‹‹እናት ልጇን እንደምታጽናና እንዲሁ አጽናናችኋለሁ››(ኢሳ.፷፮፥፲፫)

መምህር ሚክያስ ዳንኤል

የካቲት ፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የእግዚአብሔር ነቢይ ኢሳይያስ በዚያን ዘመን ይኖሩ ለነበሩት እስራኤላውያን እንዲናገር በታዘዘው መሠረት ይህን ቃል ነገራቸው፤ ‹‹እናት ልጇን እንደምታጽናና እንዲሁ አጽናናችኋለሁ፡፡›› (ኢሳ.፷፮፥፲፫)

ከነበሩበት መከራና ከጭንቀታችው ሁሉ እንደሚያጽናናቸው እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ አማካኝነት ተስፋ ሰጣቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ቃል በዚያን ዘመን ላለው ሕዝብ ብቻ የሚያልፍ ሳይሆን ዛሬ ያለነውም ትውልድ በተለይም እኛ ልናስተውለው የሚገባ ቃል ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቻችን በዚህ ጊዜ ነግቶ እስኪመሽ፣ ስንወጣና ስንገባ፣ ቀናት ሲፈራረቁ በጭንቀትና በኀዘን ተውጠን፣ መከራና ሥቃይ እየተፈራረቀብንና በችግር ውስጥ እየኖርን በመሆኑ ደስታ አጥተናል፡፡ ይህም የሆነበት ያለንበት የመጨረሻው ዘመን ዋዜማና የከፋ ስለሆነ በዚህ ዘመን የሚኖሩ አብዛኛውም ሰው በክፋትና ኃጢአት ውስጥ በመሆናቸው በሕይወት ውጣ ውረዳቸው ውስጥ ለመወጣት፣ በምድር ለአምልኮና ለመኖር ይጨነቃሉ፡፡

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ ባለከው መልእክት ፍጻሜው እስከ ዓለም ድረስ ለሚጸኑ ለክርስቲያኖች ዘመኑን እንዴት መዋጀት እንዳለባቸው እንዲህ ሲል አሳስቧቸዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህንን ዕወቅ››   (፪ጢሞ.፫፥፩) ይህም የሚያስጨንቅ ዘመን አሁን ያለንበት ስምንተኛው ሺህ ዋዜማ ነው፡፡ ለዚህም መሠረታዊ ምክንያቶች ሲዘረዝር እራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ አፍቃሪዎች፣ ትምክህተኞችን፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ንጽሕናና የጎደላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ እርሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፡፡  አማኝ፣ ክርስቶሳውያን፣ በእግዚአብሔር ሀልወት የአምልኮት መልክ ያላቸው አላቸው፤ ኃይሉን፣ አዳኝነቱን፣ ጠባቂነቱን፣ ፈጣሪነቱን፣ መግቦቱን ግን ክደዋል፡፡ ‹‹ማን ነው የሚጠብቀንና ከዚህ የሚያወጣን?›› በማለት እንጠራጠራለን፤ እንጨነቃለን፡፡ ነገ ምን ይፈጠራል ብሎም ሰው በሐሳብ ይዋዥቃል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሊቀ አእላፍ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ብሎታል፤ ‹‹ሰይጣን እንደ አጃ ሊያበጠራችሁ አሁን ልመናን ለመነ፡፡›› (ሉቃ.፳፪፥፴፩)

ከዚህም ኃይለ ቃል እንደምንረዳው ከምን ጊዜውም በላይ የሰይጣን መጫወቻ እንደሆንን ነው፡፡ በዚህ ጊዜም ወንድም ወንድሙን የሚገልጽበት፣ እርስ በርስ የምንበላላበት፣ ሰይጣን የሰለጠነበት ዘመን እንደሆነ እንረዳለን፡፡

ስለዚህ ይህ ቃል በብሉይ ኪዳን ለእስራኤል ዘሥጋ ቢሆንም ፍጻሜው ግን ለእኛ ለእስራኤል ዘነፍስ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተጻፈው በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን በግብጽ ባርነት ውስጥ ሆነው እንደ ጭቃ እየተቦኩ፣ እንደ ድንጋይ እየተቀጠቀጡ፣ እጅግ  ጽኑ በሆነ መከራ ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ እናት ልጇን ከጭቃ ጋር የምታቦካበት፣ ማጣፊያው ያጠረበት እጅግ ክፉ ዘመን ነበር፤ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ስለዚህ ሲናገር እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ነገር ግን እንዳስጨነቁአቸው መጠን እንዲሁ በዙ፥ እጅግም ጸኑ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ተጸይፈዋቸው ነበር። ግብፃውያንም የእስራኤልን ልጆች በመከራ ገዟአቸው። በጽኑ ሥራ፥ በጭቃ፥ በጡብም በእርሻም ሥራ ሁሉ፥ በመከራም በሚያሠሩአቸው ሥራ ሁሉ፥ ሕይወታቸውን ያስመሯአቸው ነበር።›› (ዘፀ.፩፥፲፪-፲፬) በዚህም ጊዜ ራሔል አለቀሰች፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኸች፤ ሕዝቡም ሁሉ አብረው ጮኹ፤ እግዚአብሔርም መከራቸውን አየ፤ ጩኹታቸውንም ሰማ፤ ፈርዖን ልቡ በትዕቢት የተወጠረ ስለነበረ ሕዝቡን ለመልቀቅ ባይፈልግም እንኳን እግዚአብሔር ግን በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት እስራኤልን ነጻ አወጣቸው፡፡ በዚህም ጊዜ በሚስደንቅ ሰባት ተአምራት ተደረጉ፤ ደመና ከላይ ፀሐይ እንዳያቃጥላቸው ከሥር የአሸዋ ግለት እንዳይለበልባቸው እየተንከባከበ፣ እንዳይራቡ መናን ከሰማይ እያወረደ፣ እንዳይጠሙ ከዐለት ውኃ እያፈለቀ፣ አሕዛብን ነቅሎ እያስወገደ፣ ማርና ወተት ወደ ምታፈውሰው ሀገር አስገባቸው፡፡ በዚያም ሀገር ሲገቡ በአምልኮት እንዳይቸገሩ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት ሥፍራ ሥርዓቱን ጨምሮ ካህናትንና የሚመክሩና የሚገሥጹ መምህራንን አሟልቶ ሰጣቸው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እንደተጻፈው ‹‹ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድነው ነው›› እንዳለው ሁሉንም ሙሉ አድርጎ ነፃ አወጣቸው፡፡  (ኢሳ.፭፥፬)

ሆኖም ግን አስራኤላውያን በማግሥቱ ይህን ሁሉ ዘነጉ፤ እርሱንም ትተው ባዕድ አመለኩ፤  ከዚህም አልፎ አስተማሪ መካሪና ገሣጭ ነቢያትንና መምህራንን መስደብ፣ ማዋረድ፣ ማሳደድና መቀጥቀጥ ጀመሩ፡፡ ምክንያቱም ኃጢአተኛ ሰው እውነትን አይወድም፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በመካድ በደል ይፈጽማል፡፡ ትንቢተ አሞጽ ላይ እንዲህ የሚል ኃይለ ቃል አለ፤ ‹‹በበሩ ዐደባባይ የሚገሥጸውን ጠሉ፥ እውነትም የሚናገረውን ተጸየፉ። ድሀውንም ደብድባችኋልና።›› (ሐሞ.፭፥፲-፲፩)

በዚህ ጊዜም ብዙዎቻችን እውነትን ክደናል፤ እንሸሻለንም፤ ሙገሳን እንጂ ተግሣጽን አንወድም፤ እናንተ ጀግኖች፣ ሊቃውንት፣ መምህራን፣ ክርስቲያኖች ስንባል ደስ ይለናል፡፡ ነገር ግን ‹‹ልክ አይደላችሁም፤ ተሳስታችኋል፤ ያደረጋችሁት ተግባር ከክርስትና ምግባር ውጪ ነው›› ስንባል ይከፋናል፤ እንናደዳለን፤ የተናቅንም ስለሚስለን አጸፋውን በክፋት እንመልሳለን፡፡

እግዚአብሔር አዝኖባችኋል፤ ንስሓ ግቡ ተብሎ ሲነገረን መቀበል አንፈልግም፡፡ መከራና ሥቃይ የበዛብንም በራሳችን ኃጢአት እንደሆነ ማመን ያቅተናል፡፡ ንስሓ ለመግባታና እና ተጸጽተን ከመመለስ ይልቅ እናጎራጉራለን፡፡

በትንቢተ ኤርሚያስ ላይ እንደተጻፈው ‹‹እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰው ወይኑን እንደሚቃርም፥ እንዲሁ ከእስራኤል የቀሩትን ፈጽሞ ይቃርሟቸዋል፤ እጅህንም እንደ ለቃሚ ወደ እንቅብ ዘርጋ። ይሰሙኝስ ዘንድ ለማን እናገራለሁ? ለማንስ አስጠነቅቃለሁ? እነሆ፥ ጆሮአቸው ያልተገረዘች ናት፤ ለመስማትም አይችሉም እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቃል ለስድብ ሆኖባቸዋል፥ ደስም አያሰኛቸውም።›› (ኤር.፮፥፱-፲)

የእግዚአብሔር ቃልን መስማት የሚያስደስታአቸው አሕዛብና እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል፡፡ ልክ የአረማውያን ባቢሎናውያን ንጉሥ ናቡከነዶጾርን አስነሥቶ ሕዝበ እስራኤልን እንደቀጣው ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም በስደት፣ በመከራ እና በቸነፈር ቀጣቸው፤ ‹‹ስለዚህም የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ጕልማሶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ገደላቸው ጕልማሳውንና ቈንጆይቱን ሽማግሌውንና አሮጌውን አልማረም ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው።›› እንዲል፤ (፪ዜና.፴፮፥፲፯)

ልባችን ሲደንድን እና ክፉ ስንሆን ክፉ ንጉሥ እንደሚያስነሣብን በዚህ መረዳት እንችላለን፡፡ ክርስቲያን ብንባልም ሠርጋችን በጭፈራ፣ ምርቃትችን በጥቁር ጋውን፣ በየመሸታ ቤቱ በመገኘት በዝሙት ውስጥ የምንኖር ሆነናል፡፡ ስለዚህም በንስሓ ሕይወት መኖራችንን ያጠራጥራል፡፡ ‹‹ደግሞም የካህናቱ አለቆች ሁሉ ሕዝቡም እንደ አሕዛብ ያለ ርኵሰት ሁሉ መተላለፍን አበዙ በኢየሩሳሌምም የቀደሰውን የእግዚአብሔርን ቤት አረከሱ።›› (፪ዜና.፴፮፥፲፬) ከማንም በላይ ቤተ መቅደስን እኛ ቀድመን አረከስን፤ ስላስደፈርን ጠላቶቻችን ደፍረውታል፡፡

የአባቶቻችንን አምላክ እግዚአብሔርን ለሕዘቡና ለማደሪያው ሲያዝን በመልክቶኞች እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር፡፡ እነርሱ ግን የእግዚአብሔርን ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪመጣ ድረስ ፈውስም እስከማይገኝላቸው በእግዚአብሔር መልእክተኖች፣ በመምህራን፣ በካህነትና በሃይማኖት አባቶች ይሳለቁ ነበር፡፡ ‹‹እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፥ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፥ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፥ ቃሉንም ያቃልሉ፥ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር፤ ስለዚህም የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ጕልማሶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ገደላቸው፤ ጕልማሳውንና ቈንጆይቱን ሽማግሌውንና አሮጌውን አልማረም ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው።›› እንዲል፡፡ (፪ዜና.፴፮፥፲፮-፲፯)

ስለዚህም እግዚአብሔር ረስተውተው ነበርና እነርሱን መልሶ ተዋጋቸው፤ ሕፃናትንና ሴቶችን ሳይቅር ሳይምር ሁሉንም ቀጣቸው፤ ‹‹እነርሱ ግን ዐመፁ፤ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ፤ ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፥ እርሱም ተዋጋቸው›› ተብሎም ተጽፏል፡፡ (ኢሳ.፷፫፥፲)

በዚህ ጊዜም አምላካችን እግዚአብሔር እኛን በርኃብ፣ በጦርነትና በበሽታ እየቀጣን ያለው እርሱን ስለረሳንና ስላልታዘዝንለት እንዲሁም ስላላመለክነው ነው፡፡ ‹‹ሁሉን አብዝቶ ስለ ሰጠህ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍሥሐና በሐሤት አላመለክህም፤ በራብና በጥማት በዕራቁትነትም ሁሉንም በማጣት እግዚአብሔር ለሚልክብህ ለጠላቶችህ ትገዛለህ እስኪያጠፋህም ድረስ በአንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭናል›› እንዲል፤ (ዳግ.፷፫፥፵፯)

ስለዚህ ሰዎች ኃጢአት ስንሠራ በጸጸት አምላካችንን ይቅርታ ልንጠይቅ ይገባል እንጂ በትዕቢትና ፈጣሪንን በመዳፈር ለባሰ ጥፋት እንዳንዳረግ መጠንቀቅ አለብን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እርሱ ኃጢአት ሳይኖርበት በቅድስና ሕይወት እየኖረ እንኳን አምላኩን ለሕዝቡም ጭምር እንዲህ ሲል ተማጽኗል፤ ‹‹አቤቱ፥ ኃጢአታችን ብዙ ነውና፥ በአንተም ላይ ኃጢአት ሠርተናልና ኃጢአታችን ይመሰክርብናል፤ ነገር ግን ስለ ስምህ ብለህ አድርግ።›› እኛም እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ እንደ ሥራችን ሳይሆን እንደ ቸርነቱ እንዲምረን ልንማጸን ይገባል፡፡ የእስራኤል ሕዝብም በመቅሠፍት ሲቀጡ ያደረጉት ይህንን ነበር፡፡  ‹‹ማረን፤ ይቅር በለን፣ በድለናልና›› በማለትም ተማጸኑ፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጐበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይኔ ሳታቋርጥ ዝም ሳትል ዕንባ ታፈስሳለች›› ተብሎ እንደተጻፈ በቸርነቱ ከሰማይ እስኪጎበኘን ድረስ ማልቀስ እንደሚገባም ከእነርሱ ተምረናል፡፡ እስራኤላውያንን ቀን ከሌሊት እያነቡ ተማጽነው ቸርነትንን ምሕረትን አግኝተዋልና፡፡ (ኢሳ.፲፬፥፯፣ሰቆ.ኤር.፫፥፵፱)

ጸሎታችን፣ ምሕላችንና ሰምቶና ጾማችንን ተቀብሎ እንዲምረን የቅዱሳን አማላጅነት እንደሚስፈልገን ልናምንም ይገባል፡፡ ‹‹የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ፦ አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቈጣኋቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?›› ብሎ እንደተጻፈ ቅዱስ ሚካኤል ለእስራኤላውያን እንዳማለደቸው እኛንም ከዚህ መከራ ሥቃይ አውጥቶ ሰላም እንዲሰጥንም የመላክትን፣ የቅዱሳን፣ የጻድቃንና የሰማዕታትን ምልጃ ያስፈልገናል። (ዘካ.፩፥፲፪)

እግዚአብሔር አምላክም በዚህ ጊዜ ወደ ሕዝቡ ተመልሶ ይቅርታንና ምሕረትን አድርጎላቸዋል፡፡ በንስሓም ስለ ተመለሱ ከወዱቁበት አነሣቸው፤ ከተሰበሩበት ስብራት ጠገናቸው፤ ርኃቡንም አጠፋላቸው፤ አጽናናቸውም፡፡ እኛንም እንድንጽናና ስለ ሠራነው ኃጢአት በመጸጸት በንስሓ መመለስ አለብን፡፡ እግዚአብሔርም አጽናኛችን እንደሆነ በትንቢተ ኢሳይያስ ላይ ‹‹የማጽናናችሁ እኔ ነኝ››  ተብሎ ተጽፏልና፡፡ (አሳ.፶፩፥፲፪)

ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲያጽናናን በንስሓ ተመልሰንና ለሕጉ ተገዝተን በሥርዓቱ ልንኖር እንዲሁም በጾም በጸሎት እና በስግደት ልንተጋ ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!