‹‹በማስተዋል ዘምሩ›› (መዝ.፵፮፥፯)

ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ልበ አምላክ መዝሙረኛው ነቢዩ ዳዊት እግዚአብሔር አምላኩን ዘወትር እንደሚያመሰግን ‹‹ስለ እውነት ፍርድህ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ‹‹ ብሎ እንደተናረ መዝሙራተ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን ለማመስገንና እንዲሁም ለመማጸን የሚጠቅሙን መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ መዝሙር ማለት ‹‹ምስጋና፣ ውዳሴ፣ ጸሎት›› ማለት እንደሆነ በመጽሐፈ ስዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት በተባለ መጽሐፋቸው ያስረዳሉ፡፡  (መዝ. ፻፲፰፥፻፷፬፣ገጽ ፬፻፳፬)

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ሕዝበ ክርስቲያን ላለፉት አንድ ሺህ አምስት መቶ ዓመታት  ያህል ለእግዚአብሔር  ምስጋና  ያቀርቡ የነበረው በቅዱስ ያሬድ ዜማ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በመላእክት ዓለም የተማራቸው ግእዝ፣ ዕዝል እና አራራይ የተባሉት ዜማዎች የሥላሴን አንድነት የሚያመለክት ናቸውና::ግእዝ በአብ ሲመሰል‹‹ርቱዕ ሎቱ ነአኩቶ›› ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን ማለት ነው፤ ዕዝል ወልድ ጽኑዕ መከራ ተቀብሎ አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ ነው፡፡  አራራይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ፤ የሚያራራ ጥዑም ዜማ ማለት ሲሆን ጥዑም ሀብተ መንፈስ ቅዱስን እንደ ተጎናጸፍን ለማስረዳት ነው። የቅዱስ ያሬድ የዜማዎቹ ባሕርያት የፊደል ቅርጽ የሌላቸውና ምሳሌነት ያላቸው ፰ ዐበይት ምልክቶች  አሉት። የእነዚህም ምልክቶች ምሳሌያቸውና ምሥጢራቸው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ስለኛ የተቀበለውን መከራ መንገላታት የሚያስታውሱ ናቸው። አምላካችን እግዚአብሔርን እንድናመሰግንበት  ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጠብቃ ያቆየችልን  የቅዱስ ያሬድ ዜማ ሥርዓት፣ ባህልና  የመሣሪያዎቹ  ትርጉም  ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ መልእክት ያለው ነው፡፡ (ጾመ ድጓ)

በመሆኑም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መዝሙራት በየጊዜው የተነሡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አባቶች ለመዝሙር ይገለገሉበት የነበረውን የዜማ የቅዱስ ያሬድ ዜማን ስልት መከተል አለባቸው፡፡ ምክያንቱም አንድ መዝሙር ኦርቶዶክሳዊ የሚያሰኘው የመዝሙሩ መልእክት፣ የዜማ ስልቱ፣ የዜማው መሳሪያ እንዲሁም ዝማሬውን የምናቀርብበት ሥርዓቱን ጠብቆ መንፈሳዊነትን ተላብሶ የተገኘ ሲሆን ነው:: ከላይ እንደተገለጸውም መንፈሳዊ ይዘት ያለው ዝማሬ ሥርዓት ባለው አቋቋምና ሽብሻቦ፣ በከበሮ፣ በመሰንቆ፣ በእንዚራ፣ በዋሽንት እንዲሁም በበገና ታጅቦ ሲቀርብ ደምቆና አሸብርቆ በተመስጦ እንድናመሰገን ይረዳናል፡፡

ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምንሰማቸው አንዳንድ የኦርቶዶክሳዊ መዝሙራት  ይዘታቸውን እየለወጡ በመሄዳቸው አንዳንዶቹ እንዲያውም ወደ ዘፈንና ወደ መናፍቃን ዝማሬ ተቀይረው የጠላት ማሳቻ መንገድ እየሆኑ መምጣቸውን ሳንገነዘብ አልቀረንም፡፡ ነቢዩ ዳዊትም ‹‹በማስተዋል ዘምሩ›› ሲል በመዝሙሩ እንደተናገረው ኦርቶዶክሳዊ መዝሙራትን መለየትና በተለይም አምላካችንን የምናመሰግንበት፣ አጽዋማትና ክብረ በዓላትን የምንዘክርበት እንዲሁም በችግርና መከራ ጊዜ የምንማጸንበት የንስሓ መዝሙራትን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ (መዝ.፵፮፥፯)

በዘመናት የወጡ መዝሙራት በተለያዩ ተጽእኖዎች የተነሣ ኦርቶዶክሳዊ ይዘታቸውን ለመልቀቃቸው  በቀደምት የሚነሡ ችግሮች በርካታ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-

ከዘፈን የተወሰዱ ዜማዎች

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚወጡ መዝሙሮች በያሬዳዊ የዜማ ስልት የሊቃውንቱን ማኅሌታዊ ዜማ ትተው፣ ዘማርያኑ በዓለማዊው ዘፈንና በመንፈሳዊው ዜማ መካከል መረገጫ ያጣ ዜማ  በምስልና በድምፅ እያቀረቡልን ነው፤ ነገር ግን ይህ ምእመናን ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ ቀላል ነው፡፡  ለምሳሌ፡-

  • ‹‹ሐና ዘመዴ ዘመዴ …›› የሚለው መዝሙር ከ ‹‹እንዲያው የምሩ›› የሚለውን ሕዝባዊ ዘፈን ጋር መመሳሰል፤
  • ‹‹እመኑ በሱ ድንቅ ያደርገል ጌታ …›› የሚለው ‹‹በላይ በላይ›› ከሚለውን ዘፈን ጋር መመሳሰል፤
  • ‹‹እመቤቴ ማርያም እመቤቴ ሆይ›› የሚለው መዝሙር የሙሉቀን መለሠ ‹‹ተከልከይ ባዋጅን›› ከሚለው ጋር መሰሳሰሉ አብዛኛው ክፍል ከሕዝባውያን ዘፈኖች ውስጥ እየተቀነጫጨቡና መጠነኛ ቅርጽ ለውጥ እየተደረገባቸው እንደሚሠሩ ለመረዳት ይቻላል፡፡
  • በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ማርያም ድንግል ንጽሕት›› የሚለው መዝሙር ዜማው በቀጥታ ከዘፋኝ አረገኸኝ ወራሽ ካሴት ላይ ‹‹ተኝቼ አየሁሽ እቴ ዓለሜ›› ከሚለው የተወሰደ ነው፡፡
  • ‹‹በሰማይ ጉባኤ ይወደሳል ስሙ›› የሚለውና ‹‹ተዋሕዶ መመከያዬ፣ የዘላለም ቤቴ›› የሚሉት መዝሙሮች በቀጥታ የተወሰዱት ከአሰፋአባተ የማትበላ ወፍ ውስጡ ‹‹ሆ በል ገበሬው (አራሹ ገበሬው)›› ከሚለው ዘፈን ነው፡፡

ከፕሮቴስታንት የተወሰዱ መዝሙሮች

በአሁኑ ጊዜ ግጥማቸውና ዜማቸው ከፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች መዝሙራት የተወሰዱ መሆናቸውን ተገንዝበን ይሆናል፡፡ አሁን ሳይቀር መናፍቃን ቤት የገቡና ከነርሱ ለእኛው በስጦታ እየተበራከቱልን ያሉ እንደሆነ እነርሱ ራሳቸው‹‹አሁን ገና የሚመቹ መዝሙሮች አወጣችሁ!››ሲሉንም አድምጠናል፡፡ በየጉባኤውም በየክብረ በዓላት ላይ መስማት የተዘወተረው ‹‹አለን በእግዚአብሔር ፍቅር አለን…››የሚል ይህ ለእኛ ይገባል? ደጋግመን የምንለው፣ ጥላችን ከመልእክታቸው አይደለም/ አንዳንዶቹ የመልእክትም ችግር እንዳለባቸው ሳንዘነጋ አባቶች ሊቃውንት ሳይነግሩንም ሆነ የዓለማዊ ዜማ ደራስያን ሳይጠቁሙን የዜማዎቹ ዓለም መመሳሰል በቀላሉ ማወቅ አያዳግተንም፡

በተሐድሶ የማንሸራተት ተግባር

የተሐድሶ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ባጭር ጊዜ ውስጥ በመለወጥ፣ ሕዝቡ በቁጥጥራቸው ሥር ሆኖ፣ በኢትዮጵያዊ ባሕል ፈንታ የምዕራባውያን ባህል ተስፋፍቶ፣ ያሬዳዊ ሳይሆን ምዕራባያዊ ዝማሬ እየተዘመረ ሌላ ዓለም እንዲፈጠር አድርገውታል፡፡

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመሆን ነጠላ ሳይለብስ ማገልገል፣ የኦርቶዶክሳውያን የአነጋገር ቃና /ላሕይ/፣ የመዝሙር ሥርዓት፣ ትምህርተ ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት የሚል ሐሳብ በማንሣትና የመናፍቃንን መዝሙር ሕዝቡ እንዲሰማው ማድረጋቸው ችግሩ እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡

የመመሪያ አለመኖር

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንደ ጥንታዊነቷና ሐዋርያዊነቷ መጠን በዚህ ዙሪያ ዘመኑን የዋጀ ሕግ አውጥታ እርሱን ብትተገብር ችግሩን እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ይቻል ነበር፡፡ አሁን ያሉት መዘምራንም ሙሉ በሙሉ ሊፈረድባቸው የማይገባው ይህ ባለመኖሩ ምክንያት ነው፡፡ ‹‹ሕዝቡ ይቀበለዋል፣ ጥሩ ነው በሚሉትና አቅማቸው በፈቀደው መጠን የሚሄዱት ለዚህ ነው፡፡››

በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ተቋማዊ ሥርዓት አለመኖሩ ለችግሩ መንሥኤ ሆኖአል፡፡ ይህ ባለመዘጋጀቱ በፕሮቴስታንቱ የምናየው አንገት መድፋት፣ ዓይን መጨፈን ‹‹እያየን ነው›› ‹‹አንገት መድፋት፣ ዓይን መጨፈን›› የሚል ሕግ የለም፤ ቀድሞ በማእከል ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ይቀርብ የነበረው የመዝሙር አገልግሎት በ፲፱፸፫ ዓ.ም በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በወጣው ደንብ መሠረት ቁጥጥሩ ለአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ዝግጅት ለሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላት በመስጠቱ ምክንያት በመዝሙር ዙሪያ የሚከሠቱትን ችግሮች በአንድነት አጥንቶ የሚያስተካክል ክፍል አልተገኘም፡፡ ስለዚህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበና አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የደረሰውን በመዝሙራት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያስችል ዘንድ እንደቀድሞው የመዝሙር ዝግጅትን በማእከላዊነት የሚመራ አካል በቤተ ክህነት በኩል መመሪያ አለመዘጋጀት ነው፡:

የባህል ተጽእኖ

ከእኛ ባህል ውጭ በሆነ ባህል መማረክን ከጀመርን ከርመናል፡፡ የምንጠላው የፕሮቴስታንት የመዝሙር ባህል፣ የምንሸሸው ዘፈንና ጠባዩ በአጠቃላይ ሌላው የባህል ተጽእኖው በእኛ ላይ የሚያመጧቸው ተጽእኖዎች መኖራቸውን ልንሸሽገው የምንችለው ነገር አይደለም፡፡

አሁን አሁን ‹‹እገሌ ጉባኤያችንን ያቀዘቅዝብናል፤ ሞቅ የሚያደርገው እገሌ ነው፤ ልዝዝ አትበይ…›› የሚሉ ቃላት ይደመጣሉ፤ ከዚህም የተነሣ የሰውነት እንቅስቃሴያችንም ዝላይን እስከ ማካተት ደርሷል፡፡ በእውነት ለመናገር ዝላይ በዘፈን እንኳ አልፎ አልፎ የማይታይ ክስተት ብቻ ነበር፤ ይህን የመሰሉ ሌሎች ብዙ የባህል ተጽእኖዎች አሉ፡፡

የተዛባ አመለካከት

በሰዎች ዘንድ ስለ መዝሙራት ብዙ የተዛቡ አመለካከቶች አሉ፡፡ ከእነርሱም መካከል ‹‹መዝሙር አምልኮ ነው ወይንም ‹‹መዝሙር አምልኮ ሳይሆን የአምልኮ መገለጫ ነው›› የሚሉ ናቸው፡፡ አምልኮ ሕያዊት ነፍስ ያለው ሁሉ መላእክትን ጨምሮ ፈጣሪና ሁሉን ቻይ ለሆነው አምላክ ብቻ የሚቀርብ አገልግሎት ነው፡፡ አምልኮ ስግደትንና ውዳሴን /ቅዳሴን/፣ ማኅሌትን፣ መሥዋዕትን፣ መገዛት፣ ጾምን፣ ጸሎትን ያጠቃልላል፡፡ እውነተኛ አምልኮ እግዚአብሔር የሚፈልገውን እና የሚወደውን ማድረግ ነው፡፡ አምልኮ ሲቀርብ በመገዛት፣ በትሕትና፣ በየዋህነትና በተረጋጋ መንፈስ መሆን አለበት፡፡

ከዚህም ሌላ የማኅበረሰቡ መዝሙርን የማዘመን ፍላጎት የፈጠረው የተዛባ አመለካከት ነው፡፡ ይህም ዓለማዊነት በዝማሬዎቹ ላይ እንዲንጸባረቁ አድርገዋል፡፡  ታዲያ መዝሙራችን እንዲህ ዓይነት ተጽእኖ እየፈጠረ ነው ወይስ እየተፈጠረበት? መጤን ያለበት ነገር ይህ ነው፤ ምዕራባዊያኑ አስበው አዲስ የሠሩትን ነገር ‹‹ዘመናዊ››  እያሉ መጀመሪያ ዜጋቸውን ከዚያም ቀሪውን ዓለም ያግባቡታል፤ በዚህም ውጤታማ ሆነዋል፡፡ ለመዝሙራችን ፈተና ውስጥ መግባት አንዱ ምክንያት ግን ይህን የመሰሉ አስተሳሰቦችን በበቂ ሁኔታ ሳይረዱ በሌሎቹ ወጥመድ ውስጥ ዘው ብሎ የመግባት ችግር ነው፡፡

ለቤተ ክርስቲያን ትምህርት ባይተዋር መሆን

በርካታ ዘማርያን በጋራ የሚያነሡት ችግር በቤተ ክርስቲያን የድምጽ መቅረጫ ክፍል ያለመኖር ሲሆን ይህም ሲባል ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለውን መመልከት ይቻላል፡፡ የመዝሙር ግጥም ስናዘጋጅ ግጥሙን የሚያርም የሚያስተካክል አካል፣ ከግጥሙ በኋላ ዜማ ሠርቶ የሚያቀርብ፣ ከዜማው በኋላ በውስጡ የሚካተቱት የማስታወቂያ፣ የፊልም ቅንብር፣ ማሳተሚያ ወዘተ የመሳሰሉት የተመቻቹ ሁኔታዎች አለመኖራቸው የምስል ወድምጽ መዝሙራት ላይ ችግሩ ሊፈጠር ሆኖአል፡፡ ምክንያቱም የሚሠሩት በሚያውቁት እየሆነ በመምጣቱ ነው፡፡

ዘማርያን ወደ መዝሙር የገቡበት ሁኔታ ጥናት ቢጠይቅም ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ወስነው ነው፤ ለዚያም የሚገባውን ተምረው፣ በዚህ ላይ ጸጋቸውን አውቀው ነው ለማለት ግን አይቻልም፡፡ ለመዝሙርና ለዘማርያንም በዚህ አገልግሎት ያበቃ ዘንድ የተዘጋጀ ትምህርት በእኛ ሀገር እስካሁን የለም፤ ስለዚህ ተምሮ የሚዘምር የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ የቤት ክርስቲያኒቱን ዜማ በደንብ የተማሩትና ትምህርተ ሃይማኖትንም ጠንቅቀው የሚያውቁ አንዳንዶች እንኳ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ዕውቀታቸው ረድቷቸው ጥሩ መዝሙር አቀረቡልን እንጂ መዝሙርን የተመለከተ ትምህርት እስከምናውቀው ድረስ የለም፡፡

የማዕከላዊ አሠራር አለመኖር

ቤተ ክርስቲያኗ የመዋቅራዊ አሠራር ጀማሪና አስተማሪ የመሆኗን ያህል እስከ አሁንም ድረስ ያሏት አሠራር ማዕከላዊነትን ያልጠበቁ መሆናቸው በተለይም አገልግሎቱን ለማስተዳደር ከሥርዎች፣ ከመርሆዎችና መመሪያዎች ይልቅ በአገልጋዮች በጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፤ ስለዚህም ማዕከላዊ አሠራር ለማጠናከርና አገልግሎቱን ከልማዳዊ አሠራር ለማላቀቅ አልተቻለም፡፡

መዝሙራት ወደግላዊነት እያደሉ ለመምጣታቸው

በአሁኑ ጊዜ እየወጡ ያሉ መዝሙሮች አንድ ጠባይ ይታይባቸዋል፡፡ ይህም ግጥማቸው ‹‹ለእኔ፣ እኔ…›› የሚሉ ስሜቶችን የያዙ መሆናቸው ነው፡፡

ለእግዚአብሔርም ሆነ ለቅዱሳን በምናቀርበው ላይ የወል የሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱን የዶግማ አገላለጽ የሚያሳይ ትውፊት ነበር፡፡ ‹‹እኔ፣ ለእኔ…›› የሚሉ አገላለጾች አንዳንድ ጊዜ በመልክእ ድርሰቶች ላይ ቢገለጹም መጠንና ወሰን አላቸው፡፡ የአሁኖቹ አብዛኛዎቹ መዝሙሮች አሁን የሚገልጹበት ደረጃ ብዙ ችግር ባይኖረውም ዕድገቱንና ፍጥነቱን ስናየው ግን ትልቅ ችግር እንዳያስከትል ያሰጋል፡፡

በመዝሙራት ችግር ዙሪያ ለመወያየት ፈቃደኛ አለመሆንና ግዴለሽነት

ይህ በሦስት አካላት ላይ ማለትም በዘማርያን፣ አሳታሚዎችና በቤተ ክርስቲያን አባቶች ላይ ጐልቶ ይታያል፡፡

በዘማርያን

ለመማርና ለማወቅ ሲፈልጉና ሲጥሩ ነቃሾችን ለመፈለግ ግድ ያላቸው አይመስሉም፡፡ በቅርባቸው ያሉትንና የሚያውቁትን አሳይተው ትክክል ነው ካሏቸው በዚያው የመርካትና ነቅሰው የሚያዩትንና የሚያዳምጡትን ለመፈለግ ግድ የለሽ ይሆናሉ፡፡ የተለየ ትጋት ቢያደርጉ እንኳ ራሳቸውም ቀስ በቀስ ሊያርሟቸው የሚችሉአቸውን ነገሮች ተራ ምእመን እንኳ ሊያያቸው የሚችላቸው ስሕተቶች የሚፈጽሙት በግደለሽነት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በአሳታሚዎች

ዋና ጉዳያቸው የገበያ ጉዳይ ስለሆነ መታየቱን እንኳ የሚወዱት ለገበያ ካልሆነ በቀር በትክክል መጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት አይታይም፡፡ ምክንያቱም ጥሩ መዝሙሮችን የምናየው ከዘማሪው/ዋ/ ትጋትና ጥንቃቄ እንጂ ከአሳታሚው ባለመሆኑ ነው፡፡ ይህም ግን ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያን

አባቶች በቤተ ክርስቲያን ሕዝቡ እንዳይደናገጥ እና ዘማሪውም እንዳይደነግጥ ብለው በመድረክ ላይ የሚታዩ ኢ-ኦርቶዶክሳዊ የዝማሬ ሁኔታዎችን እንኳ ቦታና ጊዜ መርጦ ቀስ አድርጎ መምከር አልተሞከረም፡፡ ሁሉም በዚህ መጠላትን ስለሚፈራ ግድ የለሽ ሆኗል፤ አንዳንዶች እንደውም ‹‹በጣም ጥሩ ነው›› ሁሉ ይላሉ፡፡

በተለያዩ ቦታዎች ለሚዘጋጁ የመዝሙር የውይይት መርሐ ግብሮች ላይም ለሚቀርቡ ችግሮች ተወያይቶ ችግሩን ለመቅረፍ ፈቃደኞች አለመሆንና ግዴለሽ መሆን እስካአሁን በተደረጉት መርኃ ግብራት አለመገኘታቸው በግልጽ ያስረዳናል፡፡

ነገር ግን ኦርቶዶክሳዊ መዝሙራት እንደ ቀደምት በመልክቱ፣ በዜማ ስልቱና በሥርዓቱ መቅረብ አለበት፡፡ በተለያዩ ወቅት የወጡና ወደ ፊትም የሚወጡ ዝማሬዎችንም ሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመዝሙራት ግጥሞችን የቤተ ክርስቲያንን መሠረተ እምነት፣ ቀኖናና ትውፊት የጠበቀ መሆኑን  የመዝሙር መሣሪያዎቹ ቤተ ክርስቲያን የምትቀበላቸውና ዜማው ያሬዳዊ መሆኑን በማስተዋል መዘመር ያስፈልጋል፡፡ በአዘማመር፣ አሸባሸብ፣ አለባበስና የዜማ ስልት የሆነው የቅዱስ ያሬድ ዜማዎች  መሠረት በመሆናቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተጻፈና ባልተጻፈ ሕግ መዝሙራትን  እንድንገለገልባቸው አስተምራናለች፡፡  ስለዚህም እኛም ይህን ሥርዓት ለመተግበር የአባቶቻችንን አደራ ጠብቀን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ይኖርብናልና ሁላችን ኃላፊነት እንውሰድ!

እግዚአብሔር አምላክ እንድናመሰግነውና እንድናገለግለው ይርዳን፤ አሜን፡፡