የሎጥ ዘመን በዚች ቅድስት ሀገርና ሕዝብ ላይ አይደገምም!!!

ዘመኑ የሎጥ ዘመን ሆኖአል፡፡ በዚያ ዘመን የተነሡ የሰዶምና የገሞራ ሕዝቦች እግዚአብሔርን እያወቁ “እናይ ዘንድ ሥራውን ያፋጥን፤ እናውቃትም ዘንድ የእስራኤል ቅዱስ ምክር ይምጣ”(ኢሳ.5፡19)በማለት እግዚአብሔርን በመገዳደር ወንዱ ከወንዱ ጋር ሴቷም ከሴቷ ጋር በመዳራታቸው ምክንያት እግዚአብሔር ተቆጥቶ ከሰማይ እሳትና ዲንን በማውረድ ፈጽሞ ያጠፋቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡(ዘፍ.18፡16-32፤19)እነርሱን ያጠፉአቸው ዘንድ የተላኩም መላእክት የእግዚአብሔር ቁጣ በእነዚህ ላይ ምን ያህል  እንደነደደ ሲገልጡ “እኛ ይህቺን ስፍራ እናጠፋታለንና ጩኸታቸውም (ተግዳሮታቸውም)  በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ሆኖአልና፤ እናጠፋት ዘንድ እግዚአብሔር ልኮናል”(ዘፍ.19፡13)  ብለዋል፡፡ በዚህ ዘመንም እንደ ምዕራባውያኑ የእግዚአብሔርን ሕልውና ሽምጥጥ አድርገው የካዱ ወገኖች በሀገራችን ውስጥ ተነሥተዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች ይህን ጸያፍ የሆነ ድርጊታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ በገንዘብ ፍቅር በሰከሩ ግብረ ገብ በሌላቸው ባለ ሀብቶች የሚደገፉ ናቸው ፡፡ ነገር ግን ማንም እንዳይስት ይጠንቀቅ፡፡  እነዚህ ወገኖች ለገንዘብ በማጎብደድ በዚህ ደሃ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በቡሃ ላይ ቆረቆር እንዲሉ ባሕሉና ሃይማኖቱ ፈጽሞ የማይፈቅደውን ከተፈጥሮ ሥርዐት የወጣውን ግብረ ሰዶማዊነትን ለገዛ ጥቅማቸው ሲሉ እንዲስፋፋ እየደከሙ ይገኛሉ፡፡

 

የምድሪቱም ሳይንቲስቶች በእነርሱ ላይ ሠልጥኖ የሚገዛቸውን የሰይጣንን ፈቃድ ለመፈጸም ሲሉ ግብረ ሶዶማዊነትን ተፈጥሮአዊ ነው በማለት ሕዝቡን ያወናብዳሉ፤ ለእነርሱም ከለላ ይሰጣሉ፡፡ የእነዚህ የሰይጣን የግብር ልጆች ቃልን የሚሰማና የሚቀበል ወገን እግዚአብሔር “በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡንም ከእግዚአብሔር የሚመልስ ሰው ርጉም ይሁን”(ኤር.17፡5) እንዳለ የተረገመ ነው፡፡  ለመሆኑ ስለነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 

መጽሐፍ ቅዱስ ስለእነዚህ ደፋሮች “እውነትን በዓመፃቸው ለሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ከሰማይ ይገለጣልና እግዚአብሔር ስለገለጠላቸው ስለእግዚአብሔር ሊታወቅ የሚችለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና፡፡ የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርንነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ”፡፡ (ሮሜ.1፡18-21)በማለት የመሰከረባቸው ሲሆኑ “ጥበበኞች ነን ሲሉ የደነቆሩ ሰውንና ገንዘብን ወደ ማምለክ የመጡ በግብራቸው አራዊቶችን የመሰሉ እንዲሁም በድፍረት ይህን ጸያፍ ተግባር ተለማምደው ከዚህ ክፉ ልማዳቸው  መውጣት የተሳናቸው ወገኖች ናቸው፡፡ እነዚህና አጫፋሪዎቻቸው እግዚአብሔር ከመንጋው የተለዩ ይሆኑ ዘንድ በክፉ ምግባራቸው የገለጣቸውና እንደ ምርጫቸው ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ የሰጣቸው ወገኖች ናቸው፡፡ ልዩ መለያቸውም ወንዱ ከወንዱ ጋር ሴቷም ከሴቷ ጋር መዳራታቸውና ዓመፃ ሁሉ ግፍን መመኘትንና ክፋት የሞላባቸው ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡(ሮሜ.1፡26)

 

እነዚህ ወገኖች ግብረ ሶዶማዊነት ተፈጥሮአችን ነውና ልንከለክል አይገባንም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ በእውን ተፈጥሮአቸው ከእኛ ተፈጥሮ የተለየ ነውን?ተፈጥሮአቸውስ ከሆነማ እንደ ሕጋዊው (ወንድና ሴት) ጋብቻ ድንበር ዘመን ባሕል ሳያግደው በሀገሩና ሕዝቡ ሁሉ ዘንድ በተፈጸመ ነበር፤ ተቃውሞም ባልገጠመው ነበር፡፡ ለአፈጻጸሙም የገንዘብ፣ የልዩ ልዩ ምክንያቶች ከለላና የሰልፍ ሆታ ባላስፈለገው ነበር፡፡ ይህ የሚያስረዳው ፍጹም ከተፈጥሮ የወጣ ክፉ ምግባር መሆኑን ነው፡፡ስለዚህም የዚህ ነውረኛ ድርጊት አቀንቃኞች ተፈጥሮአዊ አይደለምና ምክንያትንና ጥግ ፈለጉለት፡፡ ለዚህም በሰብአዊ ሕሊና የሚደረገውን ዓለማቀፋዊ ልግስናን (ዕርዳታን) እንደ መደራደሪያ (እንደማባበያ) ተጠቀሙበት፡፡ አቤት ክፋት፡፡

 

እነዚህ ወገኖች ተፈጥሮአችን ከእናንተ ጋር አንድ ነው የሚሉ ከሆኑ ተፈጥሮአዊ ጠባያቸውን ጠብቀው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሊኖሩ ይገባቸው ነበር፡፡ በጥቂቶች ላይ ብቻ የሚታይ ነው ከተባለስ በሰዶምና ገሞራ ሕዝቦች ሁሉ ላይ ይህ አስነዋሪ ተግባር ስለምን ታየ? (ዘፍ.18፡20፤19፡4) ተፈጥሮአዊ ከሆነስ እንዴት እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ እሳትንና ዲንን አዝንቦ ፈጽሞ አጠፋቸው? የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደ እነርሱ አሳብ ከሆነ ከመጀመሪያው ስለምን ወንድ ብቻ ወይም ሴት ብቻ አድርጎ ሰዎችን አልፈጠራቸውም? ስለምንስ ሰዎችን ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው? ለዚህ የመከራከሪያ አሳብ የሚሰጡት አንዳች መልስ የላቸውም፡፡ ይልቁኑ ቅዱስ ጴጥሮስ “ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነው”(2ጴጥ.2፡19) እንዲል የእግዚአብሔርን ሕልውና በመካዳቸውና ለሰይጣን ፈቃድ በመገዛታቸው ለዚህ ነውረኛ ድርጊት ተላልፈው የተሰጡ የጥፋት ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖችና አጫፋሪዎቻቸው ተፈጥሮአዊ የሆነውን ሕግ ሽረው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሲቃወሙ ትንሽ እንኳ እፍረት አይሰማቸውም፡፡ ይህ ነገ በራሳቸው ልጆቻቸው ላይ እንደሚፈጸም ዞር ብለው ማሰብ ተስኖአቸዋል፡፡ ነገር ግን በሕዝቡ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ እንዲነድ ታውረው ይህን አጸያፊና ነውረኛ ተግባርን ለማስፋፋት ሲሉ የኑሮው ውድነት ባስጨነቀው ምስኪን ሕዝብ ላይ ሌላ መከራ ሊጭኑበት ደፋ ቀና ይላሉ፡፡ ይህን ምስኪን ሕዝብ ለእነዚህ ግብረ ሰዶማውያን አካሉን እንዲገብር ሲሉ ይህን አስነዋሪ ድርጊት በመዲናችን በአዲስ አበባ ያስተዋውቃሉ፡፡ ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ ጥቂት ባለሀብቶችም ለእነርሱ ከለላና ጥብቃ በማድረግ ክፉ ተግባራቸውን እንዲፈጽሙ ለምቾቶቻቸው ይጠነቃቃሉ፡፡ ይህ በእውነት እጅግ አጸያፊና በዚህ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ፈጽሞ ያልታየና ያልተሰማ ታላቅ አዋራጅና አጸያፊ ተግባር ነው፡፡ የቤተክርስቲያናችን አስተምህሮም ይህን ድርጊት እጅግ ፈጽሞ ይቃወማል፡፡

 

ስለዚህም እንደነዚህ ካሉ ወገኖች ጋር በምንም ነገር የሚተባበር ክርስቲያን ቢኖር  እንደ ሎጥ ሚስት በራሱ ላይ ጥፋትን የሚያመጣና ሐዋርያት ያስተማሩንን ትምህርት የሚቃወም የወንጌል ጠላት ነው፡፡ ስለዚህም ቤተክርስቲያን ካስተማረችው ትምህርት ውጪ ተፈጥሮአዊ ሕግን የሚጻረር ይህን እኩይ ተግባርን የሚፈጽም፣ የሚያበረታታ፣ የሚያስተምር ክርስቲያን ሁሉ ከክርስቶስ ኅብረት የተለየና የተወገዘ ነው፡፡ (ሮሜ.2፡26፣32፤2ቆሮ.11፡16፤ገላ.1፡9)

 

አምላከ ነዳያን ይህቺን ሀገር ከእነዚህ ከጠገቡ ክፉ አውሬዎች እኩይ ተግባር ይጠብቃት፤ ከዚህ ከነውራቸው የሚጸጸቱበትን ልቡና ይመልስላቸው፡፡ የሚረዱአቸውንም ሐሳባቸውን ወደ በጎ ይመልስ ለዘለዓለም አሜን!!