ሐዊረ ሕይወት ወደ አዲስ ዓለም ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊካሄድ ነው
የካቲት 14 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ
በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ የታሰበው ሐዊረ ሕይወት ወደ ርእሰ አድባራት ወገዳማት አዲስ ዓለም ደብረ ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን መጋቢት 21 ቀን 2006 ዓ.ም ሊካሄድ መሆኑን፤ የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ዋና ጸሐፊና የጉዞው ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ተሾመ ገለጹ፡፡
ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት የጉዞው ተቀዳሚው ዓላማ መሆኑን አቶ ግርማ ተናግረው፤ በዕለቱ በብፁዐን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፤ ስብከተ ወንጌል በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሚሰጥ ከመሆኑ በተጨማሪ የቅኔ መምህራን ቅኔ የሚቀኙበት፤ ዘማርያንም ወረብና መዝሙር የሚያቀርቡበት መሆኑ ተገልጠዋል፡፡ በመሆኑም በወርኃ ጾም በሚከናወነው ጉዞ በመሳተፍ ምእመናን ነፍሳቸውን በወንጌል ያለመልሙ ዘንድ አቶ ግርማ አሳስበዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ በማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ ይሰጣል ያሉት ሰብሳቢው፤ የማኅበረ ቅዱሳንን አገልግሎት ያልተረዱ ሰዎች ካሉም በመርሐ ግብሩ በመገኘት ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለሀገር ብሎም ለዓለም እያበረከተ ያለውን መንፈሳዊ ዕሴቶችን መገንዘብ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ዘርፈ ብዙና የምእመናንን ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ ምእመናን የድርሻቸውን እንዲወጡ ማስቻል የጉዞው ተጨማሪ ዓላማ መሆኑን ያስታወሱት ሰብሳቢው፤ በገንዘብ፣ በጉልበት እንዲሁም በአሳብ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እንዲደግፉ መርሐ ግብሩ ያግዛል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ተጓዦች የጉዞውን ትኬት ከማኅበሩ ጽ/ቤትና ሱቆች ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
ርዕሰ አድባራት ወገዳማት አዲስ ዓለም ደብረ ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ከአዲስ አበባ 55 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ታቦተ ማርያም ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ጀምሮ በቤተ መንግሥት አካባቢ እንደቆየችና በዐፄ በዕደ ማርያም ዘመነ መንግሥት መንዝ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ታንፆላት ምስሐለ ማርያም ተብላ በታልቅ ክብር ነበረች፤ በግራኝ መሐመድ ጊዜ ንጉሡ ሲሰደዱ ታቦቷን ከመቅደስ አውጥተው በአካባቢው በሚገኝ ዋሻ በባህታውያን ሲጠብቋት ኖረዋል፡፡ በተለይ ከዐፄ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ የቤተ ምንግሥትና የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ የሚያሳዩ ቅርሶች የሚገኙባት ደብር መሆኗን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡