መዓርግ አግኝቶ ለቤተ ክርስቲያን አደጋ የሚሆንበት ነገር እንዳይፈጠር በመነኮሳት አሿሿምና አገልግሎት ላይ ክትትል ሊያደርጉ ይገባል፡፡
ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ገንዘብ የዘረፈ፣ የአስተዳደር በደል ያደረሰ፣ መንጋውን ሳይመራ በቤተ ክርስቲያን ላይ ችግር ሲፈጥር የነበረውን አባት ወደ ሌላ ቦታ ተወስዶ ይሾማል፡፡ ይህ የሚያሳየው በቀድሞው ቦታ ሲያጠፋ የነበረውን ጥፋት ሌላ ቦታ ሔዶ ይደግመዋል፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት አሠራሮች መቅረት መቻል አለባቸው፡፡ ዛሬ መንግሥት በሥራ ብልሹነት፣ በሙስና፣ በእምነት ማጉደል ከሓላፊነት የሚያነሣቸውን ሰዎች በሌላ ቦታ በሓላፊነት አይመድባቸውም እንዲቀጡ ያደርጋል እንጂ፤ በእኛም ቤተ ክርስቲያን እነዚህ ነገሮች መለመድ አለባቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት በቤተ ክርስቲያን ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የአንድ ክርስቶስ አካል እንደሆኑ ታስቦ ለአገልግሎት የሚያስፈልጉ ንዋየ ቅድሳትና በቂ መተዳደሪ ሀብት በእኩል መጠን ማግኘት ባለመቻላቸው ዕጣን፣ ጧፍ…፣ እንዲሁም አገልጋይ ካህናትም በማጣት እስከ መዘጋት የደረሱ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ጥሩ ገቢ ኖሯቸው፣ ጥሩ ደመወዝ የሚያገኙ ገዳማት አድባራት አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ የፋይናንስ አሠራሯን ማስተካከል ይጠበቅባታል፡፡ ተመራጩ ቅዱስ ፓትርያርክ ቤተ ክርስቲያን አንድ ወጥ የሆነ የፋይናንስ አያያዝ ሊኖራት እንደ ሚገባና የተቸገሩት እንዲረዱ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሌላው ቤተ ክርስቲያን የምታደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ የምንሰማው ከቤተ ክርስቲያን ሳይሆን፤ ከውጭ አካላት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በፓርላማ ስብሰባ ጊዜ “በፓርላማው እንዲህ፣ እንዲህ አንኳር ነገሮች ተነግረዋል፤ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡ በማለት መገናኛ ብዙኃኑ ለሕዝቡ መረጃ ያቀብላሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ግን በየጊዜው ምን እየተደረገ? ምን እየተሠራ? እንዳለ አናውቅም፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን ግን ቤተ ክርስቲያኗ የሠራቻቸውን መስማት፣ ማወቅ ያለብን ከቤተ ክርስቲያኗ ነው፡፡ ተመራጩ ፓትርያርኩም ለዚህ ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ወቅታዊ መረጃዎች ለምእመናን የሚደርሱበትን መንገድ ሊያመቻቹ ይገባል፡፡
ስለ ነገዋ ቤተ ክርስቲያን ዕድገት ወጣቶችን የሚመለከተን በመሆኑ፤ በምን አቅጣጫ መሔድ፣ አስተዋጽኦአችንንም እንዴት ማበርከት እንዳለብን ከአባቶቻችን ጋር በመመካከር የድርሻችንን እንወጣ፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ይበጃል የምንለውን ገንቢ የሆኑ አስተያየቶች አሁን በሐመር መጽሔት በሚሰጥበት አግባብ እንስጥ፡፡
-
ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት 20ኛ ዓመት ቁጥር 7 ኅዳር 2005 ዓ.ም.