abune lukas 01

“ስለ ሃይማኖታችንና ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ዘብ የምንቆምበት ወቅት አሁን ነው”

/ብፁዕ አቡነ ሉቃስ/

ኅዳር 26 ቀን 2007 ዓ.ም.

abune lukas 01የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታሪክ ከገጠሟት ልዩ ልዩ ፈተናዎች ይልቅ በዚህኛው ትውልድ የደረሰባት ፈተና (ሙስናና ብልሹ አሠራር፤ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ በውጭ ካሉ አባቶች ጋር ያልተቋጨው ዕርቀ ሰላም) ወደ ፊት እንዳትራመድ አድርጓታል፡፡ በእርግጥ የቤተ ክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ችግሮች እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ችግሮችን ከማውራት ይልቅ መፍትሔው ላይ ማተኮር ለቤተ ክርስቲያኒቱም ለመንጋውም ጠቃሚ ስለሚሆን ነው እንጂ፡፡

 

በዚህ ሒደት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ ችግሮች በጥልቀት እየተወያየ መፍታሔ የሚሰጠው ቅዱስ ሲኖዶስ በዘንድሮው ጥቅምት 2007 ዓ.ም ባካሔደው ጉባኤ ብዙ ደስ የሚያሰኙ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ይህንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክተን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ከብፁዕ አቡነ ሉቃስ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

የሠላሳ ሦስተኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቅዱስ ሲኖዶስ እይታ ምን ይመስል ነበር?

የሠላሳ ሦስተኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በአህጉረ ስብከት፣ በድርጅቶች፣ በልማት ተቋማት ከፍተኛ ለውጥ የታየበት፣ በማኅበራዊና በሰብአዊ እንቅስቃሴም መልካም ነገሮች የታየበት ነው፡፡ ዕድገት ነበረው፤ ለውጥ ነበረው፡፡ ይሁን እንጂ በስብሰባው ላይ አላስፈላጊ የሆኑ ጎኖች ነበሩት፡፡ ይህም ጥቂት የሚባሉ ታዛቢ ግለሰቦች የፈጠሩት ሁካታ፤ አግባብነት የሌለው ጥያቄ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ክፍተት እንደ እጥረት በማየት እርምት እንዲሰጥ በምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፡፡

 

ወደፊትም እንዲህ አይነት ችግር እንዳይፈጠር ቃለ ዐዋዲው፤ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ በሚያዘው መሠረት ጉባኤው የሚመለከታቸው ተሳታፊዎችና ታዛቢዎች ቦታ ቦታቸውን ይዘው እንዲቀመጡ ይሆናል፡፡ በጋራ መግለጫው የተወሰኑትንና ቅዱስ ሲኖዶስ እርምት እንዲሰጥባቸው የወሰነባቸውን ተግባራት መፈጸምና አለመፈጸማቸውን ክትትል የሚያደርጉ ቋሚ ሲኖዶስ፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የአህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ጊዜ ወስዶ በጥልቀት የተወያየባቸው ነጥቦች ምን ምን ናቸው?


የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የውይይት አጀንዳዎች አጠቃላይ 21 ነበሩ፡፡ በውይይቱ ወቅት ሰፊ ጊዜ የወሰደው አንደኛው አጀንዳ የተረቀቀው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ መወያያ አሳቡም ሊቃነ ጳጳሳቱ ተጠሪነታቸው ለማን ይሁን የሚለው ጉዳይ ነበር፡፡ የፊተኛው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ለቅዱስ ሲኖዶስ ይላል፡፡ አሁን ግን ሊቃነ ጳጳሳቱ ተጠሪነታቸው ለፓትርያርኩና ለቅዱስ ሲኖዶስ የሚል አሳብ ተነሥቶ ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ሐዋርያት ተጠሪነታቸው ለአንዱ እግዚአብሔር ነው፡፡ የጉባኤው መሪ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በፊትም አሁንም ሊቃነ ጳጳሳቱን የሚሾመው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ስለዚህ የሊቃነ ጳጳሳት ተጠሪነት በፊት በነበረው እንዲቀጥል በአንድ ድምፅ ተስማምተዋል፡፡

 

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሊቃነ ጳጳሳት ዝውውርም ተነሥቷል፡፡ ሊቃነ ጳጳሳትን ማዘዋወር የሚችለው ቋሚ ሲኖዶሱ መሆን እንዳለበት ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፡፡ ለሃይማኖት፣ ለሥርዓት፣ ለምእመናንና ለሀገሪቱ የሚጠቅሙ ብዙ አሳቦች በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

 

ሁለተኛው የማኅበራት ጉዳይ ነው፡፡ በልዩ ልዩ አገልግሎቶች በማኅበር ስም ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ ማኅበራት በምን መልኩ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ሥር ይሁኑ በሚለው ምልዓተ ጉባኤው በስፋት ተወያይቷል፡፡ እገሌ ጥሩ ነው እገሌ መጥፎ ነው የተባለ ማኅበር የለም፡፡ ልጆቻችን ለቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ጠቃሚዎች ናቸው፤ መጀመሪያ ሰዎች ለቤተ ክርስቲያን ያስፈላጓታል በማለት ደስ ደስ የሚሉ አሳቦች ተነሥተዋል፡፡ በዚህም የልጆቻችን አገልግሎት ጠቃሚ እንደሆነ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በደንብ አምኖበታል፡፡

 

ልጆቻችንን ማቅረብና መውደድ እንደሚገባም ሁሉም ተስማምቷል፡፡ ስለዚህ ማኅበራት በሙሉ ተጠሪነታቸው ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ገቢያቸውንና ወጭያቸውን ቤተ ክርስቲያኒቱ በምትጠቀማቸው ሞዴላ ሞዴሎች እንዲጠቀሙ ተወስኗል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳንስ?


በማኅበረ ቅዱሳንም ላይ የተለየ አቋም የለም፡፡ ልጆቻችን፤ አገልግሎታቸው በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን እያሳየ ያለው ተግባር ጠቃሚ ነው፤ ገደማትን፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችንና ሌሎች ልማቶችን በተመለከተ ማንኛውንም ሥራ በአጋርነት እየሠራ ያለ ትልቅ ማኅበር መሆኑን ምልዓተ ጉባኤው አምኗል፡፡ እንዲያውም ምሁራን ያሉበት፣ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለሃይማኖት፣ ለሥርዓት፣ ለሀገር፣ ለልማት የሚጠቅሙ ሰዎች ያሉበት ነው የሚሉ ትልልቅ አሳቦች ተነሥተዋል፡፡ ወደ ፊትም የቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ሆኖ እንደሚቀጥል ታምኖበታል፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ ምልዓተ ጉባኤው በአንድ ድምፅ በዚህ መልክ ነው የተረዳው፡፡ ለአሁኑ ቀድሞ ወደ ነበረበት ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ሆኖ ተጠሪነቱ ግን ለማደራጃ መምሪያው ሊቀ ጳጳስ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ቁጥጥሩን፣ ግምገማውንና ክትትሉን የሚያደርገው ደግሞ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ነው፡፡

የማኅበራት ሕግ ሲወጣም እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉት ማኅበራት ክፍል “ሀ”፣ ሌሎች ማኅበራት ክፍል “ለ” በሚል አደረጃጀት ሥርዓት እንዲይዝ ይደረጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ገንዘቡን በቤተ ክርስቲያኒቱ ሞዴላ ሞዴሎች እየተጠቀመ ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውል በሚል ተወስኗል፡፡ ገንዘቡ ለምን ለምን አገልግሎት እንደ ዋለ መከታተል እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጣ የለም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት አይቶ በስፋት ተመልክቶ አስደሳች በሆነ መልኩ የወሰነው ይኼን ነው፡፡

 

ሌላው ስለ ሰላም ነው፡፡ ያለ ሰላም እግዚአብሔርን ማየት አይቻልም እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ በውጭ ያለው ዕርቀ ሰላም እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡ ዝርዝር ሁኔታው ወደፊት የሚወሰን ይሆናል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳዎች 21 ሆነው ሳለ በመግለጫው ግን 9ኙ ብቻ ነበር እንዲካተቱ የተደረገው፣ ለምን?


የዚህ ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶስ ለዓለም መገለጽ የነበረባቸውን ለይቶ ነው መግለጫ የሰጠው፡፡ ሌላው የቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ አሠራር ስለሆነ ውሳኔዎቹ ተለይተው ነው የቀረቡት፡፡

ሙስና ቤተ ክርስቲያኗን ምን ያህል ነው የጎዳት?

 

ያለፉትን ጊዜያት ጨምሮ አሁን ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታ ስናይ በሙሰኞች እየታመሰች ትገኛለች፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ስሟ በማይገባ (በሙስና) እንዲጠራ አድርገዋል፡፡ የእነዚህ ሰዎች ማንነት ሲፈተሸ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ያልሆኑ ገንዘቧን እንደፈለጉ የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ቤተ ክርስቲያኗ የመልካም አስተዳደር ባለቤት እንዳትሆን በተለያየ ስልት ሲያከሽፉ ቆይተዋል፡፡ በተለይ ችግሩ እንደመዥገር ተጣብቆ ያለው አዲስ አበባ ላይ ነው፡፡

 

በቤተ ክህነቱ ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራር እንዳይሰፍንና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የማይገባቸውን ቦታ ስም እንዲሰጣቸው አድርጓል፡፡ የችግሩ ስፋት በዚህ አያበቃም፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን በዘረኝነትና በጎጠኝነት እንድትተበተብ የፈጠረው ቁርሾ ከባድ ነው፡፡ ገጠር ብትሔድ እንዲህ ዓይነት ችግር የለም፡፡

ካህኑም ምእመኑም ጉቦ አይሰጥም፣ አይቀበልም፡፡ ችግሩ ያለው አዲስ አበባ ዙሪያ ነው፡፡ ለሕዝቡም እየነገርን ከርመናል፤ አንተ ሕዝብ ገንዘብህን ጠብቅ!፤ አንተ ወጣት ቤተ ክርስቲያኗን ከነጣቂዎች ጠብቅ! እኛ ማስተማር ስላለብን ስንናገር ከርመናል፡፡

 

እንደ እውነቱ እኮ እኛ እየመራናቸው፣ ሰንበት ተማሪዎቻችን ጠንካራ ቢሆኑ ኖሮ ከሰባክያን፣ ከቀሳውስትና ከማኅበራት ጋር ተባብረው ሙስናን ከቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት ይበቁ ነበር፡፡ በደንብ ተደራጅተው ገንዘቧን የሚበሉትን መቆጣጠር ይችሉ ነበር፡፡ ሌባ ፈሪ ነው፤ ሌባ ግንባር ለግንባር አይዋጋም፡፡ በሙዳየ ምፅዋቱ ብቻ ታጥረው ቀሩ እንጅ እንደቅዳቸው ቢሆንማ ቤተ ክርስቲያኗን ያጠፏት ነበር፤ ግን አልሆነላቸውም፡፡

ወደ ፊት ሙስናን ከቤተ ክርስቲያቱ ለማጥፋት ምን የተጀመረ እንቅስቃሴ አለ?

ይህ የሚያበቃበት ጊዜ በቅርብ ቀን እንደሚሆን እምነት አለኝ፡፡ ሙስና ይቁም እያልን ሁሉ ጊዜ ስንጮህ ቆይተናልና፡፡ መጀመሪያ መሣሪያ ይዞ ማስወጣት ሳይሆን ማስተማር ስላለብን ቀደም ብለን እያንዳንዱ ምእመን እስኪሰርጸው ድረስ እያስተማርን ነው፡፡ አሁን ግን በአባቶቻችን ሊቃውንት እየተረቀቀ ያለው መሪ እቅድ ሲጠናቀቅ የሙሰኞች ሰንሰለት ይበጣጠሳል ብለን እናምናለን፡፡ ምክንያቱም መሪ ዕቅዱ ለካህናቱ፣ ለሰበካ ጉባኤው፣ ለሰንበት ተማሪዎች፣ ለማኅበራቱ ከፍተኛ አቅም ይፈጥርላቸዋል፡፡ እነዚህ አካላት ተባብረው ከሠሩ ቤተ ክርስቲያን ከሙስና ትጸዳለች፡፡

 

በዚህ አሠራር ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ የሚፈለገው ለውጥ ይመጣል ባይ ነኝ፡፡ በመሪ ዕቅዱ ካህኑ፣ አለቃው፣ ሒሳብ ሹሙ፣ ፀሐፊው እስከ የት ድረስ ነው ሓላፊነታቸው፣ የተቆጠረው ገንዘብ መዋል ማደር ያለበት የት ነው፤ ገንዘብ ቆጠራው ላይ ማን ይገኝ እና ሌሎች አሳቦች ይካተታሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቷ በምእመናን እጅ፣ በካህናት እጅ ስትሆን ነው ትክክል የምትመጣው፡፡ አለበለዚያ. . . ቤተ ክርስቲያኒቱን ባዶ ያደርጓታል፡፡ ይህ መቆም አለበት፡፡ እስከዛው ግን እያስተማርን እንደሆነ ሙሰኞች ይወቁት፡፡

ይልቅስ?


ቤተ ክርስቲያኒቷ ገና ያልሠራቻቸው ብዙ የቤት ሥራዎች አሉባት፡፡ ይህንን ነው መሥራት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ብዙ የልማት ሥራዎች ያስፈልጓታል፡፡ በበቂ ሁኔታ የረዳናቸው ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች የታሉ?፣ የምናሳድጋቸው ዕጓለማውታ ሕፃናት የታሉ? የታለ አረጋውያንን የምንጦረው? ስብከተ ወንጌል ያልተዳረሰባቸውን ጠረፋማ አካባቢዎች የታለ አስተምረን ያስጠመቅናቸው? ቤተ መጻሕፍት አዳራሽ የት ነው ያለው?፤

 

መኪና ጋራዥ ገብቶ ሲለወጥ እኛ ግን ሰውን የምንለውጥበት መንፈሳዊ ጋራዥ የት ነው ያለው? ስለዚህ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ማኅበራት፣ አባቶት ካህናት እንደዚሁም ደግሞ ከላይም ከታችም ያሉ ምእመናን በሙሉ መጀመሪያ ትኩረታቸው ስለ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዐት፣ ስለ ልማት፣ ስለ አንድነትና ስለ ፍቅር መሆን ይገባዋል፡፡ አበክሬ የምገልጸው የእምነታቸው፣ የሥርዓታቸው፣ የታሪካቸው፣ የሀገራቸው ፍቅር እንዲኖራቸውና ለሃይማኖታቸውና ለሀገራቸው ጠበቃ እንዲሆኑ ነው፡፡

በተለይ ማኅበራት፡- በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ማኅበራት አሉ፡፡ መጀመሪያ ቤተ ክርስቲያንን ማስቀደም አለባቸው፡፡ የእኔ መኖር ለቤተ ክርስቲያን ምን ጠቀመ? ማለት አለባቸው፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ተጠግተው የእኔ ድርሻ ምን መሆን አለበት ብለው አባቶችን በመጠየቅ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ሰው ለቤተ ክርስቲያን ዘብ መቆም አለበት፡፡ ይህቺ ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነች ቤተ ክርስቲያናችን እና አንጋፋ ሀገራችን በልጆቿ ማፈር የለባትም፤ ሌቦች ጥቂት ሆነው ብዙዎች ደጅ ሆነው ሲመለከቱ ያሳፍራል፣ በቤተ ክርስቲያኒቷ ሙስና አለ ማለት ያሳፍራል፣ በቤተ ክርስቲያን ድሆች ሲጦሩ፣ ልጆች ሲማሩ፣ መጻሕፍት ሲነበቡ አለማየት ያሳፍራል፡፡ ስለዚህ በአንድነት ስለቤተ ክርስቲያን ዘብ የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው፡፡

 

በቤተ ክርስቲያኒቷ አሁን ያለው እጥረት ተቀራርቦ አለመሥራት፤ አለ መወያየት ነው፡፡ እኛ በአብዛኛው ያሳለፍነው በመወነጃጀል ነው፡፡ ይሄ ደግሞ አየነው የት እንዳደረሰን፡፡ አንዱ አንዱን ሲወነጅል ቤተ ክርስቲያኗን ምን ያህል እንደጎዳት፤ ምን ያህል እሞት አፋፍ እንዳደረሳት ባለፉት ጊዜያት አይተነዋል፡፡ ሁሉም በየራሱ የሚሔድ ከሆነ በጎ አይሆንም፡፡ ተቀራርቦ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ትልቅ የመቀራረብ ሥራ መሠራት አለበት፡፡

 

በአባቶቻችን መሪነት አንድ ሆነን አንተ በዚህ ዝመት፤ አንተ በዚህ ሒድ መባባል ይቻላል፡፡ እንደ ገበሬ አረሙን ወደ ውጭ እየጣሉ፣ የወደቀውን ሰው እያነሡ መሔድ ይቀረናል፡፡ ተቀራርቦ አለመተቻቸትም ይቀረናል፡፡ ጥሩ ወተት ለማግኘት እላሟ ሥር ያለውን መዥገር መንቀል ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም በየራሱ መቅረት መተው አለበት፡፡ አሁንም ጊዜው አለ ተቀራርበን እንሥራ ነው የምንለው፡፡ ምእመናንን ከተኩላዎች፣ ከነጣቂዎች መጠበቅ አለብን፡፡

 

በተጠራጣሪዎችና አማኝ ባልሆኑ አካላት የሚነገር፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከት ዘለፋ ከቀያጮች፣ ከበራዦች፣ ከስም አጥፊዎች የሚላኩ የኑፋቄ ቃላትን አለመቀበል ነው፡፡ የዘመኑን መሣሪያ ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የሚተጉ ተቃዋሚዎች ብዙዎች ናቸው፡፡ እነዚህን መቃወም መቻል አለብን፡፡ ሌላው ሥርዓቱንና ትውፊትን መጠበቅ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊ የሆነው ሥርዓቱን እያከበረ ሌሎችን ይወዳል፣ እምነታችን ሁል ጊዜ የአንድነት፣ የሰላም ምልክት ናት፡፡ መሠረታችን ፍቅር ነው፡፡ ቃሉ ሰውን ውደድ ስለሆነ በዚህ እንትጋ ነው የምለው፡፡

ምንጭ፤- ስምዐ ጽድቅ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኅዳር 1-15 ቀን 2007 ዓ. ም.