ዕረፍተ አቡነ ሀብተ ማርያም

ዲያቆን መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን 

ኅዳር ፳፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በተከበረች በኅዳር ፳፮ ቀን ንዑድ ክቡር ንጹሕ መነኰስ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ አባታችን አቡነ ሀብተ ማርያም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። ይህም ቅዱስ አባት የትውልድ ሀገሩ የራውዕይ በምትባል በስተ ምሥራቅ ባለች ሀገር ውስጥ ሲሆን በዚያም ስሙ ፍሬ ቡሩክ የሚባል አንድ ደግ ሰው ነበረ። ይህም ከክቡራን ሰዎች ወገን የሆነ ሰው እጅግ ሀብታምም የነበረ ሲሆን በሕጋዊ ጋብቻ ያጋቡት ቡርክት የሆነች ስሟ ዮስቴና የምትባል ሚስት ነበረችው። እርሷም በበጎ ምግባርና ሥራ የተጌጠች ናት። ይህችውም ደግ እናታችን በሕግ ተወስና ሳለች በጽኑዕ ገድል፣ በጾም በጸሎት በምጽዋትና በስገድትም ትጋደል ነበር።

በኋላም ጌታችን ስለ መንኖ ዓለምና መንኖ ይሪት የተናገረውን አስባ ለምናኔ ሀብቷን ሁሉንም ነገር ጥላ በቅርብ ወዳለ በረኃ ሄደች። በዚያም ወደሚገኝ አንድ ዋሻ ብትገባ ድንገት አንድ ደግ ባሕታዊን አገኘች። ያም ባሕታዊ ስለ አመጣጧ በተግሣጽ መልክ ቢጠይቃት እርሷ የመጣችው በዚያ ሰው እንደ ሌለ አስባ እንደሆነ ነገረችውና ከዚያ ወጥታ ወደ ሌላ ዋሻ ልትሄድ ስትል በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ከእርሷ ደግ የሆነ ቅዱስ ፍሬ እንደሚወጣ ነግሮ ወደ ዓለም እንድትመለስ አዘዛት። እርሷም “እግዚአብሔር የወደደው ይሁን” ብላ እያመሰገነች ተመልሳ ሳለ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ይህን ታላቅ ጻድቅ ፀንሳ ወለደች። በዚህም ሁላቸውም እጅግ ተሰኙ። እንደ ሥርዓቱም ሲጠመቅ የመጽሐፍ ስሙን “ሀብተ ማርያም” አሉት። እርሱ በሕግ በሥርዓት እያደገ ሄደ። ወደ ቤተ ክርስቲያንም ሲወስዱት “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ” የሚለውን ጸሎት ቢሰማ እጅጉን ወደዳት። እርሷንም ይዞ ከቤቱ ሌሊቱን የሚጸልይና የሚጋደል ሆነ።

በኋላም አባቱ እረኝነት ሰዶት ሳለ በዚያ በጎቹን ሲጠብቅ ሳለ የበግ ጠባቂዎቹን “ዛሬ ዝናም ይዘንማልና እንግባ” አላቸው። እነርሱም “ምን ደመና አለና ነው፤ ቀኑ ብራ ነው” አሉት። ባልሰሙትም ጊዜ እርሱ በጎቹን ይዞ ወደ ቤቱ እንደገባ ኃይለኛ ዝናም፣ ነፋስና መብረቅ የቀላቀለ ዘነመ። በሌላም ጊዜ እንዲሁ አንድ እረኛ በጉልበት በአባ ሀብተ ማርያምን በትሩን ነጠቀው። “መልስልኝ” ብሎ በስመ እግዚአብሔር ቢያምለውም እምቢ አለው። ኋላም በተወው ጊዜ እግዚአብሔር ያን እረኛ በአየር ላይ ሠቅሎ አዋለው። እረኞቹም አባ ሀብተ ማርያምን በለመኑት ጊዜ እግዚአብሔር ነውና ስለ ስሙ ብሎ የቀጣው መሐሪው እርሱ ከወደደ ይማረው ሲል ያ እረኛ ተፈታና ወረደ። መጥቶም ከአባታችን እግር ወደቀ፡፡

ከብዙ ዘመናት በኋላም ስሟ እለ አድባር ወደምትባል ገዳም ገብቶ ከአባ መልከ ጼዴቅ እጅ መነኰሰ። ታላቅ ተጋድሎንም ይጋደል ጀመር። በባሕር መካከልም በመቆም መዝሙረ ዳዊትን ይደግምና ግንባሩም የባሕሩን አሸዋ እስኪነካ አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳል። እህልም መቅመስን ትቶ ልክ እንደ ዋልያዎች የዱር ቅጠል የሚመገብ ሆነ። ዐርባ ዐርባ፣ ሰማንያ ሰማንያ ቀንም የሚያከፍል ሆነ። በሌሊትም ቁሞ በማደር (በትጋሃ ሌሊት) በቀንም አራቱን ወንጌላት ዘወትር ይጸልያል። ይህን ጽኑዕ ተጋድሎውንም ያየ አምላካችን ተገለጠለት። አባ ሀብተ ማርያምም ከግርማው የተነሣ ደንግጦ በግንባሩ ተደፋ። ጌታችንም እፍ ብሉ አጽናንቶ ኃይል ጽንዕ ሰጥቶ አሥነሳውና ‹‹ወዳጄ ሀብተ ማርያም ላጠፋህ ሳይሆን ኃይል ጽንዕ ቃል ኪዳንም ልሰጥህ ነውና የመጣሁት አትፍራ›› አለው።

ጽኑዕ ተጋድሎው በሰማያት ስለ መጻፉ፣ የቅዱስ ማቴዎስንና የማርቆስን ወንጌል በሚያነብ ጊዜ ከሌሎች ሥውራን አበው ጋር የሚገናኝበትን የብርሃን ሠረገላ እንደ ሰጠው፣ የቅዱስ ሉቃስንና የቅዱስ ዮሐንስን ወንጌል በሚያነብ ጊዜ ደግሞ ሥጋውን ደሙን ለመቀበል ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄድበትን የእሳት ሠረገላ እንደ ሰጠው ቃል ኪዳን ገባለት። ሰባት እጅግ የሚያስደንቁ አክሊላትንም አቀዳጀው። አንዱ ስለ ድንግልናው፣ ሁለተኛው ዓለምንና በውስጡ ያለውን ስለ መመነኑ፣ ሦስተኛው ፍጹም ስለ ሆነው ምንኲስናው፣ አራተኛው አራቱን ወንጌላት አዘውትሮ በማንበቡ፣ አምስተኛው ስለፍቅሩ ሲል ረኃብና ጥምን በመታገሡ፣ ስድስተኛው በልቡ ቂምንና በቀልን ባለማኖሩ፣ ሰባተኛው ደግሞ ስለ ንጹሕ የክህነት አገልግሎቱና በንጽሕና ስለሚያሣርገው መሥዋዕቱ መሆኑን ነገረው። መታሰቢያውን ለሚያደርጉና በስሙ ለሚዘክሩ፣ ከእነርሱ ጋር የሚኖርበትን አምስት መቶ የወርቅ አምዶስ ያሏትን ቦታ ሰጠሁህ አለው። ቅዱሳን መላእክትም ሁላቸው እየተደሰቱ ‹‹ወንድማችን ወደማያልቀው ሰማያዊ ደስታ ልንወስድህ መጥተናል››  አሉት።

ይህንንም በተናገረ ጊዜ ጌታችን በሦስትነቱ ተገልጦ ታየው። ‹‹መታሰቢያህን ለሚያደርግ፣ በስምህ ለቤተ ክርስቲያን መባ ለሚሰጥ፣ ወደዚህች አገር አገባዋለሁ። አራቱን ወንጌልም እያነበብህ ስለኖርህ የየአንዲቱን ቃል ፍሬዋን አንዳንድ ሺህ አደረግሁልህ። ይኸውም ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ልጆችን መጽሐፈ ገድልህን ለሚያነቡና በእምነት ለሚሰሙ፣ የገድልህን መጽሐፍ በተነበበበት ውኃ ለሚረጩ፣ ለሚነከሩበት ይህ ቃል ኪዳን ሰጥቼሃለሁ።›› ከዚህም በኋላ ጌታችን ሦስት ጊዜ ሳመው። ነፍሱም ከሥጋው በሰላም ተለየች። ቅዱሳን መላእክትም በታላቅ ደስታ እያመሰገኑ አሣረጓት።

እግዚአብሔር አምላካችን በዚህ ታላቅ ጻድቅ ጸሎት ይማረን፤ በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።