ዝክረ ግማደ መስቀሉ!

በሦስተኛው ክፍለ ዘመን በሮም ግዛት እየመነመነ የሔደውን ክርስትናን እምነት ለመጠበቅ የሀገሪቱ ንግሥት ዕሌኒ ልጇን ቆስጠንጢኖስን ከልጅነቱ ጀምሮ ስለ ክርስትና ሃይማኖትና ስለ ክርስቲያኖች መከራ ታስተምረው ጀመር፡፡ ይህም በእርሱ ላይ ስለ ክርስትና እንዲሁም ስለ ክርስቲያኖች በጎ አመለካከትን ፈጠረ፡፡ ንጉሡም በሮም ከነገሡት ቄሣሮች በተሸለ መንገድ ክርስትናን እንዲቀበል አደረገው፡፡

ልጇ ቆስጠንጢኖስ በነገሠበት ዘመን በሦስት መቶ ዓመታት ውስጥ የክርስቲያኖች የነጻነት ዐዋጅን ለመጀመሪያ ጊዜ ዐወጀ፤ ከዚህም በኋላ ክርስትና ብሔራዊ ሃይማኖት ሆነች፡፡ በሦስት መቶ ሃያ ሰባት ዓ.ም. ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ከተቀበረበት ቦታ ፈልጋ ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች፡፡ ይህንንም አንዲያሳካላት ፈጣሪዋን ለመነችው፤ ሥእለትም ተሳለች፡፡ ልጇ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ከሆነላት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ መስቀሉን እንደምትፈልግ እና በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትን እንደምታሳንፅ ጭምር ለእግዚአብሔር ተሳለች፡፡

ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ክርስትናን መቀበሉን ለማስመስከር በሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ዓ.ም. አምኖ ተጠመቀ፡፡ ከዚህ በኋላ ግማደ መስቀሉን ለማግኘት እንዲያመቻት ቅድስት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ከተጓዘች በኋላ ስለ መስቀል ለማወቅ መረመረች፤ ጠየቀችም፤ ሆኖም ያለበትን ቦታ የሚነግራት ሰው ማግኘት አልቻለችም፡፡ እርሷም ተስፋ ሳትቆርጥ ተግታ በመፈለጓ አንድ ኪራኮስ የተባለ አረጋዊ የጎልጎታን ኮረብታ ሊያሳያት ችሏል፤ ነገር ግን ከሦስቱ ተራሮች መካከል መስቀሉ የሚገኝበትን ለይቶ ለማወቅ ባለመቻሉ ንግሥት ዕሌኒ ወደ አምለኳ ጸለየች፡፡ ከሦስቱ ተራሮች የቱ እንደሆነ ለመለየት በእግዚአብሔር መልአክ ርዳታ ደመራ አስደምራ ብዙ እጣንም በመጨመርና በማቃጠልም ጸሎት ተደረገ፡፡ በዚህም ጊዜ የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ በመውጣት በቀጥታ ተመልሶ መስቀሉ ባለበት ተራራ ላይ በማረፍና በመስገድ መስቀሉ ያለበትን ትክክለኛ ስፍራ አመለከታት፡፡ የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራም በዚህ ተገለጸ፤ ቅዱስ ያሬድም ‹‹ጢሱ ሰገደ›› ሲል ገልጾታል፡፡

ቅድስት ዕሌኒም መስከረም ፲፯ ቀን ቁፋሮ እንዲጀመር አዘዘች፡፡ ቁፋሮውም ሰባት ወር ያህል ከፈጀ በኋላ መጋቢት ፲ ቀን ሦስት መስቀሎች በአንድነት ተገኙ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል መለየት ግን አልተቻለም ነበር፡፡ ስለዚህም ሦስቱን መስቀሎች ወደ ሞተ ሰው በመውሰድ በተራ በተራ አስቀመጧቸው፤ ያን ጊዜ ጌታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል የሞተውን ሰው በማስነሳቱ መስቀሉ ተለየ፤ ተአምሩም ተገለጸ፡፡ ቅድስት ዕሌኒና መላው ክርስቲያን ለመስቀሉ ሰገዱለት፡፡

በየሀገሩ ያሉ ክርስቲያኖች የመስቀሉን መገኘት በሰሙ ጊዜ መብራት አብርተው ደስታቸውን በመግለጥ ለዓለም እንዲታወቅ አደረጉ፡፡ ንግሥቷም ለመስቀሉ ቤተ መቅደስ ከሠራችለት ጊዜ ጀምሮ መስከረም ፲፮ ቀን በክርስቲያኖች ዘንድ መስቀል ይከበራል።

ግማደ መስቀሉ በኢየሩሳሌም ከቆየ ከብዙ ዓመታት በኋላ የየሀገሩ ነገሥታት መስቀሉን ለራሳቸው ለመውሰድ ጥል ውስጥ ገቡ፡፡ በዚህን ወቅት ከአንጾኪያ፣ ከኤፌሶን፣ ከአርማንያ፣ ከግሪክ፣ ከእስክንድርያ እና ከመሳሰሉት ሀገሮች የተሰበሰቡ የሃይማኖት መሪዎች እርቅ አወረዱ:: ከዚህም በሻገር መስቀሉን ለአራት ከፍለው በስምምነት ተካፍሉት፤ ከንዋያተ ቅድሳት ጋርም  ወስደው በየሀገራቸው በክብር አስቀመጡት:: አህጉራችን አፍሪካ የደረሳት የቀኝ ክንፉ ስለነበር የመስቀሉን ክፍል የግብፅ ፓትርያርክ ተረክቦ ከታሪካዊ ንዋየ ቅድሳት ጋር በክብር አስቀመጠው፡፡

በዚያን ዘመን የነበረው የኢትዮጵያ ንጉሥ ዳግማዊ አፄ ዳዊት ግብፅ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች አማሌቃውያን እያደረሱባቸው ከነበረው ተጽዕኖ ነጻ እንዲወጡ አደረጋቸው፡፡ ለምስጋናም የግብፁ ፓትርያርክ የከበሩ ስጦታዎችን ላኩላቸው:: የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የምትፈልገው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀሉን እንጂ ወርቅ ስላልነበረ ንጉሥ ዳግማዊ ዳዊት ይህን ገለጹላቸው:: በመሆኑም የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ግማደ መስቀሉን ከሌሎች ንዋየ ቅድሳት ጋር ለኢትዮጵያ ሰጠች:: ግማደ መስቀሉም በግሸን ማርያም ገዳም በእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ይገኛል:: መስቀሉን ለመዘከርም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በወርኃዊ በዓመት በዓሉ መጋቢት ፲ ታከብረዋለች:: መስከረም ፲፮ እና መስከረም ፲፯ ቀን ደመራ ደምራ ጸሎትና ምሥጋና ታቀርባለች።

በሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ዓ.ም. በቅድስት ዕሌኒ የተገኘው ቅዱስ መስቀሉ ምሥጢር ይገልጽልን  ዘንድ መጸለይ ይገባል፡፡ ‹‹የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚብሔር ኃይል ነው›› (፩ ቆሮ ፩፥፲፰)  እንደተባለውም፤ በመስቀሉም እንድንባረክ መስቀሉን እንድሸከም ያስፈልጋል፡፡ ‹‹እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ›› (ማቴ. ፲፮፥፳፬) እንዲል፤ የክብሩና የፍቅሩን መገለጫ መስቀልን የምንሸከምበት መንገዶች ብዙ እንደሆነ ቤተክርስቲያን ትገልጻለች፡፡ መስቀል በቤተክርስቲያን ጉልላት፣ በካህናት በምእመናንና በምእመናት አንገት እንዲሁም በልብሳቸውም ላይ ይኖራል:: መስቀል ለሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ  በመሆኑ ሥራ ሲጀመርና ምግብ ሲቀርብ በመስቀል አምሳያ እናማትባለን፡፡ የሁሉ መጀመሪያ ቅድመ ዓለም የነበረ አሁንም ያለ ወደፊትም የሚኖር አምላካችን ነውና፤ እርሱም ለእኛ ሲል መከራ እንደተቀበለልን እና በመስቀሉ ፍቅሩን እንደገለጸልን ሁሉ እኛም ወሮታውን መመለስ ይጠበቅብናል፡፡

ምንጭ፤‹‹የመስቀል ደመራ በዓል ታሪክና አከባበር››፤ የቅዱስ ገብርኤል እና አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን-ኖርዌይ