‹‹አባታችሁ አብርሃም የእኔን ቀን ያይ ዘንድ ተመኘ፤ አይቶም ደስ አለው›› (ዮሐ. ፰፥፶፮)

አባ ፍቅረማርያም መኩሪያ

ታኅሣሥ ፲፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን በሰበከበት በዘመነ ሥጋዌ እርሱ የሚያስተምረውን ትምህርት እና የሚያደርገውን ገቢረ ተአምራት ወመንክራት ሰምተውና አይተው አይሁድ ቅናት አደረባቸው፡፡  ጌታችንንም በክፋት በሚከታተሉበት ጊዜ የእርሱን ጌትነትና የባሕርይ አምላክነት በትምህርት እየገለጠ ብዙ ተአማራት ቢያሳያቸውም በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ እንዲሁም በሥጋ ተገልጦ ሲመላለስ ስላዩት አምላክነቱን ተጠራጥረው እንዲህ አሉት፤ ‹‹በውኑ ከሞተው ከአባታችን አብርሃም ትበልጣለህን? ነቢያትም ሞቱ፤ ራስህን ማን ታደርጋለህ?›› (ዮሐ. ፰፥፶፫-፶፱)

ጌታችን ኢየሱስ ግን ‹‹…አባታችሁ አብርሃም የእኔን ቀን ያይ ዘንድ ተመኘ፤ አይቶም ደስ አለው›› አላቸው፡፡ አይሁድም ‹‹ገና ሃምሳ ዓመት ያልሞላህ እንዴት አብርሃምን አየህ? ብለው ጠየቁት፤ እርሱም ቅድመ ዓለም በነበረው ዘመን የማይቆጠርለትን ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ድንግል ማርያም የተወለደው ልደት ዘመን የሚቆጠርለት ቢሆንም ቀዳማዊ ልደቱን ያልተረዱ አይሁድ ጌታችንን እንዲህ ባሉት ጊዜ  ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም ሳይለወድ እኔ አለሁ›› አላቸው፡፡ ከዚያም ሊደበድቡት ድንጋይ አነሡ፤ ጌታችን ኢየሱስም ተሰወራቸው፡፡ (ዮሐ. ፰፥፶፮-፶፱)

አባታችን አብርሃም የእግዚአብሔርን ቀን ለማየት ተመኝቶ አልቀረም፤ አይቶም ሐሴት አድርጓል፤ ይህም ደስታ ሥጋዊ ማለትም በልተው ጠጥተው እና ለብሰው የሚያገኙት ሳይሆን መንፈሳዊ ሐሴት ነው፡፡ ካልቀመሱት እና ካልደረሱበት በስተቀር የማይታወቅም ነው፡፡ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ፲፫ ጀምሮ ታሪኩ ተጽፎ እንደምናገኛው ቅዱስ አብርሃም ወንድሙ ሎጥን ተለይቶ በከነዓን በሚኖርበት ጊዜ አምስቱ ነገሥተ ኮሎዶጎሞር ሰዶምና ገሞራ ደርሰው ሎጥን ከእነ ቤተሰቦቹ፣ ሀብትና ንብረቱ እንደማረኩት አብርሃም ሰማ፡፡ አብርሃምም ፫፲፰ ቤተሰቦቹን ይዞ ሎጥ ተማሮኮበት ወደነበረው ፈጥኖ በመድረስ አምስቱ ኮሎዶጎሞርን ድል ነሥቶ ሎጥን ወደ ቀደመ ርስቱ መለሰው፡፡ ከተማረኩትም ውስጥ ብዙዎችን ስለመለሳቸው እና ብዙ ምርኮ ስላገኘ ደስ እያለው ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡ ‹‹አብርሃምም የወንድሙ ልጅ ሎጥ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ ወገኖቹንና ቤተሰቦቹን ሁሉ ቈጠራቸው፤ እነርሱም  ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ሆኑ፤ እስከ ዳን ድረስ ተከትሎ አሳደዳቸው፡፡ እነርሱም ከብላቴኖቹ ጋር በሌሊት ደረሰባቸው፤ መታቸውም፤ በደማስቆ ግራ እስካለችውም እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው፡፡ የሰዶምን ፈረሶች ሁሉ አስመለሰ፤ ደግሞም የወንድሙን ልጅ ሎጥንና ንብረቱን ፥ሴቶችንና ሕዝቡንም አስመለሰ››  እንዲል፤ (ዘፍ. ፲፬፥፲፬-፲፮)

በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዘመን በ፫፳፭ ዓ.ም. አምላካችን እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወልድ ፍጡር ነው ብሎ አርዮስ ተነሥቶ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ፫፲፰ ሊቃነ ጳጳሳት ተሰብስበው መስከረም ፳፩ ጀምረው ኅዳር ፱ ጉባኤያቸውን ፈጽመው እውነተኛዋን የቀናችውን የጸናችውን ነቢያትም ትንቢት የተናገሩላትን ጌታ ሰው ሆኖ የሠራትን ሐዋርያት የሰበኳትን ሃይማኖት በሚገባ አጽንተዋታል፡፡ አብርሃም የጌታ፣ ሎጥ  የሃይመኖትና  ፫፲፰ ሰዎች የሊቃውንት ምሳሌ ናቸው፡፡ ይህንን ስላደረገ አብርሃም ደስ አለው፡፡ ይህችን ርትዕት ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት ይዘን እኛም ምርኮ እንድናገባ ያስፈልጋል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ሥጋውን የቆረሰለትና ደሙን ያፈሰሰለት ሰውነት በጣዖት አምልኮ፣ በዝሙት፣ በርኩሰት፣ በዘረኛነት ተማርኮ በውጭ ተጥሏል፡፡ ስለዚህ ከተማረከበት እንድናወጣው እግዚአብሔር ለዚህ ሥራ እያንዳንዳችንን ጠርቶናል፡፡ እኛም በትሕትና የተሰጠንን እንዲያጸናልን እየለመንን መኖር ያስፈልጋል፡፡

አባታችን አብርሃም እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ሲወርድ አምላክን ከወለደች በድንጋሌ ሥጋ ድንጋሌ ነፍስ ከጸናች ከድንግል ማርያም ሰው ሲሆን ለማየት ስለተመኘ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ገልጦለታል፡፡ አብርሃም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሊፈጽም ደስ ብሎት ዐሥራቱን በኩራቱን ቀዳምያቱን ይዞ ወደ አመለከተው ተራራ ሲደረስ ባሕታዊ መልከጸዴቅ ይኖርበት ከነበረው ዋሻ ወጥቶ፤ ኅብስተ አኮቴት ጽዋ በረከት ይዞ ተቀበለው፤ መረቀውም፤ ‹‹አብርሃም ሆይ፥ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የእግዚአብሔር ክቡር ፍጥረቱ አንተ ነህ፤ ጠላቶችህንም በእጅህ የጣለልህ እግዚአብሔር ክቡር ምስጉን ነው›› አለው፡፡ አብርሃምም ዐሥራቱን በኩራቱን፤  አቀረበለት፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር ወልድን ሰው መሆን አብርሃም አረጋገጠ፤ ዮርዳኖስን ተሻግሮ የመሄዱ ምሥጢር የጥምቀት ምሳሌ ነው ይላሉ አባቶቻችን፤ ዮርዳኖስ ወንዝን ተሻግሮ መልከጼዴቅን አግኝቶታል፡፡ መልከጼዴቅም የሰጠው ኅብስተ አኮቴት ጽዋዕ በረከት የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ምሳሌ ነው፡፡ ነገር ግን ለአብርሃም መልከጸዴቅ ንጽሕናውን ከጠበቀለት በኋላ ነበረ ኅብስተ አኮቴት ጽዋዕ በረከት የሰጠው፡፡ እኛም ተጠምቀን ሥጋው ደሙን እንቀበላለን፤ በኋላም በምግባር ያሳደፍነውን በንስሓ ታጥበን ሥጋ ወደሙን እንድንቀበል ማሳያ በመሆኑ ነው፡፡ አብርሃምም የቅዱስ ቁርባን ምሥጢር ተገልጦለታልና ደስ አለው፡፡ (ኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ ምዕራፍ ፲፬)

የአብርሃም ጸጋ ይህ ብቻ አልነበረም፤ ከመንፈሳዊ ትጋቱ በተጨማሪ አላፊ አግዳሚውን እንግዳ እየተቀበለ ሲኖር ወደ አብርሃም ቤት እንግዶች እንዳይሄዱ እውነትን በሐሰት እየለወጠ ራሱን  በድንጋይ የተመታ እያስመሰለ በአራቱም ማእዘን እየተገኘ ‹‹ወደ አብርሃም ቤት አትሂዱ፤ እርሱ አኮ የወትሮ አብርሃም አይደለም፤ እኔ ያበላኛል፤ ያጠጣኛል፤ አርፋለሁ ብዬ ብሄድ ራሴን በድንጋይ ገምሶኝ ከራሴ የሚወርደውን ደም ተመልከቱ፡፡ እንደ እኔ እንዳትሆኑ አትሂዱ›› እያለ ወደ ቤቱ እንግዳ ከለከለበት፡፡ አብርሃም ደግሞ ያለ ምስክር እንዴት ማዕድ ይቆረሳል ብሎ ሳይበላና ሳይጠጣ ሦስት ቀን ሰነበተ፡፡ በሦስተኛ ቀንም የእርሱን ደግነት የሰይጣንን ክፋት የተመለከተ ልዑል እግዚአብሔር ወደ አብርሃም ቤት አንድነት በሦስትነት መጣ፡፡

አብርሃምም ዓይኖቹን አንስቶ ሲመለከት ሦስት አረጋዊያንን አየ፤ ሮጦ ሄዶም ተቀበላቸው፡፡ ‹‹ውኃ እናምጣላችሁ፤ እግራችሁን እንጠባችሁ፡፡ ከዛፉም ሥር ዕረፉ፤ እንጀራም እናምጣላችሁና ብሉ፤ ከዚያም በባሪያችሁ ዘንድ ከአርፋችሁ በኋላ፥ ወደ አሰባችሁት ትሄዳላችሁ›› አላቸው፡፡ ምኞቱም ሁሉ ተሳካለት፤ እግዚአብሔርም አንድነቱንና ሦስትነቱን ገለጠለት፡፡ ‹‹እንደምታየን ሽማግሌዎች ነን፤ የመጣነው ደግሞ ከሩቅ ነው፡፡ ስለዚህ አዝለህ ወደ ድንኳንህ አስገባን›› አሉት፡፡ አንደኛውን አዝሎ ወደ ድንኳን ሲያስገባ ሁለቱ በግብር አምላካዊ ገብተው ተገኙ፡፡ አብርሃምም ነገሩ እየረቀቀበት ሲሄድ በጓዳ ለነበረችው ለሚስቱ ሣራ ‹‹ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ ለውሺ፤ እንጎቻም አድርጊ›› አላት፡፡ አብርሃምም ለሚስቱ ይህንን ያለበት ምክንያት ምሥጢረ ሥላሴን ስለተረዳ ነበር፡፡ ሦስቱ መስፈሪያ የሦስተነታቸው ምሳሌ ሲሆን አንዱ እንጎቻም ተዳርጎ መጋገሩም ደግሞ አንድነታቸውን ይገልጻል፡፡ ሚስቱም እንዳዘዛት አድርጋ ጋግራ አቀረበች፤ እርሱም ቤት ለነበረ አንድ ብላቴና ወይፈኑን አርዶ አወራርዶ እንደያመጣለት ካዘዘው በኋላ ከወተትና ማር ጋር አብሮ አቀረበላቸው፡፡ እነርሱም አብርሃምን ደስ ለማሰኘት በሉ፤ ከዚያም የታረደው እና የተወራረደው ወይንም ተነሥቶ በድንኳኑ ደጃፍ ‹‹ስብሐት ለአብ፣ ስብሐት ለወልድ፣ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ›› ብሎ ሥላሴን አመሰገነ፡፡  አብርሃም ደነገጠ፤ ‹‹እንግዳ ከመጣልህ በትሑት ሰብእና በቅን ልቡና ሆነህ ተቀበል፤ እንግዳ ካልመጣ ጾምህን አትደር፤›› አሉት፤ ከዚያም ይስሐቅ የሚባል ልጅ እንደሚወልድ ነገሩት፡፡ (ዘፍ. ፲፰፥፩-፰፣ አንድምታ ትርጓሜ ምዕራፍ ፲፰)

ሥሉስ ቅዱስ በአብርሃም ድንኳን በመገኘታቸው በእርጅና የነበረ የሣራ ማሕፀን ተፈታ፤ ከሦስቱ አንዱም ‹‹የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ወደ አንተ ተመልሼ እመጣለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች›› አለ፡፡ ሣራ ግን በድንኳኑ ደጃፍ በስተኋላው ሆና ይህን ስትሰማ ‹‹እስከ ዛሬ ገና ነኝን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል›› ብላ በልቧ ሳቀች፡፡ አእምሮ ያረቀቀውን፣ ልቡና ያመላለሰውን የሚያውቅ ፈጣሪ ‹‹ሣራን ለብቻዋ በልብዋ ምን አሳቃት፤እስከ ዛሬ ገና ነኝን? በእውነትስ እወልዳለሁን? ጌታዬም አርጅትዋል፤ እነሆ እኔንም አርጅቻለሁ ብላለች፤ በእውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅን ታገኛለች›› አለ፡፡ ሣራም ስለ ፈራች አልሳቅሁምአለች፤ እርሱም አይደለም፤ ሳቅሽ እንጂ አላት›› በዚህም ልጇን ይስሐቅ ብላ ጠራችው፡፡ አብርሃምም ጎዶሎው ሞላለት፤ ጻድቁ አባታችን ሥላሴን ሲያስተናግድ በድንኳኑ ውስጥ ምንም ዓይነት ደባል ነገር አልበረም፡፡ አምላኩ እግዚአብሔርም ብቻ ነበር፤ ‹‹እኔና ቤት ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን›› እንዲል፤ (ዘፍ. ፲፰፥፲፭፣ ኢያ. ፳፬፥፲፭)

እኛስ የምናመልከው እውነት እግዚአብሔርን ብቻ ነውን? በእኛ ድንኳን እግዚአብሔር እንዲያድር ደባል ነገር መኖር የለበትም፡፡ አብርሃም ዘረኛ አልነበረም፤ እንግዳ ተቀብሎ ያበላው ያጠጣውም ያገኘውን ሰው ሁሉ እንጂ ቋንቋ ወይንም ዘር እየጠየቀ አልበረም፡፡ በዚህም  እግዚአብሔርን በአንድነትና በሦስትነት በቤቱ ለማስተናገድ በቅቷል፡፡         

የአብርሃም ድንኳን የእመቤታችን ምሳሌ ናት፤ አብርሃምም በሥላሴ ፊት ሞገስ በማግኘቱ ሥሉስ ቅዱስን እንዳስተናገደ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን ተልኮ የነገራት ይህንን ነበር፤ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት ባለሟልነትን አግኝተሻል›› ብሎ የሥላሴ ማደሪያ እንድትሆን መመረጧን አብሥሯታል፡፡ የአብ ሙሽራ፣ የወልድ እናት፣ የመንፈስ ቅዱስ ንጽሕት አዳራሽ የምታበለውም ለዚህ ነው፡፡  (ሉቃ. ፩፥፴)

ቅዱስ አብርሃም ይህ ምሥጢር የተገለጠለት ከብዙ ፈተና በኋላ ነበር፤ ሕይወቱን በሙሉም በፈተና ኖሯል፤ ተርቧል፤ ተጠምቷል፤ ተሰዷልም፤ እግዚአብሔር የሚገለጥለት ጻድቅ ሰው ሆኖ እንኳን አብርሃም በሥጋው ይፈተን ነበር፡፡ እግዚአብሔርንም ለሦስተኛ ጊዜ ያየው ልጁ ይስሐቅን ከወለደ በኋላ ነበር፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን ዳግም ፈተነው፤ ‹‹የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ከፍተኛው ተራራ ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው›› አለው፤ በስተርጅና የተለወደ ልጅ ቢያሳሳም አብርሃም ግን ለእግዚአብሔር ሊሰጠው አልሳሳም፡፡ እንደሰማም ይዋል ይደር ሚስቱንም ላማክራት አላለም፤  ‹‹ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና  በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ፈጽሞ አበዛዋለው፤ ዘርህም የጠላት ሀገሮችን ይወርሳሉ፤ የምድር አሕዛብ በዘርህ ይባረካሉ›› ብሎ የገባለት ቃል ኪዳን በይስሐቅ በኩል እንደሚፈጸም ቢያውቅም አልተጠራጠረም፡፡ (ዘፍ.፳፪፥፪፣፲፯-፲፰)

ስለዚህም አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ይዞ ሁለት ሎሌዎቹን አስከትሎ ሦስት ቀንና ሌሊት ከተጓዘ በኋላ እግዚአብሔር ከአዘዘው ተራራ ደረሱ፤ ከእግረ ደብሩም ሎሌዎቹን ትቶ ይስሐቅን እንጨቱን እንዲሸከም ካደረገ በኋላ ሸተሉን እና እሳቱን በእጁ ይዞ ሎሌዎቹን ‹‹እኔና ልጄ ወደዚያ ተራራ ሄደን እንሰግዳለን፤ ሰግደንም ወደ እናንተ እንመለሳለን›› አላቸው፡፡ ተነሥተውም ሲጓዙ ይስሐቅ ‹‹አባቴ ሆይ፥ አለ፤ እርሱም፥ ልጄ፥ ምንድን ነው? አለው፤ እሳቱና ዕንጨቱ ይኸው አለ፤  የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት አለ?›› አለው፡፡ አብርሃምም ልጁን ‹‹ልጄ ሆይ፥ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል›› ብሎ መለሰለት፡፡ ከተራራውም ሲደርሱ መሠዊያውን ሠራ፤ ዕንጨቱንም ረበረበ፤ ልጁ ይስሐቅም እርሱ መሥዋዕቱ እንደሆነ ዐወቀ፤ ‹‹አባቴ ስወራጭ እጅህን እንዳላስቆርጥህ እሰረኝ›› አለው፤ አብርሃምም ልጁን አስሮ በመሠዊያው በዕንጨቱ ላይ በጀርባው ሲያስተኛው ‹‹የልጅ ዓይኑ ብክን ብክን ሲል ያሳዝናልና እራርተህና አዝነህ ትተኸኝ ከፈጣሪህ ጋራ እንዳትጣላ ደረቴ አስተኛኝ›› አለው፤ አብርሃምም ልጁን በልቡ አስተኛው፤ እጁን ዘርግቶም ልጁን ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሣቶ አንገቱ ላይ ሊያሳርፍ ሲል እግዚአብሔር አብርሃምን ጠራው፤ ‹‹አብርሃም! አብርሃም አለው፤ እርሱም እነሆኝ አለ፤ በብላቴናው ላይ እጅህን  አትዘርጋ፤ አንዳችም አታድርግብት፤ ለምትወደው ልጅህ ከእኔ አልራራህለትምና አንተ እግዚአብሔር የምትፈራ እንደሆንህ አሁን ዐውቄአለሁ›› አለው፡፡ (ዘፍ.፳፪፥፲፩-፲፪፣ አንድምታ ትርጓሜ ምዕራፍ ፳፪)

አብርሃምም ዓይኖቹን ቀና አድርጎ ሲመለከት ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ የተያዘ በግ ለአብርሃም ወረደለት፤ ያንን በግም በልጁ ፈንታ ሠውቶ ደስ እያለው ተመለሰ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ሲል የመሠዋቱን ምሥጢር ተመልክቷል፤ ይስሐቅም የክርስቶስ ምሳሌ ነውና፡፡ ልጁን በሦስተኛው ቀን በሕይወት አግኝቶታል፤ የባሕርይ አምላክ ክርስቶስም በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ ወደ በመቃብር ወርዶ በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል የተነሣ መሆኑን ያመለክታልና ይህን ምሥጢር እግዚአብሔር አምላክ ለአብርሃም ገለጠለት፡፡ ዕፀ ሳቤቅ እመቤታችን ምሳሌ ናት፤ ቅጠል የበዛበት ሐረግ በመሆኑ የድንግል ማርያም ምስጋናዋ የበዛ ንጽሕናዋና ቅድስናዋ የተለየ  ከነገደ መላእክት በክብር የሚመስላት በጸጋ የሚተካከላት እንደሌለ አመላካች ነው፡፡ በዚህም የእመቤታችንን ክብር ገልጾለታል፡፡ የበጉ ከሰማይ መውረድም የጌታችንን ከሰማይ መውረድ የሚያመለከት ነው፤ አብርሃም የሰዋው አንድ በግ ነው፤ ይህም የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ አንድ ልጁን የመሠዋዕቱ ምሳሌ ነው፤ ስለዚህ አባታችን አብርሃም ይህንን ምሥጢር ለማወቅ ከነቢያት ይቀድማል፡፡ ምክንያቱን ምሥጢሩን ነቢያት በትንቢታቸው የገለጹት ለሕዝቡም በትምህርታቸው ያስታወቁት ከዚህ በኋላ ነው፡፡

አባታችን አብርሃምም ይህንን ሁሉ ምሥጢር ተረድቶና ፈጣሪው እግዚአብሔርን ደስ አሰኝቶ እና አገልግሎ በክብር ዐረፈ፤ እኛንም እያማለደን በሰማይ ቤት ይኖራል፤ ‹‹በምድር የሠሩት በሰማይ ይከተላቸዋል›› እንደተባለው በዚህም ምድር የሠራውን ሥራ በሰማይ እየተገበረው ይገኛል፡፡ ሥራውም እንግዳ መቀበል ስለነበር ዛሬ እኛም ‹‹ከምድር የሚለየቱን ሁሉ በአብርሃም አቅፍ አሳርፍልን›› እያልን እንደምንለው አሁንም እንግዳ እየተቀበለ ይገኛል፡፡ (ራእ.፲፬፥፲፫)

የአብርሃም በረከት ይደርብን፤ እኛም በሰማነው፣ ባየነውና በተረዳነው ሃይማኖታችንን፣ አጽንተን እና ቅዱሳንን መስለን እንድንኖር እግዚአብሔር ይርዳን፤ አሜን፡፡