ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሊጠብቁ ይገባል!
ሐምሌ ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
ሥርዓት የሃይማኖት መገለጫ እንደመሆኑ በመሠረት እምነት (ዶግማ) የምናምንባቸውን ተግባር የምንገልጽበትና ተግባራዊ የምናደርግበት መንገድ ነው፤ ሥርዓቱ ሲሠራና ሲፈጸምም ሃይማኖታዊ አንድምታና ነጸብራቅ ይኖረዋል፡፡ ጥምቀት፣ጸሎት፣ ቅዳሴ፣ ቁርባን፣ ጾም፣ ስግደት እንዲሁም ሌሎች የሃይማኖት ምሥጢራትን ለመፈጸም በማመን ብቻ የሚያበቁ ሳይሆኑ የአፈጻጸምና አተገባበር መንገድ (ሥርዓት) ያስፈልጋቸዋልና፡፡
በቤተ ክርስቲያን በቁጥር በርካታ የሆኑ ምእመናን አንድ መሆን እንዲችሉ ሥርዓትን ሠርታለች፡፡ ማኅበረ ምእመናን የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ብዙ ቢሆኑም እንኳን አንድ ልብና አንድ ሐሳብ ሆነው እንዲጸልዩ፣ እንዲሰግዱ፣ እንዲያመሰግኑ፣ እንዲያስቀድሱ፣ እንዲቆርቡ እንዲሁም እንዲዘምሩ ለማድረግ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ካህናት ሲቀድሱ ምእመናን በኅበረት ተሰጥኦ ይቀበላሉ፤ በጋራ ሆነው ይጸልያሉ፤ በዓላትን በአንድነት ያከብራሉ፤ በሰንበት ጽዋ ማኅበር በአንድነት ያዘጋጃሉ፤ ቅዱሳንን በጋር ይዘክራሉ፡፡
ነገር ግን ይህን የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሚጻረሩ ተግባራትን የሚፈጽሙ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን በድፍረት ሲገቡ መመልከት ከጀመርን ሰንብተናል፡፡ ለምሳሌ የቅዳሴ ሥርዓትን አቋርጦ መግባትና መውጣት፣ በትምህርተ ወንጌልም፣ በቅዳሴ እንዲሁም በሌሎች የጸሎት ሰዓታት ላይ ማውራት፣ ሥርዓት የሌለው አልባሳት በተለይም ሴቶቸ (አጭር እና ሰውነትን የሚያሳይ ልብስ) መልበስና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ሥርዓቱን መጠበቅ ሲገባ ግን የመተላለፋችን ምክንያት አንድም ሥርዓቱን ባለማወቅ ስለሆነ እያንዳንዱ ምእመን መጠበቅ ያለበትን ሥርዓት ማወቅና መተግበር ይጠበቅበታል፡፡
የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እጅግ አስፈላጊ ነው፤ የሥርዓቱ ተጠቃሚዎችም ካህናቱና ምእመኑ እግዚአብሔርን ለማገልገልና አምልኮትም ለመፈጸም ይጠቅማቸዋልና ዕውቀቱም ሆነ ትጋቱ ከሁለቱም ወገን አስፈላጊ ነው፡፡ ምእመናን ለቤተ ክርስቲያንና በውስጧ ለሚገኙ ንዋየ ቅድሳት ተገቢውን ክብርና ጥንቃቄ እንዲያውቁ፣ አውቀውም የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንዲጠብቁ እንዲሁም የተቻላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ይጠበቃል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ትውፊትም ተጠብቆ እንዲቆይና ለትውልድ እንዲተላለፍ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው፡፡
ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሚደረግ ክብርና ጥንቃቄ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ዋጅቶ የመሠረታት እንዲሁም ወደ እርሱ የቀረቡትንም የምታክብር የእግዚአብሔር ቤት ናት፡፡ በመሆኑም ወደ እርሷ ስንሄድ የሚገባ ክብርና ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ ሥርዓትን በመጠበቅ ረገድ እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይም ሆነ ምእመን ተገቢውን ክብርና ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ ይህም ማለት ሥርዓቷን በመጠበቅና በማስጠበቅ ሁሉም የተቻለውን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የሚደረግ ጥንቃቄና ክብር ማለትም ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚደረግ ማለት ነውና፡፡
የልቡና ዝግጅት
ማንኛውም ምእመን ወደ ቤተ መቅደስ ለመሄድ ሲያስብ አስቀድሞ የልቡና ዝግጅት ያስፈልገዋል፡፡ ይኸውም ልቡናውን ከቂም ከበቀል፣ ከክፋት ከተንኮል ከዝሙት ንጹሕ የማድረግ ዝግጅት ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ አስቀድሞ ራሱን “ካልመረመረ ልቡናንና ኩላሊትን የሚመረምር እግዚአብሔር ይመረምረዋልና፡፡ (መዝ.፯፥፱፣ዘዳግ. ፲፥፲፮፣ መዝ.፶፥፲፯)
ንጹሕና ሥርዓት ያለው ልብስ መልበስ
ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤት በመሆኗ ውስጣችንም ሆነ ውጫችንም ንጹሕ መሆን ስለሚጠበቅበት የምንለብሰው ልብስ ልክ እንደ ልቡናችን ንጹሕ መሆን አለበት፡፡ ቤተ መቅደስ የጌቶች ጌታ የነገሥታት ንጉሥ የሐዲስ ኪዳኑ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሠዋበት ንጹሕ /ቅዱስ/ ቦታ ነው፡፡ እመቤታችንም ቅድስት ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ሐዋርያት ነቢያት ጻድቃን እንዲሁም ሰማዕታት ሁሉ ጋር በረድኤት ከእኛ ጋር ስለሚኖሩ ንጹሕ ልንሆን ይገባል፡፡ ስለዚህ ወደ ቤተ መቅደስ በምንሄድበት ቀን ንጽሕናችንን መጠበቅና ነጭ መልበስ አለብን፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ሰውነትን የሚሸፍን ልብስ መልበስ እንደሚገባ ልናውቅ ይገባል፤ በተለይም ሴቶች ረዥም ቀሚስ እንጂ አጭር ቀሚስ ወይንም ሰውነትን የሚያሳይ ልብስ መልበስ የለባቸውም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር ቤት ስንሄድ ሀሳባችንም ሆነ ልባችንን በሙሉ ለአምላካችን መስጠን ሲኖርብን ነገር ግን ሥርዓት የሌለው አለባበስ በተለይም ሰውነትን የሚያሳይ ልብስ የምንለብስ ከሆነ ሀሳባችን ከመበታተኑም በላይ በውስጣችን የዝሙት ሀሳቦች ሊመጡብንና ኃጢአት ሊያሠሩን ይችላሉና ክርስቲያናዊ አለባበስን ልንጠብቅ ይገባል፡፡
ልብስን ማደግደግ ወይም ነጠላን በትእምርተ መስቀል መልብስ
ከነጭ ልብሳችን ጋር የምንለብሰው ነጠላችን ግራና ቀኝ በትእምርተ መስቀል አምሳል የሚለበሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል ጌታችን በዓርብ ቀን የተቀበላቸውን መከራና ለማሰብና በመልእልተ መስቀል መሰቀሉን ለማሰብ ነው፡፡
ነጭ ልብስ የምንለብስበት ምክንያት
፩. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ሳለ ፍጹምነቱንና ክብሩን የሚገልጽ ነጭ ልብስ ለብሷል፤ ቤተ ክርስቲያንም ክብርት ቤቱ ስትሆን ከምእመን ጋር አንድ የሚሆንባት የሠርግ ቤት ስለሆነች ወደ እርሷ ስንሄድ እንደ ሙሽራ የምንለሰብሰው ነጭ መሆን አለበት፡፡
በምድራዊ ሕይወታቸው መከራና ሥቃይ ተቀብሎው ተጋድሎአቸውን የፈጸሙ በክብር ከሚያልፈው ዓለም ወደ ማያልፈው ዓለም የሄዱ የቅዱሳን፣ የጻድቃን እና የሰማዕታት መገለጫም እንዲሁ ነጭ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ዋጅቶ ወደ መሠራት ቤቱ ስንሄድ በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን መንግሥተ ሰማይቱን እንደምንወርስ እያመንንና እያስብን ነጭ እንለብሳለን፡፡
፪. ቅዱሳን መላእክት ከእኛ ጋር መሆናቸውን ለማሰብ
ቅዱሳን መላእክት በክብራቸው የሚገለጡት ከበረዶ ይልቅ የነጣ ነጭ ልብስ ለብሰው ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶና ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኃላ ቅዱሳን አንስት ሽቶ ሊቀቡት ወደ ተቀበረበት ቦታ ሲሄዱ መላእክት ነጭ ልብሰው ለብሰው ተገልጠውላቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ነጭ መልበስ ለእነርሱ መታሰቢያም ነው፡፡ (ማቴ.፳፰፥፪-፮)
መባዕ /ሥጦታ/ መስጠት
እያንዳንዱ ምእመን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄድ ካለው ባዶ እጁን ይሄድ ዘንድ ተገቢ አይደለም፡፡ መባዕ ወይንም ስጦታ የሚሆን ዕጣን፣ ሻማ፣ ጧፍ ሊሰጥ ይገባል፡፡ መባዕ መስጠት እንዳለብን የእግዚአብሔር ቃል ያዛልና፡፡ (ዘፀ. ፳፭፥፪፣ዘሌ. ፩፥፫፣ዘኁ.፯፥፲፪)
በትምእርተ መስቀል አማትቦ ደጃፉን መሳለም
በአንድ አምላክ ቅድስት ሥላሴ ስም መላ ሰውነታችንን በትምእርተ መስቀል ምልክት በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ስም ማማተብ ሁሌም መዘንጋት የለበትም፡፡ የዚህም ትርጉም እግዘኢብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማይት ወርዶ በመስቀል ተሰቅሎና ወደ ሲኮል ወርዶ ነፍሳትን አውጥቶ ወደ ገነት እንዳስገባቸው የሚያመለክት ነው፡፡
የቤተ መቅደስን በር መሳለም
በትእምርተ መስቀል ካማተብን በኋላ የቤተ ክርስቲያንን ቅጽር (ደጅ) በመሳም ወደ ውስጥ በሥርዓት መዝለቅ ያስፈልጋል፡፡
በቤተ መቅደስ ውስጥ መስገድ
በመጽሐፍ ቅዱሰ ተጽፎ እንደሚገኘው አንድ ምእመን ወደ ቤተ መቅደሱ ከገባ በኋላ ለፈጣሪው እግዚአብሔር የአምልኮት ስግደት መስገድ አለበት፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን ለአምላኩ እግዚአብሔር በቤተ መቅደስ እንደሰገደ እና አምላክም ደስ እንደተሰኘበት ሁሉ እኛም በቤቱ ተገኝተን የሁሉ አምላክ ለሆነው የሚገባ ክብር በመስጠት ልንሰግድ ይገባል፡፡ (፪ኛዜና.፯፥፫)
በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ላሉት ቅዱሳት ሥዕላት (ስዕለ አድኅኖ) መስገድ
ቅዱሳን ሥዕላት በቤተ መቅደስ ተሥለው አንዲቀመጡ እንዲሁም አንዲሠገድላቸው የእግዚአብሔር ክብር ፈቃዱ ነው፡፡ ቅዱሳት ሥዕላትን መሳል የተጀመረው በኦሪት ዘመን ሙሴ በእግዚአብሔር ታዝዞ በታቦቱ ማደሪያ በሥርዓት መክደኛው ላይ የቅዱሳን መላእክትን (የኪሩቤል) ምስል በሳለበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ቅዱሳት ሥዕላትን አክብረን እነርሱን የፈጠረ እና ያከበረ አምላክ እግዚአብሔርን በማመስገን ልንሰግድላቸው ይገባል፡፡ (ዘፀ. ፳፭፥፲፰)
ጫማ አድርጎ ወደ ቤተ መቅደስ አለመግባት
ቤተ መቅደስ የተቀደሰች ሥፍራ በመሆኗ በውስጧ ስንቆም ጫማችን ልናወልቅ እንደሚገባ ቅዱሳት መጻሕፍት ይጠቅሳሉ፡፡ የእግዚአብሔር ሰራዊት አለቃም ኢያሱን ‹‹የቆምክባት ምድር የተቀደሰች ናትና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ … ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው፤ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ›› እንዲል፤ (ኢያ. ፭፥፲፭)
ታቦተ ሕጉ ወደ አለበት፣ መሥዋዕት ወደ ሚሠዋበት፣ ቃለ እግዚአብሔር ወደ ሚነገርበት አንዲሁም ቅዱሳን መላእክት ወደ ሚዘምሩበት ቅዱስ ሥፍራ ወደ እግዚአብሔር ቤት ስንገባ ጫማችንን ማውለቅ አለብን፡፡
ነውር ያለበት ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን አለመግባት
ቤተ ክርስቲያን የእግዘኢብሔር ቤት በመሆኗ አፍአዊ የሰውነታችንንም ሆነ የልብሳችን ንጽሕና ልንጠብቅ እንደሚገባን ከተረዳን በአካላችን ላይ የሚሸትና የሚያዥል ቊስል ካለብን ወይንም የተለያየ ፈሳሽ ከሰውነታችን የሚወጣ ከሆነ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መግባት የለበትም፤ ሥጋወ ደሙንም መቀበል አይገባውም፡፡
ሴት ልጅ በወር አበባ በምታይበት ወቅት ቤተ መቅደስ አለመግባት
- ከላይ እንደተገለጸው አንድ ምእመን ከሰውነቱ ፈሳሽ የሚወጣ ከሆነ ወደ ቤተ መቅደስ መግባት አይችልምና ሴትም የወር አበባ በምታይበት ወቀት ወደ ቤተ መቅደስ መግባት አይፈቀድላትም፡፡
- ሥጋ ወደሙ መቀበል ስለማትችል
በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሴት ልጅ ልማደ አንስት (በወር አበባ) ወቅት ወደ ቤተ መቅደስ እንድትገባ እንደማይፈቀድላት ሁሉ ንጹሕ ሳትሆን ወይንም ከደም ሳትነጻ ሥጋ ወደሙን መቀበል አትችልም፡፡
- በአቅም ማነስ
በወር አበባ ወቅት ሴት ልጅ የተለያዩ ሕመምና ድካም ስሜት በሰውነቷ ላይ ስለሚፈጠር ቆማ ማስቀደስ ወይንም መስገድ አይቻላትም፡፡ ስለዚህም አምልኮተ እግዚአብሔርን መፈጸም ስለማትችል ወደ ቤተ መቅደስ መግባት አይፈቀድላትም፡፡ ሆኖም ግን በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ዙሪያ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብና መጸለይ አትከለከልም፡፡
የሌሊት ልብስ ወይም የአሕዛብ ልብስ ለብሶ ወደ ቤተ መቅደስ አለመግባት
ምእመናን ወደ ቤተ መቅደስ ለብሰው መግባት ከሌለባቸው አልባሳት መካካል የሌሊት ልብስ አንዱ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያት የሌሊት ልብስ በመኝታ ሰዓት የሚለበስ ብቻ በመሆኑና ሊቆሽሽም ስለሚችል ለጸሎትም ሆነ ለቅዳሴ እንደዚያ ዓይነት ልብስ ለብሶ ወደ ቤተ መቅደስ ስለማይገባ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በቤተ ክርስቲያን የሚለበሱ አልባሳት በቀን የምንለብሳቸውን ንጽሕናቸው የተጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሄድ የሰውነታችንን ንጽሕና መጠበቅ አንደሚገባ መረዳት አለብን፡፡ የምንለብሰው ልብስም ሰውነትን የሚሸፍን መሆን አለበት፡፡
ወንድ ልጅ ሕልመ ሌሊት/ዝንየት/ ከመታው በዕለቱ ቤተ መቅደስ አለመግባት
አንድ ወንድ ምእመን በመኝታ ጊዜ ሕልመ ሌሊት /ዝንየት/ ከታየው ወይንም ከሰውነቱ ዘር ፈሳሽ ከወጣ ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት የለበትም፡፡ በማግሥቱ ግን ሰውነቱን ታጥቦ መግባት ይችላል፡፡
ባልና ሚስት ከተራክቦ በኋላ ዕለቱን ወደ ቤተ መቅደሱ አለመግባት
ምንም እንኳን ጋብቻ ቅዱስ መኝታውም ንጹሕ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ባልና ሚስት ሩካቤ ከፈጸሙ በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ መግባት አይፈቀድላቸውም፡፡ የዚህም ምክንያት ባለ ትዳሮች ተራክቦ የሚታገዱት በአጽዋማት፣ በዓላት፣ በጸሎት እና በቅዳሴ በመሆኑ እነዚህን ሥርዓት በቤተ ክርስቲያን መተግበር አይቻላቸውም፡፡
በቤተ መቅደስ ውስጥ ዋዛ ፈዛዛ ነገር አለመነገር (መሳቅ እና መሳለቅ ክልክል ነው)
ማንኛውንም ምእመን ወደ ቤተ መቅደስ ከገባ በኋላ ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት ለመነገጋር፣ ለማመስግን፣ እንዲሁም አምላኮት ለመፈጸም በጸጥታና በፍርሃት ማገልግል አለበት፡፡ ምንም ዓይነት ንግግርም ማድረግም ሆነ ቀልድ ማውራት የተከለከለ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደተናገረው ‹‹በምድራዊ ንጉሥ በቆምህ ጊዜ በምንም ምክንያት ቢሆን ለመሳቅ አትደፍርም፤ ታዲያ በሰማያዊ ንጉሠ ነገሥ ፊት ትስቃለህን;›› ብሏል፡፡ በተጨማሪም ‹‹በቅዳሴ ጊዜ የሚስቅ ዓለማዊ ቢሆን ወደ ውጭ ያውጡት፤ ከቅዱስ ቊርባንም አያቀብሉት›› ተብሎ እንደተነገረው የእግዚአብሔር ቤት የተቀደስች በመሆኗ ክብር ሰጥተን በፍርሃት ልንገለገልና ልናገለግል ይገባል እንጂ ሥርዓቱ በሚፈጸምበት ጊዜ በድፍረት እኩይ ተግባራትን መፈጸም ኃጢአት በመሆኑ ለቅጣት እንደሚዳርገን አውቆ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ (ዮሐንስ አፈወርቅ በመጽ. ምሥ. አን. ፮፣ ቀኖናና ሥርዓት አን. ፱)
አብዝቶ መጠጥ ጠትቶ ወይንም ሰክሮ ወደ ቤተ መቅደስ አለመግባት
ቤተ ክርስቲያን የሥጋዎ መገኛ በመሆኗ ‹‹እንዳትሞቱ ወደ መገናኛው ድንኳን ስትገቡ አንተና ልጆችህ የወይን ጠጅና የሚያሰክር ነገር ሁሉ አትጠጡ›› እንደተባለው ወደ እርሷ የሚገባ ካህንም ሆነ ምእመን መጠጥ አብዝቶ ከጠጣ በኋላ ከእነ ስካር መንፈሱ ለአገልግሎት ወደ ቤተ መቅደስ መግባት አይፈቀድለትም፡፡ አንድም ስካር ኃጢአት በመሆኑ እግዚአብሔር አምላክን ያስቆጣል፤ ያሳዝናልም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አብረውት ሥርዓቱን የሚጠብቁ ሌሎች ካህናትና ምእመናን በመጥፎ ጠረን ስለሚረብሽ ኅሊናቸውን ሰብስበው እንዳይጸልዩና ቅዳሴን እንዳይከታተሉ ይከለክላቸዋል፡፡ (ዘሌ. ፲፥፰-፲)
በቂም በቀል ሰውን አስቀይሞ፣ የሰውን ገንዘብ በማጭበርበር ወስዶ ወደ ቤተ ክርስቲያን አለመግባት
በቤተ ክርስቲያን ጸሎት ለማድረስ ልቦናችን በምናዘጋጅበት ጊዜ ኅሊናችን ንጹሕ የሚሆነው የእግዚአብሔርን ሕግ መጠበቅ ስንችል ነው፡፡ እግዚአብሔርን ለመማጸን ስንዘጋጅ ሌላ ሰውን በቂል በቀል አስቀይመን ከሆነ ፈጣሪያችን ጸሎታችንን እንደማይቀበለን መረዳት አለብን፡፡ ምክንያቱም ለሠራነው ኃጢአት ንስሓ ስለሚያስፈልገን ተጸጽተን የደበልነውን ሰው ይቅርታ መጠየቅና ፈጣሪያችንንም ይቅር እንዲለን መማጸን አለብን እንጂ በድፍረት ኃጢአት እንዳልሠራ ሰው ይቅርታን ከመጠየቅ ይልቅ ሥርዓቱን በዘፈቀደ ለመካፈል ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት ያስቀጣል፡፡ ‹‹ለጸሎት በቆማችሁ ጊዜ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ በምንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉ፡፡ እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁ ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም›› እንዲል፤ (ማር፣ ፲፩፥፳፭)
ከዚህም ጋር ተያይዞ የሰውን ገንዘብ በማጭበር ከወሰድን በኋላ በማስረሳት ጥፋተኝነታችንን አምነኖ ባለመቀበል ከእነ በደላችን ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት ኃጢአት መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ልብ ኩላለቲት የሚመረምር አምላክ የውስጣችንን ያውቃልና ለሠራነው ኃጢአት ሥርየት ሳናገኝ ወደ ቤቱ በድፍረት ከገባን በኋለኛው ዘመን ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ ይቀጣናል፡፡
በቤተ ክርስቲያን በቅዳሴ ጊዜ አቋርጦ አለመውጣት
ቤተ ክርስቲያን የሚጸለዩ ጸሎት በሙሉ በትዕግሥት ሊፈጸሙ የሚገቡ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ምእመንም በጸሎት ጊዜያቱን በትዕግሥት መታደም ይጠበቅበታል፡፡ ይህም ማለት በቅዳሴ ጊዜ ቅዳሴ ከተጀመረበት ሰዓት አንሥቶ በሰላም ግቡ እስከሚባልበት ሰዓት ድረስ በትዕግሥትና ሥርዓቱን መካፈል አስፈላጊ ነው፡፡ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ካልሆነ በስተቀር ቅዳሴ ማቋረጥ አይፈቀድም፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴ ሲጀመር እንደሚባለው ‹‹በቅዳሴ ጊዜ ከምእመን ወገን ወደ ቤተ ክርስቲያን የገባ ሰው ቢኖር ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሮ የቅዳሴው ጸሎት እስኪፈጸም ባይታገሥ ከቊርባንም ባይካፈል ከቤተ ክርስቲያን ይለይ፤ የእግዚአብሔርን ሕግ አፍርሷልና፤ የነፍስና የሥጋ ንጉሥ በሚሆን በሰማያዊ ንጉሥ ፊት መቆምን አቃሏልና›› ብለው ሐዋርያት እንዳስተማሩን ቅዳሴን ማቋረጥ የለብንም፡፡
በቤተ ክርስቲያን በማኅበር ጸሎት ወቅት የግል ጸሎት አለማድረስ
ነቢዩ ዳዊት ‹‹ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ መልካም እነሆ ያማረ ነው›› ብሎ እንደተናገረው በኅብረት መጸለይና መዘመር ተገቢ ነው፡፡ (መዝ. ፻፴፫፥፩)
ቅዱሳን ሐዋርያት በኅብረት የመጸለይን መልካምነት ተረድተው በአንድ ልብ ሆነው ይገቱ እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል፡፡ (የሐ. ሥራ.፳፬፥፬-፯)
እኛም እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን በኅብረት ሆነን መጸለይ ተገቢ በመሆኑ እነርሱን ተምሳሌት በማድረግ በተለይም ጸሎተ ኪዳንና ቅዳሴን በአንድነተንና በሥርዓቱ መሠረት ልንጸልይ ይገባል፡፡
በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን አለመገበያየት
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ በገባበት ጊዜ ሻጮች በዚያ ሲገበያዩ ባየ ጊዜ የገመድ ጅራፍ ካዘጋጀ በኋላ በጎችንና በሮዎችን እንዲሁም ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣቸው፤ የሻጮቹንም ገንዘብ በተነባቸው፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፤ ርግብ ይሸጡ የነበሩትን ደግሞ፤ ‹‹ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ አላቸው፡፡››
ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጥባት እንጂ ለሥጋዊ ፈቃድ ለሟሟላት የሚሆኑ ሸቀጦች መገበያያ አይደለችም፡፡ (ዮሐ.፪፥፲፬-፲፮)
የቤተ ክርስቲያን መገልገያ ንዋያተ ቅዱሳን ለግል አገልግሎት አለማዋል
እግዚአብሔር ነቢዩ ሙሴን ‹‹የቅብዐቱንም ዘይት ወስደህ ማደሪያውን በእርሱም ያለውን ሁሉ ትቀበላለህ፤ እርሱንም ዕቃውንም ሁሉ ትቀድሳለህ፤ ቅዱስም ይሆናል›› ብሎ እንደተናገረው
ቤተ ክርስቲያን የምትገለገልባቸው ንቃያተ ቅዱሳት ለተቀደሱ አገልግሎቶች የሚውሉ ብቻ በመሆናቸው ከዚያ ውጭ ለየትኛውም የግል አገልግሎት መጠቀም አይቻልም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ፍትሐ ነገሥት በፈትሕ መንፈሳዊ አንቀጹ ከቤተ ክርስቲያን ከተባረከ ዕቃ ወገን የሆነውን ሁሉ የብር ዕቃም ቢሆን ሰው በቤቱ ውስጥ ሊሠራባቸው እንደማይባ ጠቅሷል፡፡ (ዘፀ. ፵፥፱፣ፍት.ነገ.አን. ፩፣ቁ.፰)
በቤተ ክርስቲያን አጸድ ሥጋዊ ግብይት አለማድረግ
የአምላካችን እግዚአብሔር ማደሪያ ታቦት ባለበትና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም በሚፈተትበት በቤተ መቅደስ ዙሪያም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ ግብዣ አድርጎ መብላትና መጠጣት የተከለከለ ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ‹‹በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ግብዣ በማድረግ መጥራት አይገባም›› በማለት እንደተናገሩት በተመሠረተልን ሕግ መሠረት የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት በማክበር ሥጋዊ መግቦታችንንና መጠጣችን ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ማድረግ አለብን፡፡
በአጠቃለይ በመጽሐፍ ቅዱስ በተጠቀሰውና በቅዱሳን አባቶች በተሠራልን ሥርዓት መሠረት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ማመር፣ ማክበር፣ መተግበርና ማስከበር ከሁሉም ክርስቲያን ይጠበቃል፡፡ ይህንንም በምናደርግበት ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ ጸሎታችንን ይቀበለናል፤ አምልኮትንም በተገቢው መንገድ መፈጸም ይቻለናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በቤቱ ሰብስቦ በአንድነት ያኖረን ዘንድ ክብር ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡
ምንጭ፡- ‹‹ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን›› በሊቀ ካህናት ክንፈገብርኤል አልታዬ በ፲፱፹፫ ዓ.ም ከገጽ ፳፫-፳፰)፣ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፩፣ቁጥር ፰፣ዮሐንስ አፈወርቅ በመጽሐፈ ምሥጢር አንቀጽ ፮፣ ቀኖናና ሥርዓት አንቀጽ ፱)