‹‹ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ተሻገረች››(ቅዱስ ያሬድ)

ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ቅድስት ድንግል ማርያም በምድር ላይ ለ፷፬  ዓመት በሕይወተ ሥጋ ከኖረች በኋላ ቅዱስ ያሬድ እንደተናገረው በጥር ፳፩ ቀን ከሚያልፈው ዓለም ወደ ማያልፈው ዓለም ተሻግራለች፡፡ «ፈለሰት እምዘይበሊ ኀበ ኢይበሊ፤ ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም፣ (ከምድር ሕይወት ወደ ሰማያዊ ሕይወት) ተሻገረች» እንዲል፤  (ዚቅ ዘቅዱስ ያሬድ ነሐሴ ፲፮)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን ድል እንዳደረገ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም የልጇ መለኮታዊ ኃይል ሞትን አሸንፋ እንድትነሣ አደረጋት፡፡ ነቢዩ ዳዊት ስለ እመቤታችን ትንሣኤ እንዲህ ሲል ተናግሯል፤ ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦት…›› የታቦት መቅደስ የተባለችውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤ እርሷ ከፍጡራን ሁሉ ከፍ ከፍ ያለችና ከተለዩ የተለየች፣ ከተመረጡ የተመረጠች፣ ንጽሕተ ንጹሓን፣ ቅድስተ ቅዱሳን በመሆኗ የአምላክ ማደሪያ ለመሆን በቅታለች፡፡  እርሷም ‹‹ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬ፣ በመድኃኒቴ ሐሤትን ታደርጋለች›› በማለት ተናግራለች፡፡ (መዝ. ፻፴፩፥፰፣ሉቃ.፩፥፵፯)

ቅዱሳን ሐዋርያትም እመቤታችንን በአጎበር አድርገው ወደጌቴሴማኒ ይዘዋት በሚሄዱበት ጊዜ አይሁድ በምቀኝነት ተነሡባት፤ ሥጋዋን ለማቃጠልም ተማከሩ፤ በዚያን ጊዜም ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ከሐዋርያት እጅ ለመንጠቅ ዘሎ በመሄድ የአልጋውን ሸንኮር ሲይዝ የእግዚአብሔር መልአክ በረቂቅ ሰይፉ እጆቹን ቆረጠው፤ እጆቹም በአልጋው ሸንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ አዛኝቷ ድንግል ማርያም ግን የምሕረት አማላጅ ናትና ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን እጆቹን ይመልስለት ዘንድ በጸሎቱ እንዲማጸንለት ነግራው እንደነበረ መልሶለታል፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱሳን መላእክት ክቡር ሥጋዋን በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት፤ ከጥር ፳፩ እስከ ነሐሴ ዐሥራ ስድስት ቀን ለሁለት መቶ አምስት ቀናት ቆይታለች፡፡ ነገር ግን ሥጋዋ ያለበትን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ቢመለከትም ሌሎቹ ሐዋርያት ባለማየታቸው እመቤታችን ድንግል ማርያም ባረፈች በ፮ኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን እስከ ፲፬ ቀን ድረስ ከጾሙ በኋላ በ፲፬ኛው ቀን ሥጋዋን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀብለው በጌቴሴማኒ በሚገኘው መቃብር ቀብረዋታል፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያምም እንደ ተወደደ ልጇ  በ፫ኛው ቀን ተነሥታ መላእክት አጅበው እየዘመሩላት ወደ ሰማያት ስታርግ ሐዋርያው ቶማስ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ዕርገቷን በማየቱ መላእክት «እመቤትህ እርሷ ናት፤ ስገድላት» አሉት፤ እርሱም «ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ ይላል፤ ከደመናው ሊወድቅ ወደደ፤» ይህም ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፣ ዛሬ ደግሞ የእርሷን ትንሣኤ ሳላይ ቀርቼ ነበር በማለት ነው፡፡ እመቤታችንም «ትንሣኤየን ያየህ አንተ ነህ፤ ሌሎቹ አላዩም» ብላ ሐዋርያት ገንዘው የቀበሩበትን የሐር ግምጃ ሰጠችው፡፡

ኢየሩሳሌም በደረስ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያትን ስለ እመቤታችን ጠየቃቸው፤ እነርሱም  እንደቀበሯት ነገሩት፤ እርሱም ያየውን ምሥጢር በልቡ ይዞ «ሞት በጥር፤ በነሐሴ መቃብር፤ ለሰሚውም አያምር፤ ይህ እንዴት ይሆናል?» ቢላቸው ቅዱስ ጴጥሮስ «ድሮም አንተ ተጠራጣሪ ነህ፤ ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ እንዲሉ፤ ገንዘን የቀበረን እኛ እያለን እንዴት ትጠራጠራለህ» ብለው ሊያሳዩት ወደ መቃብሯ ሄደው መቃብሯን ቢከፍቱት ባዶ ሆኖ አገኙት፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም ተደናግጠው ተያዩ፤ ቅዱስ ቶማስ ግን እንዲህ አላቸው፤ «አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሣች፤ ዐረገች፤ ይኸው ምልክቱ» ብሎ ገንዘው የቀበሩበትን ሰበን አሳያቸው፤ እነርሱም አምነው ሰበኗን ለበረከት ተካፈሉት፡፡

ከአንድ ዓመት በኋላም ሐዋርያት በመንፈሳዊ ቅናት ተነሣስተው «ቶማስ ትንሣኤዋን አይቶ እኛ ሳናይ እንዴት ይቀርብናል» በማለት ከነሐሴ ፩ ቀን ሱባኤ ጀምሩ፡፡ ጌታም የሐዋርያትን ጾማቸውን፣ ጸሎታቸውን ሱባኤያቸውን በ፲፮ኛው ቀን እመቤታችንን መንበር ጴጥሮስን ተራዳኢ፣ ካህን እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ አቅርቧቸዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን  ጾመ ፍልሰታ ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ይጾማል፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም የሰዎች ሁሉ እናት ተስፋና መከታ ናት፤ አምላካችን እግዚአብሔር ፍጥረቱን ያድን ዘንድ ቃል ኪዳን ሰጥቷታልና እኛ ሰዎች በጸሎትና በጾም ተግተን ምሕረትን ከተወደደው ልጇ ታሰጠን ዘንድ እንማጸናት፡፡ በኃጢአታችን የተነሣ በመቅሠፍት እያለቅን እንዲሁም እርስ በርስ መስማማት አቅቶን በየፍክለ ሀገራቱ እንደ ጠላት በጦርነት እየተፋጀን በመሆኑ ችግር መከራ በእኛ ላይ በዝቶ በሰላምና በጤና መኖር ስላቃተን አብዝተን ልንጸልይ ልንጾም ይገባል፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም የምሕረት አማላጅ በመሆኗ በሠራነው ኃጢአትና በደል ከልብ ተጸጽተን ይቅርታን እንድናገኝ የእርሷ አማላጅነትና ተራዳኢነት ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም ያለ እርሷ ዓለም መዳን አይችልምና፡፡

የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ነሐሴ፣ ፲፮ ቀን፣ ገጽ ፮፻፺፭‐፮፻፺፰