የቅዱስ ኤፍሬም ቅኔያዊ መዝሙራት

ጥቅምት 30/2004 ዓ.ም

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

መግቢያ

የሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም አጭር የሕይወት ታሪክ

ቅዱስ ኤፍሬም 299 ዓ.ም ገደማ ንጽቢን በምትባለው ታላቅ ከተማ ተወለደ፡፡ ንጽቢን በጥንታዊቱ የሮም ግዛት በምሥራቅ የምትገኝ ከተማ ነበረች፡፡ አብዛኞቹ የታሪክ ጸሐፍት እንደሚስማሙበት ቅዱስ ኤፍሬም ከክርስቲያን ቤተሰብ የተገኘ ሲሆን በተወለደባት ከተማ በድቁና ሲያገለግል ረጅም የእድሜ ዘመኑን ያሳለፈ ቅዱስ ነው፡፡ አንዳንድ የታሪክ ጸሐፍት ግን የቅስና ማዕረግ አንዳለውም ይተርካሉ፡፡ ነገር ግን በአብዛኛዎቹ የሶርያ የታሪክ ጸሐፊያን ዘንድ ቅዱስ ኤፍሬም ዲያቆን እንደነበረ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ስለዚህም እስካሁን ድረስ በሶርያውያን ክርስቲያኖች ዘንድ የድቁና ማዕረግ በቅዱስ ኤፍሬም ምክንያት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ማዕረግ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም በንጽቢን ከተማ ሳለ በቤተ ክርስቲያን በሴቶች ዘማሪያን የሚቀርቡ ብዙ የመዝሙር ድርሰቶችን ደርሶአል፡፡ ቢሆንም በ363 ዓ.ም የሮም መንግሥት በመዳከሙ ምክንያት የፋርስ ንጉሥ ንጽቢን ለእርሱ ተላልፋ እንድትሰጥና በውስጡዋም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከከተማዋ ለቀው እንዲወጡ ባቀረበው የመደራደሪያ ነጥብ የተነሣ ንጽቢን ለፋርስ መንግሥት ተሰጠች፤ ክርስቲያኖችም ከከተማዋ ወጥተው ተሰደዱ፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምና ደቀመዛሙርቱም ወደ ዑር ወይም ኤዲሳ ወደምትባለው ከተማ አመሩ፡፡ በዚያም የእድሜውን ዐሰርት ዓመታት አሳለፈ፡፡ ዑር የምትባለው ከተማ በአሁኑ ጊዜ ኡርፋ በመባል የምትታወቀው በደቡባዊ ቱርክ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ በዚህም ሳለ በከተማይቱ የተነሡትን ከሃዲያንን በመቃወም ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቶ ነበር፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በሚገርም ሁኔታ የግሪካውያንን ፍልስፍና ጠንቅቆ የሚያውቅ ስለመሆኑ ከጽሑፎቹ መረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ድርሰቶቹን ሲደርስ ሴማዊውን የአጻጻፍ ስልት ሳይለቅ ነበር፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በሕይወቱ ክርስቶስን መስሎ ሲያገልግል ሳለ በተወለደ በ67 ዓመቱ ገደማ (በኤዲሳ) ዑር ተቀስቅሶ በነበረው ወረርሽኝ የተጎዱትን ሕመምተኞችን ሲረዳ ቆይቶ በመልካም ሽምግልና ግንቦት 29 በ366 ዐረፈ፡፡ (ዘመን አቆጣጠሩ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ነው)

 

ቅዱስ ኤፍሬም  ከጻፋቸው የመዝሙር ድርሰቶች መካከል

1.ስለክርስቶስ ሥጋዌ 59 መዝሙራት
2.ጾምን አስመልከቶ 67 መዝሙራት
3.ንጽቢንን አስመልክቶ 77 መዝሙራት
4.ስለክርስቶስ ሙሽራ አይሁድን በመቃወም የጻፈው 66 መዝሙራት
5.ስለቤተ ክርስቲያን 52 መዝሙራት እንዲሁም ሌላ ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚያወሳ 52 መዝሙራት
6.ስለእምነት 87 መዝሙራት
7.አሮኒየስ ለሚባለው ከሃዲ የሰጠው መልስና ስለ ገነት 56 እና 15 መዝሙራት
8.ንስሐ ስለሚገቡ ክርስቲያኖችና በሞት ለተለዩ የሚቀርቡ መዝሙራትን አዘጋጅቶአል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ  ዘፍጥረትን፣ ዘጸአትን፣ ዐራቱ ወንጌላትን፣ የጳውሎስ መልእክታትን ተርጉሟል፡፡ የቅዱስ ኤፍሬም ጸሎቱና በረከቱ በእኛ ላይ ይደርብንና ከዚህ በማስከተል ከመዝሙር ድርሰቶቹ መካከል አንዳንዶቹን እንመለከታለን፡፡
ስለገነት የደረሰው መዝሙር

በዚህ መዝሙር ቅዱስ ኤፍሬም እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ይከተላቸው የነበረውን ዓለት በመጥቀስ እግዚአብሔር ፍጥረታትን እንዴት እንደፈጠራቸውና ሌሎችም ስለገነት ያለውን አስተምህሮዎቹን እናገኝበታለን፡፡

1. እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ይከተላቸው የነበረውን አለትን አስታውሼ፤

ዓለማትን የፈጠረውን የእግዚአብሔርን ቃል ልብ አልኩ፤
እንደ ታላቅ ወንዝ ለእነርሱ ከአለቱ ውስጥ የፈለቀው ውኃ፤
በውስጡ ካለው የውኃ ቋት የተገኘ አልነበረም፤
በአለቱ ውስጥ አንድም ጠብታ ውኃ የለም፤
ነገር ግን ልክ የእግዚአብሔር ቃል ፍጥረትን ከምንም እንዳስገኛቸው፤
አንዲሁ ታላቅ የውኃ ጅረት ከደረቅ ድንጋይ ውስጥ ፈለቀ፡፡

2.ሙሴ በመጽሐፉ ስለ ሥነ ተፈጥሮ ገልጦ ጽፎልናል፤

ስለዚህም ተፈጥሮና መጽሐፍ ቅዱስ ስለፈጣሪ ምስክሮች ሆኑ፤
የሰው ልጅ ተፈጥሮን ለራሱ ጥቅም ሲገለገልባት እንደሚያውቃት፤
እንዲሁ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ በውስጡ የያዘውን መረዳት ይቻለናል፤
እነዚህን ሁለቱን ምስክሮች በሁሉ ስፍራ እናገኛቸዋለን፡፡
እግዚአብሔር የለም የሚሉትን ኢአማንያንን ለማሳፈር፣
እነዚህ ሁለቱ በሁሉም ጊዜና ሰዓት የሚገኙ የእግዚአብሔርን መኖር አዋጅ ነጋሪዎች ናቸው፡፡

3.ጌታ ሆይ የመጽሐፍህን መግቢያ ባነበብኩ ጊዜ ልቤ በሃሴት ተሞላ፤

የምንባቡ ቁጥሮችና ኃይለ ቃላት እኔን ለመቀበል እጆቻቸውን ዘረጉ፤
ይዘውኝም በፍቅር አቀፉኝ ሳሙኝም ወደ ወዳጃቸውን መርተው አደረሱኝ፡፡
የገነት ታሪኩዋ እኔን ወደ ላይ ወደ ሰማይ እንድነጠቅና ወደ ውስጥ እንድገባ አሸጋገረኝ፤
ከመጽሐፉ እቅፍ ወደ ገነት እቅፍ ተሸጋገርኩ፡፡

4.ዐይኔና ልቤ ቃሎቹ በሰፈሩበት መስመር ላይ ተጓዙ፤

በድልድይ እንደሚሸጋገር ሰው በገነት ታሪክ ወደ ላይ ተነጠቅሁ፡፡
ዐይኖቼ  ምንባቡን  ሲያነቡ አእምሮዬ ያርፍ ነበር፤  
አእምሮዬ በምሥጢር ሲነጠቅ ዐይኔ ደግሞ በተራው ከማንበብ ያርፋል፤
ከንባብ በኋላ ዐይኖቼ ሲያርፉ አእምሮዬ ምሥጢራትን በመመርመር ተጠመደ፡፡

5.ወደ ገነት መሸጋገሪያ ድልድዩንና መግቢያ በሩን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አገኘሁት፤

ስለዚህም በድልድዩ ተሸጋግሬ በበሩ በኩል ወደ ውስጥ ዘልቄ ገባሁ፤  
በእርግጥ ዐይኖቼ በውጭ ነበሩ አእምሮዬ ግን ወደ ውስጥ ዘልቆ ገብቶአል፤
በቃላት ሊገለጡ በማይችሉት መካከል ቆሜ መደነቅ ሞላብኝ፤
ስፍራው ታላቅ፣ ፀጥታ የሰፈነበት፣ ፍጹም ንጹሕና በክብር ከፍ ከፍ ያለ ግሩም ነበር፡፡
በረከቶች ሁሉ የሚገኝበትን ይህን ስፍራ መጽሐፍ ቅዱስ ኤደን ብሎ ሰየመው፡፡

 

6.    በዚያም ለቅዱሳን የሆነ አጸድና የተንጣለለ ለምለም መስክ አየሁ፤

በላዩም መዓዛው እጅግ ማራኪ የሆነ ሽቱ ተርከፍክፎበታል፤
አጸዱም በፍራፍሬዎች የተጌጠ፣ የፈኩ አበቦቹም አክሊሎች የሆኑለት ነው፤
መስኩ ርስት ሆኖ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን የሚሰጥ ሲሆን፤  
በጽድቅ ሕይወት ላልተጋው ውበቱ ማራኪ ያልሆነ ያልተጌጠ መስክ ይሰጠዋል፤  
ለተጋው ግን ውበቱ ዐይንን አፍዝዞ የሚያስቀር እጅግ ማራኪ የሆነ መስክ ያገኛል፡፡

7.    በአጸድ ውስጥም ሳለሁ ገነት ለቅዱሳን ማረፊያነት ትበቃቸዋለችን? ብዬ ጠየቅሁ፤

መሠረቴን መጽሐፍ ቅዱስ አድርጌ በመጽሐፍ ውስጥ ያልሰፈሩትን ለመመርመር ሞከርኹ፡፡
ሌጌዎን የተባለው የአጋንንት ሠራዊት በአንድ ሰው ሰውነት ውስጥ ሰፍሮ እንደነበር አስተዋልሁ፤(ማር.5፡9-10)
በቁጥራቸው እጅግ የበዙ ቢሆንም ከርቀታቸው(ከጥቃቅንነታቸው) የተነሣ እንደ አንዲት ነፍስ እንኳ ጎልተው መታየት አልተቻላቸውም፡፡

8.     በአንድ አካል ውስጥ የአጋንንት ሠራዊት ከትሞ እንዳለ ነገር ግን እጅግ ረቂቃን እንደሆኑ፤

እንዲሁ በትንሣኤ የተነሡ ቅዱሳን በገነት ውስጥ መቶ ሺኽ እጥፍ ረቀው ይኖሩባታል፡፡   
ገነት በአእምሮ ፣ ቅዱሳንም በአእምሮ የማሰብ አቅም ይመሰላሉ ፤
አንድ ሰው እንደ ፈቃዱ በአሳቡ እጅግ ሊራቀቅና ሊመጥቅ ይችላል፤
ቢፈልግ አመለካከለቱን በአንድ ነገር ላይ ብቻ ሊወስነው ይችላል፡፡
አንድ ሰው አመለካከቱን በቦታ ሊወሰን ወይም በቦታ ላይወስነው ይችላል፤

9.     መብራት ሲበራ እጅግ የብዙ ብዙ ሺኽ ጨረሮች በአንድ ቤት እንዲኖሩ ፤


ከብዛታቸው የተነሣ ቤቱ እንደማይጠባቸው፣  ከአንድ ከፈካ አበባ የሚወጣው መዓዛ አካባቢውን እንዲያውደው ነገር ግን በቦታ እንዲወሰን እንዲሁ በገነትም የሚኖሩ፤ ቅዱሳንም እንደ ብርሃኑ ጨረሮችና እንደ አበባው መዓዛ ናቸው ፡፡

ምንም እንኳ የብርሃኑ ጨረሮችና የአበባው መዓዛ በጠባብ ቦታ ላይ የተወሰኑ ቢሆንም፣
የስፍራው ውሱንነት ግን እንደልባቸው እንዲዋኙ እንዳይከለክላቸው ፤ ገነትም እንዲሁ ለቅዱሳን ናት ፡፡
ስለዚህም ገነት በውስጡዋ በመንፈሳዊ ፍጥረታት የተሞላች ብትሆንም፤
ወደ እርሱ የፈለሱትን ለማኖር ከበቂ በላይ የሆነ ሥፍራ አላት፡፡

10.     በቁጥር እጅግ የበዙ አሳቦች በመጠን ካነሱት የሰውነት ክፍሎቻችን አንዷ በሆነችው በልባችን ውስጥ ይኖራሉ ፤

የአካሉዋ ማነስ አንዱ በአንዱ እንዲወሰን ወይም አሳቦቻችንን እንደልባቸው እንዳንሸራሽር አይከለክለንም፤
ይህ እንዲህ ከሆነ እንዴት ገነት በመጠናቸው እጅግ ረቂቃን ለሆኑት ቅዱሳን ሰውነት የበቃች አትሆን !!
የቅዱሳንን ነፍሳት ርቀትን(ረቂቅነትን)ፈጽሞ በአእምሮአችን ተመራምረን የምንደርስበት አይደለም ፡፡

11.    በገነት መካከል ሆኜ እንደ ችሎታዬ መጠን ምስጋናዬን ለአምላኬ ላቀርብ ሞከርኩ፤

ድንገትም በገነት ውስጥ እንደ ነጎድጓድ የመሰለ ጥሙም የምስጋና ድምፅ ተሠማ ፤
ድምፁም ልክ በአንድ የጦር ሰፈር እንደሚነፋ መለከት ድምፅ ዓይነት ነበር፤
ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሚል የምስጋና ዝማሬ ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ ተሰማ፤
ይህን ስሰማ አምላክ ከቅዱሳኑ ምስጋናን ለእርሱ እየቀረበለት መሆኑን ተረዳሁ ፡፡
እስከዛ ጊዜ ድረስ ግን ገነት ባዶ መስላኝ ነበር፤
ነገር ግን እንደ ነጎድጓድ የሆነውን ይህን ድምፅ ስሰማ ቅዱሳን በዚያ ከትመው እንዳሉ ተማርኹ፡፡

12.    ስለዚህም ገነት በጸጥታዋና በውበቱዋ እጅግ ማረከችኝ ደስም አሰኘችኝ፤

በውስጡዋ ያለው  አጸድ ውበት አንዳች እንከን የለበትም፤  
በውስጡዋ ከሰፈነው ጸጥታ የተነሣ አንዳች ፍርሃት የለም፡፡
ገነትን ለመውረስ የተገባው ቅዱስ እንዴት ብፁዕ ሰው ነው፤
ይህችን ስፍራ እንደ ቅድስናችን መጠን ሳይሆን እንደ እርሱ ጸጋ፤
እንደ እኛ ድካም ሳይሆን እንደ እርሱ ቸርነት የምንወርሳት ናት፡፡

13.     የገነትን ድንበሮችን አልፌ ወደ ውስጡዋ ስገባ በውበቱዋ እጅግ ተደመምኩ፤

በዙሪያው ያሉትን ወዳጆቼን ወደኋላ ትቼ በደኅንነት ወደሚኖሩባት ገነት ዘለቅሁ፤
ነገር ግን ከእርሱዋ ተመልሼ የሾኽና የአሜካላ እናት ወደሆነችው ምድር ስመለስ፤
ልዩ ልየ ዓይነት ሕማማትንና  ስቃዮችን ተቀበልኩ፤
ስለዚህም ገነትን ከምድር ጋር ሳነጻጽራት ልክ እንደወ¬ህኒ ቤት ሆና አገኘኋት፤
ነገር ግን በውስጡዋ ያሉ እስረኞች እርሱዋን ትተው ሲለዩዋት ያነባሉ፡፡ (ይህ ደግሞ የሚደንቅ ነው)

14.    ሕፃናት ከእናታቸው ማኅፀን ሲወጡ ማልቀሳቸው ይገርመኝ ነበር ፤

እኚህ ሕፃናት የሚያነቡት ከጨለማ ወደ ብርሃን በመውጣታቸው ነበር ፤
ከተጨናነቀው ሥፍራ ወደ ሰፊይቱ ዓለም በመምጣቸው ነበር የሚያለቅሱት፡፡
ልክ ከእናታችን ማኅፀን ስንወጣ እንደሚሆነው በሞት ከዚህ ዓለም ስንለይም እንዲሁ እናነባለን፤
ነገር ግን ሰዎች የሚያነቡት የስቃይ እናት ከሆነችው ከዚህች ዓለም ተወልደው እጅግ ግሩም ወደ ሆነችው ገነት ሲገቡ መሆኑ ይደንቃል፡፡

15.    የገነት ጌታዋ የሆንኽ ቸሩ ፈጣሪዬ ሆይ ለእኔ ራራኝ፤

ወደ ገነት ለመግባት ምናልባት እንኳ የበቃሁ ባልሆን፤
ከአንተ ጋር ያሉ ቅዱሳን ከገነት ፍሬዎች ተመግበው ሲጠግቡ፤   
በአንተ ቸርነት ከፍርፋሬአቸው ተመግበን ሕያዋን እንድንሆን፤
በገነት  ባለው አጸድ ዙሪያ እንድንሰፍር ፍቀድልን፡፡

ይቀጥላል ….