ረብሐ ግሥ

ጥቅምት ፲፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? የእግዚአብሔር አምላካችን ስም የተመሰገነ ይሁን! የጥቅምት ወር የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜያችን ወደ ሆነው ትምህርት ከመግባታችን በፊት ስለ ባለፈው ጥቂት እናስታውሳችሁ፡፡ ከዘመን መለወጫ ጋር ተያይዞ ለንግግር የሚጠቅሙንን የመግባቢያ ዓረፍተ ነገሮችና የንግግር ስልቶች አቅርበንላችሁ ነበር፡፡ ይህም ለእናንተ የንግግር ክህሎት በሚረዳ መልኩ አዘጋጅተን ያቀረብንላችሁ በ፳፻፲፬ ዓመተ ምሕረት በድረ ገጹ በቀረቡት ትምህርቶች የተማራችኋቸውን ቃላትም ሆነ ግሦች በመጠቀም እንድትለማመዷቸው በማሰብ ነው፤ ይህንን ተግባራዊ እንዳደረጋችሁትም ተስፋችን ነው፡፡

ታስታውሱ እንደሆነ ያለፈው ዓመት የመጨረሻ ትምህርታችን ስለ ነገረ ግሥና አገባብ ነበር፤ እንደሚታወቀው ዓረፍተ ነገሮችን ለመሥራት የሚጠቅሙን ከስሞች ቀጥሎ በዋነኛነት ግሦች በመሆናቸው በእነርሱ ላይ የበለጠ ትኩረት አድርገን በዚህ ሳምንት ያቀረብንላችሁ ትምህርት ከግሥ ዓይነቶች አንዱ ስለሆነው ረብሐ ግሥ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን ስለ ግሥ ምንነት ደግመን እናስታውሳችሁ፡፡

ግሥ ማለት የተሠሩ ወይም የተሰበሰቡ ቃላትን መልእክት እንዲያስተላልፍ በዓረፍተ ነገር ውስጥ በመገኘት የሚያስር /የሚሰበስብ/ ቃል ማለት ነው።

ረብሐ ግሥ፡- ይህ የግሥ ዓይነት ዘማች ግሦችን ከቀዳማይ አንቀጽ ጀምሮ እስከ አርእስት እና ከዚያ በላይ ያሉትን ቅጽሎችን የሚያገሰግስ ማለት ነው፡፡ (ቀዳማይ አንቀጽን ማርባት/መተንተን ማለት ነው)

መራኁተ ግሥ፡- እነዚህ ደግሞ የፊደላት ዓይነት ሲሆኑ ሁልጊዜ በግሡ መጀመሪያ ላይ የሚገኙ ናቸው። መንሥኤ ግሥ ወይም አርኃውያን ተብለው ይጠራሉ። ግሥ የሚያስነሱ ቀለማት ተብለውም ይጠራሉ፤ እነዚህም፡-

ግእዝ ራብዕ ኃምስ ሳድስ እና ሳብዕ ናቸው።

ምሳሌ፡- ግእዝ—-ቀተለ፣ ቀደሰ፣ ተንበለ

ራብዕ—-ባረከ፣ ማህረከ

ኀምስ—-ሴሰየ

ሳድስ—-ክህለ

ሳብዕ—-ጦመረ ናቸው፡፡

መሠረታዊ ግሥ (ዘማች ቀዳማይ አንቀጽ) ተመሥርቶ የሚገኘው በሦስተኛ መደብ ወንድ ነጠላ ቁጥር ነው (ውእቱ)፡፡

ግሥ የማያስነሱ ቀለማቶች ሁለት ናቸው፤ ማን ማን ናቸው ቢሉ ካዕብ እና ሣልስ ናቸው።

ምሳሌ፡- ሖረ ቴሀ ይላል እንጂ ሑረ ቲሀ አይልም፡፡

  • የግሥ መድረሻ ቀለማቶች ሁለት ናቸው፤ እነዚህም ግእዝ እና ኃምስ ናቸው።
  • የግእዝ ማስረጃ ከሀ እስከ ፐ የሚገኙ ግሦች በሙሉ ናቸው።
  • የኃምስ ግን አንድ ይቤ ብቻ ነው፡፡ ይቤማ ነባር አንቀጽ አይደለም ቢሉ ካልአዩን፣ ዘንዱን፣ ትእዛዙን ይዞ ስለተገኘ ነው።

የረብሐ ግሥ ዓይነቶች

ግሥ የሚረባበት ሁለት ዓይነት መንገድ አለው። እነዚህም፡

ሀ. የዋህ ረብሐ ግሥ

ለ. መሠሪ ረብሐ ግሥ ናቸው፡፡

. የዋህ ረብሐ ግሥ

ግሥን በውእቱ ባለቤትነት (ዘማች አንቀጽ በውእቱ ስለሚጠሩ ስለሚመሠረቱ) በመራሕያን ባለቤትነት በግሥ አርስቶች ተመሥርቶ መገሰስ /ማገስገስ/ የዋህ ረብሐ ግሥ ተብሎ ይጠራል።

ምሳሌ፡

ቀተለ ቀደሰ ተንበለ
ይቀትል ይቄድስ ይተነብል
ይቅትል ይቀድስ ይተንብል
ይቅትል ይቀድስ ይተንብል
ቀቲል/ቀቲሎት ቀድሶ/ቀድሶት ተንብሎ/ተንብሎት
ቀታሊ/ቀታልያን ቀዳሲ/ቀዳስያን ተንባሊ/ተንባልያን
ቀታሊት/ቀታልያት ቀዳሲት/ቀዳስያት ተንባሊት/ተንባልያት

ሌሎችን ግሦችም በዚህ መልክ እና በመራሕያን ሙሉ ለሙሉ መዘርዘር ይቻላል፡፡

. መሠሪ ረብሐ ግስ

መሠሪ ግሥ የሚረባበት የርባታ ስልት መሠሪ ረብሓ ግሥ ይባላል፡፡ መሠሪ የሚል የስያሜ ቅጽል የተቀጸለበትም ምክንያት የግሥ መደበኛ ዘር በባለቤት ዝርዝር ላይ ሎቱን፣ ቦቱን ፣ የተሳቢ ዝርዝርን እየጨመረ በበጎ እና በክፉ ነገር ስለሚነገር /ስለሚተረጎም/ ነው።

ምሳሌ፡-

ተለውኩ ቦቱ ተከተልኩበት
ተለውኩ ሎቱ ተከተልኩለት
ተለውኩ ላቲ ተከተልኩላት
ተለውኩ ባቲ ተከተልኩባት
ተለውኩ ሎሙ ተከተልኩላቸው
ተለውኩ ቦሙ ተከተልኩባቸው

ሎቱ የበጐ ነገር አመልካች

ቦቱ የክፉ ነገር አመልካች ናቸው።

የተሳቢ ዝርዝርን ጨምሮ ሲነገር

ሎቱ እና ቦቱ በንባብ ሳይገለጹ በተሳቢ ዝርዝር ድምጽ ብቻ እየተነገሩ በጐንና ክፉ ነገርን ያመለክታሉ። በዚህ ጊዜ የመሠሪ ግሥ በጐና ክፉ ስሜት በንባብ ተለይተው አይታቁም።

ምሳሌ፡-

ተለውኩከ ተከተልኩህ (በጐም ክፉም)
ተለውኩከ ተከተልኩልህ (በጐኛ)
ተለውኩከ ተከተልኩብህ (ክፉኛ)

—(አሕየዎ ኢየሱስ ለመፃጉዕ፤ ኢየሱስ ሽባውን አዳናው) ሎቱ

—(ወአኀብኦሙ ሞክሮሙ ለመካርያን፤ የመካሪዎችን ምክራቸውን እሸሽግባቸዋለሁ) ቦቱ

እያንዳንዱ ግሥ በዚህ አማርኛ ተፈቶ በበጎና በክፉ በመነገር በ ፪፻፵ (ሁለት መቶ ዐርባ) ወይም ፪፻፹፰ (በሁለት መቶ ሰማንያ ስምንት) ዓበይት አናቅጽ ይገሰሳል።

ቀዳማይ ፹ ቀዳማይ ፺፮

ካልአይ ፹ ካልአይ ፺፮

ሣልሳይ ፹ ሣልሳይ ፺፮

ጠቅላላ ፪፻፵ ጠቅላላ ፪፻፹፰

፫ ሲባዛ በ፹—፪፻፵ ይሆናል፤ ፺፮ ሲባዛ በ፫—፪፻፹፰ ይሆናል፡፡

ምሳሌ፡-

ተለውኩከ ተለውኩኪ አእመርኩከ አእመርኩኪ
እተልወከ እተልወኪ አአምረከ አአምረኪ
እትሉከ እትሉኪ አእምርከ አእምርኪ
እትሉከ እትሉኪ አእምርከ አእምርኪ
ተለውኩክሙ ተለውኩክን አእመርኩክሙ አእመርኩክን
እተልወክሙ እተልዎክን አአምረክሙ አአምረክን
እትሉክሙ እትሉክን አእምርክሙ አእምርክን
እትሉክሙ እትሉክን አእምርክሙ አእምርክን

ከዚህ ላይ ይህን ቁጥር ልናመጣው የቻልንበት ሁኔታ ምንድን ነው ቢሉ አንዱ መራሒ ሌሎችን ስምንቱን ሲያውቃቸው ወይም ሲከተላቸው ፲ መራሕያን እያንዳንዳቸው ፹ ይሆናሉ፡፡ ይህን በቀዳማይ በካልአይ፣ በሣልሳይ አንቀጽ ስንመለከተው ፪፻፵ ይሆናል። ይህ የሚሆነው በቅርቦች እና በአነ፣ በንሕነ ነው።

  • በሩቆች ግን አንዱ/ ውእቱ የቅርቦችን፣ የሩቆችን እና የንሕነ የአነንን ስለሚያውቅ ወይም ስለሚያሰማ ፲፪ ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት ቀዳማይ አንቀጽ ፺፮ ካልአይ ፺፮ እና ሣልሳይ ፺፮ ይሆንና በጠቅላለው ፪፻፹፰ ይሆናል ማለት ነው።
  • የዋህ ግሥ እና መሠሪ ግሥ ልዩነታቸው ይህ ነው?

ምሳሌ፡የዋህ—መሠሪ

ረስየ ረስዮ
ረስዐ ረስዖ
ርእየ ርእዮ
ሰምዐ ሰምዖ
ቀደመ ቀደሞ
ቀጥቀጠ ቀጥቀጦ
ቀጸበ ቀጸቦ

ምንጭ፡- ሰዋስው ወልሳነ ግእዝ መጽሐፍ ከገጽ ፸፭‐፸፱