‹‹ዕለት ዕለት የሚያሳስበኝ የቤተ ክርስቲያን ነገር ነው›› (፪ኛ ቆሮ.፲፩፥፳፰)

መልከአ ሰላም ቀሲሰ ደጀኔ ሽፈራው

መጋቢት ፱፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ቃል የተናገረው ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው መልእክቱ ነው፡፡ ዕለት ዕለት ጽኑ የሆኑ መከራዎች ያጋጠሙት ቢሆንም ያ ሁሉ ሳያሳስበው፣ ሳይከብደውና ሳያስጨንቀው በመዓልትም በሌሊትም ዕረፍት የሚነሣው የቤተ ክርስቲያን ነገር ነበር፡፡ የተጠራው ለቤተ ክርስቲያን እንዲያስብና እንዲያገለግል በመሆኑ ቅዱስ ጳውሎስ የደረሱበትን ችግሮች ሁሉ ገለጸላቸው፡፡ ‹‹…እጅግ ደከምኩ፤ ብዙ ጊዜ ተገረፍኩ፤ ብዙ ጊዜም ታሰርኩ፤ ብዙ ጊዜም ተዘጋጀሁ›› በማለት ደብድበውና ሞቷል ብለው እንደ ውሻ ሬሳ እግሩን አስረው እየጎተቱ ከከተማ ውጪ ጥለውት እንደነበር መሰከረ፡፡ (፪ኛ ቆሮ. ፲፩፥፳፫)

ደቀ መዛሙርቱ ዙሪያውን ከበው ሲያዝኑ እርሱ ግን ብድግ ብሎ ተነሥቶ እንደገና ለስብከት ወደ ከተማ ተመለሰ፤ እነርሱም ገረማቸው፡። ‹‹እስመ በብዙኅ ጻዕር ወጻማ ሀለወነ ከመ ንባእ ለመንግሥተ እግዚአብሔር፤ በብዙ ድካምና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባለን›› እንዲል፤ (የሐዋ.፲፬፥፳፪) ሐዋርያውም በዚህ ሳያበቃ እንዲህ በማለት ያሳለፈውን መከራ ነገራቸው፤ “አይሁድ አንዲት ስትቀር አምስት ጊዜ አርባ ግርፋት ገረፉኝ፤ ሦስት ጊዜ በበትር ደበደቡኝ፤ አንድ ጊዜ በደንጊያ ተወገርኩ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረች፤ በጥልቁ ባሕር ውስጥ ስዋኝ አድሬ፣ ስዋኝ ዋልሁ፡፡” (፪ኛ ቆሮ. ፲፩፥፳፬) ይገርማል! ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በጥልቅ ባሕር በዋና ማሳለፍ እንዴት ይቻላል? ኃይልን በሚሰጥ በክርስቶስ ሁሉን እንደሚቻል ለተናገረው ለሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ግን ተችሏል፡፡ (ፊል.፬፥፲፫)

ለቤተ ክርስቲያን ካለው ጽኑ ፍቅር የተነሣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እጅግ ብዙ ጽኑ መከራን እንደተቀበለም በመቀጠል እንዲህ ይገልጻል፤ “በመንገድም ዘወትር መከራ እቀበል ነበር፤ በወንዝም መከር ተቀበልኩ፤ ወንበዴዎችም አሠቃዩኝ፤ ዘመዶቼ አስጨነቁኝ፤ አሕዛብ መከራ አጸኑብኝ፤ በከተማ መከራ ተቀበልኩ፤ በበረኃም መከራ ተቀበልኩ፤ በባሕርም መከራ ተቀበልኩ፤ ሐሰተኞች መምህራን መከራ አጸኑብኝ፡፡ በድካምና በጥረት፥ ብዙ ጊዜም ዕንቅልፍ በማጣት በመራብና በመጠማት፥ አብዝቶሞ በመጾም፥ በብርድና በመራቆት ተቸገርኩ፤ የቀረውንም ነገር ሳልቈጥር ዕለት ዕለት የሚከብደኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሐሳብ ነው” አለ፡፡ (፪ኛ ቆሮ. ፲፩፥፳፮-፳፰)

ግርፋቱ፣ ስደቱ፣ ፈተናው፣ እስራቱ፣ መንገላታቱ አላሳሰበውም፤ ዕለት ዕለት የሚያሳስበው የቤተ ክርስቲያን ነገር ነበረ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የዋጃት ቅድስት ቤታችን ናትና እርሷን መጠበቅ እንዳለበት ያውቃል፤ ይህንን ተግባር ሲፈጽምም ሰማያዊ ዋጋን እንደሚያገኝ ያውቃልና፤ መከራን ተሰቅቆና ሸሽቶ ግን የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ መሆን አይቻልም፡፡ ክርስትና እና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እስከ ቀራንዮ ድረስ መስቀል ተሸክሞ መጓዝ ነውና፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ የነገራቸው ይህንኑ ነው፤ ኃላፊነታቸውን እንዳይዘነጉና አደራቸውን እንዲጠብቁ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመበት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ከእኔ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ነጣቂዎች ተኩላዎች እንደሚመጡ እኔ አውቃለሁ፡፡ ደቀ መዛሙርትንም ወደ እነርሱ ይመልሱ ዘንድ ጠማማ ትምህርትን የሚያስተምሩ ሰዎች ከእናንተ መካከል ይነሣሉ፡፡ ስለዚህም ትጉ፤ እኔ ሁላችሁንም ሳስተምር ሦስት ዓመት ሙሉ ሌትም ቀንም እንባዬ እንዳልተገታ አስቡ” በማለት አሳስቧቸዋል፡፡ (የሐዋ.ሥራ ፳፥፳፰-፴፩)

ዛሬስ እኛን ምን ይሆን የሚያስለቅሰን? ቅዱስ ጳውሎስ እንደዚያ ስያነባ ሲያዩ ሰዎች ባለማወቅ “ዘመድ ሞቶበት ነው የሚያለቅሰው? እንዴ ሥጋዊ ጥቅም ቀርቶበት ነው እንዴ?” ይሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እርሱን ያስለቀሰው የቤተ ክርስቲያን ነገር እያንገበገበው፣ እያሳሰበውና እየከበደው ነው፡፡ የቅዱሳንን ሕይወት ብንመለከት ቅዱሳኑ በመጋዝ የተተረተሩት፣ በሰይፍ የተመተሩት፣ በእሳት የተቃጠሉት፣ የተሰደዱትና የተንገላቱት ለቤተ ክርስቲያን ካላቸው ፍቅር የተነሣ ነው፡፡ እነ ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ የተወገሩት ለቤተ ክርስቲያን ብለው ነው፡፡ እነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተፈጭተው እስኪበተኑ ድረስ ጽኑ መከራን የተቀበሉት ለቤተ ክርስቲያን ብለው ነው፡፡

ታዲያ ሐዋርያት ቅዱሳኑ መከራ በመጣ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግሉ ምእመናን እንዳይደነብሩና አዲስ ነገር እንደመጣባቸው እንዳይቆጥሩ ይመክሯቸው ነበር፡፡ “ወዳጆቼ ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደመጣባችሁ አትደነቁ፤ ነገር ግን በጌትነቱ በተገለጠ ጊዜ ደግሞ ደስ ብሎአችሁ ሐሴት እንድታገደርጉ ክርስቶስን በመከራ ትመስሉት ዘንድ ደስ ይበላችሁ፡፡ ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር የኃይልና የክብሩ መንፈስ በእናንተ ያርፋልና” እንዲል፡፡ (፩ኛ ጴጥ.፬፥፲፪-፲፬)

ለክርስቶስ ብላችሁ ብትነቀፉ ስለ ቤተ ክርስቲያን መነቀፍ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናትና፤ ይህን ማመን አለብን፤ መሠረቷም ሆነ ጉልላቷ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ደቀ መዛሙርቱን “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሌንም ተሸክሞ ይከተለኝ” ያለንም ለዚህ ነው፡፡ (ማቴ.፲፮፥፳፬) ራሱን ያልካደ ሰው መስቀሉን ሊሸከም አይችልም፡፡ በመጀመሪያ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ነው፡፡ ፈቃደ ሥጋውን ለፈቃደ ነፍሱ ያስገዛ ሰው ጨክኖ ነፍሱን ከሥጋው የሚለይበትን፣ ጽኑ መከራ የሚቀበልበት ሕይወት ይኖረዋል፡፡ የሚሸከምበት ትከሻ ይኖረዋል፤ ይህ ደግሞ የሚያስፈራ የሚያስደነግጥ አይደለም፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸዋል፡፡ “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዟችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ፡፡” (ዮሐ.፲፮፥፴፫) ይህ ለሁላችን ተስፋ ነው፤ “እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ማለቱ “እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ፤ ሞትን ድል አድርጌዋለሁ፤ ከእንግዲህ ሞት (የነፍስ ሞት) ሊያገኛችሁ አይችልም” ተብለናልና፡፡ ይህ ኃይለ ቃል በውስጣችን መቀረጽና በአእምሮአችን መሳል አለበት፡፡ ሆኖም ግን አንዳንዶቻችን አናስተውልም፤ የተጠራነው እንድናምን፣ ስሙን እንድንጠራ፣ በስሙ እንድናስተምር እና እንድንዘምር ብቻ ይመስለናል፤ ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በስሙ መከራ እንድንቀበል ጭምር መሆኑን ልናውቅ ያስፈልጋል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ይሁን እንጂ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሯችሁ እሰማ ዘንድ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ፤ የምትነበቡ መጽሐፎች ሁኑ፡፡ በአንድም ነገር እንኳን በተቃዋሚዎች አትሸበሩ፤ ተቃዋሚዎች ቢበዙ አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፡፡ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ጸጋ ሆኖም ተሰጥቷችኋል፤ ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቷችኋልና የክርስቶስ ወገኖች በመሆናችሁ ስለ እርሱ ደግሞ መከራ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ የተጠራችሁት በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ የምትሰሙት ያው መጋደል ደርሶባችኋልና” በማለት ነግሮናል፡፡ (ፊሊ.፩፥፳፯-፴)

ይህንን ሁሉ ተሸክሞ ነው ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል የሚቻለው እንጂ “እገሌ ለምን አየኝ? እገሌ ለምን ገላመጠኝ? እገሌ ለምን ተናገረኝ? ለምን እንቅፋት መታኝ? ለምን እሾህ ወጋኝ?” እየተባለ እና ያንን እያሰቡ የሚያገለግሉበት ሕይወት አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስቀልን መሸከም ነው፤ ችግሩ መስቀልን የምንሸከምበት ትከሻ ማጣታችን ነው፤ ለቤተ ክርስቲያን የሚያስብ ሰው መስቀሉን የተሸከመ ሰው ነው፡፡ “እገሌ ለምን ለቤተ ክርስቲያን አያስብም? መስቀሉን አልተሸከመም? እገሌስ ለምን ያስባል?” ማለታችን ምንም ዋጋ አያሰጠንም፡፡ እንዲያውም ለጥፋት ይዳርገናል፡፡ ዋነው ነገር ደግሞ መስቀሉን መሸከም እና ለእግዚአብሔር ቤት ማሰብ ነው፡፡

ለቤተ ክርስቲያን ማሰብ ሲባል ለአንድ ምእመን ሕይወት፣ ለመንጋውና ለማኅበረ ምእመናንም ማሰብ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ይባላሉና፤ ለቅዱሳን ስፍራ ማሰብ፣ ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓት፣ እምነትና ትውፊት ማሰብ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ማሰብ ልበ አምላክ ዳዊት በብሉይ ኪዳን ዘመን ለእግዚአብሔር ቤት እንዳሰበው ዓይነት ነው፤ እርሱ ባማረና በተዋበ ቤት ውስጥ ተቀምጦ ታቦተ ጽዮን ግን በአሮጌ ድንኳን መቀመጧ አሳስቦት እንዲህ አለ፤ “ለእግዚአብሔር እንደ ማለ፥ ለያዕቆብም አምላክ እንደ ተሳለ፡- ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፥ ወደ መኝታዬም አልጋ አልወጣም፥ ለዐይኖቼም መኝታን፥ ለቅድንቦቼም እንቅልፍን፥ ለጉንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም፡፡ (መዝ.፻፴፩፥፩-፬)

ለእግዚአብሔር ቤት የሚያስብ ልብ ያለው ሰው ነቢዩ ዳዊትን እና ቅዱስ ጳውሎስን ይመስላል፡፡ ከነቢዩ ናታን ጋር ተያይዘው ሱባኤ ቢገቡ ለንጉሥ ዳዊት የሥጋዌ ነገር ተገለጠለት፤ ለነቢዩ ለናታን ደግሞ የቤተ መቅደሱ ነገር ተገልጦለታል፤ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ምሥጢር የሚገልጽ አምላክ ነውና፡፡

ልበ አምላክ ንጉሥ ዳዊት የኢየሩሳሌምን ሰላም ይፈልግ ነበረ፡፡ ኢየሩሳሌም ሰላም እንድትሆን፣ ሕዝቦቿ በሰላም እንዲወጡና በሰላም እንዲገቡ ይፈልግ ነበር፡፡ በመዝሙሩም እንዲህ ብሏል፤ “ስለ አምላካችን፣ ስለ እግዚአብሔር ቤት ለአንቺ መልካምነትሽን ፈለግሁ፡፡” (መዝ.፻፳፪፥፱) “መልካምነትሽን” ያላት ኢየሩሳሌምን ነው፡፡ የአምልኮቱ ሥርዓት እንዳይተጓጎል፣ ምስጋናው፣ መዝሙሩ እንዳይተጓጎል፣ “ስላንቺ ብዬ ሰላምሽን ፈለግሁ” ብሎ ተናግሯል፡፡

ዛሬም በእኛ ሕይወት የሚያሳስበን ምንድን ነው? ዕረፍት የነሳን ምንድን ነው? ሌሊት እንቅልፍ የከለከለን ምንድን ነው? የምንሮጠው ለምንድን ነው? እኛን የሚያሳስበን የብርና የወርቅ ነገር ነው፡፡ ብዙ ብር ለማከማቸት፣ ብዙ ወርቅ ለማግኘት እንመኛለን፤ እናስባለን፡፡ ግን እኮ ብር ገዛን! ዛሬ ወርቅ አሸነፈን እኮ! ብርና ወርቅ ሃይማኖታችንን አስጣለን ወገን! ብርና ወርቅ ለቤተ ክርስቲያን እንዳናስብ አደረገን፡፡ ብርና ወርቅ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳንመለከት፣ ሕይወታችንን ለእግዚአብሔር እንዳንሰጥ አደረገን፤ ምንድን ነው የሚሻለን? የመረጥነው ብርና ወርቅ ከጥፋት ያድነን ይሆን? ሕይወት ይሆነን ይሆን? መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ዋጋ ይሆነን ይሆን? የእግዚአብሔር ቃል ግን እንዲህ ይላል፤ “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧል፤ እጅግም ፈጥኗል፤ ኃያሉም በዚያ በመራራ ለቅሶ ይጮሃል፤ ያ ቀን የመዓት፣ የመከራና የጭንቀት ቀን ነው፤ የመፍረስና የመጥፋት ቀን ነው፤ የመከራና የጭጋግ ቀን ነው፤ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው፤ በተመሸጉ ከተሞችና በረዘሙ ግንቦች ላይ የመለከት እና የሰልፍ ጩኸት ቀን ነው፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርተዋልና እንደ እውር እስኪ ሄዱ ድረስ ሰዎቹን ያስጨንቃቸዋል፤ ደማቸው እንደ ትቢያ ሥጋቸው እንደጉድፍ ይፈሳል፤ ከእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፡፡ እርሱም በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ይጨርሳቸዋል፤ ምድር ሁሉ በጥፋት እሳት ትበላለች፡፡” (ሶፎ.፩፥፲፬-፲፰)

ስለዚህም የእግዚአብሔር ቃል ነው የሚሻለን? ወይስ ሌላ? እንምረጥ! ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ የነበረው ንጉሥ ግን “ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል” አለ፡፡ (መዝ.፻፲፰፥፸፪) ዓለም ዛሬ “ብር ይሻለኛል፤ ወርቅ ይሻለኛል” ብላለች፡፡ እኛን የሚያሳስበን እና የሚከብደን ታዲያ ምንድን ነው? የቤተ ክርስቲያን ነገር አይደለም፤ ስለ ምንበላው መብልና ስለ ምንጠጣው መጠጥ እንዲሁም ስለ ምንለብሰው ልብስ ነው እንጂ። ሆዳችን ገዛን፤ ሥጋችን አሸነፈን፤ ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን ማስገዛት አቃተን፤ እንዴት አድርገን ነው ታዲያ ለቤተ ክርስቲያን የምናስበው?

ነገር ግን ከፍጥረታት ተማሩ ተብለናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቃል የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ ብሎናል፡፡ (ማቴ.፮፥፳፭) ለምን ስለ መብልና ስለ መጠጥ ትጨነቃላችሁ? ለልብስስ ለምን ትጨነቃላችሁ? ከእነዚህ ተማሩ” በማለት አስተማረን። ታላቁ ፍጡር የሰው ልጅ ግን ከወፎች መማር ተሣነው፤ ከሜዳ አበቦች መማር ተሣነው፤ ጌታችን መጨረሻ ላይ የተናገረው ነገር አለ፡፡ “እናንተ እምነት የጎደላችሁ እናንተንማ እንዴት እንግዲህ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንደሚያስፈልጋችሁ የሰማይ አባታችሁ ያውቃልና፤ ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ሁሉ ፈልጉ፤ ይህ ሁሉ ይጨመርላችኋል፡፡” (ማቴ.፮፥፴-፴፫)

መንግሥቱንና ጽድቁን ያስቀደመ ሰው ለቤተ ክርስቲያን ማሰብ ይችላል፤ እኛን የሚያሳስበን ግን ስለምንኖርበት ቤት ነው፡፡ ሁላችንም የምናስበው “አሁን እንደው ገንዘብ ባገኝ፣ ሎተሪ ቢወጣልኝ፣ ጥሩ ቪላ ቤት እሠራ ነበር” እያልን ነው፡፡ ለምድራዊ መኖሪያው የሚያስብ ሰው ስለ ሰማያዊ መኖሪያው እንዴት ሊያስብ ይችላል? ሰማያዊ መኖሪያውን የሚያገኝበትን ሥራስ እንዴት ሊሠራ ይችላል? ይህ እኮ ነው ትልቁ ችግር፤ “እንዲያው ገንዘብ ባገኝ፣ እንዲያው ሀብታም ብሆን” የምንል ሰዎች የምንጨነቀው ሥጋዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት ነው፡፡

ሆኖም ግን ልበ አምላክ ዳዊት ምን እንዳለው “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ቤተ ሠሪዎች በከንቱ ይደክማሉ፡፡” (መዝ.፻፳፯፥፩) ያማረ ቤት ሠርተው ሳይገቡበት የተሰደዱ፣ የሞቱ፣ የታሰሩ ሰዎች ግን አሉ፡፡ ይህን ሁሉ ብናስብ ኖሮ ለእኛ ትምህርት ነበር፡፡

በትዳር ዓለም ያለን ሰዎች የምናስበው ትዳራችንን ሞቅ ሞቅ የምናደርግበትን ነገር፣ ጥሩ ጥሩ ለመብላት፣ ጥሩ ጥሩ ለመጠጣት እና ጥሩ ጥሩ ለመልበስ ነው፤ አስተሳሰባችን ከአንድ ጠባብ ጎጆ ጣራ በታች ሆኖ ይቀራል፡፡ ይህ የሥጋዊ ሐሳብ በአእምሮአችን ከተጋረደብን እንዴት አድርገን ነው ቤተ ክርስቲያንን የምንመለከተው? እንዴት አድርገን ነው ለቤተ ክርስቲያን የምናስበው? ወደ ትዳር ዓለም ያልገባን ሰዎች ደግሞ “ማንን ላግባ? ማን ትሻላለች? ደሞዝ አላት? መልኳ ጥሩ ነው?” እያልን የማስፈልግ ሐሳብ እናስባለን፡፡ የራሳችን መስፈርት አውጥተን በማያስፈልግ ሐሳብ እንጨነቃለን፤ እንዲህ ከሆነ መንግሥቱንና ጽድቁን ማስቀደም አልቻልንም ማለት ነው፡፡

ጌታችን እንዲህ ብሏል፤ “ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና፤ እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ፡።” (ሉቃ. ፳፬፥፴፪)

እኔን እና እናንተን የሚያሳስበን ሌላው ነገር ደግሞ ሠራተኞች ስንሆን የደሞዝ ነገር ነው፡፡ ብዙዎች ለደሞዛቸው ሲሉ እውነትን አይናገሩም፤ “ይህቺን ደሞዜን ባጣትስ” ብለን ሐሰት ልንናገር ወይም በውሸት መሐላ ልንፈጽም እንችላለን፡፡ ብዙዎቻችን የምናስበው ደሞዛችን የሚያድግበትን መንገድ ነው፡፡ መቶ ሺህ ብርም ቢከፈለው የሰው ልጅ ፍላጎት አይሟላም፤ የሚያሳዝነው እኮ ይህ ነው፡፡

እስራኤል ዘሥጋን እግዚአብሔር ከምርኮ በመመለስ ከባርነት ቀንበር ነፃ ባወጣቸው ጊዜ የኢየሩሳሌምና የይሁዳ ከተሞች ጠፍተው ነበር፤ የእግዚአብሔርም ቤት ፈርሶ ሙጃ በቅሎበት ነበር፤ ሆኖም ሁሉም ለራሳቸው ያማረ ቤት ሠሩ፤ ገበሬው ሩጫው ሁሉ ወደ እርሻው፣ ሠራተኛው ወደ ሥራውና ወደ ደመወዙ እንጂ ሙጃ የበቀለበትንና የፈረሰውን የእግዚአብሔርን ቤት ዞር ብሎ የሚያይ እና የሚያስብ ጠፋ፡፡ ወገኖቼ! ስለ እግዚአብሔር ቤት የማናስብ ከሆነ የምናገኘው ሁሉ አይባረክም፡፡

አምላካችን እግዚአብሔርም እስራኤል ዘሥጋን በነቢዩ ቃል ተናገራቸው፤ “በውኑ የእግዚአብሔር ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን? አሁንም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ፤ ብዙ ዘራችሁ ጥቂትም አገባችሁ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ ነገር ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ ነገር ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ፡፡” (ሐጌ.፩፥፬-፮) ለእግዚአብሔር ቤት የማያስቡ ሰዎች ብዙ ዘርተው የሚሰበስቡት ግን ጥቂት ነው፤ ለእግዚአብሔር ቤት የሚያስቡ ግን ጥቂት ዘርተው ብዙ ይሰበስባሉ፡፡ ልዩነቱን ተመልከቱ! በቀዳዳ ከረጢት የተቀመጠ ነገር ተንጠባጥቦ መቼ እንዳለቀ አይታወቅም፡፡

ዛሬም እኛ ለደመወዛችን ብለን እግዚአብሔርን እንረሳለን፤ ለደመ ወዛችን ብለን የእግዚአብሔርን ቤት (ቤተ ክርስቲያን) እንረሳለን፤ ግን የተቀበልነው ደሞዝ መቼ እንደሚያልቅ አናውቀውም፡፡ ብዙዎቻችን “እንዴ ደሞዝ ከተቀበልኩ እኮ ፲፭ ቀን አይሞላኝም፡፡ የት ደረሰ?” እንላለን፡፡ ለምን ከተባለ በቀዳዳ ከረጢት የተቀመጠ ስለሆነ ወይም ባልተስተካከለ ሕይወት ስለተቀበልነው ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የማናስብ ከሆነ እንዲህ ከሥራችንና ከአገልግሎታችን የምናገኘው ገንዘብ አይበረክትልንም፡፡ ሁላችንም ለቤተ ክርስቲያን የምናስብ ከሆነ ደሞዛችንን እግዚአብሔር ይባርከዋል፡፡

እኛን የሚያሳስበን ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ አንድ የችግር ጊዜ ሲመጣ “ይህን የችግር ሰዓት እንዴት እናሳልፈዋለን? ወይም ይህች ደሞዜ ከወር አታደርሰኝም” ወይም “ይህን የችግር ዘመን እንዴት አሳልፈዋለሁ?” የሚለው ጉዳይ ያስጨንቀናል፡፡ ይህ ነው ሐሳብ የሆነብን ነገር ግን ደግሞ የሰራፕታዋን ሴት እናስታውሳት ዘንድ ይገባል፡፡ “በማድጋ ካለው ከእፍኝ ዱቄት፥ በማሰሮም ካለው ከጥቂት ዘይት በቀር እንጀራ የለኝም፤ ገብቼ ለእኔና ለልጄ እጋግረው ዘንድ በልተነውም እንሞት ዘንድ ጥቂት እንጨት እሰበስባለሁ” በማለት አሰበች፡፡ (፩ኛ.ነገ. ፲፯፥፲፪)

ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት በነቢዩ በኤልያስ አማላጅነት ያቺ ትንሽ ዱቄት እና ጭላጭ ዘይት ተባርካ የረኃቡ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ አላለቀችም። (፩ኛ.ነገ. ፲፯፥፲፪-፲፬) ለእኛም በጎ ሰዎች ከሆንን እግዚአብሔር ያለንን ትንሽ ነገር እንኳን ብትሆን ይባርክልናል፤ የሕይወታችን ዘመን የፈቀደልን እስኪፈጸም ድረስ የእግዚአብሔር በረከት አይለየንም፤ ይህን ልናምን ያስፈልጋል፡፡

አንዳንዶቻችን ደግሞ የልጆቻችን ነገር ያሳስበን ይሆናል፡፡ “ልጆቼን በምን አሳድጋለሁ?” በማለት ልንጨነቅም እንችላለን፡፡ ሆኖም በዚህ ጊዜ ወደ ሕይወታችን ልንመለስና ድካማችንን ልንመለከተው ይገባል፡፡ ልጆች የእግዚአብሔር ጸጋዎች ናቸው፤ በእኛ ጥበብ የተገኙ አይደሉም፤ ግን “በምን እናሳድጋቸዋለን? ምን እናበላቸዋለን? ምን እናጠጣቸዋለን? ምን እናለብሳቸዋለን? ለትምህርት ቤት ምን እንከፍልላቸዋለን?” እያልን ከልክ በላይ መጨነቅም ተገቢ አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ለመፍታት ብለንም “አራርቀን ብንወልድ፣ እንዲህ ብንጠቀም” እያልን የራሳችንን ነገር እናስቀምጣለን፡፡

በመጽሐፈ ነገሥት ካልእ የተጻፈ አንድ ታሪክ እናንሣ፤ “ከነቢያትም ወገን ሚስቶች አንዲት ሴት “ባሌ ባሪያህ ሞቶአል፤ ባሪያህም እግዚአብሔርን ይፈራ እንደ ነበረ አንተ ታውቃለህ፤ ባለ ዕዳ ልጆቼን ባሪያዎች አድርጎ ሊወስዳቸው መጥቶአል ብላ ወደ ኤልሳዕ ጮኸች። ኤልሳዕም አደርግልሽ ዘንድ ምን ትሻለሽ? በቤትሽ ያለውን ንገሪኝ አላት። እርስዋም፦ ለእኔ ለባሪያህ ከዘይት ማሰሮ በቀር በቤቴ አንዳች የለኝም አለች። እርሱም፦ ሄደሽ ከጐረቤቶችሽ ሁሉ ከሜዳ ባዶ ማድጋዎችን ተዋሺ አታሳንሻቸውም አላት፡፡ ገብተሽም ከአንቺና ከልጆችሽ በኋላ በሩን ዝጊ፥ ወደ እነዚህም ማድጋዎች ሁሉ ዘይቱን ገልብጪ፤ የሞላውንም ፈቀቅ አድርጊ አለ። እንዲሁም ከእርሱ ሄዳ በሩን ከእርስዋና ከልጆችዋ በኋላ ዘጋች፤ እነርሱም ማድጋዎቹን ወደ እርስዋ ያመጡ ነበር፤ እርስዋም ትገለብጥ ነበር። ማድጋዎቹም በሞሉ ጊዜ ልጅዋን፦ ደግሞም ማድጋ አምጣልኝ አለችው፡፡ እርሱም፦ ሌላ ማድጋ የለም አላት፤ ዘይቱም ቆመ። መጥታም ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው፡፡ እርሱም፦ ሄደሽ ዘይቱን ሽጪ፤ ለባለ ዕዳውም ክፈዪ፤ አንቺና ልጆችሽም ከተረፈው ተመገቡ አለ።” እርሷም አልተጠራጠረችም፡፡ (፪ኛ.ነገ.፬፥፩-፯) እኛ ብንሆን እንዴት ሊሆን ይችላል? ሸክላ ቢሰብሩት ይሰበራል፤ ቢያደቁት ይደቃል፤ አይደለ የምንለው?

ቅዱስ ጳውሎስ “ለፍጥረታዊው ሰው የእግዚአብሔር ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ አይረዳውም” ነው ያለው፡፡” (፩ኛ ቆሮ. ፪፥፲፬) ያቺ ሴት “ይሆንልኛል፤ ይደረግልኛል” ብላ አመነች፤ ሆነላት፤ ተደረገላት፤ ብዙ ማሰሮ ዘይት አገኘች፡፡ ከዚያ በኋላ አልቸኮለችም፤ በሯን ዘግታ ወደ ነቢዩ ኤልሳ በመሄድ “ምን ላድርግ” አለች፡፡ እግዚአብሔር በረከት ሲሰጠን ሥጋዊ ፍላጎታችንን ከምንከተል “እግዚአብሔር ሆይ ምን ላድርግበት?” ብለን ፈቃዱን ብንጠይቅ እርሱ የፈቀደውን ሥራ ለመሥራት እንችላለን፡፡

ነቢዩም “በይ ሽጪና ግማሹን ዕዳሽን ክፈይ፤ ግማሹን ልጆችሽን አሳድጊበት” አላት፡፡ ተመልከቱ! ይህች መበለት ልጆቿን የምታሳድግበት በነቢዩ በኤልሳዕ አማካኝነት አገኘች፡፡ እኛም በእግዚአብሔር ቸርነት በድንግል ማርያም እና በቅዱሳኑ አማላጅነት የሚያስፈልገንን ነገር ልናገኝ እንችላለንና ለማያስጨንቀው የሥጋ ነገር ማሰብ ትተን ዘለዓለማዊ ሕይወትን ስለምታስተገኝልን ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዕለት ዕለት ልንጨነቅ ይገባል፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያን የምናስብ ሰዎች ያድርገን፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፤ አሜን!!!