‹‹ሁሉም ነገር ከንቱ ነው›› (መክ.፩፥፪)

መምህር ሃይማኖት አስከብር

ኅዳር ፲፱፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ከፀሐይ በታች ሁሉም እንደ ጥላ የሚያልፍ መሆኑን ጠቢቡ ሰሎሞን በመጽሐፈ መክብብ መጀመርያ ላይ ሲገልጽ ‹‹ሁሉም ነገር ከንቱ ነው›› ብሎ ተናገረ። ጠቢቡ ይህን ያለው በሕይወት ካየው እና ከተረዳው ነው። እርሱም በዚህ ምድር ላይ በዕውቀት፣ በጥበብ፣ በሀብትም ሆነ በሥልጣን የሚተካከለው እንዳልነበረ በመጽሐፈ ነገሥት ተጽፏል፡፡ (፩ኛነገ ፬፥፳፱-፴፩) ሁሉንም ነገር አየው፤ ግን ሁሉም ነገር እንደሚያልፍ ተረዳው። ገና ጽሑፉን ሲጀምር እንዲህ ይላል፤ ‹‹በኢየሩሳሌም የነገሠው የሰባኪው የዳዊት ልጅ ቃል›› ካለ በኋላ ሰባኪው ‹‹ከንቱ ከንቱ የከንቱ ከንቱ ሁሉም ከንቱ ነው፤ ከፀሐይ በታች የሚደከምበት የድካም ሁሉ ትርፉ ምንድንነው?›› (መክ.፩፥፩-፪)

ጠቢቡ ይህን የተናገረበት ምክንያት ከፀሐይ በታች ያለውን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ደስታን የሚሰጠውም ሆነ ለኅሊናው ለዘለዓለም ዕረፍትን የሚሰጠው ነገር አላገኘም። ደስታን ከእግዚአብሔር ውጭ ሊያገኝ አልቻለም። በዚህ ምድር ያሉ ሀብት፣ ሥልጣን፣ ዕውቀትና ጥበብ ለኅሊናው ዕረፍት አልሰጡትም፤ ይልቁንም ጠዋት ታይተው ከሰዓት የሚጠፉ ጤዛ ሆኑበት እንጂ። ብዙ ተስፋ ያደረጋቸው ባዶ ሆኑበት፤ የብዙ ዕቁባቶች እና ሚስቶች መብዛት ለእርሱ ደስታ አልሰጡትም፡፡

ጠቢቡ የዚህን ዓለም ማንነት በመረዳት ኃላፊና ከንቱ መሆኑን ተናግሯል። ስለዚህ በዚህ ምድር ላይ የምንመካበት አንዳች ነገር እንደሌለ አውቆ ስለተረዳ ‹‹ሁሉም ከንቱ ነው›› አለ። ትምክህትስ በእግዚአብሔር መመካት ነው። ነቢዩ ኤርምያስ በትንቢቱ እንዲህ ይላል፤ ‹‹ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፤ኃያልም በኃይሉ አይመካ፤ ባለጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፡- ምሕረትንና ፍርድን፥ ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቅና በማስተዋል በዚህ ይመካ፡፡›› (ኤር.፱፥፳፫)

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ይህንንም ሐሳብ ሲያጠናክረውና ሥጋ የለበሰ ሁሉ በሥጋዊ አስተሳሰብ እና ጥበብ፣ ዕውቀት፣ ሀብት፣ ሥልጣን እንዳይመካ ይልቁንም በፈጠረው በእግዚአብሔር ፊት ትሑት ሆኖ የሰጠውን እግዚአብሔርን እንዲያመስግነው እንጂ እንዳይመካ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፤ ‹‹ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ ነገር ግን የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደተጻፈው ይሁን፡፡›› (፩ኛቆሮ.፩፥፳፱፥፴፩)

ስለዚህም በዚህ ምድር ላይ ያለው ሀብት፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ ሁሉም ነገር ራሱ ባለቤቱ መድኅነ ዓለም ክርስቶስ እንደ ተናገረው እንደ ምድረ በዳ አበቦች ነን። የምድረ በዳ አበቦች አሁን በዚህ ወቅት ስናያቸው ለምልመው አብበው ተውበው ይታያሉ፤ ማራኪ እና ሳቢ ሆነው ባለ ግርማ ሆነውም ይታያሉ። ነገር ግን አይመኩም፤ ነገ ወደ መቃጠል ወደ መጥፋት ይሄዳሉ፤ ይልቁንም እነርሱ ማበባቸውን እና ማለምለማቸውን ሳይዘነጉ ለማፍራት ነገን የሚተኩበት ፍሬ ያፈራሉ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ላይ ‹‹የምድረ በዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ እዩ፤ አይደክሙም፤ አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፡- ሰሎሞንስ እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልነበረም፡፡ “እብለክሙ ከመ ሰሎሞን ጥቀ ኢለብሰ በኩሉ ክብሩ ከመ አሐዱ እምእሉ፤ ሰሎሞንስ እንኳን በዚያ ሁሉ ባለ ጠግነቱ ከጽጌያት ሁሉ እንዳንዱ እንዳልበሰ” እነግራችኋለሁ›› በማለት የተናገረው ለዚህም ነው፡፡ (ማቴ.፮፥፳፰)

እነዚህ አበቦች ለጊዜው ቢያምሩም ይጠፋሉ፤ ይደርቃሉ፤ ነገር ግን ነገን እራሳቸውን የሚተኩበት ፍሬን አፍርተው ያልፋሉ። የሰው ልጅም ከእነዚህ አበቦች ትምህርት በመውሰድ የዚህ ዓለም ውበት፣ ጥበብ፣ ሥልጣን እና ዕውቀት የሚጠፋ መሆኑን ተረድቶ፣ ይልቁንስ በሚጠፋው ሀብትና ሥልጣን በሚደበዝዘው ወጣትነት የማይጠፋ ዘለዓለማዊ ሥራን መሥራት ተገቢ ነው። ለዚህም መድኅነ ዓለም ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ሲናገር ‹‹ምንተ ይበቁዖ ለሰብእ ለእመ ኵሎ ዓለመ ረብሐ ወነፍሶ ሀጉለ፤ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ቢገዛ ነፍሱን ካጣ ምን ይጠቅመዋል›› ብሏል፡፡ (ማቴ.፲፮፥፳፮) ስለዚህ የዚህች ዓለም ዕውቀት፣ ጥበብ፣ ሥልጣን፣ ሀብት ከእግዚአብሔር የሚለይ ከሆነ ከንቱ ነው። እግዚአብሔር የሌለበት ሁሉም ነገር ነፋስን እንደመከተል ነው። ነፋስ ብትከተለው፣ ብትከተለው ተደክማለህ እንጂ አትደርስበትም፤ አትጨብጠውም፤ በዚህ ዓለም ያሉ አማላይ እና ማራኪ የሚመስሉ ነገር ግን ደስታን እና ዕረፍትን የማይሰጡ ናቸው። ለምን ካልን መልሱ እግዚአብሔር የሌለበት እና የማይመሰገንበት ስለሆኑ ነው። ንጉሥ ሰሎሞን ከንቱ ያላቸውን ነገሮች በአጭሩ ስንገልጻቸው እንደሚከተለው ነው፦

፩. ሥልጣን

ሥልጣን (ንግሥና) አያስፈልግም ማለት አይደለም። ይልቁንም የተሾመበትን ዓላማ አውቆ በሥልጣኑ ሳይታበይ ይልቁንም በሚያልፍ ሥልጣኑ የማያልፍ ሥራ እንዲሠራ እግዚአብሔር ይሾማል። በዘመናችን ስናይ ግን ሰሎሞን እንደተናገረው የሥልጣንን ከንቱነት ያልተረዱ፣ በሥልጣናቸው መልካም ሥራ ከመሥራት ይልቅ ክፋትንና ተንኮልን በማብዛት እግዚአብሔርን ሲያስከፉትና ሲበድሉበት እናያለን። ይህ የሥልጣን ኃላፊነትን አለመረዳታቸውና አለማወቃቸው ነው። ከጠቢቡ ሰሎሞን በላይ ሥልጣን፣ ጥበብ እና ዕውቀት ያለው አልነበረም ነበር። ግን እርሱ ሁሉም ከንቱ እንደሆነ ነግሮናል። ዛሬ ዙፋን ላይ ቢሆን ነገ ይሻራል፤ ዛሬ ፈራጅ ቢሆን ነገ ይፈረድበታልና። ስለዚህ ወዳጄ ሆይ፥ ዛሬ ዙፋን መቀምጥክህን ሳይሆን ነገ መውረድህን አስብ፤ ይልቁንም ሥልጣን የሰጠህን እግዚአብሔርን አትርሳ!

፪. ሀብት

ሀብት እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠው ስጦታ ነው፤ ፈጣሪያችንን የሚያስደስት ሥራ እንድንሠራበት እንጂ ከእግዚአብሔር ተለይተን ኀጢአት እንድንሠራበት ግን አይደለም። ሀብትም ከተጠቀምንበት የእግዚአብሔር ስጦታ ስለሆነ ለኑሯችንም መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔርን የምንረሳበት ወይም ኀጢአት የምንሠራበት አይደለም። መልካም የሆነውን ሁሉ ልናደርግበት ከእግዚአብሔር የተሰጠን እንጂ። እኛማ ምን አለን! ታላቁ አባት ኢዮብ እንደተናገረው ‹‹ ከእናቴ ማሕፀን ራቁቴን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደ ምድር እመለሳለሁ፡፡›› አንዳች ነገር ሳንይዝ ከእናታችን ማሕፀን ወጣን፤ እግዚአብሔርም ሁሉን አዘጋጅቶ ሰጠን። ነገ ያልፋል፤ ትተነውም እንሄዳለን። ስለዚህ የተሰጠን የሚያልፈውን ሀብታችን ልናጣው እንደምንችል በማሰብ የማያልፍ ሥራ እንሥራበት!

፫. ወጣትነት

ወጣትነት እግዚአብሔር የሰጠን ሌላኛው ስጦታ ነው። ጠቢቡም ይህንን እንደዚህ ይገልጸዋል፤ ‹‹የጭንቅ ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፤ ደስም አሰኘው።›› (መክ.፲፪፥፩) ወንድሜ ወጣት ሆይ፥ ወጣትነት እግዚአብሔር የሰጠህ ስጦታ ነው፤ ስለዚህም በወጣትነታችን ልንሰክርበት፣ ልንዘሙትበት፣ ልንገድልበት እና ልንቀማበት ሳይሆን የተሰጠን ይልቁንም ይህንን ዕድሜ የሰጠን እግዚአብሔርን እያመሰገንን፣ ተንበርክከን ልንሰግድበት፣ ሩጠን ልናገለግልበት፣ ደካሞችን ልንደግፍበት፣ የተሰጠን ታላቅ ስጦታ ነው። ከላይ እንደዘረዘርናቸው ዕውቀትም የተሰጠ ስጦታ እንጂ ከእኛ አይደለም።

ስለዚህ ማንም ቢሆን ከራሱ የሆነ ነገር የለምና በምንም አይመካ! ይልቁንስ ከንቱ እና ኃላፊ መሆኑን አስቦ የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!