መንፈሳዊ ኮሌጆችና “ደቀ መዛሙርቱ” ምን እና ምን ናቸው?
ኅዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም
ክፍል አምስት
የተሐድሶ መረብ አድማስና የትኩረት አቅጣጫዎች በሚል ባለፉት ሁለት ዕትሞች ስለ አዲስ አበባ፣ ስለ ሰሜን ኢትዮጵያ፣ ስለ ምዕራብና ደቡብ ኢትዮጵያ የተሐድሶ መናፍቃን አቅርበንላችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ መንፈሳዊ ኮሌጆችን መሠረት ያደረገውን የተሐድሶ መናፍቃንን ዒላማ ከብዙው በጥቂቱ፣ ከረጅሙ በአጭሩ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ተሐድሶ መናፍቃን ቤተ ክርስቲያንን ፕሮቴስታንት የማድረግ ዕቅዳቸውን ዕውን ለማድረግ ትኩረት ካደረጉባቸው ተቋማት መካከል የመጀመሪያዎቹና ግንባር ቀደሞቹ የመንፈሳዊ ኮሌጆች ደቀ መዛሙርት ናቸው፡፡ እስካሁን በማኅበር ደረጃ የሚንቀሳቀሱት ከሃያ አምስት በላይ የተሐድሶ መናፍቃን ድርጅቶች ቀላል የማይባሉ አባሎቻቸው በመንፈሳዊ ኮሌጆች ተምረው ያለፉ፣ ይሠሩ የነበሩ ወይም በመሥራት ላይ የሚገኙ እንዲሁም የሚማሩ ናቸው፡፡ በመንፈሳዊ ኮሌጆች ውስጥ የሚታየው የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ከተማሪዎች ምልመላ እና ተማሪዎቹ ወደ ኮሌጆቹ ሲገቡ ከሚደረግላቸው ቅበላ ጀምሮ የሚሠራ ነው፡፡ የገንዘብ እጥረት የሚያጋጥማቸውን ደቀ መዛሙርት ደግሞ በድጋፍ ስም ይቀርቧቸዋል፡፡ መጻሕፍትንና ሌሎች አስፈላጊ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን በመዋዋስ ስም ግንኙነት በመፍጠር ኦርቶዶክሳዊ ተማሪዎችን ወደ ቡድናቸው ያስገባሉ፡፡
ከተለያዩ መንፈሳዊ ኮሌጆች የተመረቁ ደቀ መዛሙርት ኅቡዕ ቡድን መሥርተው በቤተ ክርስቲያን ላይ ሰፋ ያለ ዘመቻ ከፍተዋል፡፡ ቡድኑ ዓላማውን ለማሳካት በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተወካይ በማስቀመጥ ሥራውን ይሠራል። ይህ ስውር ቡድን በመጨረሻ ላይ ለማሣካት ዓላማ አድርጌ ተነሣኋቸው የሚላቸው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በራሳቸው መንገድና የኑፋቄ አቅጣጫ በመለወጥ ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ ካስቀመጣቸው የማስመሰያ ግቦች፡-
ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቃል በምልዓት እንዲኖርባቸው ማድረግ፣
በሥነ መለኮት ትምህርት ገንቢ ዕውቀት ያላቸውን አገልጋዮች በማደራጀት የወንጌልን እን ቅስቃሴ ማስፋፋት፣
በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ ከስንዴ ጋር አብረው የገቡትን ትምህርቶችና መጻሕፍት (አስተምህሮዎች) ማስወገድ፣
ቤተ ክርስቲያን ምንም ከማይጠቅም ወግ፣ ልማድ እና በብልሃት ከተፈጠሩ ተረታዊ ትምህርቶች ተለይታ እውነት የሆነው ክርስቶስ እንዲሰበክ ማድረግ፣
የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት በክርስቶስ ጥላ ሥር ተሰብስበው እንዲያመልኩና በአንድ እንዲተባበሩ ማድረግ፣
ወንጌል በእያንዳንዱ ቤት አንኳኩቶ በመግባት መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ፣
ወጥና ተከታታይ ትምህርትን በማዘጋጀት ወጣቶችን፣ ሕፃናትንና አረጋውያንን በማነቃቃት ለዓለም ብርሃን የሆነውን የጌታን ቃል ለሁሉም እንደየአቅማቸውና እንደየደረጃቸው ማዳረስ፣
በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት መሥራት፣
የወንጌልን ተልእኮና ለውጥ ሊያፋጥን በሚቻል መልኩ የተለያዩ ተቋማትን ማእከል በማድረግ መንቀሳቀስ፣
የቤተ ክርስቲያን ለውጥና ዕድገት የሚሹትን ሁሉ ማደራጀት፣
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እራሱን የቻለ ማኅበር ማቋቋም የሚሉ ናቸው፡፡ (ምንጭ፡- የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ገጽ ፺፬)
እነዚህን እና የመሳሰሉትን ምክንያቶች በመደርደር ቤተ ክርስቲያናችን እስካሁን ድረስ ዘመናትን የፈጀችው ወንጌልን ስትሰብክ ሳይሆን ስለ ቅዱሳን ስታስተምር ነው፤ አሁን መስበክ ያለብን ክርስቶስን ነው የሚለውን ተሐድሶ መናፍቃን ያራምዱት የነበረውን የፕሮቴስታንት አስተምሮ ይዞ የተነሣ ነው። ለቅዱሳን የማስተማር ጸጋ ስለሰጣቸው ስለ ክርስቶስ ማስተማር መሆኑን መረዳት ይገባቸዋል ቤተ ክርስቲያን ጉልላቷ ስለሆነው ስለ ክርስቶስ ሳታስተምር የዋለችበት ዕለት ያለ ለማስመሰል መሞከራቸው ስሕተት ነው፡፡ ዓላማዬን ያሳኩልኛል ብሎ ካሰማራቸው ሰዎች ሲገልጽ ደግሞ እንዲህ ብሏል፡፡ ሥራውን የሚሠራው መንፈስ ቅዱስ ሆኖ የለውጥ መሪ የሚሆኑ በእምነትና በዕውቀት የታመነባቸው የነገረ መለኮት ተማሪዎች፣ ልዩ ልዩ መምህራን፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግሉ ቀሳውስትና ዲያቆናት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ምእመናን፣ ልዩ ልዩ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ይህ ሲባል በመንፈሳዊ ለውጥ የሚሠሩትን አካላትም ያካትታል፡፡
ቡድኑ በዋነኝነት በመንፈሳዊ ተቋማት ያሉና ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎችን ቢያማክልም በግላቸውና በማኅበር ተጀራጅተው ከሚንቀሳቀሱ ማኅበራት ጋር አብሮ ይሠራል። ይህ ማኅበር ዓላማውን ለማሳካት የምንፍቅናውን መርዝ ለመርጨት ያሰበባቸው ቦታዎች መንፈሳዊ ኮሌጆች ብቻ ሳይሆኑ፤ የካህናት ማሠልጠኛ ሥፍራዎች፣ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ የቤተ ክህነት መሥሪያ ቤቶች፣ የመንግሥት የትምህርት ተቋማት እና ማኅበራት ናቸው፡፡
ለእንቅስቃሴው አስተዋጽኦ ያደረጉ ሁኔታዎች
በመንፈሳዊ ኮሌጆች ውስጥ ያለው የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ እንዲስፋፋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታዩ ከኮሌጆቹ አስተዳደራዊ መዋቅርና አሠራር እንዲሁም ከተማሪዎች ክትትል ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡
፩.አስተዳደራዊ ችግሮች
መንፈሳዊ ኮሌጆች ላይ የሚከሠቱት የአብዛኛዎቹ ችግሮች መነሻቸው አስተዳደራዊ ችግር ነው፡፡ ይህ የሁሉም ችግሮች ምንጭ ነው፡፡ መንፈሳዊ ኮሌጆች አስቀድመው አስተዳደራዊውን ችግር ቢፈቱ ሌሎችን በቀላሉ መፍታት ይችላሉ፡፡ ከገንዘብ አያያዝ፣ ከተማሪዎች ጋር ባለው መልካም ግንኙነት፣ ከመምህራን ቅጥር እና ከአስተዳደር ሓላፊዎች ምደባ ጋር ተያይዞ ብዙ ችግሮች ይታያሉ፡፡ እነዚህ አስተዳደራዊ ችግሮች ተቋሙ ዋና ጉዳዩ የሆኑት ደቀ መዛሙርትን ዘንግቶ ሌሎች ጉዳዮች ላይ እንዲጠመድ ያደርጉታል፡፡ ተሐድሶ መናፍቃኑ ደግሞ ይህንን ክፍተት በደንብ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ አስተዳደራዊውን ችግር ሃይማኖታዊ አስመስሎ ከማቅረብ ጀምሮ በየጊዜው ለአስተዳደሩ የቤት ሥራ የሆኑ ጉዳዮችን በመብት ስም እያነሡ እነርሱ የውስጥ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ይተጋሉ፡፡
፪.የገንዘብ እጥረትና የአጠቃቀም ችግር
ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንደ አንድ ችግር የሚነሣው የገንዘብ እጥረት ነው፡፡ በእርግጥ ቤተ ክርስቲያን ከማንኛውም አካል በላይ የሆነ ሀብት አላት፡፡ ይህም ሀብት የልጆቿ ዕውቀት፣ ጉልበትና ገንዘብ ነው፡፡ ይህንን በአግባቡ አቀናጅቶ የሚያሠራ መዋቅር፣ አሠራርና ስልት ባለመዘርጋቱ ግን ብዙ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት የሚሰጥባቸው ጠፍቶ ሲዘጉ ይታያሉ፡፡ ከተማ ላይ አብያተ ክርስቲያናት በሚልዮንና ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲያንቀሳቅሱ፣ እያንዳንዳቸው ከአንድ መቶ በላይ አገልጋዮች ሲኖሯቸው በገጠር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ በአንጻሩ ዕጣንና ጧፍ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን የሚከፍት አንድ ካህን አጥተው ሲቸገሩ ይታያል፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማእከላዊ የሆነ የገንዘብ አያያዝ ባለመኖሩ የተከሠተ ችግር ነው፡፡
የዚህ ችግር ውጤትም በአጥቢያዎች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ተቋማትም የሚታይ ነው፡፡ መንፈሳዊ ኮሌጆች በዚህ ከሚፈተኑት የቤተ ክርስቲያን ተቋማት መካከል ናቸው፡፡ ኮሌጆቹ እንደ ተቋም ለአገልግሎቱ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ለማሟላት የገንዘብ እጥረት ያጋጥማቸዋል፡፡ ይህ ክፍተት ደግሞ በእርዳታ ስም መናፍቃኑ ወደ ተቋማቱ እንዲገቡ በር ከፈተላቸው፡፡ በመንፈሳዊ ኮሌጆች የሚማሩ ደቀ መዛሙርትም ወደ ሌላ እምነት እንዲገቡና የተሐድሶ መናፍቃኑን ጎራ እነዲቀላቀሉ ከሚያደርጓቸው ችግሮች አንዱ የገንዘብ እጥረት ነው፡፡
፫.የምልመላ መስፈርት
ተማሪዎች ወደ ኮሌጆች የሚገቡት ከዚህ በፊት የነበራቸው ሰብእና (ማንነትና ምንነት) ተጠንቶና ታውቆ ሳይሆን ሀገረ ስብከት ላይ ወደ መንፈሳዊ ኮሌጆች ለመላክ ሓላፊነት ካላቸው አካላት ጋር ባላቸው ቅርበት ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ብዙ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ፣ ትልቅ አቅም ያላቸው ሰዎች እየቀሩ በጓደኝነት፣ በዝምድና፣ አለፍ ሲልም በጥቅማ ጥቅም ወደ ኮሌጆች የሚገቡት ተማሪዎች በርካታ ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ ወደ ኮሌጆች የሚገቡ ሰዎች ደግሞ ዐዋቂ ቢሆኑ እንጂ ክርስቲያን መሆን አይችሉም፡፡ ዐዋቂነትና መራቀቅ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ዓላማ አይደለም፡፡ ለቤተ ክርስቲያን በንባብ ላይ ከሚራቀቀው ዐዋቂ ይልቅ፣ እየተንተባተበ ወልድ ዋሕድ ብሎ የሚመሰክር ኦርቶዶክሳዊ ደቀ መዝሙር ያስፈልጋታል፡፡
በተጨማሪም ወደ ኮሌጆች የሚገቡበት የትምህርት መስፈርት ተመሳሳይ ባለመሆኑ በክፍል ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት ለአንዳንዶቹ የሚጠጥርባቸው ለሌሎቹ ደግሞ የሚመጥናቸው አልሆን ይላል፡፡ ለምሳሌ በኮሌጆች ውስጥ በመደበኛው ዲፕሎማ መርሐ ግብር ከዐሥረኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ዲግሪ ድረስ፣ ከፊደል ተማሪ እስከ መጻሕፍት መምህራን ድረስ አንድ ላይ በአንድ ክፍል የሚማሩበት ዕድል አለ፡፡ ባለዲግሪው በእንግሊዝኛ የሚሰጡ ትምህርቶች ላይ የተሻለ ግንዛቤ ሊኖረው ሲችል፣ ዐሥረኛ ክፍል የጨረሰው ከትምህርቱ በላይ ፈታኝ የሚሆንበት እንግሊዝኛ ቋንቋ ማጥናቱ ይሆናል፡፡ ወደ ግእዝ ቋንቋ ስንመጣም ችግሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ የቅኔ እና የመጻሕፍት መምህራን ግእዝን ካልቆጠረው ጋር አብረው ይማራሉ፡፡
፬.የትምህርት አሰጣጥ
ኮሌጆች ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት አብዛኛው ዕውቀት ተኮር እንጂ ምግባር ተኮር አይደለም፡፡ የትምህርት አሰጣጡም ተማሪዎች ጉዳዩን ዐውቀውት ማስተማር እንዲችሉ ማድረግን እንጂ እንዲኖሩት ማድረግን ዓላማው ያደረገ አይደለም፡፡ የነገረ መለኮት ምሩቅ ከሌሎች ሰዎች የሚለየው በዕውቀቱ እንጂ በሕይወቱ እንዲሆን የተሠራው ሥራ አናሳነው፤ ወይም የለም፡፡ ይህ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለግለሰቡ ሕይወት አንዳች ረብ የሌለው መጻሕፍትን ይዞ እንደማይጠቀምባቸው ቤተ መጻሕፍት መሆን ነው፡፡
ትምህርቱም በመምህራን እውነተኛነት፣ ታማኝነትና ክርስትና ላይ የተመሠረተ እንጂ የኮሌጆቹ አስተዳደሮች ስለሚሰጠው ትምህርት የሚያደርጉት ክትትል የለም፡፡ ኮሌጆቹ አንድ መምህር ክፍል መግባት ወይም አለመግባቱን፣ ገብቶ የሚያስተምረው የትምህርት ይዘት ኦርቶዶክሳዊ ዶግማና ቀኖናን የተከተለ መሆን አለመሆኑን የሚቆጠ ጣጠሩበት ሥርዓት የላቸውም፡፡ ይህ ደግሞ ማስተማር መንፈሳዊ አገልግሎት ሳይሆን የገንዘብ ማግኛ ሥራ አድርገው የሚቆጥሩ ብዙ መምህራን እንዲኖሩ የሚያደርግና ያደረገ አሠራር መፍጠር ችሏል፡፡
፭.የተማሪ አያያዝ
ኮሌጆች ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮችን አሟልተው በመደበኛው የቀን መርሐ ግብር የሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ባላቸው ትርፍ ጊዜ የት እንደሚሔዱ፣ ምን እንደሚሠሩ፣ ከማን ጋር እንደሚውሉ ወዘተ የሚደረገው ቁጥጥር በጣም የላላ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ትምህርት የማይሰጥባቸውን ዕለታት ተማሪዎች መገኘት ከማይገባቸው አልባሌ ቦታዎች ጀምሮ ወደ መናፍቃን አዳራሽ ሳይቀር ይሔዳሉ፡፡ ለምሳሌ በከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ሲማሩ ከነበሩ የተወሰኑ ተማሪዎች መካከል እሑድ ከዐራት ሰዓት ጀምሮ የሚሔዱበት የመናፍቃን አዳራሽ አለ፡፡ ሰፊ እረፍት ሲኖራቸው ደግሞ አዲስ አበባ እንዲመጡ በማድረግ በአሸናፊ መኮንን ሰብሳቢነት በኮሌጁ ውስጥ ስለሚሠሩት የኑፋቄ ሥራ ሥልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ የተለያዩ የመናፍቃን መጻሕፍትን በኮሌጁ ውስጥ በነጻ ያድላሉ፣ âየአሸናፊ መኮንንን መጻሕፍት ያላነበበ ተማሪ የነገረ መለኮት ተማሪ አይባልምâ የተባለ እስከሚመስል ድረስ በነፍስ ወከፍ ለሚከተሏቸው ሰዎች ሁሉ ይታደላል፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው የኮሌጆቹ አስተዳደሮች የሚያስተምሯቸው ሰዎች ሕይወት ገዷቸው የሚሠሩት ሥራ እንደሌለ ነው፡፡
፮.ከወጡ በኋላ ያለው ክትትል ማነስ
ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ከሦስቱም መንፈሳዊ ኮሌጆች ልጆችን ታስመርቃለች፡፡ ነገር ግን በኮሌጆች ውስጥ ቆይተው መውጣታቸውን እንጂ በትክክል የሚገባቸውን ነገር (ዕውቀትን ከሥነ ምግባር አስተባብረው) ይዘው መውጣታቸውን፣ ከወጡም በኋላ በተመደቡበት ሀገረ ስብከት ቤተ ክርስቲያን የምትፈልግባቸውን ያህል እየሠሩ መሆኑን፣ የሚያስተምሩት ትምህርት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መሠረተ እምነት የተከተለ መሆኑን የምታውቅበት ሥርዓት አልዘረጋችም፡፡ እስካሁን ስንት ደቀ መዛሙርት ተመረቁ? ከተመረቁት ውስጥ ስንቶች በአገልግሎት ላይ አሉ?፣ ስንቶች በሃይማኖታቸው ጸንተው፣ በምግባራቸው ቀንተው እያገለገሉ ነው? ስንቶች አገልግሎት አቁመዋል? ስንቶችስ ወደ ሌላ እምነት ገብተዋል? ወደ ሌላ እምነት እንዲገቡ ያደረጋቸው ገፊ ምክንያት ምንድን ነው? አሁን ያሉበት አቋም ምን ይመስላል? የሚሉት ጉዳዮች ለኮሌጆችም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች መሆን አልቻሉም፡፡ ይህ ክፍተት እነሱን መሣሪያ አድርገው ለመጠቀም ሌት ከቀን ለሚተጉት መናፍቃን ጥሩ ዕድል ሆኗ ቸው ውጭ ሆነው ለሚሠሩት የጥፋት ሥራ የውስጥ ዐርበኛ ሆነው የሚያገለግሏቸው ኦርቶ-ጴንጤ የኮሌጅ ምሩቃን ሰባኪ፣ የስብከተ ወንጌል ሓላፊና የደብር አስተዳዳሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድጓል፡፡
፯.የትኩረት ማነስ
በመንፈሳዊ ኮሌጆች ውስጥ በዓላማና በረቀቀ ዘዴ እየተሠራ ያለውን የተሐድሶ እንቅስቃሴ መኖሩን ካለመቀበል ጀምሮ እንቅስቃሴውን ለማስቆም የተሠሩ ሥራዎች አለመኖራቸው ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በመንፈሳዊ ኮሌጆች ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተሐድሶ ማኅበረ ቅዱሳን የፈጠረው የመወደጃ ፍረጃ እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የተሸረበ ሥውር ሴራ መሆኑን አልተረዱትም፣ ወይም ሊረዱት ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ይህ አቋም ሁለት ዓይነት ትርጉም ይኖረዋል፡፡ አንደኛው በአስተዳደር ሓላፊነት ላይ ካሉት አካላት ውስጥ ተሐድሶን የሚደግፉ፣ የውስጥ ዐርበኛ ሆነው የሚሠሩና በዓላማ የተሰማሩ ሰዎች አሉ ማለት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ትኩረት የማይሰጡ፣ ክርስትናን በጊዜያዊ ነገር የሚለውጡ፣ የሚነገራቸውን ነገር ላለመስማት ጆሯቸውን የደፈኑ እና ምን እየተሠራ እንደሆነ እንኳን መረጃው የሌላቸው ሰዎች በሓላፊነት ላይ እንደተቀመጡ የሚያስገነዝብ ነው፡፡
እንቅስቃሴው በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሰው ጉዳት
፩.ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ችግር
አንድ መናፍቅ ምንም ትምህርት የሌለውን ክርስቲያን ከማታለል ይልቅ ከመንፈሳዊ ኮሌጅ የተመረቀ ሰባኪን ማሳመን ይቀለዋል፡፡ ለዚህም ነው በተሐድሶ መናፍቃን ማኅበራት ውስጥ ከምእመኑ ይልቅ ከመንፈሳዊ ኮሌጆች ከተመረቁት ደቀ መዛሙርት መካከል የሚበዙት መናፍቅ የሆኑት፡፡ ብዙ ተመራቂዎች እንደሚናገሩት ከመንፈሳዊ ኮሌጅ የተመረቀ ሰው የመጀመሪያ የምስጋና ጸሎቱ አቤቱ መናፍቅ ሳልሆን እንድወጣ ስላደረግኸኝ አመሰግንሀለሁÃÂ የሚል ነው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቅና መናፍቅ አቻ ለአቻ የሚነገሩ ቃላት ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ንግግሮች መንፈሳዊ ኮሌጆችና ደቀ መዛሙርቱ ምን እና ምን ናቸው?ÃÂ የሚለውን ጥያቄ እንድንጠይቅ ያስገድዱናል፡፡
ለብዙ የተሐድሶ መናፍቃን መፈጠር፣ ለብዙ ምእመናን ከአገልግሎት መውጣትና ከሃይማኖት መራቅ የዋናውን ድርሻ የሚወስዱት እነዚሁ ደቀ መዛሙርት ናቸው፡፡ ሃይማኖቱን በመተውም ቅድሚያውን የሚይዘውም ያልተማረው ኅብረተሰብ ሳይሆን እነዚሁ ናቸው፡፡ የዚህ ምክንያቱ መጀመሪያ የነበራቸው የትምህርት መሠረት ወይም የትምህርት አሰጣጡ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የመናፍቃኑ የመጀመሪያ ጥቅሶች (ማሳያዎች ማለታችን ነው) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃላት ሳይሆኑ ከእነዚህ መንፈሳዊ ኮሌጆች አፈንግጠው የወጡ ሰዎች ናቸው፡፡ የደቀ መዛሙርቱ በሃይማኖትና በምግባር መውጣት የቤተ ክርስቲያን ችግር ተደርጎ ተወስዶ ለብዙ ምእመናን ከመንገዳቸው ለመውጣት ምክንያት ሆኗል፡፡
፪.ሁሉንም እንዲጠሉ ማድረግ
ከመንፈሳዊ ኮሌጆች ተመርቀው የወጡ በቃልም በሕይወትም የሚያስተምሩ፣ ሃይማኖትና ምግባር እንደ ድርና ማግ አስተባብረው የያዙ የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆች መኖራቸው እውነት ነው፡፡ በገጠር ያለችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲጠናከር አምሳና መቶ ኪሎ ሜትር በእግራቸው እየሔዱ፣ ወጣቶችን እየሰበሰቡና እያስተማሩ ሌት ከቀን የሚደክሙ ደቀ መዛሙርት አሉ፡፡ እንደእነዚህ ያሉ ደቀ መዛሙርት ያሉትን ያህል ደግሞ፣ ከርሳቸው እስከሞላ ድረስ ለሌላው መዳን አለመዳን ግድ የሌላቸው የቤተ ክርስቲያን የብብት እሳት የሆኑም አሉ፡፡ በሥጋና በመንፈስ መግባ ያሳደገቻቸውን ቤተ ክርስቲያን ከጠላቷ ከአርዮስ ጋር ወግነው ሊያፈርሷት የሚሯሯጡ የእናት ጡት ነካሾች በቁጥር እየበዙ መሔዳቸው ምእመናን እውነተኞችን አገልጋዮች እንዲጠራጠሩ፣ ከመጥፎዎቹ ጋር አብረው ደምረው እንዲጠሉ በር እየከፈተ ነው፡፡
፫.የሰውና የገንዘብ ኪሳራ
የቤተ ክርስቲያን ገንዘቧ ሰው እንጂ ብርና ወርቅ አይደለም፡፡ በመምህራን እግር ተተክተው መንጋውን እንዲጠብቁ ለብዙ ዓመታት የደከመችባቸው ልጆቿን ከማጣት በላይ ለቤተ ክርስቲያን ሌላ ኪሳራ የለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያጣችው ልጆቿን ብቻ አይደለም፤ ለእነዚህ ሰዎች ያባከነችውን ገንዘብ፣ የሰው ኃይልና ጊዜ ጭምር እንጂ፡፡ ከመንፈሳዊ ኮሌጆች የሚመረቁ እውነተኞቹ ደቀ መዛሙርት ከመድረኩ ርቀው የቢሮ ሥራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ ይህም ለቤተ ክርስቲያን ሁለት መንታ ችግሮችን አስከትሏል፡፡ አንደኛው ቤተ ክርስቲያን ስትለፋባቸው የኖረቻቸው ልጆቿ ዓላማዋን ሳያሣኩላት መቅረታቸው ሲሆን፤ ሁለተኛውና አሳዛኙ ደግሞ ሌሎች የተሐድሶ አቀንቃኞች ቦታውን እንዲይዙት ማድረጉ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ቦታውን መያዛቸው ብቻ ሳይሆን እውነተኞቹ ከመድረኩ ስለጠፉ እነርሱ እውነተኛ መስለው መታየታቸው የበለጠ ቤተ ክርስቲያንን እየጎዳት ነው፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ተሰሚነት ያለው የሚናገር፣ የሚጽፍ ወይም የሚዘምር ሰው ስለሆነ ነው፡፡
የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ በሁሉም ኮሌጆች ያለ መሆኑን ከየኮሌጆቹ በተለያዩ ጊዜያት የተባረሩ የተሐድሶ መናፍቃን አቀንቃኞች፣ ምክርና ተግሣጽ ተሰጥቷቸው የቀጠሉ ተማሪዎች ማስረጃዎች ናቸው፡፡ እንቅስቃሴው በሦስቱም መንፈሳዊ ኮሌጆች ያለ ነው፡፡ በየኮሌጆቹ ማሳያዎችን በመጥቀስ ጉዳዮችን ማብራራት ተገቢ ይሆናልና ወደዚያ እንለፍ፡፡
ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አዲስ አበባ መሆኑና መንፈሳዊ ኮሌጆች ላይ መሠረት አድርጎ የሚሠራውን የውጪውን የተሐድሶ መናፍቃን ድርጅትም ትኩረት የሳበ በመሆኑ ብዙ እንቅስቃሴዎች ይደረጉበታል፡፡ ከውጪ እስከ አገር ውስጥ መረባቸውን የዘረጉ የተሐድሶ መናፍቃን ድርጅ ቶች ሰፋ ያለ መሠረት ለመጣል ሲሞክሩ ነበር፣ አሁንም እየሠሩ ነው፡፡ እንቅስቃሴው በአብዛኛው የቀን መደበኛ ተማሪዎችን ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ከኮሌጁ ተመርቀው በተሐድሶ መናፍቃን መረብ ውስጥ ያሉ ደቀ መዛሙርት አሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በትምህርት ላይ ያሉ ወደ መናፍቃን አዳራሽ የሚሔዱ፣ ከአሸናፊ መኮንን ጋር የሚማሩ ብዙ ተማሪዎች አሉ፡፡ ፳፻ወ፮ ዓ.ም ላይ ቁጥራቸው ዐሥር የሚደርሱ ተማሪዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን የሚነቅፍና የክህደት ትምህርት ሲያሠራጩ በኮሌጁ ደቀ መዛሙርት መረጃ ቀርቦባቸዋል፡፡ ጉዳያቸውም ለኮሌጁ ቀርቦ እየታየ ሲሆን፤ የድምጽና የሰው ማስረጃ የቀረበባቸው የኑፋቄ ትምህርቶቻቸው የሚከተሉት ናቸው፡፡
፩.አማላጃችን ኢየሱስ ነው እንጂ ሌላ አማላጅ የለም፤
፪.በጸጋው አንዴ ድነናል፣ ስለዚህ ሥራ ለምስክርነት ነው እንጂ ለመዳናችን ምንም አያስፈልግም፤
፫.ኅብስቱ መታሰቢያ ነው እንጂ፣ ሕይወት የሚሰጥ አማናዊ የጌታ ሥጋና ደም አይደለም፤
፬.ለፍጡር አድኅነኒ አይባልም፣ ማርያም አታድንም፤
፭.በጸሎት ቤት ስለ ድንግል ማርያም ክብር ትምህርት ሲሰጥ âተረታ ተረትህን ተውና ውረድâ ብሎ መቃወም፤
፮.ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ መላእክት እያልን ወንጌልን አንሸቃቅጥ፤
፯.ጻድቃን ሰማዕታት፣ መላእክት አያማልዱም፣ አያድኑም፣ አያስፈልጉም፣ አንድ ጌታ አለን፤
፰.ለቅዱሳን ስግደት አይገባም፣ የአምልኮ እንጂ የጸጋ የሚባል ስግደት የለም፤
፱.ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን አትሰብክም፣ የምትሰብከው ፍጡራንን ነው፤
፲.ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀምባቸው መጻሕፍት በሙሉ ኮተቶች ናቸው፤
፲፩.እኛ የሐዲስ ኪዳን ልጆች ነን የአንድምታ መጻሕፍት አያስፈልጉንም፤
፲፪.በሐዲስ ኪዳን ካህን አያስፈልግም፣ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፣ ንስሐም መናገር ያለብን ለጌታ ብቻ ነው፤
፲፫.በጳጳሳት፣ በመነኮሳት፣ በቀሳውስት፣ በዲያቆናት እንዲሁም ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት በሚያስተምሩትና በሚማሩት፣ በሚጾሙትና በሚያስቀድሱት የኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ላይ ጸያፍ ስድብና ዘለፋ መናገር፡፡ ከሚናገሯቸው የስድብ ቃላት ውስጥ፡- ግብዞች፣ በጨለማ የሚኖሩ፣ ዶማዎች፣ ደንቆሮዎች፣ ያልበራላቸው፣ የጌታ ጠላቶች፣ ወዘተ ይገኙበታል፡፡
፲፬.ታቦት ጆሮ ስለሌለው አይሰማም፣ ስለዚህ አያስፈልግም ፣
፲፭.ሕዝቡን ለብዙ ሺሕ ዘመናት ለጣዖት ስናሰግደው ኖረናል፣
፲፮.አሁን ካለንበት የጨለማ ጫካ መውጣት አለብን፣
፲፯.ቤተ ክርስቲያን፡- ዘረኝነትንና ጽንፈኝነትን ታስፋፋለች፣ የተወሰነ ጎሳ ናት፣
፲፰.አንደኛ ዓመት ተማሪዎችን ሲያገኟቸው ቲዮሎጂ መማር ከፈለግህ የበላኸውን መትፋት አለብህ፣ ወዘተ በማለት መዝለፍና ክፉ ምክር መምከር የሚሉት ናቸው፡፡
ይህ የሚያሳየው ከዚህ ኮሌጅ ተመርቀው የተሐድሶ መናፍቃኑን ጎራ የተቀላቀሉት ሰዎች ኮሌጁን በሚፈልጉት መልኩ ለመቅረፅ ሰፋ ያለ ሥራ እየሠሩ መሆኑን ነው፡፡ ይህም ፍሬ ኮሌጁ በእነዚህ ደቀ መዛሙርት ላይ እንደሆነው በየጊዜው እያጠራ ካልሔደ ችግሩን ውስብስብ እና ከባድ ያደርገዋል፡፡
ሌላኛው ኮሌጅ የተሐድሶ መናፍቃን አቀንቃኞች âብዙ ሰዎችን ያፈራንበት ቤታችን ነው ብለው በድፍረት የሚናገሩለትâ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ነው፡፡ ተሐድሶዎችና መናፍቃኑ ከዚህ ኮሌጅ ተመርቆ ኦርቶዶክሳዊ ሆኖ መገኘት የተአምር ያህል የሚቆጠር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እነርሱም ከዚህ ኮሌጅ የተመረቀ መሆኑን ያረጋገጡትን ሰው በልበ ሙሉነት ይቀበላሉ፡፡ በኮሌጁ የኑፋቄው ጠንሳሽ መሠረት ስብሐት ለአብ ነው፡፡ የእርሱን ፈለግ ተከትለው ብዙ ጥፋት ያደረሱት ደግሞ በ፳፻ወ፬ ዓ.ም ተወግዘው የተለዩት ጽጌ ሥጦታውና ግርማ በቀለ ናቸው፡፡ ከ፲፱፻፺ ዓ.ም ጀምሮ የተከሉት እሾህ ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያንን እያደማ ይኖራል፡፡ ከዚህ ኮሌጅ ተመርቀው አንዳንዴ ፕሮቴስታንት፣ ሌላ ጊዜ ሙስሊም አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ኦርቶዶክስ ሆነው የሚተውኑ ደቀ መዛሙርት አሉ፡፡
ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ በተሐድሶ መናፍቃን ብዙ ተጽእኖ የደረሰበት ኮሌጅ ነው፡፡ ለብዙ ዓመታት በኮሌጁ እንደ ሐሰተኛ የሚቆጠሩትና አንገታቸውን ደፍተው የሚሔዱት የነበሩት ኦርቶዶክሳውያን ነበሩ፡፡ ይህ የሆነው በሓላፊነት ላይ የነበሩት መሪዎች ድጋፍ የሚሰጡት ከትክክለኞቹ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ይልቅ ለተሐድሶ መናፍቃኑ ስለ ነበር ነው፡፡ ይህ የሆነውም እንቅስቃሴውን የሚደግፉ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ስለሚያግዟቸው ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ ለውጦች እየታዩበት ነው፡፡ የዚህ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተሐድሶ ጠንሳሽ በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የመቀሌ ቅርንጫፍ ሰብሳቢ የነበረ ሰው ነው፡፡ አዳዲስ ተማሪዎች ሲገቡ አጥምደው ወደ ቡድናቸው ያስገቡ ነበር፡፡ በ፳፻ወ፮ ዓ.ም ያለውና በዛብህ የሚባሉ ቀንደኛ የተሐድሶ መናፍቃን አቀንቃኞች ከዚህ ኮሌጅ ኑፋቄያቸው ተደር ሶበት ተባረዋል፡፡
የተሐድሶ መናፍቃን ተላላኪ የሆኑት የኮሌጁ ተማሪዎች በዕረፍት ሰዓታቸው ወደ አዲስ አበባ መጥተው በአሸናፊ መኮንን አስተባባሪነት ይሰበሰባሉ፡፡ ለቡድናቸው አባላት መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአሸናፊ መኮንን መጻሕፍት እና ሌሎችም ተሐድሶዎች የጻፏቸው መጻሕፍት ይታደላሉ፡፡ ፳፻ወ፯ ዓ.ም ላይ በኮሌጁ ተማሪዎች በተደረገ የመረጃ ማጠናቀር የተደረሰበት በኮሌጁ ከሚማሩት ተማሪዎች ውስጥ ሃምሳ በመቶ ያህሉ ተሐድሶዎችና የተሐድሶ መናፍቃን ደጋፊዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የኮሌጁ ተማሪዎች ግንባር ቀደም የተሐድሶ አንቀሳቃሾች ናቸው፡፡
ስለ መንፈሳዊ ኮሌጆች ስንናገር መንፈሳዊ ኮሌጆች በእምነት የጸኑ፣ በምግባር የቀኑ ደቀ መዛሙርትን አላፈሩም ማለታችን አለመሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ከተመሠረቱበት ዓላማ አንጻር የምርቱን ያህል ግርዱም እየበዛ ማስቸገሩን ለማሳየት አቅርበናል፡፡ እንኳን ትልቅ ተቋም አንድ ግለሰብም የወለዳቸው ልጆች ሁሉ መልካሞች፣ ያስተማራቸው ተማሪዎች ሁሉ ዐዋቂዎች ወይም መንፈሳውያን እንደማይሆኑለት ይታወቃል፡፡ ይህ የነበረ፣ ያለና የሚቀጥል እውነት ነው፡፡ ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብለው ከተማሩት ሐዋርያት መካከል ይሁዳ በስንዴ መካከል የበቀለ እንክርዳድ ነበር፤ በተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ እግር ሥር ቁጭ ብለው ከተማሩት ደቀ መዛሙርት መካከልም አርዮስ በቅሏል፡፡
ነገር ግን በመንፈሳዊ ኮሌጆች ውስጥ እየታየ ያለው ንጹሕና የተቀላቀለ ስንዴ አስገብቶ እንክርዳድ የማምረቱ ጉዳይ እየጨመረ መምጣቱን አህጉረ ስብከትም እየገለጡ ነው፡፡ እዚህ ላይ ለማስገንዘብ የምንፈልገውም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አቅሟን የምታጠናክርባቸው፣ ተተኪ ሊቃውንትን የምታፈራባቸው መንፈሳዊ ካሌጆች፤ የተሐድሶ መናፍቃን መፈልፈያ ለማድረግ በዓላማ ሌት ከቀን እየተሠራ ያለውን ተግባር ምን ያህል አውቀነዋል በሚል እንጂ፤ በየኮሌጆቹ ውስጥ ሆነው አቅማቸው በፈቀደ፣ ይህን ሥውር ደባና ዘመቻ ለማጋለጥ የሚተጉ ደቀ መዛሙርት የሉም ለማለት አይደለም፡፡፡ ሆኖም ግን ተፅዕኖውና ዘመቻው ከእነሱ አቅም በላይ ስለሆነ፤ በመዋቅሩ ደረጃ ችግሩን ለመቅረፍ መሠራት የሚኖርባቸውን ተግባራት ለማመላከትና የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆኑ በየኮሌጆቹ የሚገኙ ደቀ መዛሙርትም በፅናት ሆነው የተሐድሶ መናፍቃን ዓላማ ግቡን እንዳይመታ ጥረታቸውን እንዲቀጥሉ ለማሳሰብ ነው፡፡
እውነተኞቹ ደቀ መዛሙርት እኩይ ተግባራቸውን ስለገለጡባቸው ተሐድሶ መናፍቃንም ተነካን በሚል የዋሃንን አስተባብረው ለመጮህ ወደ ኋላ የማይሉ መሆናቸውን ለማስገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ ደግመን እንጠይቃለን መንፈሳዊ ኮሌጆችና ደቀ መዛሙርትÂ ምን እና ምን ናቸው? ይህንን የምንለው ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች ተቀርፈው ኦርቶዶክሳውያን ደቀ መዛሙርት እንዲበዙና ወጥተውም በተማሩት ሙያ እንዲያገለግሉ የሚያ ደርግ ሥራ መሥራት እንደሚገባን ለማመልከት ነው፡፡