ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ


ቅዱስ ያሬድ ውልደትና እድገቱ ኢትዮጵያ ወስጥ፤ አክሱም ከተማ ነው። የተወለደውም ከአባቱ ከአብዩድና ከእናቱ ታውክሊያ ነው፤ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ እናቱ መምህር ወደ ሆነው አጎቱ አባ ጌዲዬን ትወስደዋለች፡፡ እርሱ ግን በመጀመሪያ ትምህርት ሊገባው አልቻለም፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን መምህር ጌዲዬን ያሬድን ሲገርፈው በምሬት አለቀሰ፤ ማይኪራህ ወደምትባል ቦታም ተጓዝ፤ በመንገድ ላይ ሳለ ውሃ ስለጠማ በዚያች ስፍራ ካለ ምንጭ ውሃ ጠጥቶ በዛፉ ሥር ለማረፍ ቁጭ አለ፤ ወደ ላይም በሚመለከትበት ጊዜ ከዛፉ ላይ አንዲት ትል  ከታች ወደ ላይ ስትወጣ ስትወርድ ተመለከተ፡፡ እርሱም ትኩር ብሎ አያት፤ ትሏም ያለመሰልቸት ከወጣች ከወረደች በኋላ ዛፉ ላይ መድረስ ቻለች፡፡ በዚያን ወቅት ቅዱስ ያሬድ አሰበ፤ እንዲህም አለ፤ «ይህች ትል ዛፉ ላይ ለመድረስ እንዲህ ከተጋች እኔም ትምህርት ለመማር ብታጋ እግዚአብሔር አምላክ ይገልጽልኛል»፡፡ ወደ  ጉባኤው ተመልሶ መምህሩን ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ መማር ጀመረ፤ እግዚአብሔር አምላክም የ፹፤፩ መጽሐፍትንና የሊቃውንት መጽሐፍትን እንዲሁም ሌሎች ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸውን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ገለጸለት፤ መምህር ጌዲዬን ሲሞት የእርሱን ቦታ ተረክቦ ማሰተማር ቀጠለ፡፡

በ፭፻፴፬ዓ.ም. ኅዳር ፮ ቀን፤ ወደ ሰማይ ተመነጠቀ፤ በሰማይ ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን ልዩ በሆነ ጣዕመ ዝማሬ ሲያመሰግኑ ሰማ፡፡ ወደ ምድርም በተመለሰ ጊዜ አክሱም ጽዮን ውስጥ ወደ ምስራቅ በኩል በመዞር ከሰማይ የሰማውን ዝማሬ ዘመረ፤ አርያም ብሎም ሰየመው፡፡  በዚሁም በ፭፻፴፰ ዓ.ም. ቅዱስ ያሬድ ማኅሌትን ጀመረ፡፡ ታህሳስ ፩፤ በዕለተ ሰኞ ምህላ ያዘ፤ እሰከ ታህሳስ ፮፤ ቀዳሚት ሰንበት ድረስም ዘለቀ፤ በዚያች ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል አንደተሰቀለ ሆነ ከቅዱሳን መላእክት ጋር ተገለጸለት፡፡

ቅዱስ ያሬድም ጌታ የተገለጸለትን የመጀመሪያውን ሳምንት ‹ስብከት› ብሎ ሰየመው፤ በሳምንቱም እንደገና በብርሃን አምሳል ስለተገለጸለት ያን ዕለት ‹ብርሃን› ብሎ ሰየመው፤ በሶስተኛው ሳምንት እንዲሁ በአምሳለ ኖላዊ ስለተገለጸለት ‹ኖላዊ› ብሎ ሰየመው፤ በመጨረሻም ሳምንት በአምሳለ መርዓዊ ሲገለጽለት ዕለቱን ‹መረዓዊ› ብሎ ሰይሞታል፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ያሬድ ፭ የዜማ መጻሕፍትን ደረሰ፤ እነዚህም ድጓ፤ ጾመ ድጓ፤ ምዕራፍ፤ ዝማሬና መዋሥዕት ናቸው፡፡ ከደረሳቸው የዜማ መጻሕፍትም ውስጥ ትልቁ ድጓ ነው፤ በሦስትም ይከፈላል፤ የዮሐንስ፤ አስተምህሮና ፋሲካም ይባላሉ፡፡በንባባት ብቻ ይቀደስባቸው የነበሩትን ፲፬ቱ ቅዳሴያት በዜማ የደረሳቸው ቅዱስ ያሬድ ነው፤  ዝማሬም በ፭ ይከፈላል፤ኅብስት፤ጽዋዕ፤መንፈስ፤አኮቴትና ምሥጢር ይባላል፡፡

ይህ ቅዱስ ደራሲ በተወለደ በ፸፭ ዓመቱ በሰሜን ተራራ ውስጥ ደብረ ሐዊ ከሚባል ገዳም  ግንቦት ፲፩ ቀን ተሠውሯል፡፡ የዝማሬና መዋሥዕት መምህራን የቅዱስ ያሬድን ጉባኤ ተክተው  አሁን በማስተማር ላይ እስካሉት መጋቤ ብርሃናት ፈንታ ድረስ ፵፮ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለውለታ ቅዱስ ያሬድ  መምህር ወሐዋርያ፤ መጻሕፍትን በጣዕመ ዜማ የደረሰ፤መዝሙረ ዳዊትን ጨምሮ ሌለችንም ቅዱሳት መጻሕፍትን በዜማው ያመሠጠረ ታላቅ  ኢትዮጵያዊ ሊቅ ነው፡፡