ሥራህን ሥራ
በሁዳዱ መሬት መልካም በሚያፈራው
ሠራተኛው ጥቂት መኸሩ ብዙ ነው
የእርሻው ጦም ማደር አንተን አስጨንቆህ
ከወጣህ ልትሠራ ወገብህን ታጥቀህ
አንተ ! . . . ጎበዝ . . . ደስ ይበልህ
የደረቀ መሬት . . . አለስልሰህ ዘርተህ
የአበባው ጊዜ አልፎ . . . ፍሬውን ታያለህ
በስራህ በርትተህ . . . ፀሐይ ብትጠልቅም ምሽቱ ቢነጋ
ሰነፍ ቢያንጓጥጥህ በነገር ቢተጋ
መልስ ለመመለስ . . . ወደ ኋላ አትዙር . . . በከንቱ አትድከም
ማሳው እንዳይጠፋ . . . እንዳይበላው አረም
የተዘራው ፍሬ ሠላሳ እና ስልሳ መቶ እንዲያፈራ
የተሰጠኸውን . . . ሥራ ብቻ ሥራ