የምን አለበት መዘዝ!

ክፍል ሁለት 

መልከአ ሰላም ቀሲሰ ደጀኔ ሽፈራው

መጋቢት ፫፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

፲. የቤትሳቢስ ሰዎች

የቤትሳሚስ ሰዎች ካህናት አልነበሩም፤ እነርሱም ታቦተ ጽዮን በአዲስ ሠረገላ ላይ ተጭና በወይፈኖች እየተጎተተች አዩ፤ ታቦትን የመግለጥና ታቦትን የመዳሰስ የካህናት ሥልጣን ነው፡፡ የቤትሳሚስ ሰዎች ወደ ታቦቱ ቀረቡና ገልጠው ማየትን አሰቡ፤ “ብናየው ምን አለበት” አሉ፤ የቤትሳሚስ ሰዎች አስበው አልቀሩም፤ ገልጠው አዩ፤ ወደ እግዚአብሔር ታቦት ውስጥ ተመልክተዋልናም እግዚአብሔር የቤትሳሚስን ሰዎች መታ፤  ከአምስት ሺህ ሕዝብም ፸ ሰዎችን መታ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፈት ስለ መታ ሕዝቡ አለቀሱ፤ ንስሓም ገቡ፤ የቤትሳሚስም ሰዎች ታቦቱን ነክተው በመቀሠፋቸው በዚህ ቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት መቆም እንደማይቻል አመኑ። (፩ ሳሙ. ፮፥፩-፲፱)

በዚህ መጽሐፍ ሁለተኛው ክፍል ላይ ዖዛ የተባለውን ሰው እናገኛለን፤ ይህ ዖዛ ታቦተ ጽዮን በአዲስ ሠረገላ ላይ ሆና በወይፈኖች አየተጎተተች ስትሔድ ዖዛ ከታቦቱ ኋላ ኋላ ይሄድ ነበር፤ በልቡ ግን ድፍረት ነበረበት፤ “ካህን ብቻ ነው እንዴ የሚነካው? እኔም እግዚአብሔርን አምናለሁ፤ ብነካው ምን አለበት” የሚል ድፍረት በውስጡ ነበር፤ እንዳይነካ ግን እስራኤላውያንን ፈራ፡፡ እስራኤላውያን ለሃይማኖታቸው ቀናኢ እና ቁጡ ስለ ሆኑ በድንጋይ ወግረው እንዳይገድሉት ፈርቶ ነው፡፡ መፍራት እግዚአብሔርን ነው፤ ዖዛ ምክንያት ሲፈልግ እነዚያ ወይፈኖች ናኮር የሚባል አውድማ ጋር ደረሱና ፋነኑ/ዘለሉ፤ ሰው ሰውኛውን ደንብረው ነው ልንል እንችላለን፤ የዘለሉት ግን ሕዝቡ ሁሉ “ሆ” እያለ በታቦተ ጽዮን ፊት ሲዘምር እነርሱም ዘመሩ፡፡ በአምላካችን ሥራ የተደረገ ነው፤ የበለዓምን አህያ እንዳናገረ ፣ የቢታንያን ድንጋዮች “ሆሣዕና በአርያም” እንዳሰኛቸውም እንዲሁ አደረገ፡፡ (፪ ሳሙ ፮፥፩-፲፩)

የእግዚአብሔር ጥበብ እኮ ረቂቅ ነው፤ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት “በልዎ ለእግዚአብሔር ግሩም ግብርከ፤ እግዚአብሔርን ሥራህ ግሩም ነው፤ ሥራህ ድንቅ ነው በሉት” ያለው ለዚህ ነው፡፡ (መዝ.፷፮፥፫) እነዚያ ወይፈኖች ሲፋንኑ ዖዛ ታቦተ ጽዮንን ሊይዝ አሰበ፡። ለምን ነካህ ቢሉትም ወይፈኖቹ ሲደነብሩ ታቦቱ እንዳይወድቅ ለመደገፍ ነው ብሎ መመለስ እንደሚችል እርሱን አሳመነ። ጾም ያሰለቻቸውና ለመብላት የሚፈለጉ ሰዎች ምክንያት ሲፈልጉ “ወደ አፍ የሚገባ አያረክስም” የሚል፣ እንደው “ለምን በላህ” ቢሉኝ ይህቺን እጠቅሳለሁ እንደሚለው ዓይነት ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ ሐሳብ ከጾም ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ “እጅን ሳይታጠቡ መብላት አያረክስም” ብሎ ለፈሪሳውያን ያስተማራቸው ትምህርት እንጂ ከጾም ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ነው፡፡ የሰው ልጅ በምክንያት ወደ ኃጢአት ማዘንበል ልማዱ ስለሆነ ነው፡፡ ዖዛ “ምን አለበት” ብሎ እጁን ዘርግቶ ታቦተ ጽዮንን ያዘ፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቁጣ በዖዛ ላይ እንደ እሳት ነደደ፤ ስለ ድፍረቱም እዚያው ታቦቱ አጠገብ ቀሠፈው፡፡ ይህ ቅሥፈት “የምን አለበት” መዘዝ ነው፡፡

፲፩. ንጉሡ ሳኦል

ንጉሥ ሳኦል በነቢዩ ሳሙኤል እጅ ተቀብቶ በእግዚአብሔር ፈቃድ የነገሠ ነው፡። ነገር ግን እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ ተመለሰ፤ ከዕለታት በአንድ ቀን ነቢዩ ሳሙኤል ለንጉሡ ሳኦል ሥርዓት ሠራለት፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ያቀርብ ዘንድም ትእዛዝም አዘዘው፤ “የደኅንነትን መሥዋዕት እሠዋ ዘንድ ወደ አንተ ተመልሼ እመጣለሁ፤ እስከ ሰባት ቀን ትቆያለህ” አለው፡፡ ንጉሡ ሳኦል ግን ነቢዩ ሳሙኤል ሳይመጣ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ማቅረብን አሰበ፤ ሰባት ቀን ድረስ ባልጠብቅ  ምን አለበት ባቀርብ” አለ፤ በነቢዩ ሳሙኤል አድሮ ሥርዓት የሠራለት ግን እግዚአብሔር ነው፡፡ (፩ ሳሙ. ፲፥፭)

ነገር ግን “ምን አለበት” ብሎ ሰባት ቀን ሳይጠብቅ ሠውቶ ጠበቀው፡፡ እግዚአብሔር ያዘዘውን ትእዛዝ ስላልጠበቀ መንግሥቱ እንደማይጸ ነገረው፡፡ (፩ ሳሙ.፲፫፥፰) እግዚአብሔር መሬት ወርዶ አላዘዘውም፤ እኛ ሲያዘው ያየነው ሳሙኤልን ነው፤ ሳሙኤል ደግሞ እግዚአብሔር እንዳዛዘው ነገረው፡፡ በሳሙኤል አድሮ ያዘዘው እግዚአብሔር ስለሆነ ታዲያ ነቢዩ ሳሙኤል በነገረው መሠረት ንጉሥ ሳኦል የእግዚአብሔር መንፈስ ተለየው፤ ርኩስ መንፈስም አደረበት፡፡ እየተሠቃየም ሞተ፡፡

፲፪. ንጉሥ ብልጣሶር

ይህ ንጉሥ በቤተ መንግሥቱ ድግሥ ይደግሳል፤ ሁሉም በሉና ጠጡ፤ ተሳከሩ፤ ይህ ብልጣሶርም የወይን ጠጁ ስላሞቀው አባቴ ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ዘርፎ ያመጣቸው የቤተ መቅደስ መገልገያዎች አሉ፡፡ የወርቅ ሳህን፣ የወርቅ ጽዋ፣ የወርቅ መጠጫ አለ፤ ያንን እንዲያምጡላቸው በእርሱ ለመብላትና ለመጠጣት ካህናቱ የሚለብሱትንም ልብስ እነርሱ ለመልበስ አሰቡ፡፡ በምን አለበት ያንን ሁሉ አደረገ፡፡

በቤተ መንግሥቱ ግድግዳ ላይ እጅ ብቻ ሲጽፍ አየ፤ ታዲያ ጠንቋዮቹንና አስማተኞቹን ሰበሰበና ስላየው ነገርና የጽሑፉንም ምሥጢር ጠየቃቸው፤ እነርሱም እንደ ማያወቁ ነገሩት፤ ከዚያም ሰው ሲፈለግ ብላቴናው ነቢዩ ዳንኤል ተገኘ፤ ግን ናቀው፡፡ “አንተ ነህ የእኔን ሕልም የምትፈታው?” በማለት ጠየቀው፡፡ እርሱም እግዚአብሔር እንደሚፈታለት ነገረው፡፡ ለንጉሡም  በቤተ መንግሥቱ ግድግዳ ላይ እጅ ሲጽፍ እንዳየ፣ ጽሑፉም “ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ” እንደሚል ከእነ ትርጓሜው ነግሮታል፡፡ “ማኔ ማለት እግዚአብሔር መንግሥትህን ቆጠረው፤ ፈጸመውም ማለት ነው”፤ ሥልጣንህ አበቃለነት አለው፡፡ “ቴቄል ማለት በሚዛን ተመዘንህ፤ ቀለህም፤ ተገኘህ” ማለት ነው፡፡ “ፋሬስ ማለት መንግሥትህ ተከፈለ፤ ለሜዶምና ለፋርስ ሰዎች ተሰጠ” ማለት ነው፡፡ እንዳለውም በዚያች ሌሊት የከነዓን ንጉሥ ብልጣሶር ተገደለ፤ ሥልጣኑንም ሌሎች ወሰዱበት፡፡ (ዳን.፭፥፩-፴፩)

፲፫. የአስቄዋ ልጆች

እነዚህ የአስቄዋ ልጆች እነ ቅዱስ ጳውሎስ በተሰጣቸው ሥልጣን አጋንንትን ሲያወጡ ያያሉ፤ እነርሱም “እንደ እነ ቅዱስ ጳውሎስ አጋንንትን ብናስወጣ ምን አለበት” አሉና ሰይጣን እንደ ንብ የሰፈረበት ሰው ጋር በመሄድ ሰውየው ውስጥ ያለው ሰይጣን እንዲለቅ ተናገሩት፤ እርሱ ግን ዝም አላቸው፤ በኢየሱስ ስም እንዲለቅ አዘዙት፤ ሆኖም ግን ዳግም ዝም አላቸው፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ አምላክ በኢየሱስ ስም እንዲለቅ ጠየቁት፤ ይህን ጊዜ ሰይጣኑ ተናገረ፤ “ኢየሱስን አውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተ ማናችሁ እናንተ ደፋሮች” ብሎ ተነሣባቸው፤ ጨርቃቸውን ጥለው እስኪሸሹ ድረስም ደበደባቸው፡፤ ይህም “የምን አለበት” መዘዝ ነው፡፡ (ሐዋ.፲፱፥፲፩-፲፯)

፲፬. ሐናንያና ሰጲራ

በሐዋርያት ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ቤታቸውን፣ መሬታቸውን እየሸጡና ለሐዋርያት እያስረከቡ ሁሉም ከአንድ መሶብ ይበሉ ነበር፡። ሁሉም ከአንድ ጽዋ ይጠጡ ነበር፡፡ ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ነበሩ፡፡ ሐናንያና ሰጲራ ባልና ሚስት ናቸው፡፡ እነርሱም እንደ ሕዝበ ክርስቲያኑ መሬታቸውን ከሸጡ በኋላ እንደ ሥርዓቱ ሁሉንም ማስረከብ ይገባቸው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ማንም እንደማያያቸው በማሰብ “ግማሹን ከፍለን ደብቀን ቢናስቀር ምን አለበት” አሉ፡፡

ሐናንያም ቀድሞ ሄዶ ግማሹን ከሐዋርያት ፊት አቀረበው፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን የልባቸውን አውቆ “መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን ስለ ምን በልብህ  ሞላ?” በማለት ተናገረው፡፡  ሕግንና ሥርዓትን ለመተላለፍ “ምን አለበት” የሚሉ ሰዎች ሰይጣን በልባቸው ያደረባቸው ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ጅራፍ ተገርፎ ሐናንያ በቅዱስ ጴጥሮስ እግር ሥር ወድቆ ሞተ፡።  ሰዎች ለቀብር ሲሄዱ ሚስቱ ሰጲራ አላወቀችም ነበርና መጣች፡፡ እርሷንም መሬቱ የተሸጠበትን ዋጋ ሲጠይቃት ቅዱስ ጴጥሮስን ዋሸችው፤ ሐዋርያውም መልሶ “የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ ስለ ምን ተስማማችሁ? እነሆ፥ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግር በደጅ ነው፤ አንቺንም  ያወጡሻል” አላት፤ ያን ጊዜም በእግሩ አጠገብ ወደቀች ሞተች፤ ይህ የምናለበት መዘዝ ነው፡፡ (ሐዋ.፭፥፩-፲)

ስለዚህ “በምን አለበት” ሰበብ ከእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ ልንወጣ አይገባም፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እንደ ርግብ የዋህ፣ እንደ እባብ ልባሞች (ብልጦች) ሁኑ” ያለው ያልተገባ የዋህነት ስለሚጎዳ ነው፤ ብዙ የዋሃን በየዋህነት ሃይማኖታቸውን የለቀቁ አሉ፡፡ እኛን ግን እግዚአብሔር አምላካችን በሃይማኖትና በምግባር ያጽናን፡፡

የአምላካችን እግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፤ አሜን!