‹‹መስቀል ኀይላችን፣ ጽናታችን፣ ቤዛችን፣ የነፍሳችን መዳኛ ነው››
በኢየሩሳሌም ምድር፣ በቀራንዮ ዐደባባይ፣ በዕለተ ዓርብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ሥቃይ ተቀብሎ ለሰዎች ድኅነት ሲል መሥዋዕት የመሆኑና የፍቅሩ መገለጫ ‹መስቀል› ኀይላችን፣ ጽንዓችን፣ ቤዛችን እንዲሁም የነፍሳችን መዳኛ ነው፡፡ ‹‹አይሁድ ይክዱታል፤ እኛ ግን እናምነዋለን፤ ያመነውም እኛ በመስቀሉ እንድናለን፤ ድነናልም›› እያልንም ዘወትር በጸሎታችን እየመሰከርን ስላደረግልን ነገር ሁሉ አምላካችንን እናመሰግነዋለን፡፡ መስቀል ጥንት ጠላት ሰይጣን የተሸነፈበት እና የጌታችን ክርስቶስ ቤዛነት የተረጋገጠበት የድኅነት ኃይል ነውና፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል የተለየ ክብር አለው፡፡ የሰውን ዘር በሙሉ ለማዳን ሲል ብዙ ጸዋትወ መከራ የተቀበለበትንና ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ ያገኘንበት ግማደ መስቀሉ በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ከእስክንድርያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበትን የመታሰቢያ በዓል በየዓመቱ መስከረም ፲ ቀን እናከብረዋለን፡፡
በ፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ንግሥት ዕሌኒ በዕጣን ጢስ አመልካችነት መስቀሉን ከተቀበረበት ቦታ ለማውጣት ቍፋሮ ያስጀመረችበትን የመታሰቢያ በዓል በየዓመቱ መስከረም ፲፮ ቀን ደመራ ደምረው በመለኮስ በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዓት በዐደባባይ እናከብራለን፡፡ በማግሥቱ መስከረም ፲፯ ቀንም ንግሥት ዕሌኒ ቅዳሴ ቤቱን ያከበረችበትን የመታሰቢያ በዓል ታቦት አውጥተው ዑደት በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ይከበራል፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ መስከረም ፳፩ ቀን ግማደ መስቀሉ በሚገኝበት በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም በታላቅ በዓለ ንግሥ እንዲሁም መስቀሉ ከተቀበረበት ተራራ ተቈፍሮ የወጣበት መጋቢት ፲ ቀንም በቤተ ክርስቲያን በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ በንጉሥ ዳዊትና በልጃቸው በዘርዐ ያዕቆብ አማካይነት ወደ ሀገራችን የመጣው የጌታችን መስቀል ቀኝ ክፍል በሀገራችን ኢትዮጵያ በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በግሸን ደብረ ከርቤ ይገኛል፡፡ ከቅዱስ መስቀሉና ከገዳሙ በረከት ለመሳተፍ ብዙ ምእመናን በየዓመቱ ቦታው ድረስ በመሄድ በዓለ መስቀልን ያከብራሉ፡፡
ግማደ መስቀሉ ለብዙ ዘመናት በአይሁድ ምቀኝነት በጎልጎታ ተቀብሮ ቢኖርም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተቀደሰ በመሆኑ በንግሥት ዕሌኒና በልጇ ቈስጠንጢኖስ ጥረት ከተቀበረበት ገኝቷል፤ በዚያን ወቅትም ከፀሐይ ብርሃን በላይ አብርቷል፤ ሙት አስነስቷል፤ ሕሙማንን በመፈወስ ብዙ ተአምራትን አድርጓል፡፡
መስቀል የድኅነታችን መሠረት በመሆኑም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም መስቀልን ጉልላቷ እንዲሁም የንዋያተ ቅድሳት ላይም ምልክት አድርጋ ትጠቀመዋለች፡፡ የክርስቲያኖች መዳኛ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል መሥዋዕት የመሆኑ ምሥጢር ነውና፡፡
ስለዚህም በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን ሰዎች በዚህ ምድር ስንኖር የጌታችን ኢየሱስ መከራ መስቀሉን በመቀበልና በመሸከም መኖር ያስፈልጋል፡፡ በተለይም በዚህ ክርስትናችን፣ ሃይማኖታችን እንዲሁም እምነታችን በሚፈተንበት ጊዜ ምንም እንኳን መከራና ሥቃይ ቢበዛብንም እምነታችን ሊጸና የሚችለው እንዲሁም ማንኛውንም ፈተና ማለፍ የሚቻለን በክርስቶስ ፍቅር፣ ተስፋና ትዕግሥት ጠንክረን በድኅነት መንገድ ስንጓዝ ነው፡፡
ክብር ለግማደ መስቀሉ! አምላካችን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ አሜን፡፡
ምንጭ፡ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ መስከረም