ቅድስት፡ የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት

ያቆን ደረሰ ተሾመ

መጋቢት ፮፤፳፻፲፮ ዓ.ም

የቅድስና ባለቤት የሆነው እርሱ እግዚአብሔር አምላክ ነው። እቀደስ አይል ቅዱስ፣ እባረክ አይል ቡሩክ ነው። በእርሱ የባሕርይ ቅድስና እኛን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ቡሩክ ሆኖ ባረከን፣ ቅዱስ ሆኖ ቀደሰን፣ሕያው ሆኖ ሕያዋን አደረገን። የጸጋ ቅድስናንም ከእርሱ አገኘን። ቅድስናው የተለየ፣ የከበረ፣ የሚመሰገን፣ የሚሰጥ/የሚያድል፣ የሚያነጻ፣ የሚባርክ እናም የሚያስተሰርይ ስለሆነ እንከን፣ ጉድለት የሌለበት ምሉዕ ነው። ለባለሟሎቹ ቢሰጠው የማይጎድል፣ ተከፍሎ የሌለበት ቅድስና ሆኖ እኛም የቅድስና በጸጋ ተካፋይ ሆነናል።

የተሰጠንን ቅድስና ገንዘብ እንድናደርግ እና እንድንጠቀምበት ደግሞ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምጽዋትና በሌሎች በጎ ምግባራት መትጋት ይገባናል። ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ›› እንዲል፡፡ (ዘፍ.፪፥፫፣ ዘሌ.፲፱፥፪) የት መሄድ እንዳለብንም በግልጽ ልበ አምላክ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ ስለ ትምህርትህና ስለ እውነትህ ስምህን አመሰግናለሁ፤ በሁሉ ላይ ቅዱስ ስምህን ከፍ ከፍ አድርገሃልና›› ይላል። (መዝ.፻፴፯÷፪) የተቀደሰን መሥዋዕት በተቀደሰ ቦታ እንፈጽማለን። መቼ ቢሉ፣ በሰንበት፣ በበዓላት በማኅበረ ዐቢይ/ክርስቲያኖች በሚሰበሰቡበት፣ ስመ እግዚአብሔር በሚጠራበት፣ ታቦት  ባለበት፣ እግረ እግዚአብሔር በቆመበት ቅዱስ ስሙን ከፍ ከፍ በማድረግ ቅድስናን ገንዘብ እናደርጋለን።

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ለዐቢይ ጾም ሁለተኛው እሑድ በአዘጋጀው ምስጋና አማካኝነት ዕለቱ ‹‹ቅድስት›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ትርጉሙም ‹‹የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች›› ማለት ነው።  (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ገጽ ፯፻፹፬) ቅድስት የሚለው ቃል ዕለቱ ‹‹ቅድስት›› ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት ስለ ዕለተ ሰንበት እንዲሁም ስለ እግዚአብሔር አምላክ ፍጹም ቅድስና የሚያወሳ በመሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ፍጥረታቱ የእርሱን ስም በማመስገን ይኖሩ ዘንድ ለቅድስና ሕይወት ፈጥሯቸዋልና በሰንበት እሑድ ክርስቲያኖች የቅድስና ተግባራትን ከሌላው ቀን አብዝተው ይፈጽማሉ፡፡ ዕለት ከተግባር፣ ስም ከክብር የተባበረባት ክብርት ሰንበት ቅድስት ስለሆነች ቅዱስ ያሬድ “ቅድስት” ብሎ ጠራት። ይኸውም የምትቀድስ፣ ከብራ የምታከብረን፣ አክብረናት የምንከብርባት በመሆኗ ነው።

ለዚህም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓ “ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ፤ ሀቡ ስብሐተ ለስሙ፤ አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ፤ ዝግቡ ለክሙ መዝገበ ዘበሰማያት ኀበ ፃፄ ኢያማስኖ ወኢይረክቦ ሰራቂ፤ ድልዋኒክሙ ንበሩ ዘበላዕሉ ጸልዩ ኀበ ሀሎ ክርስቶስ” ትርጉም፦ “ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ሥራውንም ለአሕዛብ ንገሯቸው፤ ለስሙም ምስጋናን አቅርቡ ሰንበትን አክብሩ፤ እውነትንም አድርጉ፤ ብል የማያበላሸው ሌባም የማያገኘው በሰማያት ያለ መዝገብን ለእናንተ ሰብስቡ፤ ተዘጋጅታችሁም ተቀመጡ፤ ክርስቶስ ወዳለበት ወደ ላይ አስቡ፡፡“  ስለዚህ ሰው ሰንበትን አክብሮ ጾሞ ጸልዮ፣ ቅድስናን ጠብቆ መኖር እንዲችል እግዚአብሔር የፍቅሩ መገለጫ የሆኑ ትእዛዛቱ ይነግሩናል።

ቅዱስ ያሬድም ወቅቱንቅድስትብሎ ሲሰይም፦

፩. የአርባ ቀን ጾም መጀመሪያ በመሆኑ፦ ዕለቱ ከዐቢይ ጾም ቀናት ውስጥ አርባው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም መጀመሪያ ስለሆነች፣

፪. ቅድስት ሰንበት ላይ በመዋሉ፣ እንግዲህ “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” ተብሏል፡፡ (ዘፀ.፳፥፰) የሰንበትን ቀን አስቀድሞ የቀደሰ የባረከ ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና፡፡” (ዘፍ.፪፥፫)

“ከምእመናን ወገን አንድስ እንኳን በእሑድ ቀን ለገንዘብ መትጋት፣ ገንዘቤን አምጣ ብሎ መጣላት እና ዋስ መያዝ አይገባውም። ሁሉም ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን በንጽሕና በትሕትና ሆነው። ዳኛ ግብሬን፣ አበዳሪ ብድሬን፣ ኤጲስ ቆጶስ ዐሥራት በኵራት፣ ነጋ ድራስ ቀረጥ አምጡ ይሉናል ብለው ሳይፈሩ ይምጡ።

፫. ወቅቱ ወርኃ ጾም በመሆኑ፦ ምእመናን ይህንን ወቅት በጾም፣ በጸሎት፣ በእንባ፣ በስግደት፣ በአርምሞ፣ በመልካም ሥራ ቅድስናን የምናገኝበት፣ ጊዜው ሰው ወደ እግዚአብሔር አብዝቶ የሚተጋበት ወቅት በመሆኑ፣ ለእግዚአብሔር የሚገባ ነገር ለማድረግ የነገር ሁሉ መጀመሪያ፣ ለመልካም ነገር መነሻው በቅድስና በንጹሕ ልቡና መቅረብ ስለሆነ ቅድስት ብሏታል።  “እስመ ጾም እማ ለጸሎት ወእኅታ ለአርምሞ ወነቅዓ ለአንብዕ መቅድመ ኩሉ ግብር ሠናይት፤ ጾም ማለት የጸሎት እናት፣ የትሕትና እኅት፣ የእንባ ምንጭ፣የመልካም ሥራ ሁሉ መጀመሪያ ናት” እንዳለው ቅዱስ ያሬድ። ”ጾምን ቀድሱ፤ ጉባኤውንም ዐውጁ” የተባልን የተሰጠንን የጸጋ ቅድስና በእጃችን ላይ መኖሩን አመላካች ቃል ነው። (ኢዩ.፩፥፲፬)

፬. የወንጌል ዛዝ በመሆኑ ዕለቱን ተጠቅሞ ዓለምን አስተምሮበታል። “ዛቲ ዕለት እንተ ገብረ እግዚአብሔር ንትፈሣሕ ወንትሐሠይ ባቲ”  ትርጉም፡- “ይህች ዕለት እግዚአብሔር የሠራት ቀን  ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን።” (መዝ.፻፲፯፥፳፬) ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ ሰንበት የጌታ ቀን ስለመሆኗ እንዲህ ይላል፤ “በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፡፡” (ራእ. ፩፥፲)

ሊቃውንቱ በፍትሐ ነገሥት “ተጋብኡ ኵሎ ዕለት ኀበ ቤተ ክርስቲያን ወፈድፋደሰ በዕለተ ሰንበት ወበበዓላት ወበዕለተ ትንሣኤ ዘውእቱ ዕለተ እሑድ” ትርጉም፦ “ሁልጊዜ በቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ፤ ይልቁንም በዕለተ እሑድ፣ በዕለተ ቀዳሚት፣ በጌታ በዓላት ወደ ቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ” በማለት አዘውናል፡፡ (ፍትሐ ነገሥት፣ ገጽ ፪፶፬)

በትጋት ጾመን፣ ጸልየን ርስቱን እንድንወርስ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ፤ የቅዱሳን በረከት ይጠብቀን።

የዕለቱ መዝሙር (ከጾመ ድጓ)፦ግነዩ ለእግዚአብሔር

ምንባባት፡ (፩.ተሰ.፬÷፩-፲፫)፣ (፩ጴጥ.፩÷፲፫-ፍጻ.፣ሐዋ.፲÷፲፯-፴

ምስባክ “እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ:: አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ፣ ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ፈጠረ፡፡ እምነትና በጎነት በፊቱ፣ ቅድስናና የክብር ገናናነት በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡” (መዝ.፺፭÷፭)

ወንጌል (ማቴ.፮÷፲፮-፳፭)

ቅዳሴ: ዘኤጲፋንዮስ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!