“የእግዚአብሔር ቤት” በሚል ርእስ የተሠራው የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት ፊልም ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ እንደሆነ ተገለጠ፡፡

ኅዳር 28/2004 ዓ.ም.
በዲ/ን ኅሩይ ባየ

የእግዚአብሔር ቤት /The abode of God/ በሚል ርእስ በጀርመናዊቷ ሚስስ ብሪጅት ማሪያ ማየር ተዘጋጅቶ በተወሰኑ ኢትዮጵያዉያን አርቲስቶች የተሠራው የኢየሱስ ክርስስቶስ የስቅለት ፊልም ከቤተ ክርስቲያን ቀኖና እና ትውፊት ውጭ እንደሆነ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ ኅዳር 28 ቀን 2004 ዓ.ም የሰጠው መግለጫ ያስረዳል፡፡

 

ሚስስ ብሪጅት ማሪያ ማቶር የተባለችው ጀርመናዊት በኢትዮጵያውያን የኪነ ጥበብ ሰዎች እንዲሠራ ያዘጋጀችው ፊልም በይምርሐነ ክርስቶስ፣ አሸተን ማርያምና በጉንዳጉንዶ ገነተ ማርያም አብያተ ክርስቲያናት ተቀርጾ ለዕይታ እንዲቀርብ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ያቀረቡት ጥያቄ ጉዳዩ ሃይማኖታዊ ስለሆነና ቀረጻው የሚካሔድበት ቦታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲየን አብያተ ክርስቲያናት ስለሆነ ጉዳዩ በቤተ ክርስቲያኗ እንዲታይና እንዲፈቀድ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

ከመንግስት ኮሚዮኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በተሰጠው አስተያየት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት በቁጥር ል/ጽ/565/279/03 በቀን 8/11/2003 ዓ.ም በሊቃውንት ጉባኤ እንዲታይ የፊልሙ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡ የሊቃውንት ጉባኤውም በተሰጠው መመሪያ መሠረት ከ11/11/2003 እስከ 15/11/2003 ዓ.ም ለአምስት ተከታታይ ቀናት ባደረገው ጉባኤ 80 ገጾች ያሉትን የፊልም ጽሑፍ መርምሮ የውሳኔ ሐሳቡን ለቋሚ ሲኖዶስ አቅርቧል፡፡

ቋሚ ሲኖዶስም ጳጉሜን 1 ቀን 2003 ዓ.ም ባደረገው ጉባኤ በሊቃውንት ጉባኤ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ የተዘጋጀው የፊልም ጽሑፍ፡-

• የክርስቶስን ቅዱስ ወንጌል በአግባቡ የማይገልጽ በመሆኑ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት፣ ትውፊትና ታሪክ ባለመጠበቁ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት መከራ መስቀሉን፣ ሕማሙን፣ ሞቱንና ትንሣኤውን ዝቅ አድርጎ በማቅረቡና ባጠቃላይ ከቤተ ክርስቲያናችን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ቀኖና ትውፊት ውጭ ስለሆነ የፊልሙ ጽሑፍ ውድቅ ሆኗል ሲል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

 

በቋሚ ሲኖዶስ በተሰጠው ውሳኔ መነሻነት የመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በቁጥር 7403/2789/2003 በቀን 18/11/2003 ዓ.ም ቀረጻው ሊካሔድበት ለታሰቡት አህጉረ ስብከቶች ማለትም ለትግራይ ምሥራቃዊ ዞን ሀገረ ስብከትና ለሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ፊልሙ እንዳይሠራና ቀረጻው ተጀምሮ ከሆነም ቀረጻው እንዲቆም በደብዳቤ አስታውቋል፡፡

 

የመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የፊልሙን ኢ-ሥርዐታዊነት ገልጦ መስከረም 4 ቀን 2004 ዓ.ም ለጀርመን ኢምባሲ፤ መስከረም 11 ቀን 2004 ዓ.ም ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ አህጉረ ስብከቶች በደብዳቤ መግለጡን የሊቃውንት ጉባኤው በሰጠው መግለጫ አስገንዝቧል፡፡

 

በመሆኑም የተሠራው ፊልም በማንኛውም አጋጣሚ ለዕይታ ቢቀርብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማታውቀውና የማትቀበለው መሆኑን ምእመናን ተገንዝበው ሕዝበ ክርስቲያኑ ራሳቸውን ከስሕተት እንዲጠብቁ የሊቃውንት ጉባኤው ጥሪውን አስተላልፏል፡፡