የከተራ በዓል በደብረ ታቦር ከተማ በድምቀት ተከበረ

 

 

ጥር10 ቀን 2006                                                                                                                      ዳንኤል  አለሙ  ደብረ ታቦር ማእከል

በደብረ ታቦር ከተማ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሰት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ማኅበራት እንዲሁም ሕዝበ ክርስቲያኑ ከሰባት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት የመጡ ታቦታትን አጅበው በአጅባር ባሕረ ጥምቀት በድምቀት ተከበረ፡፡

የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንቱ ታባታቱን በቃለ እግዚአብሔርና በቅዱስ ያሬድ ዜማ፤ ከሰ/ትቤት መዘምራንና ምእመናን ጋር በምስጋናና በእልልታ በማጀብ በዓሉን አድምቀውታል፡፡

የከተራ በዓል መንፈሳዊ ይዘት በተሞላበት ሁኔታ በነጫጭ አልባሳት በደመቁ ምእመናን እና ምእመናት ተከብሮ ሲውል፤ ለከተማው ህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባጃጆች በባንዲራ እና ምስጢረ ጥምቀቱን በሚገልፁ ጥቅሶች ተውበው የተለየ ድምቀት ሰጥተውታል፡፡ በተጨማሪ ታሪካዊ እና ለታላቁ ደብር ለደብረ ታቦር ኢየሱስ በወጣቶች የተሰራ ሰረገላ በዓሉን ካደመቁት ትእይንቶች መካከል አንዱ ነበር፡፡

ደብረ ታቦር ለሀገሪቱ ሊቃውንት መፍለቂያ በመሆን በምሳሌነት የሚጠሩ ካህናት እንደተለመደው ሁሉ የሚማርክ ጣዕመ ዝማሬአቸውና በአባቶችሽ ፈንታ ልጆችሽ ተተኩልሽ እንዳለ ነብዩ ከሊቃውንቱ እግር ሥር ቁጭ ብለው የተማሩ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ የደብረ ታቦር ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤትም ለበዓሉ አከባበር የሚሆን የድምጽ ማጉያ በመስጠት እንዲሁም ከደብረ ታቦር ወረዳ ቤተ ክህነትና ማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመተባበር የሀገሪቱን ባሕልና እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን አድርገዋል፡፡

የከተራ መርሐ ግብሩ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የ4ቱ ጉባኤ መምህር የሆኑት የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ትምህርት፤ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡ እርሳቸውም በዓለ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው አበይት በዓላት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ፤ ታቦቱ ወደ ጥምቀተ ባሕር ወርደው የሚያድሩበት ምክንያት እግዚአብሔር ወልድ በፈለገ ዮርዳኖስ መጠመቁ ምሳሌ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በጥምቀቱም የሰው ልጅ ኃጢዓት የተደመሰሰበት፤ ከኃጢዓት ባርነት የወጣበት መሆኑን ገልጸው ምእመናን ዳግመኛ ወደ ኃጢዓት ባርነት እንዳይመለሱ መትጋ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡ የጥምቀትን በዓልን ስናከብር ድኅንነት ነፍስን የምናገኝበት ከኃጢዓት ጸድተን የዘላለም ሕይወት የምንወርስበት በመሆኑ በሰላምና በፍቅር እንድናከብረው አበክረው አሳስበዋል፡፡

በዓለ ጥምቀቱ የሚከበርበት አጅባር ሜዳ አራት የታቦታት መግቢያ በሮች ያሉት ሲሆን ለብዙ ዘመናት ቅድስት ቤተክርስቲያን እየተገለገለችበት ቆይታለች፡፡ ይሁን እንጂ በሀገረ ስብከቱና በወረዳ ቤተ ክህነቱ ፈቃድና እውቅና የተቋቋመ ኮሚቴ ቢኖርም የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ አለመኖሩ፤ በህዝቡ ዘንድ ስጋት የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ስለሆነም የሀገር እና ቤተክርስቲያን ሀብት በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ተሰጥቶት የይዞታ ማረጋገጫ ሊኖረው እንደሚገባ አባቶች እና የአካባቢው ምእመናን ገልጸዋል፡፡