የስም ዝርዝር በመራሕያን

መምህር በትረማርያም አበባው
ኅዳር ፳፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ውድ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? ባለፈው ትምህርታችን የግሥ ዝርዝር በዐሥሩ መራሕያን ዓይተን ነበር፡፡ በዚህም ክፍለ ጊዜያችን ለሰጠናችሁ መልመጃ ምላሽና ስሞችን በመራሕያን እንዴት መዘርዘር እንደምችል አዘጋጅተን አቅርበንላችኋል፡፡ መልካም የትምህርት ክፍለ ጊዜ ይሁንላችሁ!

መልመጃ
የሚከተሉትን ግሦች በዐሥሩ መራሕያን ዘርዝሩ!
፩) ኮነ……ሆነ
፪) ሎሀ….ጻፈ
፫) ሰገደ….ሰገደ
፬) ጥዕየ….ዳነ
፭) ለቅሐ…..አበደረ
፮) ሐገገ……ሕግ ሠራ
፯) ሠምረ…..ወደደ

መልሾች
፩. መራሒ       ግእዝ        አማርኛ

፩) አነ ………….ኮንኩ……….እኔ ሆንኩ
፪) ንሕነ……….ኮነ………….እኛ ሆንን
፫) አንተ……..ኮንከ…………አንተ ሆንክ
፬) አንትሙ…..ኮንክሙ……እናንተ ሆናችሁ
፭) አንቲ………ኮንኪ……….አንቺ ሆንሽ
፮) አንትን……ኮንክን………እናንተ (ሴ) ሆናችሁ
፯) ውእቱ…….ኮነ………….እርሱ ሆነ
፰) ውእቶሙ…ኮኑ………….እነርሱ ሆኑ (ወ)
፱) ይእቲ…….ኮነት………….እርሷ ሆነች
፲) ውእቶን…..ኮና…………እነርሱ (ሴ) ሆኑ

፪. መራሒ     ግእዝ     አማርኛ
፩) አነ……..ሎህኩ……እኔ ጻፍኩ
፪) ንሕነ…….ሎህነ…….እኛ ጻፍን
፫) አንተ……ሎህከ……አንተ ጻፍክ
፬) አንትሙ..ሎህክሙ…እናንተ(ሴ)ጻፋችሁ
፭) አንቲ…..ሎህኪ…….አንቺ ጻፍሽ
፮) አንትን…..ሎህክሙ…እናንተ (ወ) ጻፋችሁ
፯) ውእቱ…..ሎሀ………እርሱ ጻፈ
፰) ውእቶሙ…ሎሁ……እነርሱ (ወ) ጻፉ
፱) ይእቲ………ሎሀት…….እርሷ ጻፈች
፲) ውእቶን……ሎሃ……….እነርሱ (ሴ) ጻፉ

፫. መራሒ    ግእዝ      አማርኛ
፩) አነ……….ሰገድኩ…..እኔ ሰገድኩ
፪) ንሕነ……..ሰገድነ……እኛ ሰገድን
፫) አንተ……..ሰገድከ…..አንተ ሰገድክ
፬) አንትሙ…..ሰገድክሙ..እናንተ (ሴ) ሰገዳችሁ
፭) አንቲ………ሰገድኪ…..አንቺ ሰገደሽ
፮) አንትን……ሰገድክሙ…እናንተ (ወ) ሰገዳችሁ
፯) ውእቱ…..ሰገደ……….እርሱ ሰገደ
፰) ውእቶሙ…ሰገዱ…….እነርሱ (ወ) ሰገዱ
፱) ይእቲ…….ሰገደት…….እርሷ ሰገደች
፲) ውእቶን….ሰገዳ………..እነርሱ (ሴ) ሰገዱ

፬. መራሒ      ግእዝ         አማርኛ
፩) አነ………ጥዕይኩ…..እኔ ዳንኩ
፪) ንሕነ…….ጥዕይነ……እኛ ዳንን
፫) አንተ……ጥዕይከ……አንተ ዳንክ
፬) አንትሙ…ጥዕይክሙ..እናንተ (ሴ) ዳናችሁ
፭) አንቲ……..ጥዕይኪ….አንቺ ዳንሽ
፮) አንትን….ጥዕይክሙ…እናንተ (ወ) ዳናችሁ
፯) ውእቱ…….ጥዕየ…….እርሱ ዳነ
፰) ውእቶሙ….ጥዕዩ……እነርሱ (ወ) ዳኑ
፱) ይእቲ……..ጥዕየት……እርሷ ዳነች
፲) ውእቶን…….ጥዕያ……እነርሱ (ሴ) ዳኑ

፭. መራሒ    ግእዝ       አማርኛ
፩) አነ…….ለቃሕኩ…..እኔ አበደርኩ
፪) ንሕነ…..ለቃሕነ……እኛ አበደርን
፫) አንተ….ለቃሕከ……አንተ አበደርክ
፬) አንትሙ..ለቃሕክሙ.እናንተ (ወ) አበደራችሁ
፭) አንቲ…….ለቃሕኪ…አንቺ አበደርሽ
፮) አንትን…..ለቃሕክን…እናንተ (ወ) አበደራችሁ
፯) ውእቱ……ለቅሐ…….እርሱ አበደረ
፰) ውእቶሙ… ለቅሕኩ…እነርሱ (ወ) አበደሩ
፱) ይእቲ……ለቅሐት……እርሷ አበደረች
፲) ውእቶን…..ለቅሓ…….እነርሱ (ሴ) አበደሩ

፮. መራሒ   ግእዝ       አማርኛ
፩) አነ………ሐገጉ…….እኔ ሕግ ሠራሁ
፪) ንሕነ……ሐገግነ……እኛ ሕግ ሠራን
፫) አንተ…….ሐገገ…….አንተ ሕግ ሠራህ
፬) አንትሙ…ሐገግሙ…እናንተ (ወ) ሕግ ሠራችሁ
፭) አንቲ…….ሐገጊ……አንቺ ሕግ ሠራሽ
፮) አንትን…..ሐገግን…..እናንተ (ወ) ሕግ ሠራችሁ
፯) ውእቱ……ሐገገ…….እርሱ ሕግ ሠራ
፰) ውእቶሙ…ሐገጉ…..እነርሱ (ወ) ሕግ ሠሩ
፱) ይእቲ………ሐገገት…እርሷ ሕግ ሠራች
፲) ውእቶን…….ሐገጋ….እነርሱ (ሴ) ሕግ ሠሩ

፯. መራሒ     ግእዝ         አማርኛ
፩) አነ…….ሠመርኩ…….እኔ ወደድኩ
፪) ንሕነ…..ሠመርነ……..እኛ ወደድነ
፫) አንተ…..ሠመርከ…….አንተ ወደድክ
፬) አንትሙ..ሠመርክሙ…እናንተ (ወ) ወደዳችሁ
፭) አንቲ…..ሠመርኪ…….አንቺ ወደድሽ
፮) አንትን….ሠመርክን…..እናንተ (ወ) ወደዳችሁ
፯) ውእቱ….ሠመረ………እርሱ ወደደ
፰) ውእቶሙ..ሠምሩ…….እነርሱ (ወ) ወደዱ
፱) ይእቲ…….ሠምረት…..እርሷ ወደዱ
፲) ውእቶን…..ሠምራ…….እነርሱ (ሴ) ወደዱ

ስሞች በዐሥሩ መራሕያን ሲዘረዘሩ፤
አንደኛ አካሄድ
በሳድስ የሚጨርሱ ስሞች እንደሚከተለው ይዘረዘራሉ (ይረባሉ)። ለምሳሌ “ሀገር” የሚለውን በዐሥሩ መራሕያን ለመዘርዘር፦
፩) በአነ ጊዜ “የ” ፊደልን መጨመር ነው። ሀገርየ ይላል፤ አገሬ ማለት ነው።
፪) በንሕነ ጊዜ “ነ” ፊደልን መጨመር ነው። ሀገርነ ብሎ አገራችን ይላል።
፫) በአንተ ጊዜ “ከ” ፊደልን መጨመር ነው። ሀገርከ ብሎ አገርህ ይላል።
፬) በአንትሙ ጊዜ “ክሙ” ፊደላት መጨመር ነው። ሀገርክሙ ብሎ አገራችሁ ይላል።
፭) በአንቲ ጊዜ “ኪ” ፊደልን መጨመር ነው። ሀገርኪ ብሎ አገርሽ ይላል።
፮) በአንትን ጊዜ “ክን” ፊደላት መጨመር ነው። ሀገርክን ብሎ አገራችሁ ይላል።
፯) በውእቱ ጊዜ መድረሻ ፊደሉን ወደ ካዕብ መቀየር ነው። ሀገሩ ይላል ትርጒሙም አገሩ ማለት ነው።
፰) በውእቶሙ ጊዜ መድረሻ ፊደሉን ወደ ሳብዕ ቀይረው “ሙ” ፊደልን ይጨምራሉ። ሀገሮሙ ይላል፤ ትርጒሙ አገራቸው ማለት ነው።
፱) በይእቲ ጊዜ መድረሻ ፊደሉን ወደ ራብዕ ይቀይራል። ሀገራ ይላል። ትርጒሙም አገሯ ማለት ነው።
፲) በውእቶን ጊዜ መድረሻ ፊደላቸውን ወደ ሳብዕ ቀይሮ “ን” ፊደልን መጨመር ነው። ሀገሮን ይላል። ትርጒሙም አገራቸው ማለት ነው።
በሳድስ የሚጨርሱ ስሞች ብዙ ጊዜ የሚረቡት በዚህ ሕግ መሠረት ነው። አንድ ምሳሌ ጨምረን እንመልከት። ለምሳሌ “ማኅደር” የሚለው ስም መድረሻ ፊደሉ “ር” ሳድስ ስለሆነ ከላይ ባለው ሕግ መሠረት ይረባል ማለት ነው፡፡ ይኸውም እንደሚከተለው ነው።

መራሒ           ግእዝ               አማርኛ
፩) አነ………..ማኅደርየ……….የእኔ ቤቴ
፪) ንሕነ………ማኅደርነ……….የእኛ ቤታችን
፫) አንተ………ማኅደርከ………የአንተ ቤትህ
፬) አንትሙ…..ማኅደርክሙ……የእናንተ (ወ) ቤታችሁ
፭) አንቲ………ማኅደርኪ……..የአንቺ ቤትሽ
፮) አንትን……..ማኅደርክን…….የእናንተ (ሴ) ቤታችሁ
፯) ውእቱ………ማኅደሩ……….የእርሱ ቤቱ
፰) ውእቶሙ…..ማኅደሮሙ……የእነርሱ (ወ) ቤታቸው
፱) ይእቲ……….ማኅደራ……….የእርሷ ቤቷ
፲) ውእቶን…….ማኅደሮን………የእነርሱ (ሴ) ቤታቸው

እንግዲህ የመድረሻ ፊደላቸው ሳድስ የሆኑ ስሞች በዚህ የርባታ ሥርዓት የሚረቡ ቢሆንም አምላክ የሚለው ስም ግን ‹አነ› ሲረባ በዚህ የሰዋሰው ሕግ አይገዛም፤ አፈንጋጭ ነው፡፡ ለምሳሌ አምላክ የሚለው ስም ከላይ እንደተመለከትነው ሕግ ከሆነ ማኅደር ብሎ ማኅደርየ እንዳለው አምላክ ብሎ አምላክየ ማለት ነበረበት፤ ነገር ግን ቃሉ በርባታ ባሕሪው አፈንጋጭነት የተነሣ የሚረባው አምላኪየ ተብሎ ነው፡፡

ሁለተኛ አካሄድ
ከሳድስ ውጭ ባሉ ፊደላት የሚጨርሱ ሥሞች ደግሞ በአሥሩ መራሕያን ሲዘረዘሩ የተለየ አካሄድ አላቸው። ለምሳሌ “ደብተራ” የሚለውን ቃል ብንወስድ የመጨረሻ ፊደሉ “ራ” ከሳድስ ውጭ ስለሆነ የተለየ አረባብ አለው። ይኸውም እንደሚከተለው ነው።
፩) በአነ ጊዜ “የ” ፊደልን መጨመር ነው። ደብተራየ ይላል ድንኳኔ ማለት ነው።
፪) በንሕነ ጊዜ “ነ” ፊደልን መጨመር ነው። ደብተራነ ብሎ ድንኳናችን ይላል።
፫) በአንተ ጊዜ “ከ” ፊደልን መጨመር ነው። ደብተራከ ብሎ ድንኳንህ ይላል።
፬) በአንትሙ ጊዜ “ክሙ” ፊደላት መጨመር ነው። ደብተራክሙ ብሎ ድንኳናችሁ ይላል።
፭) በአንቲ ጊዜ “ኪ” ፊደልን መጨመር ነው። ደብተራኪ ብሎ ድንኳንሽ ይላል።
፮) በአንትን ጊዜ “ክን” ፊደልን መጨመር ነው። ደብተራክን ብሎ ድንኳናችሁ ይላል።
፯) በውእቱ ጊዜ “ሁ” ፊደልን መጨመር ነው። ደብተራሁ ይላል ትርጒሙ ድንኳኑ ማለት ነው።
፰) በውእቶሙ ጊዜ “ሆሙ” ፊደልን መጨመር ነው። ደብተራሆሙ ይላል ትርጒሙ ድንኳናቸው ማለት ነው።
፱) በይእቲ ጊዜ “ሃ” ፊደልን መጨመር ነው። ደብተራሃ ይላል። ድንኳኗ ማለት ነው።
፲) በውእቶን ጊዜ “ሆን” ፊድልን መጨመር ነው። ደብተራሆን ብሎ ድንኳናቸው ይላል።
ተጨማሪ ምሳሌ “ሥጋ” የሚለውን ሥም በዐሥሩ መራሕያን ለመዘርዘር

መራሒ              ግእዝ            አማርኛ
፩) አነ…………..ሥጋየ…………የእኔ ሥጋዬ
፪) ንሕነ…………ሥጋነ…………የእኛ ሥጋችን
፫) አንተ………..ሥጋከ…………የአንተ ሥጋህ
፬) አንትሙ…….ሥጋክሙ………የእናንተ (ወ) ሥጋችሁ
፭) አንቲ………..ሥጋኪ…………የአንቺ ሥጋሽ
፮) አንትን………ሥጋክን…………የእናንተ (ሴ) ሥጋችሁ
፯) ውእቱ……….ሥጋሁ…………የእርሱ ሥጋው
፰) ውእቶሙ……ሥጋሆሙ……..የእነርሱ (ወ) ሥጋቸው
፱) ይእቲ………..ሥጋሃ………….የእርሷ ሥጋዋ
1፲) ውእቶን……ሥጋሆን………..የእነርሱ (ሴ) ሥጋቸው

ሦስተኛ አካሄድ
ብዛትን የሚያመለክቱ ስሞች በአሥሩ መራሕያን በሚዘረዘሩበት ጊዜ መድረሻቸውን ወደ ሣልስ ቀይረው ይዘረዘራሉ። በአንቲ እና በአነ ዝርዝር ጊዜ ግን መድረሻቸውንም ሳድስ አድርገው ይዘረዘራሉ። በምሳሌ እንመልከት። አዕይንት ማለት ዓይኖች ማለት ነው። ይህ በዐሥሩ መራሕያን ሲዘረዘር ምንም እንኳ የመጨረሻ ፊደሉ ሳድስ ቢሆንም ነገር ግን ዓይኖች ሲል ብዛትን ስለሚያመለክት የተለየ አካሄድ አለው።

መራሒ            ግእዝ             አማርኛ
፩) አነ…………አዕይንትየ…….የእኔ ዓይኖቼ
፪) ንሕነ……….አዕይንቲነ…….የእኛ ዓይኖቻችን
፫) አንተ……….አዕይንቲከ……የአንተ ዓይኖችህ
፬) አንትሙ……አዕይንቲክሙ…የእናንተ (ወ) ዓይኖቻችሁ
፭) አንቲ……….አዕይንትኪ……የአንቺ ዓይኖችሽ
፮) አንትን……..አዕይንቲክን……የእናንተ (ሴ) ዓይኖቻችሁ
፯) ውእቱ……..አዕይንቲሁ…….የእርሱ ዓይኖቹ
፰) ውእቶሙ….አዕይንቲሆሙ….የእነርሱ (ወ) ዓይኖቻቸው
፱) ይእቲ………አዕይንቲሃ……..የእርሷ ዓይኖቿ
፲) ውእቶን……አዕይንቲሆን……የእነርሱ (ሴ) ዓይኖቻቸው

አስተውሉ! በአነ እና በአንቲ ጊዜ መድረሻው “ት” ሳድስ ሲሆን በሌሎች ግን “ቲ” ሣልስ ነው። ለምሳሌ መልክአ ማርያም ላይ “ሰላም ለአዕይንትኪ” ይላል እንጂ ሰላም ለአዕይንቲኪ አይልም።

አንዳንድ ስሞች ከላይ ያለውን ሕግ የማይጠብቁ ይኖራሉ። ለምሳሌ “አብ” አባት የሚለው በአሥሩ መራሕያን ሲዘረዘር አቡሁ፣ አቡሆሙ፣ አቡሃ፣ አቡሆን፣ አቡከ፣ አቡክሙ፣ አቡኪ፣ አቡክን፣ አቡየ፣ አቡነ ይላል። “እም…እናት” የሚለው ግን በመጀመሪያው አካሄድ ይሄዳል ይሄውም፦ እሙ፣ እሞሙ፣ እማ፣ እሞን፣ እምከ፣ እምክሙ፣ እምኪ፣ እምክን፣ እምየ፣ እምነ ይላል ማለት ነው።

መልመጃ
የሚከተሉትን ስሞች በዐሥሩ መራሕያን ዘርዝሩ!

፩) በካብዕ (ተክሉ) (ሰድሉ) የበግ አውራ (ሚዛን
፪) በሣልስ (አካሂ) ጥገት ላም፤ አራስ ላም)
፫) በራብዕ (ሥጋ)
፬) በኃምስ (ጽጌ)
፭. በሳብዕ (መሰንቆ)

ከታች የተጠቀሱትን አፈንጋጭ ቃላት በዐሥሩ መራሕያን ዐርቡ! (እነዚህ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ቃላት ከላይ በመጣንባቸው የርባታ ሥርዓት (የሰዋሰው ሕግ) መሠረት የሚረቡ አይደሉም፡፡ ስለሆን በጥንቃቄ ለማርባት ሞክሩ!
፩) አብ
፪) አፍ
፫) እድ

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!