ዘመነ ስብከት

ታኅሣሥ ፭ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ዘመነ ስብከት ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በፊት ከታኅሣሥ ፯ ጀምሮ እስከ ፳፱ ያለው ወቅት ነው፡፡ ሳምንታቱም ስብከት፣ ብርሃንና ኖላዊ ይባላሉ፡፡ በዚህም ወቅት ስለ ጌታችን ኢየሱስ  መወለድ ነቢያት የተናገሩት ትንቢት ይሰበክበታል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም የገባለትን ቃል ይፈጽም ዘንድ ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ይወርዳል ይወለዳል ብለው በኦሪተ ሙሴ በነቢያትና በመዝሙራት መጻሕፍት ላይ አስቀድመው ትንቢት ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የተስፋውን ቃል በማሰብ ወቅቱን በጾሙት መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን በማሰብ ሕዝበ ክርስቲያኑ በሙሉ እንዲጾም በማወጅ ከልደተ አብርሀም እስከ ልደተ ዳዊት ባለው ትውልድ ውስጥ ስለ ክርስቶስ ሰው መሆን የተሰበከውን በወንጌሉ፣ በምስባኩና በመዝሙሩ ታስተምራለች፡፡

ስብከት (ከታኀሣሥ እስከ ታኅሣሥ ፲፫)

በዚህ ወቅት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሴ በሕገ ነቢያትም በትንቢት እንደጻፉለት የሚናገረው ወንጌል ይነበባል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም ‹‹ፈኑ እዴከ እምአርያም አድኅነኒ ወባልሃኒ እማይ ብዙኅ፤  እጅህን ከአርያም ላክ ከብዙ ውኃም አድነኝም››  ብሏል፡፡  ዳግመኛም ከዓበይት ነቢያት አንዱ የሆነው ኢሳይያስም  ‹‹ሰማዮችን ቀደህ ምነው ብትወርድ፤ ተራሮችም ምነው ቢናወጡ›› ብሎ ስለ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት መውረድ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ የተናረውን ትንቢት ቤተ ክርስቲያን ትሰብካለች፡፡ ቅዱስ ያሬድም በመዝሙሩ ከዓለም በፊት የነበረውንና መድኃኒት የሆነውን ወልድን እንሰብካለን በማለቱ ወቅቱ ስብከት ተብሏል፡፡ (መዝ. ፻፵፫፥፯፣ ኢሳ. ፷፬፥፩፣ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)

ብርሃን (ታኅሣሥ ፲፬ እስከ ታኅሣሥ )

ብርሃን የዘመነ ስብከት ሁለተኛው ሰንበት ነው፡፡ ይህም ነቢያት የነፍሳችን ብርሃን ይወለዳል ብለው ስለመስበካቸው እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ስለማስተማራቸው የሚታሰብበት ሲሆን በዚሁ ኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ ብርሃን መሆኑ ይሰበክበታል፤ ይዘመርበታል፡፡

በዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ መከራ ነፍስ የጸናበት የሰው ልጅ ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት በመሆኑ ነቢያት ያንን ጊዜ የጨለማ ወቅት ብለው በመግለጽ የነፍሳችን ብርሃን ይወለዳል፤ እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ስለመስበካቸው የሚታሰብበት ሳምንት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ከልደተ ዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን የነበረው ፲፬ ትውልድ ይታሰብበታል፡፡

ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ አምላክ ወልደ አምላክ ብርሃን ስለመሆኑ ‹‹ብርሃንህን እና ጽድቅህን ላክ›› በማለት ይናገራል፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም መጣ ብሎ እንደመሰከረው እውነተኛ ብርሃን ስለሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃንነት የሚሰበክበት ሰንበት ነው፡፡ (መዝ. ፵፪፥፫)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ያገኛል እንጂ በጨለማ አይመላለስም›› ብሎ እንዳስተማረው በዚህ ሰንበት ስለ እርሱ ብርሃንነትና ክርስቲያኖችም እርሱን ብርሃናቸው እንዲያደርጉት ይሰበካል፡፡ (ዮሐ. ፰፥፲፪)

ኖላዊ (ከታኅሣሥ ፳፩ እስከ ታኅሣሥ ፳፰)

ሦስተኛው የዘመነ ስብከት ሰንበት ኖላዊ ይባላል፡፡ ኖላዊ ማለት እረኛ ወይም ጠባቂ ማለት ነው፤ በዚህ ዕለት ነቢያት የእግዚአብሔር ልጅ እውነተኛ ጠባቂ መሆኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እያሰበች የምትዘምርበት እና የምትቀድስበት ዕለት ነው፡፡

ነቢያት ራሳቸውንና ሕዝበ እስራኤልን ብሎም ዓለምን እረኛቸው እንደተዋቸው በጎች በመቁጠር ስለእውነተኛው እረኛ መምጣት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሰንበት ከፍልሰተ ባቢሎን እስከ ልደተ ሰንበት ድረስ ያለው ዐሥራ አራት ትውልድ የነበረው ይታሰባል፡፡ በዚህ ሰንበት ቤተ ክርስቲያናችን እረኛ የሌለው በግ፣ ተኩላ፣ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ምክንያት ከትጉህ እረኛ የተለየው የሰው ልጅም ሰብሳቢና የሚያሰማራ ጠባቂ እንዲኖረው ነቢያት ‹‹ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ፥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፥ ተገለጥ›› (መዝ ፸፱፥፩) በማለት ይማጸኑ እንደነበር ታስተምራለች፡፡

ጌታችን ኢየሱስም የትንቢቱ ፍጻሜ ሲደርስ ‹‹መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለበጎቹ ይሰጣል›› በማለት መልካም እረኛ እርሱ መሆኑን መልስ ተናግሯል፡፡ (ዮሐ. ፲፥፲፩)

አምላካችን እግዚአብሔር ጾሙን በሰላም አስጨርሶ ለበዓለ ልደቱ ያደርሰን ዘንድ ቅዱስ ፍቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡

ዋቢ ጽሑፍ፡- ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ፣ ውዳሴ ማርያም ዘሠኑይ፣ መጽሐፈ ስንክሳር ዘታኅሣሥ