የሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ ሰባተኛ ዓመት የዕረፍት ቀናቸው ተዘከረ

በዕለቱ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት በሚል ርእስ በ፲፱፻፺፮ ዓ.ም ባዘጋጁት መጽሐፋቸው ላይ የዳሰሳ ጥናት ቀርቧል፡፡

ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ በስእለት መልክ ለእግዚአብሔር መሰጠታቸውን እኅታቸው ተናግረዋል፡፡

ወጣቱ ትውልድ የእርሳቸውን ፈለግ ተከትሎ ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ ከቻለ አባ አበራ ሕያው ናቸው እንጂ አልሞቱም ተብሏል፡፡

ግንቦት ፲፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የሊቀ ገባኤ አባ አበራ በቀለ (ስመ ጥምቀታቸው ኃይለ መስቀል) ሰባተኛ ዓመት የዕረፍት ቀናቸው መታሰቢያ ቤተሰቦቻቸው፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራሮችና አባላት በተገኙበት ግንቦት ፲፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በማኅበሩ ሕንፃ ተዘክሯል፡፡

በዕለቱ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት በሚል ርእስ በ፲፱፻፺፮ ዓ.ም ባዘጋጁት መጽሐፋቸው ላይ የዳሰሳ ጥናት ያቀረቡት ዲያቆን አሻግሬ አምጤ እንደገለጹት አባ አበራ ባለ ፬፹፬ ገጽ በሆነው በዚህ መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ ክርስትና የፍቅር ሃይማኖት መሆኑንና የሃይማኖታችን ታሪክ በፍቅር ተጀምሮ በፍቅር መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡ እንደዚሁም የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ሦስት ዐበይት ነጥቦች እንደሚያስፈልጉና እነዚህም ማመን፣ መጠመቅና ትእዛዛትን መጠበቅ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በትምህርተ ሃይማኖት መቅድማቸውም ሃይማኖት ከእግዚአብሔር ለሰው የተሰጠ መሆኑን አስረድተው እምነት የሁሉ ነገር መሠረት እንደሆነ በማብራራት መሠረት ሕንፃዎችን ሁሉ እንደሚሸከም እምነትም ምግባራትን ሁሉ እንደምትይዝ፣ ሕንፃ ያለመሠረት እንደማይቆም ምግባርም ያለ ሃይማኖት እንደማይጸና የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ትምህርት ጠቅሰው አስተምረዋል፡፡

በዳሰሳ አቅራቢው እንደተብራራው መጽሐፉ በክፍል አንድ አንቀጹ ሠለስቱ ምእት በኒቅያው ጉባኤ የደነገጉትን ጸሎተ ሃይማኖት እና በጉባኤ ቍስጥንጥንያ የተሰበሰቡ ፻፶ ሊቃውንትን ውሳኔ መጽሐፍ ቅዱስንና ሊቃውንትን መሠረት በማድረግ ያብራራል፡፡ ባጠቃላይም ስለ ሃይማኖት በመመስከር ላይ እንደሚያተኩር እና ሰይጣንን ክዶ የክርስቶስ ተከታይ ስለመሆን እንደሚያትት የጥናቱ አቅራቢ ዲያቆን አሻግሬ አስረድተዋል፡፡ ክፍለ ሁለት የክርስቶስ የማዳን ሥራና ጸጋ እውን የሚሆነው ቃሉን በመስማትና ምሥጢራትን በመፈጸም መሆኑን እንደሚያስረዳ፣ ክፍል ሦስት ደግሞ ክርስቲያናዊ ሕይወትና ምግባር በእምነት፣ በተስፋና በፍቅር መገለጡ ተብራርቶበታል፡፡

ምእመናን የመዳን ተስፋችን እውን እንዲሆን በሥስቱ አርእስተ ሃይማኖት ማለትም በእግዚአብሔር ፍቅር፣ በክርስቶስ ጸጋ እና በመንፈስ ቅዱስ ኅብረትና ረድኤት መመሥረት እንደሚገባን ይናገራል፡፡ በተጨማሪም አባ አበራ ፍቅርን አንደኛ እግዚአብሔር ለሰው ያለው ፍቅር፣ ሁለተኛ ሰው ለእግዚአብሔር ያለው ፍቅር እና ሦስተኛ ትእዛዛቱን መጠበቅ (አምላክህንና ባልንጀራህን ውደድ የሚሉትን) በማለት በሦስት ክፍል አቅርበውበታል፡፡ ይህም የአባ አበራ መጽሐፍ በዚህ ዓመት በማኅበረ ቅዱሳን እንደገና ታትሞ ገበያ ላይ ውሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሕይወት በነበሩበት ወቅት ያስተማሩት ትምህርትና ያደረጉት ንግግር በቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩምና በዲያቆን ሙሉዓለም ካሣ አስተባባሪነት በድምፅና ምስል ተቀናብሮ ለመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች የቀረበ ሲሆን ቀጥሎም ቤተሰቦቻቸውና በቅርብ የሚያውቋቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸውና የመንፈስ ልጆቻቸው አባ አበራ ፍቅርን፣ መንፈሳዊነትን፣ ደግነትን፣ ቅንነትን እና ትሕትናን የተላበሱ፣ ከስስትና ከፍቅረ ንዋይ የራቁ አባት እንደነበሩ መስክረውላቸዋል፡፡

ታናሽ እኅታቸው ወ/ሮ ጸዳለ በቀለ አባ አበራ ሕፃን እያሉ ጥቅምት ፳፰ ቀን ወላጅ እናታቸው አዝለዋቸው በመንገድ ሲጓዙ በዘመኑ ታዳጊ ወንዶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሽፍቶች ባገኗቸው ጊዜ እናታቸው አባቴ አማኑኤል ሆይ ልጄን ከነዚህ ሽፍቶች ብታድንልኝ የአንተ አገልጋይ ይሁን ብለው በስእለት መልክ ለእግዚአብሔር ሰጥተዋቸው ነበር፤ ይህም ሕይወታቸውን በሙሉ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲኖሩ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡

መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁንም ከሊቀ ጉባኤ አባ አበራ ጋር በመሆን በስብከተ ወንጌልም በአስተዳደርም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግሉ መኖራቸውን አውስተው በተለይ ለወላጅ እናታቸው ልዩ ፍቅርና አክብሮት እንደነበራቸው ተናግረዋል፡፡ አክለውም የጻድቅ ሰው መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ ራሳቸውን መሥዋዕት አድርገውና ልዩ ልዩ ፈተናዎችን ተቋቁመው ያሰቡትን መንፈሳዊ ዕቅድ ሁሉ አሳክተው ያለፉ አባት መሆናቸውን ጠቅሰው ወጣቱ ትውልድ የእርሳቸውን ፈለግ ተከትሎ ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ ከቻለ አባ አበራ ሕያው ናቸው እንጂ ሞቱ አይባልም ሲሉ መልእክታቸውን አጠቃለዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ በበኩላቸው አባ አበራ በአገር ውስጥም፣ ከአገር ውጪም በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየተዘዋወሩ ብዙ ዕውቀት መቅሰማቸውን ገልጸው፣ አክለውም ለሚሰማቸው ብቻ ሳይሆን ለሚመለከተቻውም አስተማሪ ሕይወት እንደነበራቸው፣ በሕይወት ከኖሩበት ጊዜ በላይ ካረፉ በኋላ ለብዙ ሰዎች ምሳሌ እንደሚሆኑና ሁሉም ሊማርባቸውና ሊያስታውሳቸው እንደሚገባ ገልጸው እኒህን አባት ለመዘከር ያመች ዘንድ በስማቸው የሚሰየም አንድ ስኮላርሺፕ ቢኖረን መልካም ነውና ሁላችንም ብናስብበት ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በተጨማሪም ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ፣ ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ፣ አቶ ኤርምያስ ዓለሙ እና አቶ ሙሉጌታ ምትኩ ስለ አባ አበራ መንፈሳዊ ሕይወት ተመሳሳይ አሳብና አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ከጽርሐ ጽዮን ማኅበር አባላት አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉእመቤት በላቸውም፡- ክርስትና ማለት ራስን መካድ መሆኑን የተማርሁት ከአባ አበራ ነው፡፡ ሁላችንም አንረሳቸውም፡፡ እኛ ጊዜያችን እያለቀ ነው፡፡ እናንተ ወጣቶች ትግሉን እንደእርሳቸው ታገሉት፤ ትጥቁን እንደእርሳቸው ታጠቁት፡፡ የአባ አበራን ፈለግ ተከትላችሁ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ የሚመጣባችሁን ሁሉ ፈተና በጸጋ ተቀብላችሁ ወንጌልን ስበኩ ሲሉ እናታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም በአባቶች ምክርና ጸሎተ ቡራኬ በስማቸው የተዘጋጀው ጸበል ጸሪቅ ከቀረበ በኋላ ከምሽቱ 2፡30 ገደማ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

ክቡር ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ ከአባታቸው ከግራ አዝማች በቀለ መኩሪያ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ በሸዋምየለሽ ድፋባቸው ከዐዲስ አበባ በስተምሥራቅ አቅጣጫ የረር አካባቢ በሚገኘው ልዩ ስሙ ቡኢ በተባለ ሥፍራ በዕለተ ስቅለት ሚያዝያ ፪ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ተወልደው በ፸፫ ዓመታቸው ሚያዝያ ፭ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል፡፡

ለአርባ አምስት ዓመታት ያህል ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንና ሀገራቸውን በፍጹም ፍቅር ሲያገለግሉ የቆዩት ሊቀ ጉባኤ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ካበረከቱት ከፍተኛ አተዋጽዖ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን በውኃ እንፋሎት የሚንቀሳቀስ መኪና የሠሩ ጥበበኛም ነበሩ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም እኒህ ታላቅ አባት ለቤተ ክርስቲያንና ለአገር ያበረከቱትን አስተዋጽዖ ግምት ውስጥ በማስገባት የሰባተኛ ዓመት የዕረፍት ቀናቸው እንዲዘከር አድርጓል፡፡