የምን አለበት መዘዝ!

ክፍል አንድ

መልከአ ሰላም ቀሲሰ ደጀኔ ሽፈራው

መጋቢት ፫፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

በዚህ ቃል ብዙዎች ሕይወታቸው ተጎድቷል፤ ሃይማኖታቸውም እንዲሁ፤ ለምሳሌ “ባንጾም ምን አለበት? እግዚአብሔር ምን ሠራችሁ እንጂ ምን በላችሁ አይለንም” የሚሉ አሉ፤ “መስቀል ባንሳለም ምን አለበት? ወደ ቤተ ክርስቲያን ባንሄድ ምን አለበት? እግዚአብሔር በሁሉ ቦታ አለ” የሚሉ ሰዎችም አሉ፤ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ከሕዝባችን ባህል ውጪ “በምን አለበት” የሚጓዙ ሰዎች ጥቂቶች አይደሉም።፡

ጠቢቡ ሰሎሞን በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ “አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታጥፋ” ብሏል፡፡ ምልክት የተባለው ሥርዓትና ትውፊት ነው፤ ድንበር የተባለ ደግሞ ሃይማኖት ነው፤ “አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታጥፋ” ማለት “የሃይማኖትህን ሥርዓት አታጥፋ፤ የሃይማኖትህን ምልክት አታጥፋ፤ የሃይማኖትህን ትውፊት አታጥፋ” ማለት ነው፡፡ (ምሳ. ፳፪፥፳፰)

ጾም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፤ ነቢያት ጾመዋል፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን የሁሉ ፈጣሪ ሲሆን ጾሟል፡፡ የጌታችን ደቀ መዛሙርት የነበሩትም ቅዱሳን ሐዋርያት ጾመዋል፤ በቤተ ክርስቲያናችን ሰባቱን አጽዋማት የምንጾመው መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገን፣ ትውፊተ አበውን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ይዘን ነው፡፡ ሆኖም ግን እያንዳንዱ ልክ በጎ ምግባር እንዳለውና ደግ እንደሚሠራ ሰው “ባልጾም ምን አለበት?” ይላል፤ “ባልጾም ምን አለበት” የሚል ሰው ለሆዱ አድልቶ እንጂ ለነፍሱ አድልቶ አይደለም፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል እዚህ ላይ እናነሣለን፤ በፊልጵስዩስ መልክእቱ  ላይ “በመጨረሻው ዘመን ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው ይመላለሳሉ፤ ተቃዋሚዎች ሆነው ይመላለሳሉ፤ መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሆዳቸው አምላካቸው ነው” ይላል፡፡ (ፊል.፫፥፲፰) “አልጾምም፤ ብበላ ምን አለበት?” በሚል ሰበብ አምላካችንን የሚያስከፋ ነገር እየሠራን መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ ሰው ለመሆኑ በመብል የእግዚአብሔር መንግሥት ይወረሳል? መብልና መጠጥስ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባልን?

ይህንን በተመለከተ ቅዱስ ጳውሎስ ላይ እንዲህ በማለት ይመክረናል፤ “መብል ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ብንበላ ምንም አናተርፍም፤ ባንበላም ምንም አይጎድልብንም፤ ሳንበላ ቀርተን ብንጾም ምንም አይጎድልብንም፤ ጾምን ሽረን ብንበላ ምንም አናተርፍም፤ መብል ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፡፡” (፩ ቆሮ. ፰፥፰) ታዲያ መብል ወደ እግዚአብሔር የማያቀርብ ከሆነና በልተን የማናተርፍ፣ ባንበላም የማይጎድልብን ከሆነ ጾምን ገንዘብ ማድረግ  አይገባምን?

ቅዱስ ጳውሎስ አሁንም ለሮም ክርስቲያኖች የጻፈላቸው መልእክት እንዲህ ይላል፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም፣ በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብል እና መጠጥ አይደለም፤ እንደዚህ አድርጎ ሰውነቱን ለክርስቶስ የሚያስገዛ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛልና በሰውም ዘንድ የተመሰገነ ነው፡፡” (ሮሜ ፲፬፥፲፱)

ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር መንግሥት በመብልና መጠጥ አይደለችም” ሲል አንደኛ የእግዚአብሔር መንግሥት በመብልና በመጠጥ አትወረስም ማለቱ ነው፡፡ ሁለተኛ የእግዚአብሔር መንግሥት ያላት ወንጌልን ነው፤ ወንጌል ቢፈጽሟት፣ ቢጠብቋትና ቢኖሩባት የእግዚአብሔርን መንግሥት ስለምታወርስ ወንጌልን የእግዚአብሔር መንግሥት አላት፡። ሌላው ደግሞ የእግዚአብሔር መንግሥት መብልና መጠጥ ሳትሆን በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ደስታና ሰላም ናት፤ ቢፈጽሟት የእግዚአብሔርን መንግሥት የምታወርስ ወንጌል እምነትን፣ ተስፋንና ፍቅርን ታስተምራለች፤ ትሰብካለች እንጂ መብል እና መጠጥ የሆድን ነገር አትሰብክም ማለቱ ነው፡፡ ሦስተኛ የእግዚአብሔር መንግሥት መብልና መጠጥ አይደለችም ሲል የእግዚአብሔር መንግሥት የተባለች ወንጌል ልብላ፣ ልጠጣ በሚል ሰውነት አታድርም፤ አትዋሐድም ሲለን ነው፡፡

እንግዲህ እነዚህን ሦስቱን ተገንዝበን “የእግዚአብሔር መንግሥት መብልና መጠጥ አይደለችም፤ በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታና ሰላም ናት እንጂ” ስንል ሰውነታችንን ለክርስቶስ አስገዝተናል ማለት ነው፤ በሕይወታችን ዘመን ሁሉ ደስ ማሰኘት ያለብን እግዚአብሔርን ነው፡፡ ብንበላ ብንጠጣ ደስ የምናሰኘው ደግሞ ሰውነታችንን ነው፤ ብንጾም፣ ብንጸልይ፣ ብንሰግድ፣ ብንመጸውት ግን ደስ የምናሰኘው እግዚአብሔርን ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ የተናገረው እንዲህ የሚል ቃል አለ፤ “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፤ የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሏቸው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንት፣ ዛሬ፣ ነገም ያው ነው፡። ልዩ ልዩ በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፤ ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና፡፡” (ዕብ.፲፫፥፰) ሐዋርያው “ልባችሁ በመብል በመጠጥ ይጽና” አላለም፤ ልባችሁ በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንቶ ይኑር አለ እንጂ፡፡” የእግዚአብሔር ጸጋ ያላት ወንጌልን ነው፤ “ልባችሁ በሕገ ወንጌል ጸንቶ ይኑር” ማለቱ ነው ደግሞ “እንብላ፤ እንጠጣ” እያሉ ሆዳቸው የገዛቸው እና ያሸነፋቸው ሰዎች አልተጠቀሙምና” ብሎ አስተምሮናል፡፡

በእርግጥ ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” ብሏል፤ (፩ ቆሮ. ፮፥፲፪) ይህንንም ሲል “ነጻ ፈቃድ አለኝ” ማለቱ ነው፤ እያንዳንዱ ሰው ነጻ ፈቃድ አለው፤ ያንንም ተጠቅሞ ጽድቅን ይሠራል፤ ወይም ኃጢአትን ይሠራል፤ እግዚአብሔርን የምናመልከው በነጻነት እንጂ በግድ አስጨንቆን አይደለም፡። “እነሆ እሳት እና ውኃን አቅርቤልሃለሁ፤ እጅህን ወደ ፈቀድከው ስደድ” የተባለው “ነጻነት (ነጻ ፈቃድ) አለህ” የሚለውን የሚያመለክት ነው፡፡

የሚገርማችሁ ነገር ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” ብሎ አላበቃም፤ “ነገር ግን አይጠቅምም” ብሏል፤ ታዲያ ብልጥ ነን የሚሉት “አይጠቅምምን” ተዋትና “ሁሉ ተፈቅዶልኛልን” ብቻ ያዙ፤ ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ ነገር ግን አይጠቅምም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ በእኔ ላይ አንድ እንኳን አይሠለጥንብኝም፤ እኔን አንድ እንኳን አይገዛኝም፤ መብል ለሆድ ነው፤ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ሁለቱንም ያጠፋቸዋል” አለ፡። አእምሮ ላለው ሰው የማይጠቅምን ነገር መተው ነው እንጂ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” ብሎ የሚጎዳውን አይፈጽምም፡፡ እስኪ በፈቃዳቸው የተጓዙ በምን አለበት የተጎዱ ሰዎች ምን እንደ ደረሰባቸው እንመልከት፡፡

፩. አዳምና ሔዋን

እግዚአብሔር አዳምን እንዲህ አለው፤ “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ትሞታለህ” ተብሏል። (ዘፍ.፪፥፲፮) አዳምና ሔዋን ይህን ሕግ ሰባት ዓመት ሙሉ ጠብቀው ነበር፤ ታዲያ በመጨረሻ በግዴለሽነት “ምን አለበት” ብለው የዕፀ በለስን ፍሬ በሉ፤ “ምን አለበት” ብለው የዕፀ በለስን ፍሬ እንዲበሉ ያደረጋቸው የሰይጣን ምክር ነው፤ በምን አለበት የእግዚአብሔርን ሕግ እንድናፈርስ፣ ሕግና ሥርዓት እንድንተላለፍ የሚያደርገን የሰይጣን ምክር መሆኑን ልናውቅ ያስፈልጋል።

፪. አቤልና ቃየል

በሕገ ልቦና ምንም እንኳን ሕግ ባይሠራም የመሥዋዕት አቀራረብ ሥርዓት ነበር፤ እግዚአብሔር በባሕርዩ ንጹሕ ስለሆነ ንጹሕ መሥዋዕትን ማቅረብ ይገባልና፡፡ ታዲያ አቤል “ምን አለበት” ሳይልና ግዴለሽ ሳይሆን ንጹሕ መሥዋዕትን በማቅረቡ እግዚአብሔር መሥዋዕቱን ተቀብሎታል፡። “እግዚአብሔር ወደ አቤል እና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ” እንዲል። (ዘፍ.፬፥፬) ቃየል ደግሞ በግዴለሽነት “ምን አለበት” በማለት “እንክርዳድ መሥዋዕት ባቀርብ እግዚአብሔር አይበላው” ብሎ ገለባ የበዛበት እህልና እንክርዳድ ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ እግዚአብሔር ግን አልተቀበለውም፡፡ በዚህ አላበቃም፤ “ምን አለበት ደግሞ ወንድሜን ብገድለው” አለ፤ “ምን አለበት” ብሎ አሰበ፤ አስቦ አልቀረም፤ ወንድሙን ገደለ፡፡  በዚህም አላበቃም፤ የወንድሙ የአቤል ደም ወደ እግዚአብሔር ጮኸች፤ (ዘፍ.፬፥፰-፲) ዛሬም እኮ በምድር ላይ የብዙ ንጹሐን ደም ይፈሳል፤ የእነዚያን ሁሉ ጩኸት እግዚአብሔር ይሰማል፡፡

ታዲያ እግዚአብሔር ጠየቀው፤ “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” አለው፡፡ እርሱም አለ፦ “አላውቅም የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?” በማለት መለሰ፤ ቃየል በልቡ ያሰበው “እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ እንዴ” እና “አላየሁትም” ብል ምን አለበት” በማለት አስቦ ተናገረ። እግዚአብሔርም ስለ ረገመው እርግማንን ተሸክሞ ኖረ፡፡ (ዘፍ.፬፥፱-፲፩)

፫. ሎጥና ቤተ ሰቡ

ሰዶም ኃጢአት፣ ግፍና በደል ስለ በዛባት የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሷ ላይ ነደደ፤ ከተማዋ ከመጥፋቷ በፊት ግን አንድ ጻድቅ ሰው ከእነ ቤተ ሰቡ በሰዶም ነበረ፤ እርሱም ሎጥ ነው።  ሁለት ቅዱሳን መላእክት ወደ ሎጥ መጡ፤ በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደላቸው፤ እነዚያ ሁለት ቅዱሳን መላእክት በመጨረሻ የሎጥን፣ የሚስቱንና የልጆቹን እጅ ይዘው ከጥፋት ከተማ አወጧቸው፡፡

እነዚያ ሁለት ቅዱሳን መላእክት እነ ሎጥን ከሰዶም ካወጡ በኋላ ሥርዓት ሠሩላቸው፤ ራሱን እንዲያድንና ወደ ኋላህም እንዳያይ፣ በዚህ ዙሪያ ሁሉ እንዳይቆም፣ እንዳይጠፋ ወደ ተራራው ሸሽቶ እንዲያመልጥ ነገሩት፡፡ ሎጥና ልጆቹም ይህን ሥርዓት ጠብቀው ወደ ፊት ሄዱ፤ የሎጥ ሚስት ግን “እዚህ ስፍራ ብቆም ምን አለበት” አለችና ቆመች፤ ቀጥላም “ቆምኩ፤ ምንም አልሆንኩም” ካለች በኋላ “ወደ ኋላ ብመለከት ምን አለበት” አለችና ወደ ኋላ ተመለከተች፤ በዚህም ጊዜ የጨው ሐውልት ሆና ቀረች፡፡ (ዘፍ.፲፱፥፩-፳፮)

ዛሬም እኛ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት “ጫማ አውልቃችሁ ግቡ” ተብለን ስንታዘዝ “ከእነ ጫማችን ብንገባ ምን አለበት? ዋናው ነገር ከእግረ ልቡናችን ላይ የኃጢአት ጫማ ማውለቅ ነው” ብለን አልታዘዝም ብንል፣ ጎንበስ ብሎ ጫማ ለማውለቅ ከሰነፍክን ረቂቁን የኃጢአት ጫማ ከልባችን ለማውለቅ እንዴት ይቻለናል? በትንሽ ያልታመንን በብዙ እንታመናለን?

አምላካችን እግዚአብሔር ሙሴን “አንተ ሙሴ የቆምክበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን አውልቅ” አለው፤ ሙሴ ግን “ባላወልቅ ምን አለበት” አላለም፡፡ የፈጣሪውን ትእዛዝ አከበረ እንጂ፤ (ዘፀ.፫፥፬-፭) የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ለኢያሱ ተገልጦ “የቆምክበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን አውልቅ” አለው፤ ኢያሱም “ባላወልቅ ምን አለበት” አላለም። (ኢያ.፭፥፲፭) አውልቆ ለመልአኩ ሰገደ እንጂ፤ ስለዚህ “በምን አለበት” መጎዳት የለብንም፡፡

፬. ኤሳውና ያዕቆብ

ኤሳውና ያዕቆብ መንትያዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ቀድሞ ከማኅፀን የወጣው ኤሳው ስለ ሆነ የበኩር ልጅ ተባለ፤ ያዕቆብ ደግሞ የወንድሙን ተረከዝ ይዞ ወጣ፤ የበኲር ልጅ በአባቱ ይባረካል፤ ይመረቃል፡፡ አባት የሚባርከውን ቡራኬና የሚመርቀውን ምርቃት እግዚአብሔር በሰማይ ያጸናዋል፡፡ አንድ ቀን ኤሳው የሚበሉ የዱር እንስሳትን ለማደን ሄደ፤ ግን አጣ፤ ስለዚህም ራበው፤ ወደ መንደር ሲመለስም ታናሽ ወንድሙ ምግብ ሲያዘጋጅ አየው፤ ኤሳው ከወንድሙ የሚበላ በመሻቱ “አሁን ብኩርናዬን ብሸጠው ምን አለበት” ብሎ አሰበ፤ አስቦ አልቀረም ለወንድሙ ለያዕቆብ ብኩርናውን ሸጠ፤ ለወጠ፤ ስለሆነም በረከት ቀረበት፡፡ ኤሳው ብኩርናውን ከሚለውጥ ቢርበው/ቢጾም/ ይሻለው ነበር፤ እርሱ ግን ክብሩን ሸጠ፤ ጾም አያስፈልግም ማለት ብኩርናን መሸጠ ነው፤ ክብርንና ምርቃትን መሸጥ ነው፡፡ (ዘፍ.፳፭፥፴፬)

ታዲያ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ይህኛውን መጥፎ ታሪክ እንዲህ ማበለት አስታወሰን፡፡ ስለ አንድ መብል ብሎ በኩርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ኤሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው በመካከላችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡ ከዚያ በኋላ እንኳን በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ ታውቃላችሁና በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልግ ለንስሓ ስፍራ አላገኘምና ይላል፡፡ (ዕብ.፲፪፥፲፮፣ ዘኁ. ፲፮፥፩-፶)

፭. ዳታን፣ ቆሬና አቤሮን

በብሉይ ኪዳን ዘመን ከእስራኤል ልጆች መካከል በክህነት እንዲያገለግሉት አሮንን እና ልጆቹን የመረጠ እግዚአብሔር ነው፡፡ በኦሪት ዘፀአት እንደ ተጻፈ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “አንተም ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ፣ አሮንን፣ የአሮንንም ልጆች፥ ናዳብን፣ አብዮድንም፣ አልዓዛርንም፣ ኢታምርንም፥ አቅርብ” አለው፡፡ (ዘፀ.፳፰፥፩) እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ለክህነት የሚጠሩ አሉ፤ ሥልጣነ ክህነት ሲሰጥ ደግሞ ሥርዓት አለው፤ ነገር ግን እነዚህ ሦስት ሰዎች ዳታን፣ አቤሮን፣ ቆሬን የተባሉት በሙሴ እና በአሮን ላይ በምቀኝነት ተነሡባቸው፡፡ “አስቀድመን የአሮንን ክህነት እንውሰድበት፤ ክህነቱን በእጃችን ካስገባን በኋላ የሙሴን ዳኝነትና የሙሴን ንግሥና እንወስዳለን” አሉ፤ መጀመሪያ ወደ ሙሴ ሄዱ “ለእኛም ክህነት ይገባናል” አሉ፤ ከሌዊ ነገድ ተወልደናልና አሉ፤ በተለይም ቆሬ እና ቤተ ሰቦቹ ሙሴ ምን አላቸው? አሮንና ልጆቹ ከእግዚአብሔር አግኝተው ተሹመዋል፡፡ ሥልጣኑን አግኝተዋል፤ እናንተም ከእግዚአብሔር አግኙ” አላቸው፡፡ (ዘኅ.፲፮፥፩-፳፯)

“እነ ቆሬ እኛም የካህናት ልብስ ለብሰን ጽንሕ ይዘን፣ ወደ ቤተ መቅደስ ገብተን እንደ አሮን ብናጥን ምን አለበት” አሉ፤ ሥርዓቱ ባይፈቅድላቸውም፤ “ምን አለበት” ብለው ገና ማጠን ሲጀምሩ እሳት ከሰማይ ወረደና አቃጠላቸው፡። “ሁሉም ሞቱ፤ እንደ ተለበለበ ግንድ ሆኑ” ይላል፤ ዳታንና አቤሮን አብረው መክረዋልና ከእነ ዕቃዎቻቸው፣ ከእነ ቤተ ሰቦቻቸው ይህች ግዑዟ መሬት ተከፍታ ዋጠቻቸው፡፡ (ዘኅ.፲፩፥፮)

“የምን አለበት” መዘዝ ቀላል አይደለም፤ እስራኤላውያን በሙሉ ይህንን አዩ፤ ዳታን አቤሮን ቆሬ በድፍረታቸው ተቀሰፉ እንደ ማለት ፈንታ ሕዝቡ ደግሞ ሙሴንና አሮንን እንደ ነፍሰ ገዳይ አዩአቸው፡፡ ሕዝቡ ባጉረመረመ ጊዜ እግዚአብሔር እነርሱንም በመቅሠፍት መታቸው፤ እንደ ቅጠል መርገፍ ጀመሩ፤ በዚህም ጊዜ ሙሴና አሮን በታቦተ ጽዮን ፊት ተደፍተው ወደ እግዚአብሔር ማልቀስ ጀመሩ፤ “እባክህ ለሕዝቡ ራራ” በማለትም ማለዱ፡

አያችሁ የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች! እግዚአብሔር ለሙሴ ምን አለው? “አሮን ጽንሐውን ይያዝና በሕዝቡ መካከል ቆሞ ይጠን፤ ዕጣን በታጠነ ጊዜ መቅሠፍቱ ይቆማል” አለ እግዚአብሔር፡፡ አሮን ማጠን ሲጀምር መቅሠፍቱ አሮን ጋር ሲደርስ ቆመ፤ አሮን በሕያዋንና በሙታን መካከል ቆሟል፤ ከኋላው ያሉትን ግን መቅሠፍቱ አልደረሰባቸውም፤ ወገኖቼ ከፊታችን ቅዱሳን ካሉ መቅሠፍት ወደ እኛ አይጠጋም፤ ዋናው የሚያስፈልገው ማመን ብቻ ነው፡። ከሕዝቡ መካከል በዚህ ምክንያት 14,700 ሰው አለቀ፡፡ (ኢያ.፮፥፲፰)

፮. አካን

እስራኤላውያን በምድር ወጥተው ኢያሪኮ የምትባለዋን ከመያዛቸው በፊት ይህች ኢያሪኮ የምትባል ከተማ ዙርያዋን በታላቅ ግንብ የተገነባች ነበረች፤ ታዲያ እግዚአብሔር ምን አላቸው? “ካህናቱ ታቦቱን አክብረው ፊት ፊት ይሂዱ፤ ሕዝቡ ደግሞ ከኋላ ከኋላ ይከተል፤ በመጀመሪያው ቀን ያንን ግንብ አንድ ጊዜ ዞራችሁ ዕረፉ፤ በሁለተኛው ቀን እንዲሁ አንድ ጊዜ ዞራችሁ ዕረፉ፤ እስከ ሰባተኛው ይህንን አድርጉና በሰባተኛው ቀን ያንን ግንብ ሰባት ጊዜ ዙሩ፤ ስድስት ጊዜ ስትዞሩ ዝም በሉ፤ ድምፅ አታሰሙ፤ በሰባተኛው ግን ቀንደ መለከት እየነፋችሁ፣ እየጮኻችሁ ዙሩ ግንቡ ይፈርሳል” አላቸው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ “የኢያሪኮን ከተማ በምትይዙበት ጊዜ ምርኮ ብላችሁ ወርቅና ብር እንዳትሰበስቡ የአሕዛብ ወርቅ፣ ብር እርም ይሁንባችሁ” አላቸው፡፡

ይህም ብቻ አይደለም፤ እናንተ ግን እርም ካደረጋችሁት በኋላ እርም ከሆነው ነገር ራሳችሁን ጠብቁ፡፡ እርም ከሆነው ነገር አንድ የወሰዳችሁ እንደሆነ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ፤ ታስጨንቁትማላችሁ፤ “ምን አለበት” ብላችሁ ወርቁን ብትነኩ፣ ምን አለበት ብላችሁ ብሩን ብትሰበስቡ፣ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ” ተባሉ፡፡ እንደ ተባሉት በሰባተኛው ቀን ሲዞሩት የኢያሪኮ ግንብ በእግዚአብሔር ኃይል ፈረሰ፡፡

አንድ አካን የተባለ ሰው “ወርቁንና ብሩን ደብቄ ብወስድ ምን አለበት” አለና ደብቆ ወሰደ፤ ከዚህ የተነሣ እስራኤላውያን እንደ ገና ተሸነፉና መሸሽ ጀመሩ፤ ኢያሱ በታቦተ ጽዮን ፊት እየሰገደ “እግዚአብሔር ሆይ፥ እስራኤላውያን ለምን ሸሹ?” አለው፤ በዚህ ጊዜ “እርም የሆነውን ነገር የወሰደ በመካከላችሁ አለና ያንን አስወግድ” አለው፡፡ (ኢያ.፮፥፲፯-፲፱፣ ፯፥፩፣፳-፳፩)

፯. አብድዮና ናዳብ

ቤተ መቅደስ ውስጥ ታቦተ ጽዮን ባለችበት ዕጣን ያጥኑ ነበር፤ ዕጣን ደግሞ የሚታጠንበት እሳት እግዚአብሔር ባዘዘው እሳት ብቻ ነበረ፤ እነዚህ ናዳብና አብድዩ የተባሉ ወጣቶች “እግዚአብሔር ባላዘዘው እሳት ዕጣን ብናጥን ምን አለበት፤ እሳት፣ እሳት ነው፤ ምን ልዩነት አለው” ብለው እግዚአብሔር ባላዘዘው እሳት የዕጣን መሥዋዕት አቀረቡ፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላል፤ የአሮን ልጆች ናዳብና አብድዩ በየራሳቸው ወስደው እሳት አደረጉበት፤ በላዩም ዕጣን አኖሩበት፤ በእግዚአብሔርም ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ፤ እሳትም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ በላቸው፤ በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ፡፡ (ዘሌ.፲፥፩-፯)

አሁንም አንዳንዶች መዝሙር፣ መዝሙር ነው፤ ምን አለበት የጴንጤ መዝሙር ብንዘምር ይላሉ፤ እሳት፣ እሳት ነው እንዳሉት እንደ ናዳብና አብድዩ እንዳንሆን ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በመዝሙር ሰበብ ክህደትና ኑፋቄን ያገኘናልና፡፡

፰. አፍነንና ፊነሐስን

እነዚህ ሁለቱ የሊቀ ካህናት የዔሊ ልጆች ነበሩ፤ በቤተ መቅደስ ያገለግሉ ነበር፡፡ የቤተ መቅደስን ሥርዓት ይንቁ ነበር፤ እንኳን የእግዚአብሔር ቤት የእኛ ቤት እንኳን ሥርዓት አለው፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ ግን የእግዚአብሔርን ቤት ሥርዓት ናቁ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤት ከሚመጡ ሴቶች ጋር እዛው ታቦተ ጽዮን አጠገብ ያመነዝሩ ነበር፡፡ “ምን አለበት” ብለው በድፍረት በትዕቢት አመነዘሩ፡፡

ቀጥሎም በእስራኤል ላይ ፍልስጥኤማውያን ተነሡባቸው፤ ወራሪ ጠላት በሀገር ላይ የሚነሣው እኛ ኃጢአት ስናበዛና ስንበድል ነው:: አሁን እስራኤላውያን ታቦተ ጽዮንን ይዘው ሲዘምቱ አፍኒንና ፊንሐስም አገልጋዮች ስለሆኑ አብረው ዘመቱ፡፡ በአንድ ቀን ሞቱ፤ ይህ ብቻ አይደለም፤ ታቦተ ጽዮንም ተማረከች፡፡ በዚህም ጊዜ መልእክተኛ እየበረረ መጣ፤ ሊቀ ካህናቱ ዔሊ ወንበር ላይ ተቀምጦ ልጆቹ አንደ ሞቱ ነገሩት፤ እግዚአብሔርን እንደ በደሉ ያውቅ ስለነበር ዝም አለ፤ ታቦተ ጽዮን እንደ ተማረከች ሲሰማ ግን ደንግጦ ወደቀና አንገቱ ተቆልምሞ ሞተ፤ ይህ ሁሉ የምን አለበት መመዝ ነው፡፡ (፩ ሳሙ. ፬፥፩-፳፪)

፱. ንጉሥ ዖዝያን

በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ ላይ ተመዝግቦ የምናገኘው የንጉሥ ዖዝያን ታሪክ ሌላ ምሳሌ የሚሆን ነው፤ ይህ ንጉሥ ትዕቢት አደረበት፤ ሊቀ ካህናት አዛርያስ የተባለውን ሰው የከበረ ልብስ ለብሶ አየው፤ ስለዚህም “አንተ እንዴት ከእኔ ከንጉሡ የበለጠ የከበረ ልብስ ትለብሳለህ?፤” አለው፤ እርሱም መልሶ “ከዚህ ይልቅ ካህናቱ ጽድቅን ይለብሳሉ ተብሎ ተጽፏል” አለው፡፡ ቀጠለና ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ “በንጉሡ ቀኝ ተቀመጠ፤ “እንዴት ከእኔ እኩል በቀኜ ትቀመጣለህ” አለው፡፡ እርሱም ሲመልስለት “ካህን ይነብር በየማነ፤ ንጉሥ፣ ካህን በንጉሥ ቀኝ ይቀመጣል” ተብሎብሃል” አለው፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሡ ሲፈርድ ድሃ በደለ ፍርድ አጓደለ፤ በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ዝም አላለም፤ እኛ ግን ፍርድ ሲጓደል ድሃ ሲበደል እያየን ዝም እንላለን፡፡

ከዚያም ባሻገር ንጉሡ አጣሞ የፈረደውን አቃንቶ ፈረደ፤ ንጉሡም ደስ ሳይሰኝ ሥልጣን የእርሱ በመሆኑ እና ከእርሱ እንደሚበልጥ፣ ፍርድም ከእርሱ መሆን እንዳለበት ተናገረው፡፡ የንጉሡንም ፍርድ መገሰስና ሌላ ፍርድ ለመፍረድ ሥልጣን እንደሌለውም አስገነዘበው፡፡ አዛርያስም መልሶ መፍረድ ለእርሱ የተገባ እንደሆነ፣ መንግሥትም የዐቢ ክህነት እም ሥልጣነ መንግሥት፤ ከመንግሥት ሥልጣን የክህነት ሥልጣን እንደሚበልጥ ነገረው፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡ ዖዝያን ሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ ጽንሐሕ ይዞ ቤተ መቅደስ ገብቶ ማጠንን ቁም ነገር አድርጎ እንዳልሆነና እርሱም የካህናትን ልብስ ለብሶ ጽንሐሕ ይዞ ገብቶ ማጠን እንደሚቻለው “ምን አለበት” በማለት አሰበ፡፡

ልብሰ ተክህኖውን ለብሶ ጽንሐሕን ይዞ ወደ ታቦቱ ቀረበ፤ አዛርያስ ዝም ብሎ ይሆን? እኛ እኮ ብንሆን “ይገባል ግቡ” ነበር የምንለው፤ ወይም ስለምንፈራ ዝም እንላለን፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላል፤ ካህኑም አዛርያስ እና ከእርሱም ጋር ጽኑዐን የነበሩ ሰማንያ “በድለሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክብር አይሆንልህም፤” አሉት፡፡ ንጉሥ ዖዝያንም ተቆጣ፤ የሚያጥንበትም ጽንሐሕ በእጁ ነበር፤ ካህናቱንም በተቆጣ ጊዜ በካህናቱ ፊት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በዕጣኑ መሠዊያ አጠገብ ሳለ በግንባሩ ላይ ለምጽ ወጣበት” ይላል፡። ለምጽ ደግሞ በኦሪቱ የርኩሰት፣ የመቅሠፍት ምልክት ነበርና ካህናቱ ፈጥነውም አባረሩት፤ እርሱ ደግሞ እግዚአብሔር ቀሥፎት ነበርና ይወጣ ዘንድ ቸኮለ፡፡ ዖዝያን “ምን አለበት” ብሎ በማጠኑ ተቀሠፈ እንጂ አልተጠቀመም፡፡ (፪ ዜና ፳፮፥፩-፲፯)

ይቆየን!