ለአብነት ደቀመዛሙርት የሕክምና አገልግሎትና የጤና አጠባበቅ ሥልጠና ተሰጠ

ታኅሣሥ 3 ቀን 2007 ዓ.ም.

ዲ/ን ደስታ ይዲ/ትባረክ /ከወልድያ ማዕከል/

በማኅበረ ቅዱሳን የወልድያ ወረዳ ማዕከል ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ኅዳር 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በምሥራቀ ፀሐይ ወይብላ ማርያም ቤተ ክርስቲያን የአቋቋም ጉባኤ ቤት የአቋቋም ትምህርት በመማር ላይ ለሚገኙ ሃምሳ የአብነት ትምህርት ደቀመዛሙርት የሕክምና አገልግሎት፣ የጤና አጠባበቅ ሥልጠና እና የመጸዳጃ ቁሳቁሶች  ድጋፍ አደረገ፡፡

 

በዕለቱ ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በስፍራው በመገኘት ለደቀመዛሙርቱ ትምህርተ ወንጌል በወልድያ ማእከል ጸሐፊ ዲያቆን ቃለ ጽድቅ ካሳ ማኅበረ ቅዱሳን የሚያደርገውን ድጋፍ እና አገልግሎት በማስመልከት “የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለትውልዱ ይዳረስ ዘንድ የእናንተ ደኅንነት መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር በመሆኑ ማኅበረ ቅዱሳን የአገልግሎቱ ዋና ትኩረት አድርጎ የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናል፡፡ የወረዳ ማእከሉ ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል የተለያዩ የሕክምና ባለሞያ አባላቱን በማስተባበር ይህን ስልጠና ለእናንተ አዘጋጅቷል፡፡ ምንም እናንተ ቃለ እግዚአብሔርን ያወቃችሁ ብትሆኑም ዘመኑን እየዋጀን ራሳችንን ልንጠብቅ እና ክርስትናችንን ልናጸና ስለሚገባ ሥልጠናው ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል” ብለዋል፡፡

 

ደቀመዛሙርቱ በጉባኤ ቤቱ በሚማሩበት ወቅት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በተመለከተ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ በዋነኛነትም በተለያየ ምክንያት ከሥነ ምግባር ውጭ በመሆን ከምእመናን ጋር ያላቸውን ግንኙነትም ሆነ የትምህርት ቆይታቸውን ከሚያሰናክሉ ነገሮች ተቆጥበው የጀመሩትን ትምህርት እንዲያጠናክሩ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥረት ተደርጓል፡፡

 

በወረዳ ማእከሉ የሚገኙ የማኅበረሰብ ጤና አጠባበቅ፣ የዓይን፣ የሥነ ልቦና፣ የውስጥ ደዌ ሕክምና ባለሞያዎችን በማስተባበር ለደቀመዛሙርቱ ስለ ግል እና አካባቢ ንጽሕና፣ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ሊከሰቱ ስለሚችሉ ተላላፊ በሽታዎች ትምህርት ተስጥቷቸዋል፡፡ በተጨማሪም የዓይን፤ የሥነ ልቦና፣ የውስጥ ደዌ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው የሕክምና አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ የልብስና የገላ ንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለሁሉም ደቀመዛሙርት በማከፋፈል፤ ለሆድ ውስጥ ሕመም የሚሆን መድኃኒት እንዲወስዱም ተደርጓል፡፡

 

ደቀመዛሙርቱም ትምህርተ ወንጌል እርስ በእርስ ለመማማር እና የስብከት ዘዴን ለማጠናከር የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ክፍሉም ከሚመለከታቸው አካላትና ከማኅበሩ አባላት ጋር በመሆን ለጥያቄያቸው ምላሽ እንደሚሰጥ ተገልጾላቸዋል፡፡

 

በተጨማሪም ለመጠለያ ቤት ግንባታ ፕሮጀት የወረዳ ማእከሉ ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል እንቅስቃሴ እንደሚያካሂድና ለመጸዳጃ ቤት መስሪያ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን እንደሚያቀርብም ተገልጿል፡፡

 

የጉባኤ ቤቱ የአቋቋም መምህር መሪጌታ ሀብተ ማርያም በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት “ማኅበሩን ከዚህ በፊት በሚሠራው ተግባር አውቀዋለሁ፡፡ በርካታ ፈተናዎችን እያለፈ ተስፋ ባለመቁረጥ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲህ መፋጠኑ ሊያስመሰግነው ይገባል፡፡ ዛሬም በዚህ ጉባኤ ቤት ላለን ይህን የመሰለ ሥልጠና እና የሕክምና አገልግሎት መስጠቱ የቤተ ክርስቲያንን ትንሣኤ የሚናፍቅ እና ለቤተ ክርስቲያን ጥብቅና የቆመ መሆኑን ያስገነዝበናል እና ተማሪዎቼም ብትሆኑ ይህን ልትገነዘቡ ይገባል፡፡ ከዚህ በተለየ በርካታ ችግሮች ስላሉብን ወደፊት ማኅበሩ አይዟችሁ እያለ ከጎናችን እንዳይለየን” ብለዋል፡