‹‹ኢየሱስ ክርስቶስንም በማምለክ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ››  (፪ ጢሞ. ፫፥፲፪)

ዲያቆን ዘካርያስ ነገደ

ስደት የተጀመረ በአባታችን በአዳምና፥ በእናታችን በሔዋን ነው፡፡ እነዚህ ወላጆቻችን ሕገ እግዚአብሔርን አፍርሰው በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ፥ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ተፈርዶባቸው ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ከነበሩበት ተድላ ደስታ ካለበት ገነት ተሰድደው ወደ ምድረ ፋይድ ወርደዋል፡፡ በዚያም በስደት ዘመን ሳሉ የዳግማዊ አዳም የመሲሕ ክርስቶስን መምጣት ደግሞም ምክንያተ ድኅነት የሆነች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ከእነርሱ ዘር የመገኘቷን ነገር ሲናፍቁ ኖረዋል፡፡ ሊቁ አባ ሕርያቆስ እመቤታችንን ባመሰገነበት ድርሳኑ ‹‹አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት፤ ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው አንቺ ነሽ›› በማለት እንዳመሰገናት አባታችን አዳም ፭ ሺሕ ፭፻ ዘመን እስኪደርስ ተስፋው ይፈጸምለትና ከተሰደደበት ይመለስ ዘንድ ዘመኑን ሲቆጥር ኖሯል፡፡

የቅዱሳን ስደት

ቅድመ ልደተ ክርስቶስም ሆነ ድኅረ ልደተ ክርስቶስ እጅግ ብዙ የሆኑ ቅዱሳን ስለ ጽድቅ ተሰድደዋል፡፡ ጌታችን በአንቀጸ ብፁዓን ትምህርቱ ‹‹ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ÷ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና፡፡›› በማለት ከእርሱ አስቀድሞ በዚህ ምድር የነበሩ ነቢያት ስደትን ጨምሮ የተቀበሉትን መከራ ነግሮናል፡፡ (ማቴ. ፭፥፲፪)፡፡

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከፈርዖን፥ ዳዊትም ከሳዖል ፊት መሸሻቸውና መሳደዳቸው በመጽሐፍ የተገለጠ ነው፡፡ ነቢዩ ኤልያስም ከንጉሡ አክዓብና ከንግሥቲቱ ኤልዛቤል ሸሽቶ መሰደዱን እናነባለን፡፡ (፩ነገ. ፲፱)

ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ከዚያች ከተማ ቢአሳድዷችሁ ወደ ሌላዪቱ ከተማ ሽሹ›› (ማቴ.፲፥፳፫) በማለት እንዳሰማራቸው ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያትም አይሁድን ከመፍራታቸው የተነሣ በየጊዜው ሸሽተዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በደማስቆ ከተማ ከንጉሥ አርስጣስዮስ በታች የሆነው አለቃ ሊይዘው በወደደ ጊዜ ምእመናን በመስኮት ቅርጫት አውርደውት ከእጁ ማምለጡን ጽፏል፤ (፪ቆ. ፲፩፥፴፪)፡፡ ደግሞም ስለተቀበላቸው የስደት መከራዎች ለቅዱስ ጢሞቴዎስ ሲገልጥ በዘመኑ ስደትና መከራ መቀበሉን ከሁሉም ደግሞ እግዚአብሔር እንዳዳነው ነግሮታል፡፡ (፪ጢሞ. ፫፥፲፩)

ስደትን መታገሥ

የቅዱሳን ስደት ቤተ ክርስቲያን በዓለም ሁሉ እንድትሰፋ፥ ወንጌል በዓለም ሁሉ እንዲሰበክ ምክንያት ሆኗል፡፡ ቅዱሳን በደረሱበት ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን ሠርተዋል፤ ወንጌለ መንግሥትን ሰብከዋል፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች ክርስቶስን በማምለካቸው የሚጠብቃቸው ስደት መኖሩን ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስንም በማምለክ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ፡፡›› ተብሎ ተገልጧል፡፡ ሆኖም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ትዕግሥትም መከራ ነው፤ በመከራም ተስፋ ይገኛል፤ ተስፋም አያሳፍርም፥ በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን መልቶአልና፡፡›› በማለት በዚህ ፈተና የሚጎበኙትን ያጽናናቸዋል፡፡ (፪ጢሞ. ፫፥፲፪፤ ሮሜ. ፭፥፬)

ቅዱስ ዳዊት ‹‹በእግዚአብሔር የምታምኑ ሁላችሁ፥ ታገሡ ልባችሁንም አጽኑ›› ይለናል፡፡ ዳግመኛም፤ ‹‹እግዚአብሔርን በትዕግሥት ደጅ ጠናሁት፥ እርሱም ተመልሶ ሰማኝ፥ የልመናዬንም ቃል ሰማኝ፡፡ ከጥፋት ጕድጓድ ከረግረግ ጭቃም አወጣኝ፥ እግሮቼንም በዓለት ላይ አቆማቸው፥ አረማመዴንም አጸና፡›› በማለት ከመጣብን መከራ የሚያወጣን፥ ሊመጣብን ካለው ደግሞ የሚጠብቀን እርሱ እግዚአብሔር በመሆኑ በፍጹም እምነትና መታመን በጽናትና በትዕግሥት ልንቀበለው ይገባል፡፡ (መዝ.፴፱፥፩)

ቅዱስ ጴጥሮስ ስደትን የመሰሉ መከራዎች ሲገጥሙን መታገሥ እንደሚኖርብን ሲያስተምር ‹‹በድላችሁ የመጣባችሁን ብትታገሡ፥ ምስጋናችሁ ምንድን ነው? ነገር ግን መልካም እየሠራችሁ፥ የደረሰባችሁን ግፍ ብትታገሡ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የምታስመሰግን ይህች ናት›› ሲል ዳግመኛም ደግሞ ‹‹ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ፤ የሚያስፈራራችሁንም አትፍሩ፥ አትደንግጡም፡፡›› በማለት ትዕግሥታችን ያለ ዋጋ እንደማትቀር ያሳስበናል፡፡ (፩ጴጥ. ፪፥፳፤ ፪፥፲፬)

የስደት ፍሬ

መሰደድ መታዘዝ ነው፤ በክርስትናም መሰደድ መኖሩን ከላይ ባነሣናቸው የቅዱሳት መጻሕፍት ኃይለ ቃላትና ምሳሌ ባደረግናቸው ቅዱሳን ሕይወት ተመልክተናል፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ከዚያች ከተማ ቢያሳድዷችሁ ወደ ሌላዪቱ ሽሹ፤›› በማለት እንዳዘዘን ክርስቶስን በማምለካችን የሚያሳድደን ቢኖር በተድላና በሐሴት እንቀበለዋለን፡፡ ብዙዎች ቅዱሳን ይህን ፈጽመዋል፤ በዘመናችንም ለዚህ የተመረጡ ክርስቲያኖች በሃይማኖታቸው ምክንያት ሲሳደዱ ተመልክተናል፤ እየተመለከትንም ነው፡፡

ታዲያ ይህን መከራ በአኰቴት ስንቀበል ዋጋችን ምንድንነው? ማለታችን አይቀርም፡፡ ጌታችን በአንቀጸ ብፁዓን ትምህርቱ እንደገለጠው ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው በማለት እውነትንና ጽድቅን ለማወቅ ወይም ለማስተማር፣ በምናኔ ምክንያት ሀገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ ወይም የተሰደዱ ብፁዓን መሆኗቸውን ተናግሯል፡፡ ለእነዚህ ቅዱሳን የሰው ሀገሩ ምግባሩ ነውና ስለ ጽድቅ ሲሉ መከራ ለተቀበሉት ሁሉ ሀገረ ሕይወት ገነት መንግሥተ ሰማያት ለእነርሱ ተሰጥታለች፡፡