ልደቱ ለአቡነ ዘርዐ ብሩክ
በትንቢት ‹‹ከአንዲት ሴት ልጅ በጸሎቱ ዓለምን የሚያድን፣ በአማላጅነቱ ነፍሳትን የሚዋጅ ልጅ ይወለዳል›› ተብሎ ከተነገረ ከብዙ ዘመን በኋላ እግዚአብሔርን የምታመልክ ስሟ ማርያም ሞገሳ የምትባል ሴት ልጅ ተወለደች:: ያችንም ሴት ልጅ እናትና አባቷ ለአቅመ ሔዋን እስክትደርስ ድረስ እግዚአብሔርን በመፍራትና በዕውቀት አሳደጓት:: ዕድሜዋም ለትዳር ሲደርስ እናትና አባቷ እግዚአብሔርን ለሚፈራ ስሙ ደመ ክርስቶስ ለሚባል ሰው ዳሯት::
በዚያን ጊዜ ስልጣኑ ከሰማይ የሆነና ክብሩ እጅግም የሆነ ልጅ ጸነሰች:: እርሱን ከጸነሰች ጊዜ ጀምሮ እስክትወልደው ድረስም ልብሷን አትታጠቅም፤ ለወገቧም መቀነትን አትፈልግም ነበር:: በእናቱ ማህፀን ተአምራትን እንዳደረገ እንደ ዘካርያስ ልጅ እንደ ዮሐንስ በደስታ እየሰገደ በእናቱ ማህፀን ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ያደርግ ነበርና:: እርሷም የመውለጃዋ ቀን እስኪደርስ በጾምና በጸሎት ተወስና ስታገለግል ኖረች::
በነሐሴ ፳፯ ቀን በሰው ዘንድ የተናቀ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ይህን ክቡር ጻድቅ ወለደችው:: በተወለደም ጊዜ በእናትና አባቱ እንዲሁም በሀገሩ ሰዎችም ዘንድ ፌሽታ ሆነ፤ እስከ ሰባት ቀንም ድረስ ግብዣ አደረጉ:: ይህም ጻድቅ ባሕታዊ በተወለደበት (ክርስትና) በተነሳበት ቀን በካህናት አፍ ጸጋ ክርስቶስ ተባለ:: የኃጢአት ማሰሪያን ሁሉ ያስርና ይፈታ ዘንድ ጵጵስና በሾመው ጊዜ እግዚአብሔር ያወጣለት ሁለተኛው ስሙ ዘርዓ ብሩክ ነው:: ሦስተኛ ስሙ ደግሞ ጸጋ ኢየሱስ (በጸሎት ተደጋግሞ ብዙ ይገኛል) ይባላል::
ከልደቱ በኋላ ያንንም ሕፃን አባቱና እናቱ እስከ ሰባት ዓመቱ ድረስ እግዚአብሔርን በመፍራት፣ በአምልኮት እና በዕውቀት አሳደጉት:: ሰባት ዓመት ሲሆነው የሚያልፈውንና የሚጠፋውን ዓለም ሁሉ እንዳያይ ዓይኖቹ ታወሩ:: የልጃቸው ዓይኖች በጠፉበት ቀን እናትና አባቱ አዘኑ፤ ታውሮም በቤታቸው አንዲት ዓመት ኖረ:: ከተወለደ ሰባት ዓመት ሲሆነው ረቡዕና ዓርብን መጾም ጀመረ:: እናትና አባቱም በተወለደ በሰባት ዓመቱ ሲጾም ባዩት ጊዜ ሀዘናቸው ወደ ደስታ ተለወጠ::
ከዚህም በኋላ በእኒህ እንዲተዳደር ብሎ እንደተናገረው መጽሐፍትን ቢማር ያለበትን ነውር እንደሚሰውር እና በእነዚህም እንዲተዳደር አውቀው የቤተ ክርስቲያንን መጽሐፍት ሁሉ እንዲያስተምረው ለመምህር ሊሰጡት ተማከሩ::
እርሱ ሲማር እግዚአብሔር ብርቱ መከራንና የሚያስጨንቅ በሽታ አመጣበት:: አባትና እናቱም በልጃቸው ላይ የሆነውን ነገር አይተው ዓይኖቹ የታወሩ ‹‹ይህ ልጃችን በምን ይተዳደራል? በዚህ ዓለምስ አኗኗሩ እንደምን ይሆናል?›› ብለው ታላቅ ሀዘንን አዘኑ::
እግዚአብሔርም ከእርሱ (ከእግዚአብሔር) በቀር መጻሕፍትን ሁሉ ከማንም እንዲማር እንዳልፈቀደለት ፈጽመው አስተውለው አላወቁም ነበር:: ይህ ትንሽ ሕፃን ግን ለአባትና ለእናቱ ሲታዘዝ (ሲያገለግላቸው) ኖረ:: ሐዋርያትም በሲኖዶሳቸው እንዳዘዙት ከተወለደ ፲፪ ዓመት ሲሆነው ይጾም ነበር::
ዐሥራ ሁለት ዓመት ከሆነውም በኋላ የጌታችንን ጾም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾመ፡፡ አምላክን የወለደች የእመቤታችን ማርያምን ጾም፣ ሐዋርያት የሠሩትን ጾም፣ ሁሉ መጾም ጀመረ::
አባትና እናቱም በዐሥራ ሁለት ዓመቱ ጾሙን ሁሉ ሲጾም አይተው ተደሰቱ:: ይህ ሕፃን ልጃቸው በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ እንደጸና አላወቁም::
እግዚአብሔር አምላክም ለዚህ ጻድቅ አባት መጻሕፍተ ብሉያትንና መጻሕፍተ ሐዲሳትን፤ መጻሕፍተ ሊቃውንትንና መጻሕፍተ መነኮሳትንም፤ አዋልድ መጻሕፍትንም፤ የመላእክትንና የሰውን ነገር (ፍትህን ሁሉ፤ የማኅሌታይ የቅዱስ ያሬድንም ዜማ) ገለጠለት፤ እግዚአብሔር ይህንን ድንቅ ተአምራት ለወዳጁ ለብፁዕ አባታችን ለአቡነ ዘርዐ ብሩክ የተሰጠው ገና በልጅነቱ ነበር::
ለእኛም ፈጣሪያችን እንዲሁ ተአምራትን ያድርግልን፤ በመከራችን ጊዜ ደስታን ያሰማን፤ ለእርሱ እንደገለጠለት መጻሕፍትን ሁሉ ይግለጥልን፤ መታሰብያውን ለምናደርግ፣ ስሙንም ለምንጠራ እና በጸሎቱ ለምንማጸን ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቹ በጻድቁ ጸሎት ነፍሳችንን ይማርልን፤ አሜን !!!
ምንጭ፤ ገድለ ዘርዐ ብሩክ