የስደት ጦስና ተስፋ

ሰኔ 19 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ

ወቅቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ብላቴ የውትድርና ማሠልጠኛ ጣቢያ እንዲሔዱ የተገደዱበት ነበር፡፡ ተማሪዎቹ በወቅቱ የነበረው መንግሥት ባዘዘው መሠረት ወደ ማሠልጠኛ ጣቢያው ሔደው ለወራት የውትድርናውን ትምህርትና ሥልጠና ወሰዱ፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጥበቃ ሥልጠናው አልቆ ወደ ጦር ግንባር መወሰጃ ጊዜአቸው ሲደርስ ያዘመታቸው መንግሥት በኃይል ሥልጣኑን ለቀቀ፡፡ በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በአውቶቡስ ተጉዘው ብላቴ በረሃ የከተሙት ተማሪዎች መንግሥት ሲፈርስ የእነሱም ካምፕ ፈረሰ፡፡ ግማሹ ወደየመጣበት ሀገሩ፤ ግማሹ ደግሞ ከሚወዳት እናት ሀገሩ ተለይቶ ወደ ኬንያ ተሰደደ፡፡

ወደ ኬንያ ከተሰደዱት ተማሪዎች አንዱ ክብረት /ትክክለኛ ስሙን ቀይሬዋለሁ/ ነበር፡፡ ክብረት ወደ ኬንያ የተሰደደው ጠላ ጠምቀው በቆልት አብቅለው በመሸጥ ያስተማሩትንና የሚወዳቸውን እናቱን ለመለየት እየጨነቀው ነበር፡፡ ምንም እንኳን ምርጫቸው እንደ አብሮ አደግ ጓደኛቸው ክብረት ወደ ኬንያ መሔድ፤ ከዚያም አውሮፓ¬ ወይም ካናዳ ከተቻለም አሜሪካ መግባት የነበረ ቢሆንም፤ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ከብዙ ድካምና ረሃብ በኋላ አገራቸው የገቡት የክብረት ሁለት የሠፈር ልጆች፤ እንደደረሱ ለክብረት እናት በማለዳ ሔደው “እትዬ አበባ /ስማቸው አይደለም/ እንኳን ደስ አለዎት እኛ ፈሪዎች ወደ አገራችን ስንመጣ ደፋሩና ነገን ያሰበው ልጅዎ ኬንያ ገባ፡፡ ራሱን ለውጦ ይለውጥዎታል” ይሏቸዋል፡፡ ይህ አባባላቸው የክብረት ጓደኞች እንዳሰቡት ለእትዬ አበባ የምሥራች አልነበረም፡፡ ድንጋጤው ኡኡታውና ደረት ድቂው ዕድሜ የጎሰመውን አካላቸውን አዝለፍልፎ ለጣላቸው እትዬ አበባ መርዶ ነበር፡፡ ምክንያቱም ለእትዬ አበባ ስደት ማለት ሞት ነው፡፡ እንኳን ጠላ ጠምቀው በመሸጥ ላሳደጉት ብቸኛ ልጃቸው ለማንም ኢትዮጵያዊ ተመኝተውትም አያውቁ፡፡

ይህ በቅርቡ ሃያ ዓመት የሞላው እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ ትላንት የእኛ እናቶች ስደትን እንደሞት ያዩ ነበር፡፡ ተሰደደ/ች ሲሏቸው ሞተ/ች ብለው ያለቅሱ፤ ይጮኹ ነበር፡፡ ወዳጅ ዘመድ ተሰብስቦም ያስተዛዝን ነበር፡፡ ዛሬ ግን ተቀይሯል፡፡ የአንድ ቤተሰብ አባል እንኳን ሔደ ተብሎ፤ የደስታ ድግሱ ፌስታው የሚጀመረው ገና የግብዣ ወረቀት ሲላክ ነው፡፡ የስደት ጉዞው እውን ሲሆን ቪዛ ሲመታለትማ /ሲመታላትማ/ ሰርግና ምላሽ ነው፡፡ ትላንት እነ እትዬ አበባ ልጅዎ ውጭ አገር ሔደ ሲባሉ ልባቸው በሐዘን ተወግቶ ቀሪ ዘመናቸውን በለቀሶና በቁዘማ ፈጽመው ወደ መቃብር ይወርዱ ነበር፡፡ ዛሬ እናት ወይም አባት የልጃቸውን መሰደድ በኩራትና በደስታ ሲናገሩ እንሰማለን፡፡ ለዛሬው ወጣት ወንድሜ ወይም የፍቅር ጓደኛዬ ውጭ አገር ነው ማለት በኩራት የሚናገሩት ስኬት ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ) አንባብያን አሳባችሁን ስጡ፡፡

በየትኛውም መንገድ ወይም ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ትተው በስደት ሕይወታቸውን እንደሚገፉ እርግጥ ነው፡፡ ቁጥራቸው ውጭ ካሉት ወገኖቻችን ቢልቅ እንጂ የማያንስ ኢትዮጵያውያንም እነሱም ውጪ እንዳሉት እንዲሰደዱ ሲጸልዩ፣ ሲሳሉ፣ ገንዘባቸውን ሲያባክኑ፣ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ሲጥሉ እንደሚኖሩ ምስክሮች ነን፡፡ “የውጭ ጉዞዬ እንዲሳካ ቤቱ መጥቼ አልቅሼ ነበር፤ ተሳክቶልኝ አሁን እዚህ እገኛለሁና እልል በሉልኝ” የሚሉ ማስታወቂያዎች በየዐውደ ምሕረቱ እንሰማለን፡፡ “ይህ ደላላ ቪዛ ሊያስመታልኝ ይህን ያህል ሺሕ ብር ሰጥቼው ካደኝ” የሚሉ ፕሮግራሞች በኤፍ ኤም ሬድዮዎቻችንም ጭምር እናደምጣለን፡፡ “ሊቢያ ለመግባት በረሃ አቋርጠው ሲጓዙ የበረሃው ዋዕይ ሕይወታቸውን ቀጠፋቸው፤ የመን ለመግባት በጀልባ ተጭነው ሲቀዝፉ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ጀልባቸው በሞገድ ተመትታ በመስጠሟ ሁሉም አለቁ” የሚሉ ዜናዎች በየጊዜው እናነባለን፣ እንሰማለን፡፡ “በዚህ ዐረብ አገር ትሠራ የነበረች ኢትዮጵያዊት በአሠሪዋ አሲድ ወይም የፈላ ውኃ ተደፋባት፤ ከፎቅ ተወረወረች፤ አስከሬኗ መጣ” የሚሉ መርዶዎች መስማት ልማዳችን ሆኗል፡፡ ይህ ሁሉ ለምን ሆነብን) አንባብያን አሳባችሁን፤ ገጠመኞቻችሁን የደረሰባችሁን ሁሉ ወደ ዝግጅት ክፍሉ ላኩ፡፡

በልዩ ልዩ ምክንያት ከሀገር ወጥተው ከውቅያኖሱ ባሻገር ከሚኖሩት ወገኖቻችን በዕውቀታቸውና በሙያቸው አገሩ ፈልጎአቸው በስኬት የሚኖሩ ያሉትን ያህል፤ ኑሮ ከሀገሩ እንግዳ ባሕልና የአየር ጠባይ የበለጠ ከብዶአቸው በምሬትና በመሳቀቅ የሚኖሩ፤ አልፎ አልፎም ራሳቸውን የሚያጠፉ እንዳሉ እንሰማለን፤ እናያለንም፡፡ ይህ ችግር በተለይ ገና የስደቱን ኑሮ አሐዱ ብለው በጀመሩት ይበዛል፡፡ ከብዙ ጸሎትና ድካም በኋላ ያሰቡት ተሳክቶ የሔዱ ወገኖች የቅርብና የልብ ወዳጅ ዘመድ ካጠገባቸው ከሌለ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ብዙ ጊዜ እንደምንሰማው ገና እንደሔዱ የሚያጋጥማቸው ችግር ሕሊናቸውን ከመጉዳቱ ባሻገር ጠባሳው በስደት ሕይወታቸው ሁሉ ዘልቆ ኑሮአቸውን ከባድ ያደርግባቸዋል፡፡

የሥነ ልቡና ምሁራን አንድ ሰው የጠበቀውን እና የጓጓለትን ነገር ሲያጣ የሚያጋጥመውን ሥነ ልቡናዊ ስብራት ሥነ ልቡናዊ መራቆት /Psychological Crisis/ ይሉታል፡፡ በአገራቸው ምድር ሳሉ ሁሉም ለምለም ሆኖ በምናብ ይታያቸው የነበረ የባዕድ ምድር፤ ምድሩ ላይ ቆመው ሲያዩት ልምላሜው በቀ ላሉ ምግብ የማይሆን ሆኖ ሲያገኙት፤ በአጭሩና ካለ ብዙ ድካም በኪስ እንደሚታጨቅ ያሰቡት ገንዘብ ብዙ ድካምና ራስን ዝቅ ማድረግ እንደሚጠይቅ ሲረዱ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ጭንቀታቸው በርትቶም የጤና እክል ይገጥማቸዋል፡፡ ይህ የጤና ችግር ደግሞ በስደቱ ምድር በጉልበታቸው ሮጠው በዕውቀታቸው ተወዳድረው ሕይወታቸውን እንዳያሻሽሉ ዕንቅፋት ይኾንባቸዋል፡፡ ለመሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያን የስደትን ሕይወት ሲጀምሩ ከፍተኛ መደናገጥ፣ መታመምና አልፎ አልፎም ኅልፈተ ሕይወት የሚያጋጥማቸው ለምንድን ነው) የተወሰኑትን ምክንያቶች ከዚህ በታች እናያለን፡፡

1. የተሳሳተ መረጃ
ሀገር ቤት ያለን ኢትዮጵያውያን ስለውጭው ዓለም የምንረዳው በዋና ነት በዚያ ከሚኖሩ ወገኖቻችን ነው፡፡ ምንም እንኳን የባዕድ ሀገር ሕይወት ምን ዓይነት እንደሆነ ካዩትና ከደረሰባቸው እውነቱን የሚናገሩ ቢኖሩም፤ በአብዛኛው በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለዕረፍት ወደ ሀገራቸው ሲመጡም ሆነ እዚያው ባሉበት ሆነው ለወዳጅ ለዘመዳቸው የሚያስረዱት፤ በእጅጉ እንደሚመች፣ ሰው ዐቅሙ እስካለው ድረስ ሥራ አማርጦ በመሥራት ገንዘብ እንደሚዛቅበት ነው፡፡ ለዚህ ከእውነት የራቀ ምስክርነታቸው ማስረጃ ለማድረግም ብዙ ደክመው /በግሌ እንዳየሁትም/ ለራሳቸው በአግባቡ ሳይመገቡና ሳይለብሱ ያጠራቀሟትን ገንዘብ ወደዚህ ሲልኩ ጥቂቷና በብዙ ድካም ያገኟት ገንዘብ በሀገራችን ምንዛሬ በርክታ ከወዳጅ ዘመድ እጅ ስትገባ የስደት ሀገሩን ለምለምነት ትሰብካለች፡፡ በፎቶ ግራፍ ተቀርጾ የሚላከው በረጅሙ ወርኃ በረዶ ወቊር የገረጣ ፊት ሀገር ቤት ለሚኖረው ሰው የባዕድ አገር ሕይወትን ምቾት የሚሰብክ ነው የሚመስለው፡፡

በሀገራችን የዲዮስጶራ ሰርግ የሚባል አለ፡፡ የዲዮስጶራ ሰርግ አንድ ወይም ሁለቱ ተጋቢዎች ከውጭ መጥተው ጋብቻቸውን የሚፈጽሙበት ሰርግ ነው፡፡ ይህንን ሰርግ ልዩ የሚያደርገው /ሁሉም ማለት አይደለም/ ወጪው በእጅጉ የበዛ፤ የሰርጉ ታዳሚዎች እስከሚሰለቻቸው ድረስ መብል መጠጡና የመናፈሻው ሥርዓት የበዛ፣ ሙሽሮች የሚሞሸሩበት መኪናም ጭምር ከሰማይ የወረዱ እስከሚመስል ድረስ ለታዳሚ ዓይን ግራ የሚያጋባ፤ በጥቅሉ “የናጠጠ” ሰርግ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ያየ ወጣት ታዳሚ በሀገሩ በድሎት የሚኖርም ቢሆን እንኳ እሱም ባሕር ማዶ ተሻግሮ በመሥራት በልጽጎ በመመለስ በተመሳሳይ ሁኔታ ማግባትን ይመኛል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የብዙዎች ዲዮስጶራ ተጋቢዎች የውጭ ሕይወት እዚህ መጥተው ሰርጋቸውን ድል ባለ ሁኔታ እንደደገሱለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ያላቸውን ካሟጠጡ በኋላ ከሌላውም ተበድረው ድል ያደርጉታል፡፡ ይህ ከእውነታ ውጭ የሆነ የዲዮስጶራ ወገኖቻችንን የውጭ አገር ገለጻና ካላቸው በላይ ገንዘብ መርጨት ሲያዩና ሲሰሙ የቆዩ ወገኖች እነሱም ዕድሉን አግኝተው ሲሔዱ፤ ያ በርቀት የሳሉት የባዕድ ምድርና ሕይወት እንዳልጠበቁት ሆኖ ሲያገኙት ከፍተኛ የመንፈስ ስብራት ያጋጥማቸዋል፡፡

2. የገቡት ቃል
ኢትዮጵያውያን የስደት ሕይወት እንደጀመሩ ለከፍተኛ የመንፈስ ስብራት የሚዳርጋቸው ሌላው ምክንያት ሀገራቸውን ከመልቀቃቸው በፊት ለወዳጅ ዘመዳቸውና ጓደኛቸው ገብተውት የሚሔዱት ቃል ኪዳን ነው፡፡ ከላይ ባየነው መልኩ ወደ ውጭ እንደሔዱ በገንዘብ ባሕር ላይ የሚሰጥሙ ይመስላቸውና ለቪዛው ፕሮሰስና ለትራንስፖርት እንደሁም ለሽኝት ድግስ ብዙ ብር ይበደራሉ፡፡ ወደውጭ ለሚሔድ የሚያበድር አይጠፋምና፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አብረዋቸው ሲቸገሩ ለኖሩት ወላጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ከፍተኛ የዕርዳታ ተስፋ ይሰጣሉ፡፡

ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ እንደሚታየው የስደት ሕይወት እንደተጀመረ ከተሻለ ኑሮ ላይ አያፈናጥጥም፡፡ ተሰዳጁ ሥራ ያዘም አልያዘ ከገባበት ቀን ጀምሮ ውጭ ስላለው ሕይወት አስቀድሞ በመረዳት ራስን አሸንፎ መሠረት ለማስያዝ ረጅም ጊዜ ይወስዳል፡፡ በዚህ ስደት ተሰዳጁ ሀገሩ ትቶት የመጣውን ቃልኪዳን እያሰበ፤ አብረውት ሲቸገሩ የነበሩ ቤተሰቦቹን ጉጉትና ጠኔ በሕሊናው እየሳለ ይጎዳል፡፡ ጉዳቱም የመንፈስ ስብራት ይሆንና ሠርቶ ሊያገኝበት ከሀገሩ ይዞት የሔደው ጉልበት እየደከመ በሽታ ላይ ይወድቃል፡፡ ይህ ጉዳት እንዲደርስበት ያልፈለገ ደግሞ ገንዘብን በአቋራጭ ለማግኘት ሲል ኢትዮጵያዊ መልኩና የሀገሩ ሕግ በማይፈቅድለት ተግባር ተሠማርቶ የባሰ ችግር ላይ ይወድቃል፡፡

3. አለመዘጋጀት
እንኳን ለቀዋሚ ኑሮ ይቅርና ለጊዜያዊ ዕረፍት ወይም ሥራ የሚደረግ ጉዞ ከፍተኛ ዝግጅትን ይጠይቃል፡፡ ከዝግጅቶቹ ውስጥ ስለሚሔዱበት ሀገር ባሕል፣ ቋንቋና አሠራር ማወቅ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚታየው በርካታ ወገኖቻችን ወደ ውጭ የመሔድ ዕድል ሲያጋጥማቸው፤ ለራሳቸውና በዚያ ለሚያገኟቸው ዘመ ዶች የሚያካፍሉት ሽሮና በርበሬ እየሸ ከፉ በአውሮፕላን ገብተው የሚበሩባትን ቀን በጉጉት ከመጠበቅ ባለፈ ሁኔታ ዝግጅት አያደርጉም፡፡ በዚህም የተነሣ እንደሔዱ ከፍተኛ ድንጋጤና ሥነ ልቡናዊ ጫና ውስጥ ይገባሉ፡፡ ሥራ ለመፈለግ የሀገሩን ቋንቋ በሚገባ አላወቁም፣ በነጻነት ለመንቀሳቀስ አስቀ ድመው ስለሀገሩ አነዋወርና ሕግ አላጠኑም፡፡ ይህ ዓይነት ችግር በተለይ ኢትዮጵያውያን በማይበዙባቸው ሀገራት ጎልቶ ይታያል፡፡

ኑሮአቸውን በስደት የሚጀምሩ ወገኖች ለወዲያው ለሚያጋጥማቸው የሕሊና ስብራት ምክንያቶቹ እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ለአብነት ያህል ከተጠቁሱት የምንገነዘበው ግን የስደት ሕይወት ሀገር ላይ ተቀምጦ እንደሚያስ ቡት የተመቻቸ /የተደላደለ/ እንዳልሆነና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እንዳሉ በመረዳት ተዘጋጅቶ መሔድ እንደሚገባ ነው፡፡ በሚቀጥለው ዕትም በተለይ የስደት ሕይወትን የሚመሩ ወገኖች ከሚደርስባቸው ሥነ ልቡናዊ ስብራት ለመታደግ በዚያ ካለችው ቤተ ክርስቲያንና ምእመናኗ ምን ይጠበቃል) የሚለውን እንመለከታለን፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያላችሁ ምእመናን የሕይወት ተሞክሯችሁንና ለሌላው ትምህርት ይሆናል የምትሉትን በዝግጅት ክፍሉ የስልክና የፖስታ ሳጥን ቁጥር፣ በኢሜይል እንዲሁም በአካል እየመጣችሁ እንድታደርሱን በአክብሮት እንጋብዛለን፡፡

መፍትሔዎች፡-

  1. በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስለሚኖሩበት ምድርና ሕይወት ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ እውነቱን በአገር ቤት ለሚኖሩ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ይግለጹ፡፡ ሥራ ለማግኘት ምን ያህል ርቀት እንደሚጓዙ፣ ከብዙ ድካም በኋላ ስለሚያገኙት ገንዘብ፣ በወር ስለሚሸፍኑት ቢል ብዛት፤ ስለአየር ጠባዩ፣ ስለ አሠሪና ሥራ ግንኙነት፣ ስለ ቤተሰብ ሕይወት ወዘተ. . . በግልጽ ቢናገሩ ወገኖቻችን በመጓጓትና ትልቅ ነገርን በመጠበቅ ሔደው ከመደንገጥ፣ ከበሽታ ነጻ ይሆናሉ፡፡

  2. በተለያየ ምክንያት ሀገራቸውን ለቀው የሚሔዱ ሰዎች በተቻላቸው መጠን የሚሔዱበትን ሀገር እንደሀገራቸው ሁሉ የራሱ ተግዳሮት የሌሉት፣ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንደሆነ አድርገው መሣል የለባቸውም፡፡ ይህንን ካደረጉ ለቀሪ ዘመዶቻቸው የሚገቡት ቃል አይኖርም፡፡ ቢኖርም ሊያጋጥም የሚችለውን ተግዳሮት ግንዛቤ ውስጥ የከተተ ይሆናል፡፡

  3. ኑሮአቸውን በባዕድ ምድር ለማድረግ ወስነው የሚሔዱ ወገኖች አስቀድሞ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ማድ ረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እዚያ ሲሔዱ ከሚበሉትና ከሚጠጡት በተጨማሪ ሀገሩ ምን ዓይነት የአየር ጠባይ አለው) ቋንቋውን በሚገባ አውቀዋለሁን) ሕግጋቱና የአነዋወር ይትበሃሉ ሁሉ ምን ይመስላል) ወዘተ ለሚሉት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ መያዝ /ማዘጋጀት/ ይገባቸዋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር  

 

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት 17 ከግንቦት 16-30 ቀን 2005 ዓ.ም.