የጽጌ ወር

መስከረም ፳፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ምድር በአበቦችና በዕፅዋቶች ተሞልታ የምታሸበርቅበት ወቅት የጽጌ ወር በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ የመዳኛችን ተስፋ የሆነችውና የዓለምን ቤዛ የወለደችን ቅድስት ድንግል ማርያም አበባውን በሚያስገኙት ዕፀዋትና በምድር፣ የተወደደ ልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ በአበባው እንደሚመሰሉ ቀደምት ነቢያት አስተምረውናል፡፡ ይህም ዕፀዋትና ምድር መልካም መዓዛ ያለውን አበባና ጣፋጭ የሆነውን መዓር እንደሚያስገኙ የተናገሩት እመቤታችን የቅዱሳን መዓዛቸው የሆነውን ጌታችንን መውለዷን ለመግለጽ ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ከእሰይ ሥር በትር ትወጣለች፤ ከእርሷም አበባ ይገኛል›› በማለት ጌታችንን በአበባው እመቤታችንን ደግሞ በበትር መስሎ ተናግሯል፡፡ ንጉሥ ሰሎሞንም  ‹‹በምድራችን አበባ ታየ›› በማለት ጌታችንን በአበባ እመቤታችንን በምድር መስሏታል፡፡ (ኢሳ.፲፩፥፩፣መኃ.፪፥፲፪)

ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ደግሞ እንዲህ በማለት ገልጿል፤ ‹‹ከእሰይ ሥር የተገኘች መዓዛዋ ያማረ አበባ አንቺ ነሽ፡፡›› እርሱ የተናገረው እመቤታችንን በአበባ (በጽጌ) ልጇን በመዓዛው መስሎ ነው፡፡ (እሑድ ውዳሴ ማርያም) ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን ፀንሳ በነበረበት ወቅት ወደ ግብጽና ኢትዮጵያ በተሰደደችበት በጽጌ ወር ለዮሴፍ አንዳንድ ጊዜ እንደ ጽጌረዳ አበባ ቀይ ሁና፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እንደ ሮማን አበባ ነጭ ሁና ትታየው ነበር፡፡ በብዙ ኅብረ አምሳል ማለት ከራድዮን በሚባል ነጭ ወፍ፣ በአምሳለ ጸምር (በቀይ ግምጃ)፣ በአምሳለ ነበልባልና በሐመልማል፣ በእሳትና በቅጠል፣ በሌሎችም ልዩ ልዩ መልክ ባላቸው ምሳሌዎች የተመሰለ ጌታን ጸንሳ ስለነበር መልኳ ይለዋወጥ ነበር፡፡ ዮሴፍም የሚያውቀውና ቀይ የነበረው መልኳ ተለውጦ እንደ ሮማን አበባ ጸዓዳ ነጭ፣ ነጭ የነበረው እንደ ጽጌረዳ ቀይ ሲሆንበትና መልኳ ሲለዋወጥበት እየደነገጠ ማርያም እያለ እርሷ መሆኗን ስሟን በመጥራት ያረጋግጥ ነበር፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስም ‹‹የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም›› በማለት የተናገረው እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ አተረጓጐም ዮሴፍ መልኳ እንደ ጽጌረዳና እንደ ሮማን አበባ ይለዋወጥበት ስለነበር በአንድ ኅብረ መልክእ (በአንድ ዓይነት መልክ) እንዳላወቃት ለመናገር ነው፡፡ (ማቴ ፩፥፳፭)

በዚህም ወቅት እግዚአብሔር ምድርን በአበባ ማስዋቡ እስከ ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ በቀደሙት አባቶቻችን ዘንድ ዘመነ ጽጌ እየተባለ በቤተ ክርስቲያን ቢዘከርም እንደ አሁኑ ማኅሌተ ጽጌ ሰቆቃወ ድንግል እየተቆመ የእመቤታችን ስደት አይታሰብበትም ነበር፡፡ ቅዱስ ያሬድ በዚህ ወቅት ምድር በአበባ የሚያስውቡትን የሽቱ ዕፀው ናርዶስ ቀንሞስ ሮማን የመሳሰሉትን እያነሣ ምድር በእነዚህ ሁሉ አበባዎች እንዳጌጠችና እንደተዋበች የተናገረውን የየቀኑን መዝሙር እየዘመረች ቤተ ክርስቲያናችን እግዚአብሔርን ታመሰግንበት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ከቅዱስ ያሬድ በኋላ የተነሡት ሊቃውንት ስለእመቤታችን መሰደድ ድርሰት የደረሱ ሊቃውንት የነቢያትን ምሳሌ መነሻ በማድረግ እመቤታችንን አበባውን በሚያስገኙ ያማሩ የሽቱ ዕፀው፣ ልጇን በጽጌ በአበባ እየመሰሉ ማኅሌተ ጽጌና ሰቆቃወ ድንግልን ከደረሱ ማኅሌቷንም መቆም ከጀመሩ በኋላ ወርኃ ጽጌ (የጽጌ ወር) ተብሎ ከመታሰቡ በተጨማሪ የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ሁኖ መከበር ጀምሯል፡፡

በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን  በአባ  ዜና  ማርቆስ  አስተማሪነት  ከአይሁዳዊነት  ወደ ክርስቲያንነት የተመለሰው አባ ጽጌ ብርሃንና (ጽጌ ድንግል) አባ ገብረ ማርያም መምህር ዘደብረ ሐንታው ሁለቱ ማኅሌተ ጽጌንና ሰቆቃወ ድንግልን ደርሰው የእመቤታችን ስደት እያሰቡ ማኅሌት መቆም ከጀመሩበት ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ማኅሌቱ ሳይቋረጥ ቀጥሏል፡፡ ምእመናንንም የእመቤታችን ስደት ለማስታወስ በስሟ ማኅበር በመመሥረት ምንም እንኳን ጾሙ የፈቃድ ቢሆንም ጾም እየጾሙ ዝክር እየዘከሩ ያከብሩታል፡፡ ማኅበሩም የሚጠጣው በቤተ ክርስቲያንና ወይም በቤታቸው ውስጥ ነው፡፡ ከቤታቸው የማይጠጡበት ምክንያት እመቤታችን በረኃ ለበረኃ ስለተሰደደች ያንን ለማስታወስና እንደ እመቤታችን በመንገድ የደከመን እንግዳ ለመቀበል ነው፡፡

የማኅሌተ ጽጌ ደራሲ የሆነው አባ ጽጌ ብርሃን (ድንግል) ከመጠመቁ በፊት ዘካርያስ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ ለማመን ያበቃችውም ገባሪተ ኃይል የሆነች የእመቤታችን ሥዕል ናት፡፡ ብዙ ተአምራትን ስታደርግ ስላየ ወደአባ ዜና ማርቆስ በመሄድ ተምሮ ለማመን በቅቷል፡፡ ከአባ ዜና ማርቆስ ትምህርተ ሃይማኖትን ተምሮ በምንኵስና ሕይወት መኖር ከጀመረ በኋላም ለማመን ያበቃችውን ገባሪተ ኃይል ሥዕል ሳይሳለም አይውልም ነበር፡፡

ከሥዕሏ ፊትም ሲቆም የሚያቀርበው እጅ መንሻ (መባዕ) ስለሌው ይጨነቅ ነበር፡፡ በኋላ ግን ይህ የጽጌ ወር ሲደርስ በየቀኑ ሃምሳ ሃምሳ የጽጌረዳ አበባ እየፈለገ እንደ ዘውድ እየጎነጎነ ለዚያች ምስለ ፍቁር ወልዳ ሥዕል ያቀዳጃት ነበር፡፡ በጋው ሲወጣ የጽጌረዳው አበባ ስለደረቀበት ከሥዕሏ ተንበርክኮ ‹‹እመቤቴ በየቀኑ የማመጣልሽ የጽጌረዳ አበባ ደረቀ፤ ስለአበባው ፈንታ መልአኩ ተፈሥሒ እያለ ያመሰገነሽን ምስጋና በአበባው ቁጥር ልክ ሃምሳ ሃምሳ ጊዜ እንዳመሰግንሽ ፍቀጅልኝ›› በማለት ተማጸነ፡፡ ከዚህ በኋላ በየቀኑ ‹‹ተፈሥሒ ፍሥሕት›› የሚለውን የመልአኩን ምስጋና በየቀኑ ሲያቀርብላት ምስጋናው እንደጽጌረዳ አበባ እየሆነ ከአንደበቱ ሲወጣ እመቤታችን አበባውን እየተቀበላች ስትታቀፈው ሰዎች እያዩ ያደንቁ እንደነበር ገድለ ዜና ማርቆስ ያስረዳል፡፡ እርሱም በድርሰቱ እንዲህ ሲል ገልጾታል፤ ‹‹አባዕኩ ለኪ ስብሐተ ተአምር ዘይሤለስ በበሃምሳ ህየንተ ጽጌያት ሃምሳ ለስዕልኪ አክሊለ ርእሳ፤ ለሥዕልሽ ዘውድ ይሆን ዘንድ ሃምሳ የጽጌ ረዳ አበባ አቀርብልሽ  ስለነበረው  ፈንታ  ሦስት  ጊዜ  ሃምሳ(መቶሃምሳ)  የሚሆን  ምስጋናን አቀረብኩልሽ›› በማለት፡፡ ስለዚህ በጽጌ ወር ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር ምድርን በአበባ ማስጌጡን ማሰባችን እንዳለ ሁኖ በተጨማሪ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንና የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስደት እናስብበታለን፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ጸሎታችንንና ጾማችን ለድኅነት ያድርግልን፤ አሜን፡፡