‹‹ጌታውን ደስ ያሰኘ ታማኝና ቸር አገልጋይ ማነው?›› ቅዱስ ያሬድ

ዲያቆን ግዛዉ ቸኮል

መጋቢት ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የዐቢይ ጾም ስድስተኛው ሰንበት (ሳምንት) ገብር ኄር በመባል ይታወቃል፡፡ ገብር ኄር ማለትም ‹‹ቸር፣ ታማኝ፣ ቅን አገልጋይ›› ማለት ነው፡፡ ይህንን ስያሜ ያገኘበት ምክንያት ከዋዜማው ጀምሮ የሚዘመረው ጾመ ድጓ ‹‹ገብር ኄር ወገብር ምእመን ገብር ዘአሥመሮ ለእግዚኡ፤ ጌታውን ደስ ያሰኘ ታማኝና ቸር አገልጋይ ማነው?›› በማለት በቅዱስ ያሬድ ዜማ ሊቃውንቱ ስለሚያመሰግኑ ነው፡፡ (ጾመ ድጓ ዘገብር ኄር)

በዚህ ዕለትም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸውና በማቴዎስ ወንጌል ላይ የተመዘገበው የአንድ ባለ ሀብትና የሦስት አገልጋዮቹ ታሪክ ይነበባል፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀንም ያ ባለጠጋ አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዱ እንደአቅሙ ለአንዱ አምስት መክሊት፣ ለአንዱ ሁለት መክሊት፣ ለአንዱም አንድ መክሊት ሰጠና ወደሌላ ሀገር ሄደ፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ ተመልሶ መጣ፤ አገልጋዮቹንም ትእዛዙን መፈጸም አለመፈጸማቸውን፣ መታዘዝ አለመታዘዛቸውን ለማወቅ ጠየቃቸው፡፡ በዚህን ጊዜ አምስት መክሊት የተሰጠው ወጥቶ ወርዶ ነግዶና አምስት አትርፎ ደርቦ ዐሥር ስላመጣ ለጌታው እንዲህ አለው፤ ‹‹አቤቱ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት አተረፍሁ›› ብሎ አምስት መክሊት አስረከበ፡፡ ጌታውም፡- ‹‹መልካም፥ አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ እሾምሀለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡›› ሁለት መክሊት የተቀበለውም መጥቶ፡- ‹‹አቤቱ፥ ሁለት መክሊትን ሰጥተኸኝ አልነበረምን? እነሆ ሌላ ሁለት መክሊትን አተረፍሁ›› አለ፤ ጌታውም ‹‹ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡›› አንድ መክሊት የተቀበለው መጣና እንዲህ አለ፡- ‹‹አቤቱ፥ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፥ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ስለ ፈራሁም ሄድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፤ እንግዲህ እነሆ፥ መክሊትህ፡፡›› ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፡- ‹‹አንተ ክፉና ሰነፍ አገልጋይ፥ እኔ ካልዘራሁበት የማጭድ፥ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ ታውቃለህን? ገንዘቤን ለለዋጮች መስጠት በተገባህ ነበር፤ እኔም ራሴ መጥቼ ገንዘቤን ከትርፉ ጋር በወሰድሁ ነበር፡፡›› ከዚያም ጌታቸው ‹‹ይህን መክሊት ከእርሱ ተቀብላችሁ ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ ላለው ሁሉ ይሰጡታልና፤ ይጨምሩለታልም፤ ለሌለው ግን ያንኑ ያለውን ይወስዱበታል፡፡ ክፉውን አገልጋይ ግን፥ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወደ አለ ጨለማ አውጡት›› ብሎ አገልጋዮቹን አዘዘ፡፡ (ማቴ.፳፭፥፲፬-፴)

ባለ አምስት መክሊት የነበረው አገልጋይ ፍጹም ትምህርትን ተምሮ መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ ደቀ መዝሙር ባፈራ መምህር ይመሰላል፡፡ ባለ ሁለት መክሊት የተባለ ፍጹም ትምህርትን ተምሮ መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ ባወጣ መምህር ይመሰላል፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ቀሌሜንጦስን፣ ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዳፈሩ ማለት ነው፡፡ ባለ አንድ መክሊት የተባለ ተምሮ ሳያስተምር የቀረ ነዉ፡፡ ዕውቀት፣ ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት እያለው በግዴለሽነት ኃላፊነቱን ያልተወጣ ነው፡፡ ፍጹም ትምህርት የተማረው ወጥቶ ወርዶ መክሮና አስተምሮ ራሱን አስመስሎ አወጣ፡፡ ባለአንዱ መክሊት ዐላውያን ‹‹እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ፣ መናፍቃን ተከራክረው ምላሽ ቢያሳጡኝ›› ብሎ ፈርቶ ሃይማኖቱን በልቡ በመያዝ ደብቆ በሚኖር ዓይነት ሰው ይመሰላል፡፡ ባለአምስት የተባለ ነቢዩ ሙሴ ነው፤ አምስቱን ብሔረ ኦሪት ጽፏልና፡፡ ሁለት የተባሉ ብሉይና ሐዲስ ናቸው፤ ባለአንድ የተባለ ይሁዳ ነው፡፡ አምላኩን ሽጦ፣ አባቱን ሰልቦ፣ እናቱን አግብቶ ንስሓ ሳይገባ ሞቷልና፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ባላአምስት የተባሉ ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው፤ ቆሞሳትን፣ ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትን በአንብሮተ እድ ይሾማሉ፤ ያጠምቃሉ፤ ያቈርባሉና፡፡ ባለሁለት የተባሉ ቀሳውስት ናቸው፤ እነርሱም ያጠምቃሉ ያቆርባሉና፡፡ ባለአንድ መክሊት የተባሉ ዲያቆናት ናቸዉ፤ ለተልእኮ ይፋጠናሉና፡፡ በዚህ ዘመን ባለ አምስትም፣ ባለ ሁለትም፣ ባለ አንድም ቢሆኑ የተሰጣቸውን መክሊት ተጠቅመው ወጥተው ወርደው ካተረፉ ‹‹ወደ ጌታህ ደስታ ግባ›› የሚለውን ቃል ሰምተው በተድላ ይኖራሉ፡፡

ከዚህ ታሪክ እንደምንገነዘበው ዛሬም እያንዳንዳችን እንደአቅማችን ከአምላካችን ዘንድ የተሰጠን መክሊት እንዳለን ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ወደ ዓለም ያመጣነው የለንምና›› እንዳለ ወደዚህ ዓለም ከመጣን በኋላ መንፈሳዊ ስጦታም ይሁን ቁሳዊ ነገሮች ሁሉንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ተቀብለናል፡፡ በእርግጥ አላስተዋልንም እንጂ ከእግዚአብሔር ያልተቀበልነውና የእኛ የምንለው ነገር ቢኖር ኃጢአት ብቻ ነው፡፡ የምንሰጠው የእርሱን ለእርሱ ነው እንጂ የራሳችን የሆነ ምንም ሀብት የለንም፡፡ (፩ኛ ጢሞ. ፮፥፯)

ታዲያ በዚህ ዘመን ያለን ምእመናን ከጌታችን በተቀበልነው ጸጋ ለእርሱ ታማኞች የሆንን ስንቶቻችን ነን? ራሳችንንስ ቢሆን ምን ያህል ተረድተናል? ቤተክርስቲያንን አገልግለናል? ምክንያቱም የተፈጠርንበት ዓላማ እንድናገለግል ነውና፡፡ አንድ ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር ሁላችንም እንደየአቅማችን እንጂ ከአቅማችን በላይ ባልተሰጠን ነገር እንደማንጠየቅ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ላይ ‹‹እግዚአብሔርም በሰጠን ጸጋ መጠን ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት የሚናገር እንደ እምነቱ መጠን ይናገር፡፡ የሚያገለግልም በማገልገሉ ይትጋ፤ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥም በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛም በትጋት ይግዛ፤ የሚመጸውትም በደስታ ይመጽውት›› እንዳለ ሁላችን በአቅማችን መሥራት እንዳለብን ያስተምረናል፡፡ በሌላ በኩል ሐዋርያው ‹‹መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው›› በማለት በሁሉ አድሮ ሁሉን የሚሠራ እግዚአብሔር አንድ እንደሆነ ነገር ግን የሥራ ክፍል ደግሞ እንዳለው እንድንረዳ ያስተምረናል፡፡ (ሮሜ ፲፪፥፮-፰፣ ፩ኛ ቆሮ. ፲፪፥፬-፲፩)

በዚህ ዘመን በየትኛውም መንገድ ቢሆን ታማኝነት የጠፋበት፣ እኛ ሰዎች በተለያዩ ነገሮች ራሳችንን በመተብተብ ከእግዚአብሔር ኅብረት ተለይተን ማገልገልን ለተወሰኑ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ብቻ የሰጠን ሁነናል፡፡ በዚህም በቤተክርስቲያንና በአማኞቿ ላይ ብዙ ችግሮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነናል፤ አሁንም ቢሆን ከተኛንበት መንቃት ያስፈልገናል፡፡

በዚህ ዘመን ለምንኖር አገልጋዮች አገልግሎታችንን የሚያዳክሙ ነገሮች ምንድን ናቸው?

. የመንፈሳዊ ሕይወታችን መዛል፡- መንፈሳዊ ዝለት በሁለት መንገድ ሊፈጠር ይችላል፡፡ አንደኛው ያለ አቅም የተጀመረን መንፈሳዊ ተግባር ቀስ በቀስ ማቋረጥና ወደቀድሞው ሥጋዊ ሕይወት መመለስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቀስ በቀስ ያደገን መንፈሳዊ ሕይወት የሚጠይቀውን መንፈሳዊ አኗኗር ከመሰልቸት የሚመጣ ነው፡፡ በሁለቱም መንገድ በሕይወቱ ወደኋላ የተመለሰ ሰው ለአገልግሎት (ለመታዘዝና ለመታመን) የነበረው ፍቅር ይቀንስና ሁልጊዜ መጸጸትን ብቻ ሥራው ያደርጋል፤ ‹‹የነበርኩ›› ሕይወትንም ይለማመዳል፡፡

. ምቹ ሁኔታዎችን መሻት፡- ሰዎችን መርጦ መታዘዝና ማገልገል ቀላል ነው፤ ሰው ሲመቸው ማገልገል ሳይመቸው ከቤተክርስቲያን መቅረትንም ገንዘቡ ያደረጋል፡፡ ነገር ግን እስከ መጨረሻው ጸንቶ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ደግሞ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሁሉ ሰማዕትነትን መክፈል ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ የአገልግሎትን ጣዕም አንረዳውም፡፡ ‹‹በዝግታ ቆመህ በጊዜውም ያለጊዜውም ቃሉን ስበክ፤ በሁሉም እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ገሥጽ፤ ዝለፍ፤ ፈጽመህ አጽናና፤›› ያለውን የሐዋርያውን ቃል ማሰብ ጠቃሚ ነዉ፡፡ (፪ኛ ጢሞ. ፬፥፪)

፫. ዓላማን መርሳት፡- መታዘዝም ሆነ መታመን ትርጒም የሚኖረው በዓላማ ሲፈጸም ነው፡፡ ኃላፊነትን መርሳት ከመስመር ያርቀናልና ሁልጊዜ የመጣንበትን ዓላማ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ነገር ግን ከተመሠረተው በቀር ሌላ መሠረት ሊመሠርት የሚችል የለም›› ብሎ እንደተናገረው መሰባሰባችንን ለሌላ ዓላማ መጠቀምም ሆነ ማሰብ ተገቢ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፫፥፲፩)

፬. ባላገለግልም እጸድቃለሁ ብሎ ማሰብ፡- በእርግጥ ለጽድቅ የሚያበቃን የእግዚአብሔር ቸርነት እንጂ የእኛ በጎ ምግባር ብቻ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ነቢዩ ኤርምያስም ‹‹ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና›› በማለት ተናግሯል፡፡ ባላገለግልም እጸድቃለሁ ብሎ ማሰብ ራስ ወዳድነት ከመሆኑም በላይ ድርሻንም አለመገንዘብና አለማወቅም ጭምር ነው፡፡ ባለአንዱ መክሊት ድርሻውን ስላልተወጣ የተፈረደበት ለዚህ ነው፡፡ ‹‹በብዙ ድካምና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ ይገባናል›› በማለት መጽሐፍም ያስረዳናል፡፡ (ሰቈ. ኤ. ፫፥፳፪፣ ሐዋ. ፲፬፥፳፪)

በጎ አገልጋይ ለመሆን ምን እናድርግ?

፩. መታዘዝ፡- የሰው ልጅ በፈጣሪው አርአያና አምሳል ሲፈጠር የሚያዝም የሚታዘዝም ሆኖ ነው፡፡ አገልግሎት (መንፈሳዊነት) መታዘዝ ነው ስንል እንደ ባለአምስቱና ባለሁለቱ አገልጋዮች ያለምንም ማጉረምረም ከኃጢአት በስተቀር ሁሉንም ተቀብሎ ማከናወን ማለት ነው፡፡ አብርሃም ‹‹ልጅህን ሠዋልኝ›› የሚለውን የእግዚአብሔርን ጥያቄና ትእዛዝ የተቀበለው በጸጋም በደስታም ነው፡፡ ነቢያት፣ ሐዋርያት ኃላፊውን ዓለም በማይታየው ዓለም ለውጠው መንፈሳዊ ተልእኮን እንዲወጡ ለእግዚአብሔር ቃል ሲታዘዙ በደስታ ነበር፡፡ ስለዚህ እኛም የአባቶቻችንን መታዘዝ መታዘዛችን ልናደርግ ይገባናል፡፡

፪. በትጋት ማገልገል፡- ከዘመነ አበው ጀምሮ የእግዚአብሔር ወዳጆች እየተባሉ የሚጠሩ ሁሉ የፍቅረ እግዚአብሔር መገለጫቸው ትጋታቸው ነበር፡፡መንፈሳዊ ሕይወት ከትጋት ውጭ መለኪያ የለውም፡፡ ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት የተመረጡት ከሥራ ቦታቸው ነው፡፡ ጌታችን ሲመርጣቸውም እጅግ በጣም ትጋትን ለሚጠይቅ ተልእኮ ነበር፡፡ ዋጋን ለመቀበል ከጠዋት እስከ ማታ በአገልግሎት መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም በምሳሌ ‹‹በሥራው ታካች የሚሆን የሀብት አጥፊ ወንድም ነው›› በማለት ትጋት የመንፈሳዊ ዋጋ መጠበቂያ መሆኑን አስረድቷል፡፡ (ማቴ. ፲፥፩-፲፬፣፳፥፩-፲፪፣ ምሳ.፲፰፥፱)

፫. በተስፋ የተመላ ትጉህ አገልጋይ መሆን፡- የሰው ልጅን በተለይም በመንፈሳዊ ሕይወት የሚመሩ የእግዚአብሔር ወዳጆችን ከሌላው ሥነ-ፍጥረታት የተለዩ የሚያደርጋቸው ተስፋ ነው፡፡ የተወለደው የማደግ ተስፋ፣ ያደገው የመኖር ተስፋ፣ በኃጢአት የወደቀው በንስሓ የመነሣት ተስፋ፣ ቤተክርስቲያንን የማገልገል ተስፋ፣ መንግሥተ ሰማያትን የመውረስ ተስፋ ለሰው ልጆች በተለይም ለእኛ ለክርስቲያኖች የተሰጠን ተስፋችን ነው፡፡

ነቢያትን በትንቢት ያጸናና መከራውን እንዲታገሡ ያደረጋቸው፣ ሐዋርያትን በሐዋርያነት ያጸናና በሰማዕትነት ያጠነከራቸው፣ ከዘመነ አበው እስከ ዕለተ ምጽአት ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር አስተሳስሮ የሚኖር ኅቡእ ሰንሰለት ተስፋ ነው፡፡ አባቶቻችን ‹‹የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን›› ማለታቸው የፍርድ ቀን መኖሩን በተጨባጭ በመንፈሳዊ ዓይን ከሩቅ በማየታቸው ነው፡፡ በሰዓቱ ዋጋን ለመቀበል ግን በተስፋ የተመላ ትጉህ ሠራተኛ (አገልጋይ) ሆኖ መገኘት የግድ ነው፡፡

በአጠቃላይ እኛም ኦርቶዶክሳውያን በመንፈሳዊ አገልግሎት ነግደን እንድናተርፍበት ከጌታችን የተሰጠንን መክሊት በግዴልሽነት፣ በትዳር፣ በትምህርት እና በቦታ ርቀት ምክንያት አንዳችን ካንዳችን ባለመስማማት ለራሳችን ሰበብ እየፈጠርን እንደ ባለአንዱ አገልጋይ ከቀበርነው ቆይተናል፡፡ ጌታችንም የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት ስለማናውቅ ከቀበርንበት አውጥተን ልናተርፍበት ይገባናል፡፡ ‹‹እነሆ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ የመዳን ቀን ዛሬ ነው›› እንዳለ ሐዋርያው አትርፎ መገኘት ለእኛ ለክርስቲያኖች የግድ ያስፈልገናል፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፮፥፪)

ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ‹‹መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ፤ በጎ ሥራ እየሠራ ጌታው ያገኘው ቸርና ታማኝ አገልጋይ ማነው?›› እንዳለ ታማኝነት እና መታዘዝ ከሌለን፣ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ከራቅን፣ በጌታችንም ፊት መሾም መሸለም፣ ወደ ዘለዓለማዊ ደስታ መግባት አይኖረንም፡፡ ስለዚህ በተሰጠን ስጦታ፣ ሀብት፣ አቅም፣ ጊዜ፣ ቦታና ዕድሜ ሥጦታውን ለሰጠን እግዚአብሔር ታምነንና በአገልግሎት ጸንተን ወጥተው ወርደው አትርፈው ከተሾሙት ወገን እንዲደምረን አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱ ይፍቀድልን፤ አሜን፡፡