ግእዝ ዘኢትዮጵያ

በመዝሙርና ኪነ ጥበባት አገልግሎት ክፍል
የካቲት ፲ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

እፎ ኃደርክሙ…

ተናገረው ይውጣ እንጂ አንደበትህ አይዘጋ
የአባቶችህ መገለጫ ዜማቸውን አትዘንጋ

የዕውቀታቸውን ምሥጢር የማንነታቸውን አሻራማ
አንተ ከረሳኸውማ… የአባቶችህ ልጅ አልሆንክማ…

ሲሆን ሲሆን ከነየኔታ አስበልጠህ
በያሬዳዊ ዜማ ቃኝተህ
ግእዝን በግእዝ ላይ ጨምረህ
አዘመንከው አሉ ከአባቶችህ አስበልጠህ
ዋሸሁ እንዴ መቼም እኔ ያንተ አባትህ…

አንተን ወልጃለሁና እንዴት ብዬ እዋሻለሁ
ባአንደበቴስ አብላለሁ

ዘመን አመጣሹ ራዲዮ… “እንግሊዘኛ”…
በግእዝ ተተካ ሲል ሰሞኑን አወጋኛ
ጋዜጣው ፈረንጁ በግእዝ ተክኖ ንግግሩ ገባኛ

ጀርመን የመጻሕፍት ቤት አሜሪካን የቅኔ ውል…
ጣልያን ቅዳሴ ማስመረቅ ይዘዋል
ባንተ ውዱ ልጄ በግእዝ አምነዋል

ይህ ነው የልፋቴ ውጤት ዛሬ…
በጦር የመወጋቴ ጢሻ ለጢሻ የመዞሬ
ለማቆየት ነበር ላንተ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለዛሬ

ታዲያ አኮራኸኝ በቤተ መቅደስ ጠብቀህ
ረቂቅ ምሥጢራቸውን ሳታውቅ ለፈረንጆች አሳውቀህ

ኪስህ ብር ሲሞላው በዘመን ላይ ስትዘምን
በዋሻ በመቅደሱ ያኖርኩትን አንጡራ ሀብቴን…

እያወጣህ ስትመነዝር

ኅሊናህ የተከፈተ መቃብር ሆኖ ሆድህ እንደተራራ ሲከመር
የቅኔ መምህሩ ቅኔን ለማስመረቅ ፈረንጅ ሀገር ትበር?

ወቼ ጉድ!…

ቅኔን ጥለህ ወደ አውሮፓ ስትበር
ያባቶችህ አጥንታቸው እሾህ ሆኖ የማይወጋህ እያየህ ብር
አንተን የመሰለ ምሁር ለገንዘብ ቆጠራ ወደ አውሮፓ ትበር?

የኔ ዘመን ! . . . የቅኔ ተማሪ ምንኛ ተሞኘ
አኩፋዳ አንጠልጥሎ ቆላ ደጋ እየረገጠ የእመአምላክ ስሟን ናኘ

እሾህ እግሩን እየወጋው ውሻ ከጐን ሲጐንጠው
በበግ ለምድ አጊጦ… ውርጭ እና ሀሩሩ ሳይበግረው

ከየኔታ ማዕድ ሲቋደስ ሃሌ ሲል ያድር ነበር፡፡
የብራናው ምሥጢር ገብቶት
የዕውቀት ብልሃቱ ተብራርቶለት

እያዜመ ኑሮበታል
እያዜመ ከብሮበታል

የላሊበላ ቋጥኝ ምሥጢር
የአክሱም ሐውልት መከበር

እንዲገባህ ውስጥህ ካሻ
ሂድ ለግእዝ አምላክ አቅርብ እጅ መንሻ

ማንነትህን ታገኛለህ በሰማያዊ ቋንቋ ቅላፄ ተንቆርቁሮ
በግእዝ የፊደል ገበታ ተቀምሮ

ያ!. . . የኔ ዘመን ምሁር ስለሆዱ ሳይሆን ስለሀገሩ ሲያስብ ኖሮ
ቆዳ አልፍቶ ቀለም ነክሮ

በፍልስፍና ወርቅ ያጌጠ… በመድኃኒት ቅመማ የመጠቀ
ብዙ መጻሕፍት ጽፎ ነበር… ማንነትህን ያሳወቀ

ሂድ ጠይቅ ተረዳ ደብር ገዳማቱን
የግእዝን ጥበብ የዕውቀት ቦታውን
ለማወቅ ከፈለክ ሀገሩን

ዛሬ አውሮፓ አሜሪካ በብራና ፍለጋ ቢታክቱ
ወደው እንዳይመስልህ አቅል ነሥቷቸው ነው ጥበባዊ ሀብቱ

ፍራንክፈርት ቦስተን ዩኒቨርሲቲ ገብተው ግእዝን ቢያጠኑ
ዜማውን አድንቀው ስለአፈጣጠሩ ሲያስብ ቢኖሩ
ቦታውን አውቀው ነው ወደዚያ የሰፈሩ…
የዕውቀትን ፀሐይ መጀመሪያ በሩ

ኢትዮጵያዊ ብርሃን ግእዝ ዘሐበሻ
መጽሐፈ ሕይወት ጥበብን ለሚሻ
መጽሐፈ ፀሐይ የዓለም መጠንሰሻ

ግን ልጄ!…

ያሰኘውን ምሥጢር ሳትረዳ
ባሕር ማዶ ብትፈረጥጥ በሀብት ማዕበል ብትነዳ
በግእዝ መክበርህ ኅሊናህ እያወቀው ለመካድ ብትዳዳ
እንዳለብህ ዕወቅ የማይዝግ የማይነጥፍ ኢትዮጵያዊ እዳ

ግእዝ ዘሐበሻ!

አባቴ ሲተርት ልጅ እያለሁ ሲያስተምረኝ
በሀገር ሥነ ጽሑፍ ለሆዳም በሬ ጭድ ያዙለታል ሲለኝ
አይ ልጅነቴ የበሬን ሆድ ለመሙላት መሰለኝ

ነገር ግን ምሥጢሩ ሌላ ነው
ለራስ ወዳድ ስግብግብ ሰው
የተሰጠ መለያ ነው

ዛሬም የኔ ልጆች!

በማኅሌት ቅዳሴ ባቋቋሙ ተከሌ
በያሬድ ዝማሬ በዋሽራ ቅኔ
በደብር ዐባይ ዜማ ሰለል ኩላ ለኔ

ይሰጠኝ ልቃኘው ምራኝ ልከተልህ
በቁጥሩ ዝለቀው ዜማ ልበልልህ
ካልቻልክ ልቀቅልኝ ባባቶች ወንበር
እኔው ልተካና ስማቸውን ላክብር

እያልክ የተመጻደክበትን
በሰማያዊ ቋንቋ ቅላጼን…
ሰማየ ሰማያትን የጐበኘህበትን
ቢጠይቁህ ግእዝን…
አላውቀውም ስትል ነቀነክ ራስክን
ዲያቆን መሪጌታ የኔታ ቀኝ ጌታ ደብተራ ተማሪ መባልህን ካድኸን

መልስ እንጂ ተናገረኝ
የግእዝ ሀገሩ ኢትዮጵያ ነው በለኝ
በአባቶችህ ሀብት ኩራና አኩራኝ

የግእዝን ትንሣኤ አብስረኝ
የግእዝ ሀገሩ ኢትዮጵያ ነው በለኝ
በግእዝ ልትከብር ዛሬ ቃል ግባልኝ
ኢትዮጵያዊ ግእዝ ለዓለም አሰማልኝ

ግእዝ የኢትዮጵያ…

ኢትዮጵያም የግእዝ መሆኑን አስነግር
በተዋሕዶ ቤት በሀበሻ ምድር!