dn. reda wube

ዲያቆን ረዳ ውቤ አረፉ

ኅዳር 17 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


dn. reda wubeበሲዳሞ  ክፍለ ሀገር፣ ቡሌ ወረዳ በሚገኘው ጎንፈራ ቀበሌ፥ ከወላጅ አባታቸው አቶ ውቤ አብዲና ከእናታቸው ከወ/ሮ መሰለች ተመስገን፥ መጋቢት 5 ቀን 1955 ዓ.ም የተወለዱት ዲ/ን ረዳ ውቤ፤ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በልዩ ልዩ የሕክምና መስጫ ተቋማት ሲረዱ ቆይተው  በ50 ዓመታቸው ኅዳር 10 ቀን 2005 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተው፥ ኅዳር 11 ቀን 2005 ዓ.ም በቡራዩ ፄዴንያ ስመኝ ማርያም ገዳም ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡

 

ዲያቆን ረዳ ውቤ ከልጅነት ዕድሜያቸው አንሥቶ ለቤተ ክርስቲያን  ትምህርትና አገልግሎት ከነበራቸው ጽኑ ፍቅር የተነሣ፥ ከመምህራቸው አባ ኀይለ ማርያም ግብረ ዲቁናን ተምረው በ1969 ዓ.ም በወቅቱ የሲዳሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ብፁዕ አቡነ በርቶሎሚዎስ መዓረገ ዲቁናን ተቀብለዋል፡፡ከዚህ በኋላ ከ1969 እስከ 1977 ዓ.ም የይርጋለም ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ሰንበት ትምህርት ቤትን በመመሥረትና ለአምስት ዓመታት በሰብሳቢነት፣ እንዲሁም ሰንበት ትምህርት ቤቱን በመወከል በደብሩ የሰበካ ጉባኤ በጸሓፊነት አገልግለዋል፡፡ ዲያቆን ረዳ ከ1978 እስከ 1980 ዓ.ም በባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲቲዩት በነበራቸው የትምህርት ቆይታ፥ በባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት በአባልነት ተመዝግበው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች  ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲሄዱና በሰንበት ትምህርት ቤት እንዲሳተፉ፡ አልፎም ዛሬ በመላ ሀገሪቱ እየተካሄደ ላለው የግቢ ጉባኤ መጀመር ምክንያት ለመሆን የበቁ ሰው ናቸው፡፡

 

በዲ/ን ረዳ ውቤ ሕይወትና በአገልግሎታቸው ዙሪያ ከተዘጋጀው የግለ ሕይወት ታሪካቸው ለመረዳት እንደተቻለው፡- የመጀመሪያዎቹን ክርስቲያኖች የአንድነት ኑሮን መሠረት በማድረግ በተቋቋመው የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ አንድነት ኑሮ ማኅበርን ከጥቅምት 2 ቀን 1990 ዓ.ም ጀምሮ በመቀላቀል ነፍሳቸው ከሥጋቸው እስክትለይ በዚያው ቦታ ቆይተዋል፡፡ በዚሁ ቆይታቸውም ማኅበሩን በልዩ ልዩ ሓላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን ማኅበሩ ባካሄዳቸው 15 ዙር የሰባክያነ ወንጌል ሥልጠናዎች ላይ በመምህርነት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም ከ1990 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዕለተ ረፍታቸው የማኅበሩ የሰባክያነ ወንጌል ማሠልጠኛ ትምህርት ክፍል ሓላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡

 

መላ ዘመናቸውን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሰጡት ዲያቆን ረዳ ውቤ  የሳንባ፣ የልብና የጨጓራ ሕመማቸውን ታግሰው ቤተሰባቸውና ማኅበሩ እንዳይጨነቅ ሕመምተኛ ሳይመስሉ የተጣለባቸውን ሓላፊነት በትጋት ተወጥተዋል፡፡ዲያቆን ረዳ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ነበሩ፡፡