ለጥምቀት በዓል በክብር የወጡት ታቦታት በክብር ተመልሰዋል
ጥር 11 ቀን 2006 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ለጥምቀት በዓል ከመንበራቸው በክብር የወጡት ታቦታት ወደመጡበት አብያተ ክርስቲያናት በእልልታና በዝማሬ ታጅበው ተመልሰዋል፡፡ከሌሊቱ 12፡30 ሰዓት ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፤ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፤ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ከሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዩልዮስ፤ ከተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የመንግሥት ተወካዮች ጋር በመሆን በጃንሜዳ ጥምቀተ ባሕር ተገኝተዋል፡፡
በቅዱስነታቸው መሪነት የጸሎተ ወንጌል ሥርዓት በማድረስ በዐራቱም ማእዘናት፤ ከዐራቱም የወንጌል ክፍሎች ዕለቱን በማስመልከት ምንባባት ተነበዋል፡፡ ቀጥሎም ቅዱስነታቸው ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ሆነው ጸበሉን ባርከው ለምእመናን ረጭተዋል፡፡
የጥምቀት ሥነሥርዓቱ ቀጥሎም የወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሰንበት ትምህርት ቤቱ መዘምራን ዕለቱን በማስመልከት ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡የሕንድ ኦርቶዶክስ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዩልዮስ ባስላለፉት መልእክት “የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እኅትማማቾችና የቀረበ ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ታሪክና ትውፊት ያላት በመሆኗ የጥምቀት በዓልን በደመቀና ማራኪ በሆነ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓት የምታከብር ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን ናት” ብለዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በመጨረሻ በሰጡት ቃለ ምዕዳን “ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ይቀድስ፤ ያጣነውን ልጅነት ይመልስልን ዘንድ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ሰላሙንም አደለን፡፡ ይህንንም ጠብቀን መኖር ይገባናል” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም በትናንትናው ዕለት በክብር ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር የወረዱት ታቦታት በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንና ምአመናን ታጅበው ወደየመጡበት በክብር ተመልሰዋል፡፡ የቅዱስ ሚካኤል ታቦታት ግን በነገው እለት የሚመለሱ በመሆኑ በዚያው ይገኛሉ፡፡