ሠራተኛ ጉባኤያት በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ድርሻ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ
ሚያዚያ 15 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዳዊት ደስታ
የማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል የሠራተኛ ጉባኤ የአንድነት መርሐ ግብር ሚያዚያ 13 ቀን 2005 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተካሄደው መርሐ ግብር ሠራተኛ ጉባኤያት በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ድርሻ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ፡፡
የመርሐ ግብሩን ዓላማ አስመልክቶ የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ሓላፊ የሆኑት ኀይለ ማርያም መድኅን “በአዲስ አበባ ማእከል ሥር ሆነው የሚማሩ 22 የሚደርሱ የሠራተኛ ጉባኤያት ለቤተ ክርስቲያን እውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውን ሊያበረክቱ የሚያስችላቸውን ነገር ማስጨበጥና በተደራጀ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን በአቅም ማገልገል የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው” በማለት ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም እንደዚህ ዓይነት መርሐ ግብር ሲዘጋጅ የመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ ወደፊት የተለያዩ የሠራተኛ ጉባኤያትን በአንድነት ለማጠናከር በቤተ ክርስቲያን ከዚህ ቀደም ከሚሠሩት የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ ለማድረግ የታሰበ ነው በማለት ሓላፊው ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ “የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮና ዓላማ እና የልጆቿ ድርሻ” በሚል ጥናታዊ ጽሑፍ፣ ትምህርተ ወንጌልና መዝሙር ቀርቧል፡፡ በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ አስተያየትና ጥያቄዎች ቀርበው ከጥናት አቅራቢው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ሲሳተፉ ያገኘናቸው አቶ ተስፋዬ አሻግሬ “በዛሬዋ ቀን በመገኘቴ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ ምክንያቱም በርካታ መሥሪያ ቤቶች ጉባኤ ያካሂዳሉ፡፡ ከመማር ባለፈ ምንም ድርሻ እንዳለን እንኳ አናውቅም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ቤተ ክርስቲያናችን ከኛ ከልጆቿ ብዙ ነገር እንደምትጠብቅና መሥራት እንደምንችል አውቄበታለው” በማለት ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ በተደረገው መርሐ ግብር ከአምስት መቶ በላይ የሆኑ በተለያየ መሥሪያ ቤት የሚሠሩ የሠራተኛ ጉባኤ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡