‹‹ነገን ዛሬ እንሥራ!››

ክፍል ሁለት

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

መጋቢት ፲፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? ባለፈው ሳምንት ‹‹ነገን ዛሬ እንሥራ›› በሚል ርእስ ባቀረብንላችሁ ጽሑፍ ቤተ ክርስቲያን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዴት እየተላለፈች ወደ እኛ  እንደደረሰችና እኛም እንዴት ከአባቶቻችንና እናቶቻችን እንደተረከብናት በጥቂቱ የዳሰስንበትን ክፍል አድርሰናችኋል፡፡ በዚህ በክፍል ሁለት ደግሞ ከክፍል አንድ የቀጠለውንና “ቤተ ክርስቲያንን እኛስ እንዴት ለቀጣዩ ትውልድ እናስተላልፋት?፡ የሚለውን ክፍል ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ መልካም ንባብ!

ቤተ ክርስቲያንን እንዴት እናስተላልፋት?

ቤተ ክርስቲያን እንዲሁ አልጋ አልጋ በሆነ ሁኔታ ወደ እኛ እንዳልደረሰች በክፍል አንድ አይተናል፡፡ ራሳቸውን የካዱና ሁለንተናዊ ሕይወታቸውን ለቤተ ክርስቲያን ክብር አሳልፈው የሰጡ አባቶች ለዚህ ትውልድ በቅብብሎሽ ያደረሷትን ቤተ ክርስቲያን  እኛ የዛሬዎቹ ትውልዶችስ እንዴት ለማስተላለፍ ለማውረስ አስበናል? አባቶቻችን ካወረሱን አጉድለን ወይስ አትርፈን ነው የምናስተላልፋት? ክብረ ክህነትን አጎድለን ነው፤ ወይስ አሙልተን? ክብረ ምንኩስናንስ? የምእመናንስ ቁጥር ጨመርን ወይስ ቀነስን? ዶግማ ቀኖናዋንስ ሸራረፍን ወይስ ጠብቀን ዘለቅን? መታፈርና መከበሯንስ ጨመርንላት? ወይስ አጎደልነባት?

በርካታ ልንመልሳቸው የሚከብዱብን ጥያቄዎች፣ ልናስተካክላቸው የሚገቡ ብልሽቶች፣ ልንሞላቸው የሚገቡ ጎደሎዎች እንዲሁም ልንጠግናቸው የሚገቡ ስብራቶች አሉብን፡፡ በብዙ መልኩ ከተቀበልነው አጉድለናል፣ ለክብሯ የሞቱላትን ቤተ ክርስቲያን ተረክበንና ለክብራችን ስንል ዝቅ እንድትል ምክንያት ሁነናል፡፡ ለጥቅሟ ሲሉ በታሰሩላት አባቶችና እናቶች ቦታ ተቀምጠን ለጥቅማችን ስንል ልእልናዋን አስደፍረናል፤ እንድናገለግላት ተመርጠን አገልግይን ብለናታል፤ ወይም ተገልጋይ ሆነንባታል፤ የተሰበሰቡትን እየበተንን፣ የተከበሩትን እያቃለልንና የታፈሩትን እያስደፈርን ቤተ ክርስቲያኗን ሸክሟን በማቅለል ፋንታ ሸክም ሆነንባታል፡፡

ዶግማዋ እየተሸራረፈ፣ ቀኖናዋ እየተጣሰ፣ መታፈር መከበሯ ቀርቶ የውስጥም የውጭም ጠላት በዝቶባት፣ የዜና ማሟሟቂያ የውሬ ማድመቂያ፣ የልጆቿ ማሸማቀቂያ፣ የጠላቶቿ መሳለቂያ የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለልጆቻችን እናወርሳለን? ወይስ በቀደመ ገናንነቷና ክብሯ  እናሸጋግራተለን? የሚለው ለነገ የማይባል የቤት ሥራችን ነው፡፡

አሁን ላይ የቤተ ክርስቲያኗ ተግዳሮት በጣም ዘርፈ ብዙ መሆኑ ለማንም የተደበቀ አይደለም፡፡ ከምንም በላይ ተሰሚነቷን፣ ተከባሪነቷን፣ ሉዓላዊነቷን መመለስ የታፈረችና የተከበረች ማድረግ፣ አጥር እንደ ሌለው ቤት ማንም አልፎ ሄያጅ፣ ዘው ብሎ የሚገባባትና የፈለገውን የሚፈጽምባት፣ ቤተ ክርስቲያን ለልጆቻችን ላለማውረስና የትውልድ ባለዕዳ ላለመሆን አብዝተን መትጋት አለብን፡፡ በኦሪት ዘጸአት ላይ ያለውን ታሪክ እናስታውስ፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ በግብጽ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፤ ከአስገባሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቃለሁ››  (ዘጸ. ፫፥፯)

በዘመናችን ክርስቲያኖች ካስገባሪዎቻቸው የተነሣ መከራቸው በዝቷል፡፡ ደማቸውን በከንቱ የሚያፈሱ፣ ሀብት ንብረታቸውን የሚዘርፉባቸው፣ መድረሻ እንዲያጡ በሜዳ ተበትነው እረኛ እንደሌላቸው በጎች እንዲቅበዘበዙ የተደረገበት  ወቅት መሆኑንና  በጥቅሉ ቤተ ክርስቲያን በስደት ላይ ያለችበት መሆኑን ማንም አይዘነጋውም፡፡

ከገዥዎቻቸውና ከአስገባሪዎቻቸው የሚታደግ፣ ባሕርን ከፍሎና ደመና ጋርዶ የሚያሻግር፣ ነጻ ሆኖ ነጻ የሚያወጣ ሙሴ መሆን ከቤተ ክርስቲያን አባቶችና አገልጋዮች አሁን ይጠበቃል፡፡ ያለበዚያ አደራውን መብላት ነው፡፡ ክፉ ገዥዎች ሕዝቡን ሊለቁት ይገባል፤ ብዙዎቹን በዘረኝነት፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በልዩ ልዩ ሁኔታ፣ ግማሾቹን በኃይል ተብትበው ይዘዋቸዋል፡፡ ያገለግሉት ዘንድ ደግሞ እግዚአብሔር ይፈልጋቸዋልና፤ ሙሴን ሆኖ መገኘት በፈርኦን ፊት በድፍረት ቆሞ ያገለግሉት ዘንድ እግዚአብሔር ይፈልጋቸዋልና ሕዝቡን ልቀቅ፡ ብሎ መናገር እውነተኛ ሙሴ መሆን አሁን ያስፈልጋል፡፡ (ዘጸ.፭፥፩) ምክንያቱም በደሙ የዋጃት ቤተ ክርስቲያን በደሙ የዋጃቸው ምእመናን ናቸውና፡፡

ቤተ ክርስቲያን ስደቷ እንዲቆም፣ መከራዋ ዳርቻ እንዲኖረው፣ የሀገር ባለውለታነቷ ተዘንግቶ እየደረሰባት ላለው መከራና ስደት ማብቂያና መቋጫ እንዲኖረው፣ አንድነቷን የሚፈታተኗት ኃይሎች አደብ እንዲገዙ፣ እንደ ወርቅ የነጻው፣ እንደ ዕንቁ የሚያበራው ዶግማዋና ቀኖናዋ ለነገው ትውልድ ተጠብቆ ይተላለፍ ዘንድ ከምንም በላይ የተሰሚነትና ቅቡልነት ደረጃዋን ለማሳደግ ብዙ ሥራዎች መሥራት ይገባናል፡፡

የነገዋ ቤተ ክርስቲያን በክብረ ክህነት፣ በክብረ ምንኩስና፣ በምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት፣ በመልካም አስተዳደር ረገድ፣ በሀብትና ንብረት አስተዳደርና በሰው ኃይል ስምሪት፣ በጋብቻ ሕይወትና በሕፃናት አስተዳደግ እንዲሁም በወጣቶች ሕይወት፣ በወንጌል አገልግሎትና በዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ በመንፈሳዊና በቁሳዊ ልማት ረገድ፣ ማኅበራዊ ተሳትፎዋ የጎላ፣ ተጽእኖ ፈጣሪነቷ ታላቅ እንደ ጥንቱ እንዲሆን፣ ተነጋግረው  ብቻ ሳይሆን በዐይን ጥቅሻ የሚግባቡ አባቶች፣ አገልጋዮች እንዲሁም ምእመናን እንዲኖሯት ከፍተኛ ሥራ መሥራት ከዚህ ትውልድ ይጠበቃል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ከእነ ክብሯ ለልጆቻችን ለማስተላለፍ አዲስ ነገር መፍጠር የሚጠበቅብን አይደለም፡፡

ትናንትን ለመመለስ፣ የአባቶቻችንን መንገድ ብቻ መፈተሽ፣ የጥንካሬያቸው ምክንያት ምን እንደነበር መረዳት፣ ቤተ ክርስቲያንን ገናና ያደረጓት፣ ታፍረው ተከብረው ያስከበሯት፣ “ምን ቢያደርጉ፣ እንዴት ቢሠሩ፣ ምን ዓይነት ሰብእናን ቢላበሱ ነው” ብሎ መጠየቅ፣ መልሱንም ከታሪካቸው ከገድላቸው መረዳት ብቻ በቂ ነው፡፡ በእኛ እምነት ቤተ ክርስቲያንን ያተለቃት፣ ያገዘፋት፣ የታፈረች የተከበረች ያደረጋት፣ በጨለማው ዓለም ውስጥ የምትበራ ድንቅ ፋኖስ ያደረጋት ዋና ነገሮች አልጫውን የሚያጣፍጥ፣ ጨለማውን የሚያበራ ድንቅ የሆነ የቅድስና ሕይወት ያላቸው አባቶችና እናቶች የነበሩ መሆኑ ነው፡፡

እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ብርሃን የነበሩ አባቶቻችን ደግሞ ክብራቸውና ቅድስናቸው  ከክብረ ክህነትና ክብረ ምንኩስና የሚመነጭ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዘመናችን የተፈተነችውና ከቀደመ ልዕልናዋ ዝቅ ያለችው ክብረ ክህነትና ክብረ ምንኩስና በገጠመው ተግዳሮት ነው ብሎ መናገር ድፍረት አይሆንም፡፡ የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ከፍ ያለች እንድትሆን፣ የቀደመ ተወዳጅነቷን፣  ተሰሚነቷን፣ ተከባሪነቷንና ተገዳዳሪነቷን ለመመለስ ብዙ ሥራዎችን መሥራት የሚጠበቅብን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ከሁሉም ሥራዎች የሚቀድሙ፣ ለሁሉም ሥራዎች መሠረትና መሥሪያ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው ብለን የምናምንባቸው ነገሮች ክብረ ክህነትና ክብረ ምንኩስና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የቤት ሥራዎቻችን መሆን ሲችሉ ነው፡፡

እነዚህ ሁለት ዐበይት ጉዳዮች ትናንት ለነበረችው፣ ቤተ ክርስቲያን የቅድስና፣ የክብር፣ የልዕልና፣ የመታፈር የመከበር ምንጭ ምክንያት እንደነበሩ፣ እንዚህ ሁለት የቤተ ክርስቲያን ቁልፍ ጉዳዮች ተግዳሮት ሲገጥማቸው ቤተ ክርስቲያን ተግዳሮት እንደገጠማት ፈተና  ውስጥ መግባቷን መረዳት አይከብድም፡፡ ስለሆነም ከዛሬዋ ከፍ ያለች፣ ቤተ ክርስቲያን ነገ እንድትኖረን ሐዋርያዊ የሆነው የክህነት ቅብብሎሽና የምድር መላእክት የሰማይ ሰዎች ያስባለው ምንኩስና ወደ ክብሩ ወደ ታሪኩ ሊመለስ ግድ ይላል፡፡

ውድ አንባብያን! የክብረ ክህነትንና  ምንኩስናን ምንነትና ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን እንዴት መተላለፍ እንዳለበት በቀጣይ ክፍሎች ይዘን እንቀርባለን፤ ቸር እንሰንብት!