‹‹ጽዮንን ክበቧት›› (መዝ.፵፯፥፲፪)

ዲያቆን ዮሐንስ ተመስገን

ኅዳር ፳፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

መጽሐፈ ኦሪት ዘፀአት የታቦተ ጽዮንን ነገር እንዲህ ይተርከዋል። ሙሴ እስራኤልን ከካራን ወደ ከነዓን ይዞ ሲወጣ በሲና ተራራ ፵ መዓልትና ሌሊት ከዘረጋ ሳያጥፍ ከቆመበት ሳይቀመጥ በፍጹም ጽሙና ሁኖ በጾምና ጸሎት እግዚአብሔርን ጠየቀው። የለመኑትን የማይነሣ የጠየቁትን የማይረሳ እግዚአብሔርም ዐሥርቱ ትእዛዛት የተጻፈበትን ሁለት ጽላት ለሙሴ ሰጠው። ሙሴም ወደ ሕዝበ እስራኤል ይዞ ወረደ። እስራኤል አሮንን አስገድደው፤ በጌጦቻቸው የጥጃ ምስል ያለው ጣዖት ሠርተው እያመለኩ ቢጠብቁት ሙሴ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን ታቦት ሰበረ። ዳግመኛም እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ቀድሞዎቹ አድረገህ ቅረጻቸው ብሎ ጽላትን እንዲያዘጋጅ አስተማረው። ሙሴም እንደታዘዘው አድርጎ ሠራ። (ዘፀ.፳፬ እና ፳፭) ‹‹ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ሙሴ ጽላቶቹን ባይሰብር ጽላትን መሥራት እንዴት ይቻል ነበር? (ሮሜ ፰፥፳፰)

ለ፭፻ ዓመታት ገደማ በእስራኤል ብዙ ገቢረ ተአምራትን ስታደርግ የነበረችዋ ይህች በሙሴ የተቀረጸች ታቦት በቀዳማዊ ምኒልክ በኩል ለኢትዮጵያ ተሰጠች። (መጽሐፈ ክብረ ነገሥትን ሙሉውን ያንብቡ) የቤተ ክርስቲያን መረጃዎች ስለ አመጣጧ እንዲህ ያስነብበናል፤ ‹‹በማእከላዊ ትግራይ አክሱም ሀገረ ስብከት አክሱም ከተማ የምትገኘው ታቦተ ጽዮን በቀዳማዊ ምኒልክ ከኢየሩሳሌም መጥታ በምኩራብ ትኖር ነበር። ይህም ከጌታ ልደት በፊት ፱፻ ዓመት ገደማ ነው።›› (የቤተ ክርስቲያን መረጃዎች፣ በሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት፣ ገጽ ፪፻፭)

በምኩራብ ብትቆይም አብርሃ እና አጽብሐ የተባሉት ነገሥታት ፲፪ መቅደስ ፸፪ አዕማድ ያላት የመጀመሪያዋን ቤተ ክርስቲያን አሠርተውላታል። ቀጣዩ ቤተ መቅደስ በዐፄ አንበሳ ውድም ተሠርቷል፤ ይህን ደግሞ ግራኝ አቃጠለው፤ መልሰውም ዐፄ ፋሲል አሠርተውታል፤ አሁን ያለውን ደግሞ በዘመናዊ መንገድ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ አሠርተዋል፤ ይህን ተከትሎም የጽዮን በዓል በታላቅ ድምቀት ኅዳር ፳፩ ይከበራል።

ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር ናት ከምትባልባቸው ምክንያቶች አንዱ ይህ የጽላተ ሙሴ ወደ ሀገራችን መምጣት ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ኅዳር ፳፩ ቀን በታላቅ ክብር ታከብረዋለች፡፡ በዚሁ ዕለት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወዳጆች ምእመናን በዓሉን ለማክበርና ለመሳለም ወደ አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን በብዛት ይገሠግሳሉ፡፡ ዕጣን፣ ጧፍ፣ ዘቢብና መባ ይሰጣሉ፡፡ ካህናቱም ከዋዜማው ጀምረው በከበሮና በጸናጽል ስብሐተ እግዚአብሔር ያደርሳሉ፡፡ በድርሳነ ጽዮን መጽሐፍ እንደተገለጠው በጽዮን ፊት እንደ የመዓርጋቸው ቆመው ‹‹ዕግትዋ ለጽዮን ወህቀፍዋ፤ ጽዮንን ክበቧት፥ በዙሪያዋም ተመላለሱ›› የሚለውን መዝሙር ከዳዊት እያወጣጡ ይጸልያሉ፤ ይዘምራሉ፡፡ ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ የታቦተ ጽዮንን ተራዳኢነት በምእመናን ፊት ይመሰክራሉ፡፡ (መዝ. ፵፯፥፲፪)

ታቦት የአመቤታችን ምሳሌ ነውናም ነቢያት ስለ ክርስቶስ በተለያየ ኅብረት፣ ትንቢትና አምሳል እንደ ተናገሩ ሁሉ ክርስቶስ ስለሚገኝባት አማናዊት ድንግል ማርያምም ተናግረዋል፤ እግዚአብሔር ወልድ ወደዚህ ዓለም በሥጋ ማርያም ከመገለጡ በፊት ከእግዚአብሔር ተልከው ሕዝቡን ከአምልኮተ ጣዖትና ከገቢረ ኃጢአት እንዲጠበቅ የሚመክሩ፣ የሚያስተምሩና የሚያጽናኑ ነበሩ፡፡ (ሉቃ.፲፮፥፲፯፣ኢሳ.፵፥፩፣ኢሳ.፵፬፥፩-፲፩) የነቢያት ትንቢት ዋናው ዓላማም እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቡን እንደተዋቸው እንደማይቀር፣ ወደዚህ ዓለም መጥቶ. ሰው ሆኖ ተገልጦ. ወንጌልን አስተምሮና ስለ እኛ መከራን ተቀብሎ እንደሚያድነን መግለጥ ነበር፡፡ በዚህም ስለ እግዚአብሔር ማደረያ እመቤታችን ትንቢት ተናግረዋል፡፡ (ኢሳ.፯፥፬፣ማቴ.፩፥፳፫፣ሚክ. ፭፥፪)

በታቦት ሰሌዳ ላይ ‹አልፋ ወዖ› የሚለው ስመ እግዚአብሔር እንደተቀረጸ ሁሉ በአማናዊቷ ታቦት በእመቤታችን ማሕፀንም ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀርጿል። በዚህ ዕለት በኢትዮጵያ የሚከበረው ታቦተ ጽዮን ባለችባት አክሱም ብቻ አይደለም። በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም በታነጹ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በተለያዩ ቦታዎች ይከበራል።

ስለዚህም ተወዳጆች ሆይ! ጽዮንን እንክበባት! በእርሷ ምልጃና ጸሎት እንዲሁም ተራዳኢነት አምላካችን እግዚአብሔር ምሕረቱን ያወርድልን፣ ሰላምና ፍቅር ይሰጠን ዘንድ!

የአምላካችን የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የቅድስት ድንግል ማርያም አምላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!