«ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች»መዝ፤ ፷፯፥፴፩

በሕይወት ሳልለው 

ሀገራችን ኢትዮጵያ ክርስትናን ከተቀበሉት ቀደምት ሀገሮች አንዷ ናት፤ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር፤ ፷፯፥፴፩ ላይ «ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች» ብሏል፡፡

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ኢትዮጵያዊት ሴት ባገባበት ዘመን ኢትዮጵያ በሕገ ልቡና አምልኮተ እግዚአብሔርን ትፈጽም ነበር፤ የብሉይ ኪዳን እምነትና የሕገ ኦሪት ሥርዓት ደግሞ በንግሥተ ሳባ ዘመነ መንግሥት መጀመሩን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ ይህም የሆነው ንግሥተ ሳባ ስለ ንጉሥ ሰሎሞን ጥበብና አገዛዝ ለማወቅ እጅግ ትመኝ ስለነበር ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛ በተማረችው ትምህርተ ኦሪት ነው፡፡

በዚያን ዘመን ታምሪን የተባለ ጎበዝ የነጋዴዎች አለቃና የንግሥት ሳባ አገልጋይ ነበር፤ ብልህና አስተዋይ ስለነበር ወደ ኢየሩሳሌም በተጓዘበት ወቅት የንጉሥ ሰሎሞንን ጥበብና አገዛዝ አደነቀ፡፡ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ሲመለስ ስለንጉሡ ለኢትዮጵያዋ ንግሥት ይነግራት ነበር፤ እርሷም ይህንን በሰማች ጊዜ በዓይኗ ለማየት፤ ጥበቡንም በጆሮዋ ለመስማት ተመኘች፡፡ ለሕዝቦቿም እንዲህ አለቻቸው «ወገኖቼ!፤ ነገሬን አድምጡኝ፤ እኔ ጥበብ እሻለሁ፤ልቤም እውቀትን ትፈልጋለች፤ በጥበብም ፍቅር ተነድፌአለሁ፤ በጥበብ ገመዶችም ተይዣለሁ፤» (ክብረ ነገሥት ፳፬)፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ሀገሩ ሂዳ ጥበብን ለመመርመር እንደምትሻ ለአገልጋይዋ ነገረችው፤ ታምሪንም ምኞቷን ያሳካ ዘንድ ጉዞዋን አመቻቸላት፤ሕዝቦቿም ንግሥታቸውን ወደ ጠቢቡ ሀገር ሸኟት፡፡

ለስድስት ወር ከተጓዘች በኋላ ኢየሩሳሌም ደረሰች፤ ስለእርሷ ከነጋዴው ታምሪን የሰማው ንጉሥ ሰሎሞን በክብር ተቀበላት፤ «የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ስም፤የእግዚአብሔርን ስም በሰማች ጊዜ ሰሎሞንን በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች፤» ቀዳማዊ ነገሥት ፲፥፩-፲፫፡፡ ስለ ጥበብ የሚያውቀውን ሁሉ ነገራት፤አስተማራትም፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለዚያን ጊዜ ትውልደ አይሁድን ሲወቅሳቸው እንዲህ ብሏቸዋል፤ «በፍርድ ቀን ንግሥተ አዜብ ትነሳለች፡፡ ይህችንም የቃሌን ትምህርት ያልሰሙትን እነዚያን ትውልዶች ትዋቀሳቸዋለች፤ ትፋረዳቸዋለች፤ ታሸንፋቸዋለችም፡፡የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና»(ክብረ ነገሥት ፳፩)፤ንግሥተ አዜብ ያላትም የኢትዮጵያን ንግሥት ነው፡፡

ከዚያ በኋላ ንጉሡ ከእርሷ ዘር ሊያገኝ ወደደ፤ለስድስት ዓመት በእርሱ ግዛት ተቀመጠች፡፡ ንግሥተ ሳባም ፀነሰች፤ ሆኖም ወደ ሀገሯ የመመለሻ ጊዜ ሲደርስ ንጉሡን «እሄድ ዘንድ ተወኝ» አለችው፤ ንጉሡም እንድታስታውሰው ብሎ የጣት ቀለበቱን ከእጁ አውልቆ ሰጣት፤ በብዙ ግርማም ሸኛት፤(ክብረ ነገሥት ፴‐፴፩)፡፡

ከዘጠኝ ወርና አምስት ቀናት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ላይ በነበረችበት ወቅት ዲሰሪያ ውስጥ ባላ በተባለ ከተማ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ሀገሯ ስትደርስ ከንጉሡ ሰሎሞን የተማረችውን ጥበብ እንዲሁም የተቀበለችውን የኦሪት እምነት ለሕዝቦቿ አስተማረች፤ ግዛቷንም በሕገ እግዚአብሔር እንዲመራ አደረገች፡፡

ልጇም ምኒልክ ፲፪ ዓመት በሞላው ጊዜ አባቱን እንድታሳየው ለእናቱ ደጋግሞ ይጠይቃት ጀመር፤ንግሥተ ሳባም የልጇን ጭንቀት ለማቅለል አባቱም እናቱም እርሷ እንደሆነች ልታሳምነው ሞከረች፡፡ እድሜው ፳፪ በደረሰ ጊዜ ምኒልክ አባቱን ለማየት ወደ እስራኤል እንደሚሄድ ነገራት፤ ከነጋዴው ታምሪን ጋርም ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዙ፡፡

የልጁን ወደ ሀገሩ መምጣት የሰማው ንጉሥ ሰለሞን እጅጉን በመደሰቱ በክብር ተቀበለው፤  ግርማ ሞገሱና መልኩ አባቱን ይመስል ነበር፤ ሲያገኘውም ልጁ መሆኑን አምኖ እንዲቀበል ለምልክት ብላ እናቱ የሰጠችውን ቀለበት አሳየው፡፡ ንጉሡ ግን መልካቸው መመሳሰሉ ብቻ በቂ ማስረጃ መሆኑን በፍቅር አስረዳው፤ አቅፎም ሳመው፡፡

ነገር ግን ምኒልክ የእናቱ ናፍቆት ነበረበት፤ ለአባቱም ወደ ሀገሩ መመለስ እንደሚፈልግ በነገረው ጊዜ ንጉሡ እጅግ አዘነ፡፡ ሐሳቡን ለማስለወጥ ብዙም ጣረ፤ በእርሱ ተተክቶ እንዲነግሥ ጠየቀው፤ ልጁ ግን ሊስማማ አልቻለም፡፡ በመሆኑም ንጉሥ ሰሎሞን መኳንቱን አማክሮ በስመ ዳዊት መርቆና ባርኮ ወደ ሀገሩ ላከው፤ ወደ ኢትዮጵያም በተመለሰ ጊዜ በአባቱ አገዛዝ ሥርዓት ቀዳማዊ ምኒልክ  ተብሎ ነገሠ፤ ሕገ ኦሪትም በሀገራችን በይፋ ታወጀ፡፡