ደብረ ምጥማቅ

ግንቦት ፲፱ ቀን ፳፮፲፫ ዓ.ም

ግብጽ በምትገኘው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም በተሠራችው ደብረ ምጥማቅ ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ ድንግል ማርያም ከግንቦት ፳፩ ጀምሮ እስከ ፳፭ ቀናት በተከታታይ በመገለጧ ሕዝበ ክርስቲያን በዓሏን ያከብራሉ፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወደ ምድረ ግብጽና ኢትዮጵያ በተሰደደች ጊዜ በአሁኑ ጊዜ ደብረ ምጥማቅ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ ዐርፈው ነበር:: ጌታችንም ቦታውን ባርኮ የእርሷ መገለጫ እንዲሆን ቃል ኪዳን ገብቶላት ስለነበር ጊዜው በደረሰ ሰዓት ደብረ ምጥማቅ ተገድሞ የበርካታ መነኮሳት በዓት ሆነ:: በደብረ ምጥማቅም እመቤታችንም ቅድስት ድንግል ማርያም ብርሃን ተጎናጽፋና በሠራዊት መላእክት ታጅባ ተገልጣለች፤ በዚያን ጊዜም ሱራፌል ማዕጠንታቸውን ይዘው ሰገዱላት፤ እንዲህ እያሉም አመሰገኗት፤ ‹‹አብ በሰማይ አይቶ እንዳንቺ ያለ አላገኘም፤ ባንቺም ሰው ሆነ፡፡›› (መጽሐፈ ስንክሳር ግንቦት ፳፩ ገጽ. ፫፻፲፰)

ሰማዕታትም እንደየክብራቸው ማዕረግ ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ሊሰግዱ ረቂቃን በሆኑ ፈረሶቻቸው ተቀምጠው ወደ እርሷ ቀረቡ፤ በመጀመሪያ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሁሉም ቀድሞ ከሰገደላት በኋላ ሌሎቹም በተመሳሳይ መልኩ ሰገዱላት፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ መርቆሬዮስ በዱሪ ፈረስ ተቀምጦ ወደ እርሷ በመምጣት ሰገደላት፡፡ ጻድቃን በአንድነት ቀርበው ለክብሯ ሰገዱላት፤ ቀጥሎም በንጉሥ ሄሮድስ በግፍ የተገደሉት ሕፃናት ለእርሷ ሰገዱ፤ በደስታና በፍቅርም ተጫወቱ፡፡ በዚያ የተሰበሰቡትም ክርስቲያኖች፣ እስላሞችና አረማውያን ይህን በአዩ ጊዜ ደስታ ሞልቶባቸው በተለየ ዓለም ያሉ ይመስላቸው ነበር፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ግንቦት ፳፩ ገጽ. ፫፻፲፰)

አባ ጽጌ ድንግልም በደብረ ምጥማቅ በታላቅ ክብር ለምእመናን የታየችው የአምላክ እናት የድንግል ማርያምን መገለጥ በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ እንዲህ በማለት ገልጾታል፤ ‹‹አመ ትበርቂ በደብረ ምጥማቅ ኀምሰ ዕለታተ፣ ትእምርተ ገጽኪ ይርአይ እስከ ይትነሣእ ዘሞተ፣ሚ መጠነ ማርያም ታሥተፌሥሒ ትፍሥሕተ፣ ኅድጊሰ ጽጌ ፍቅርኪ በጊዜ ንቃሁ መዓልተ፣ ብፁዕ ዘርእየኪ በሕልሙ ሌሊተ፤ የፊትሽን መልክ ያይ ዘንድ የሞተ ሰው እስኪነሣ ድረስ በደብረ ምጥማቅ ለአምስት ቀናት ያህል በተገለጽሽ ጊዜ ማርያም ምን ያህል ደስ ታሰኚ ኖሯል! በቀን የታየው የፍቅርሽ አበባ ይቅርና ሌሊት በሕልሙ ያየሽ ምስጉን ነው፡፡›› (ማኅሌተ ጽጌ)

በደብረ ምጥማቅ ከተሰበሰቡት ሕዝብ መካከል እናትና አባታቸው፣ ዘመዶቻቸው እንዲሁም ባልንጀሮቻቸው የሞቱባቸው ሰዎች ቅድስት ድንግል ማርያም እንድታሳያቸው በለመኗት ጊዜ እንደ ቀደመ መልካቸው አድርጋ ታሳያቸው ነበር፡፡ አንዳንዶች ደግሞ መሀረባቸውን ወደ ላይ በሚወረውሩት ጊዜ እርሷ የወደደቻቸው እንደሆነ በእጅዋ ተቀብላ መልሳ ትጥልላቸዋለች፤ ሁሉም ለበረከት ይካፈሉታል፡፡ እነርሱም ወደ ቤታቸውም ለመሄድ በሚፈልጉ ሰዓት ተሰናብተውና በተባርከውም ይሄዳሉ፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ግንቦት ፳፩ ገጽ. ፫፻፲፱)

የደብረ ምጥማቅና የአካባቢዋ ሰዎች እመቤታችን ድንግል ማርያምን ያዩባቸው ቀናት አረማውያኑ ያመኑበት፣ የበደሉት በምልጃዋ ቸርነትን ምሕረትን ያገኙበት፣ ያመኑት ደግሞ የተባረኩበት ዕለታት ነበሩ፡፡ ሕዝቡ እርሷን ተመኝተው ያጡት ወይንም ጠይቀው ያልተፈጸመላቸው ምንም ነገር አልነበረም:: ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ ደናግል፣ መነኮሳት መላእክትና ሊቃነ መላእክትም ለድንግል ማርያም ሲሰግዱ ይታዩ ነበር::

ከዚህ በኋላ በዘመናት ይኖሩ የነበሩ ቅዱሳን የአምላክን እናት ለማየት ብዙዎች ተመኝተዋል፤ የመልክአ ማርያም ደራሲ ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ የአምላኩን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን ፊቷን ለማየት ሽቶ ‹‹ሰላም ለመልክእኪ ዘተሠርገወ አሜረ ዘያበርህ ወትረ ፍቅርትየ አንቲ እንተ ታበድሪ ፍቅረ አርእዪኒ ገጸ ዚኣኪ ማርያም ምዕረ ዘኢይሰምዖ ካልእ እንግርኪ ነገረ፤”
ዘወትር የሚያበራ ፀሐይን ጌጥ ላደረገ መልክሽ ሰላምታ ይገባል፤ ፍቅርን የምትመርጪ (የምታስቀድሚ) አንቺ የምወድሽ ማርያም ሌላ የማይሰማው ነገርን እነግርሽ ዘንድ አንድ ጊዜ ያንቺን ፊት ግለጪልኝ (አሳይኝ)››  በማለት ተማፅኗታል፡፡ (መልክአ ማርያም)

ነቢዩ ዳዊት ‹‹ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኲሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር፤ የምድር ባለጠጎች አሕዛብ ሁሉ በፊትሽ ይማለላሉ›› በማለት ትንቢትን እንደተናገረላት በርካት ቅዱሳን ሰዎች ቅድስት ድንግል ማርያምን ተገልጻላቸው ለማየት ተመኝተዋል፤ ልመናቸው ተሰምቶላቸው የአምላክ እናት ተገልጻላቸው ፊቷን ለማየትን ክብሯን  ለመግለጥ ቅዱሳን አባቶች፣ ጻድቃን ሰማዕታት በቅተዋል፡፡ ይህም የሆነው በፍጹም ልቡናቸው በመማፀናቸውና በፍጹም ትጋት የጌታቸውን እናት ሲያገለግሉ በመኖራቸው እንደሆነ የጻድቃኑ ገድል ምስክር ነው፡፡ እነርሱም ሌት ከቀን ምኞታቸው ይሳካላቸው ዘንድ በጸሎት ይማፀኑ ነበር፡፡ (መዝ. ፵፬፥፲፪)

እመቤታችን ድንግል ማርያምም ጸሎታቸውን ሰምታ ያሰቡትን ትፈጽምላቸው ነበር፤ ምኞታቸው ከተሳካላቸው ቅዱሳን አባቶች መካከል አባ ይስሐቅ አንዱ ነው፤ ይህ ቅዱስ አባትም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በፍጹም ልቡናው ይወዳት ስለነበር ለሰባት ዓመታት  አምላኩን ክብርት እናቱን ያሳየው ዘንድ በጸሎቱ ተማጸነ፡፡ ዘወትር ከሠርክ ጸሎት በኋላ ሌሎች መነኮሳት ለመኝታ ወደ የበዓታቸው ሲሄዱ አባ ይስሐቅ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕሏ ፊት ቆሞ ሦስት መቶ ስግደትን እየሰገደ ይማፀን ነበር፡፡ ከስግደቱም ጋር  ‹‹ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ አርእየኒ እመከ አሐተ ሰዓተ፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለአንዲት ሰዓት እናትህን አሳየኝ›› እያለ ይጸልይ ነበር፡፡ በእንደዚህም ሁኔታ ለሰባት ዓመት ከቈየ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በታላቅ ግርማ ተገለጸችለት፤ የልቡም መሻት ምን እንደሆነ ጠየቀችው፤ አባ ይስሐቅም የርሷን ገጽ ያዩ ዐይኖቹ ሌላ ነገርን ማየት እንደማይሹ ነገራት፤ ከተወደደ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ እንድታማልደውም ተማጸናት፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያምም ልመናውን ተቀበለች፤ ከዚያም በኋላ የዕረፍቱ ቀን ከሦስት ቀን በኋላ መሆኑን አሳወቀችው፤ ባርካውም ወደ ሰማይም በክብር ዐረገች፤ ይህ ቅዱስ አባት ይስሐቅም እርሷን ካየ በሦስተኛው ቀን ዐረፈ፡፡  (መጽሐፈ ስንክሳር ታኀሣሥ ፳፩ ገጽ.፬፻፺፪)

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በደብረ ምጥማቅ ተገልጣ የሕዝቡን ምኞት እንደፈጸመችላቸው የእኛንም በጎ መሻት ትፈጽምልን፤ አሜን፡፡