‹‹ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊትም ጾመ›› (ማቴ.፬፥፪)

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለከበረው ጤንነታችሁ እንዴት አላችሁ? የመንፈቀ ዓመቱ ትምህርት ተጠናቆ ፈተና ተፈትናችሁ ጥሩ ውጤት እንዳመጣችሁ ተስፋችን ነው፤ በርቱ!

ልጆች! በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ውጤታችሁ ዝቅ ያለ ተማሪዎች በቀጣዩ በደንብ አጥንታችሁ ጥሩ ውጤት እንደምታመጡ እንጠብቃለን፤ የወደፊት ምኞታችሁ እንዲሳካ ጎበዝ ተማሪዎች መሆን ይጠብቅባችኋል፤ ትመህርቱን እንዲገልጥላችሁና ማስተዋል ጥበብን እንዲሰጣቸሁ ደግሞ እግዚአብሔረን በጸሎት ልትጠይቊ ይገባል፤ መልካም!!!

ልጆች! ለዛሬ የምንማረው ስለ ዐቢይ ጾም ነው፤ ዐቢይ ማለት ታላቅ ማለት ነው፤ አባቶቻችን በሠሩልን ሥርዓት መሠረት ከሰባት ዓመት በላይ የሆኑ ክርስቲያኖች ሁሉ እንዲጾማቸው የታወጁ ሰባት አጽዋማት አሉ፤ ከእነዚህ መካከል ደግሞ አንዱ ዐቢይ ጾም ነው::

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ይህን ጾም ጾሞ እንድንጾም ሥርዓቱን የሠራልን ጌታችን ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ በገዳመ ቆሮንቶስ ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ጹሞ እኛም መጾም እንዳለብን አስተማረን፤ ጌታችን የጾመው በመብል ምክንያት ከገነት የወጣውን አዳም ለመመለስ እና ጾማችንን በጾሙ ሊባርክልን ነው፡፡

ጌታችን ከገዳመ ቆሮንጦስ ጹሞ ሲያበቃ ሰይጣን በሦስት ዓይነት ፈተና ቀረበው፡፡ የመጀመሪያው ፈተና ስስት ነው፤ ዲያብሎስ ድንጋዩን ወደ ዳቦነት እንዲለውጥ በማሳሳት ፈተነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለሰይጣን መታዛዝ እንደማይገባ ሲያስተምረን በትዕግሥት ‹‹ሰው በእግዚአብሔር ቃል ጭምር እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም›› በማለት አሸነፈው፡፡ ሁለኛው ፈተናው ትዕቢት ነው፤ ከመቅደስ ጫፍ ወስዶ ዘሎ እንዲወርድለት ‹‹..ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሱሃል›› የሚለውን በመጥቀስ ነገረው፡፡ (መዝ ፺÷፲፪ (ይሁንና ጌታችንም በጥቅስ የመጣውን ሰይጣን (አሰናካዩን) በጥቀስ አፋን አስያዘው፤ ‹‹ጌታ አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ተጽፎል›› አለው፡፡ (ዘፍ.፬÷፮)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እኛም ሁሌ ለሚጠይቁን ሁሉ መልስ ለመስጠት የምንችል መሆን እንዳለብን ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ አስተምሮናናል፡፡ እንደገናም ጌታችን ተራራ ላይ ወጣ፤ ሰይጣንም የዓለምን ግዛት ከነክብሩ በማሳየት ‹‹ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሀለሁ›› ብሎ ሦስተኛውን ፈተና አቀረበ፡፡ ንጉሥ በመንግሥቱ ለመጡበት ቀናዒ ነውና አምላካችንም ለአምልኮቱ ቀናተኛ ስለሆነ ‹‹ሂድ አንተ ሰይጣን፤ ለጌታህ ለአምላክ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምላክ ተብሏል››በማለት በፍቅረ-ንዋይ የመጣበትን ፈተና ገንዘብን በመጥላት አሸንፎታል፡፡ሰይጣንም እንደ ትቢያ በኖ ጠፍቷል፡፡ (፩ኛጴጥ. ፫÷፲፩፣ዘዳ.፯÷፲፫)
ልጆች! ከላይ ባሉት ሦስት ፈተናዎች ጌታችን ሲፈተን ለእኛ አርአያ ለመሆን ነው፡፡ ስስትን በትግሥት፣ ትዕቢትን በትሕትና፣ ፍቅረ ነዋይ (ገንዘብን) በመጥላት ዲያቢሎስን ማሸነፍ እንደምንችል ለሁላችን አስተምሮናል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ይህ ጾም የተለያዩ ስያሜዎች አሉት፤ ጠላታችን ሰይጣን ድል የተደረገበት ጾም ስለሆነ የድል ጾም ይባላል፤ ስለእኛ ብሎ ጌታችን ስለጾመው ደግሞ የካሣ ጾም ይባላል፡፡ እንግዲህ እኛም ይህንን ጾም እንደ አቅማችን ልንጾም ይገባናል ልጆች በጾም ወቅት ደግሞ ክፉ ነገር ማድረግ፣ ከሰዎች ጋር መጣላት፣ ሰዎችን የሚያሳዝን ነገሮች ማድረግ የለብንም፤ መልካም!!!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በዐቢይ ጾም ያሉ ሳምንታት የራሳቸው የሆነ ስያሜ አላቸው፤ ጾሙን ስንጾም ጌታችን ያደረጋቸውን ተአምራት፣ ያስተማራቸውን ትምህርት እያሰብን እንድንጾም በማለት አባታችን ቅዱስ ያሬድ ለእያንዳንዱ ሳምንት ስያሜ ሰጥቷቸዋል፡፡ የተወሰኑትን እንመለከት በዐቢይ ጾም ውስጥ ከመጀመሪያው እሑድ አንስቶ እስከ በዓለ ትንሣኤ ድረስ ዘጠኝ ሳምንታት አሉ፤ ለዛሬ እስከ እኩለ ጾም ያሉትን እንመልከት፡፡

፩ኛ.ዘወረደ፡- የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል፤ በዚህ ሳምንት ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማያት መውረዱን፣ ከአመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን እና እኛን ማዳኑን የሚያወሱ ምስጋናዎች ይቀርባሉ፤ ትምህርቶች ይሰጣሉ፤ በዚህም ውለታውን እያሰብን ሳምንቱን እናሳልፋለን፡፡

፪ኛ.ቅድስት፡- ሁለተኛው ሳምንት ደግሞ ቅድስት ይባላል፤ በዚህ ሳምንት ደግሞ አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ እኛም እንደ ሕጉ ከተጓዝን የባሕርይ ቅድስናውን በጸጋ እንደሚሰጠን፣ ስለሰንበት ቅድስና ይነገርበታል፤ይታወስበታል፤ እኛም ከኃጢኃት ርቀን በቅድስና ሕይወት መኖር እንደሚገባን እንማርበታልን፡፡

፫ኛ.ምኩራብ፡-ሦስተኛው ሳምንት ምኩራብ ይባላል፤ በዚህ ወቅት ደግሞ ጌታችን በምኩራብ (የጸሎት ቤት) ማስተማሩንና ቃሉን በቤተ እግዚአብሔር እየመጣን መማር እንዳለብን ቤተ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ተግባራትን የምንፈጽምባት ቅድስት ሥፍራ እንደሆነች የምንማርበት ሳምንት ነው፡፡ ጌታችን ከቤተ መቅደስ ገብቶ የማይገባ ሥራን በቤተመቅደስ ይሠሩ የነበሩትን የገሠጸበት፣ ቤተ መቅደስ የጸሎት ቤት መሆኗን ያስተማረበት መታሰቢያ ነው፡፡ (ማቴ. ፳፩፥፲፪-፲፫)

፬ኛ.መፃጉዕ:- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደተጻፈው ፴፰ (ሠላሳ ስምንት) ዓመት በአልጋ ላይ የታመመውን በሽተኛ መፈወሱን እንዲሁም ሕሙማን እንደፈወሰ፣ ሙታንን እንዳስነሣ የሚዘከርበት፣ ተአምራቱ፣ ቸርነቱ ምሕረቱ የሚነገርበት ሳምንት ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ ለዛሬ በዚህ አበቃን፤ ቀሪዎቹን የሳምንታት ስያሜ በቀጣይን እንማማራለን፡፡

ይቆየን!