ነገረ ድኅነት በመጽሐፍ ቅዱስ – ካለፈው የቀጠለ

በዳዊት አብርሃም

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ከዚህ ቀጥለን ደግሞ የጴጥሮስን እና የይሁዳን መልእክት እንመልከታለን፤

  • “ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥ ኃጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ አድርጎ ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን ዐመድ እስኪኾኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ ከፈረደባቸው ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ፥ ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፥ በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል” (፪ኛ ጴጥ. ፪፥፮)፡፡
  • “ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ፦ እነሆ፥ ጌታ በዂሉ ላይ እንዲፈርድ፥ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ዂሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ዂሉ ‹ኃጢአተኞችን ዂሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል› ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ” (ይሁዳ፣ ቍጥር ፲፬-፲፭)፡፡

እነዚህንና ሌሎች ተመሳሳይ ጥቅሶች በብዛት አሉ፡፡ ይህን ዂሉ ከተመለከትን በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አንዲት ቦታ ላይ የጻፋትን አንዲት ጥቅስ ብቻ መዝዘን በመውሰድ ኃጢአትን “የሚያደርጉ ይጸድቃሉ” ወደሚል ስሕተት ከመውደቅ እንጠበቃለን፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ በሌላ ቦታ እንዲህ ሲል አስተምሯልና፤ “ወይስ ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢኾኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝራዎች ወይም ቀራጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌባዎች ወይም ገንዘብ የሚመኙ ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” (፩ኛ ቆሮ. ፮፥፱-፲)፡፡

በአንድ ጥቅስ መመርኮዝ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ አይደለም፡፡ በዚህ መልክ ድምዳሜ ላይ መድረስም ኦርቶዶክሳዊ መንገድ አይደለም፡፡ አንድ ጥቅስ አንሥቶ የኾነ ዐሳብ መሰንዘር የሚፈልግ ሰው ቢያጋጥም ጥቅሱ የቱንም ያህል ግልጽ መልእክት ያለው ቢኾን እንኳን “እንዲህ ለማለት ነው” ተብሎ ለመደምደም አያስችልም፡፡ ኦርቶዶክሳዊ የኾነ ሰውም በተነሣው ርእሰ ጉዳይ ላይ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ምን እንደሚሉ ለማወቅ ይጥራል፡፡ ዐሳቡን የተሟላ የሚያደርጉት በጉዳዩ ላይ ሌሎች የቅዱደሳት መጻሕፍት ክፍሎች ተሟልተው ሲቀርቡ ነው፡፡ ሌሎች ጥቅሶች አንዱን ጥቅስ ግልጽና የማያሻማ እንደዚሁም የተሟላ ያደርጉታል፡፡

ይህንም በሚቀጥሉት ስለ ነገረ ድኅነት ከተጻፉት ጥቅሶች አንጻር እንመልከት፤ “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም” (ኤፌ. ፪፥፰-፱)፡፡ ይህ ኃይለ ቃል መልእክት “ሥራ አያስፈልግም፤ እምነትና ጸጋ ብቻቸውን ለመዳን በቂ ናቸው” የሚል ይመስላል፡፡ ነገር ግን ሳንቸኩል አንድ ቍጥር ወረድ ብለን ንባባችንን ብንቀጥል እንደዚህ የሚል መልእክት እገኛለን፤ “እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን” (ኤፌ. ፪፥፲)፡፡

ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት፤ “በጸጋ ከኾነ ግን ከሥራ መኾኑ ቀርቶአል፤ ጸጋ ያለዚያ ጸጋ መሆኑ ቀርቶአል” (ሮሜ. ፲፩፥፮)፡፡ አሁንም በዚህ ጥቅስ ሳንወሰን በዚያው ምዕራፍ ወረድ ብለን ንባባችንን እንቀጥል፤ “መልካም፤ እነርሱ ከአለማመን የተነሣ ተሰበሩ፤ አንተም ከእምነት የተነሣ ቆመሃል፡፡ ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ፡፡ እግዚአብሔር እንደ ተፈጠሩት ለነበሩት ቅርንጫፎች የራራላቸው ካልኾነ ለአንተ ደግሞ አይራራልህምና፡፡ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፥ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ” (ሮሜ. ፲፩፥፳-፳፪)፡፡

ይህ ማለት ምን ማለት ነው? በክርስቶስ ደም ዂላችንም መዳንን አግኝተናል (ድነናል)፡፡ ኾኖም ከእርሱ ጋር ካልተጣበቅን ማለትም እስከ መጨረሻው ድረስ ከእርሱ ጋር እንድንኖር የሚያደርገንን የጽድቅ ሥራ መሥራት ካልቻልን የመቆረጥ ቅጣት ይደርስብናል፡፡ ከግንዱ ተቆርጦ ዕጣው መድረቅና መጠውለግ እንደ ኾነበት ቅርንጫፍ እንኾናለን፡፡

አሁንም ሦስተኛ ምሳሌ እንጨምር፤ “ትምክህት እንግዲህ ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል፡፡ በየትኛው ሕግ ነው? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፥ በእምነት ሕግ ነው እንጂ። ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቈጥራለንና” (ሮሜ. ፫፥፳፯-፳፰)፡፡ ይህን ጥቅስ ስናነብ “ለመዳን ሥራ አያስፈልግም” ከሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ እንዳንቸኩል ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ወደ ሌላ ቦታ መሔድ ሳያስፈልገን ጥቂት ብቻ ዝቅ ብለን እናንብበው፤ “እንግዲህ ሕግን በእምነት እንሽራለንን? አይደለም፤ ሕግን እናጸናለን እንጂ” (ሮሜ. ፫፥፴፩)፡፡

አራተኛ ምሳሌ “ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚኾነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም” (ቲቶ ፫፥፬-፮)፡፡ ይህ ጥቅስ መዳን የሚገኘው በጥምቀትና በመንፈስ ቅዱስ ሥራ መኾኑን እንደሚገልጥ ልብ እንበል፡፡

ይህም መዳን “በእምነት ብቻ” የሚለውን ኑፋቄ የሚቃወም ዐሳብ ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ሐዋርያው የሥራን አስፈላጊነት ሲገልጥ እንዲህ ይላል፤ “ቃሉ የታመነ ነው፤ እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ፥ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ፡፡ ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው” (ቲቶ ፫፥፰)፡፡

አንድን ጥቅስ አንሥተን ስንናገር ያን ማድረጋችን ለጥቅማችን እንኳን ቢኾን በዚያ በአንዱ ጥቅስ ላይ ብቻ ልንመሠረት አይገባንም፡፡ ለምሳሌ “ጻድቅ እንደ ኾነ ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ዂሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ ዕወቁ” (፩ኛ ዮሐ. ፪፥፳፱) በሚለው ኃይለ ቃል ውስጥ ጽድቅን ማድረግ አስፈላጊ መኾኑ ተገልጧልና “ለመዳን ጽድቅ ማድረግ በቂ ስለ ኾነ እምነት፣ ጥምቀትና ሌሎች ምሥጢራት አያስፈልጉም” ወደሚል ጽንፈኛ አቋም ልንወድቅ አይገባም፡፡

ሐዋርያው በሌላ ቦታ ደግሞ ፍቅር ከሞት ወደ ሕይወት የሚመልሰን መኾኑን ያስተምራል፡፡ “እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ኾንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል” (፩ኛ ዮሐ. ፫፥፲፬)፡፡ በዚህ ጥቅስ ላይ ተመሥርተን ደግሞ “ለመዳን ወንድሞችን መውደድ በቂ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ ብንደርስ አሁንም ልክ አይደለንም፡፡

ሐዋርያው ስለ ፍቅር ታላቅነት ደጋግሞ ሲያስተምር “እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል” በማለት አስተምሯል (፩ኛ ዮሐ. ፬፥፲፮)፡፡ ስለ ፍቅር ለማስተማር ብለን እንኳን ቢኾን በዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ልንመሠረትና ሌላውን ችላ ልንል  አይገባንም፡፡ ለምሳሌ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ፍቅር ሲያስተምር “ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ዂሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” ሲል ፍቅር ከእምነት እንደሚበልጥ ተናግሯል (፩ኛ ቆሮ. ፲፫፥፪)፡፡

በተመሳሳይ መልኩ “እንዲህም ከኾነ፥ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው” በማለት የፍቅርን ታላቅነት አስረድቷል (፩ኛ ቆሮ. ፲፫፥፲፫)፡፡ ስለዚህ “መዳን በእምነት ብቻ” የሚል ሰው እነዚህን ጥቅሶች ምን ሊያደርጋቸው ይችላል? በአንጻሩ በአንድ ጥቅስ ተወስኖ መደምደም የለመደ ሰው የፍቅርን ታላቅነት የሚያወሳውን ጥቅስ በመምዘዝ “መዳን በፍቅር ነው” ብሎ እንዳይስት መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡

ጌታችን ለወጣቱ ባለ ጸጋ “ወደ ሕይወት ልትገባ ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ” (ማቴ. ፲፱፥፲፯) ባለው ላይ ብቻ ተመሥርተን “ለመዳን መንገዱ ይሔ ብቻ ነው” ማለት ትልቅ ስሕተት ነው፡፡ ያለ እምነት የሚፈጸም መልካም ሥራ ብቻውን እንደማያድን አውቀን፣ “ለመዳን ሕግጋትን መጠበቅ ይበቃል” ከሚል ስሕተት ወጥተን፣ እንደዚሁም ስለ እምነትና በጸጋው ስለ መዳን በሚናገሩ አንዳንድ ጥቅሶች ላይ ብቻ ማተኮሩን ትተን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር በትዕግሥትና በጥንቃቄ ማጥናት እንዳንሳሳት ይረዳናል፡፡

ከዚሁ ዂሉ ጋርም “እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይኾን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንኾን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና፤ መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል” የሚለውን የሐዋርያውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል (፪ኛ ቆሮ. ፫፥፮)፡፡

የመዳንን ትምህርት ለመረዳት በፊደል ሳይኾን በመንፈስ ኾነን፣ በአንድ ጥቅስ ላይ ብቻ ሳንወሰን ወይም ጉዳዩን ከአንድ አቅጣጫ ብቻ ሳንመለከት በስፋትና በጥልቀት የኾነውን ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት በማወቅ መጽናት፣ ለሚጠይቁንም ምላሽ መስጠት ያስፈልገናል፡፡ በአንድ ጥቅስ ላይ ተመሥርቶ ነገረ ድኅነትን ለማወቅ መሞከር ከባድ ስሕተት ውስጥ እንደሚጥለን ለማወቅ አንድ ምሳሌ ተመልክተን ጽሑፋችንን እናጠቃልላለን፤

መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ቦታ “የጌታን ስም የሚጠራ ዂሉ ይድናል” ይላል (ሮሜ. ፲፥፲፮)፡፡ ይህን ጥቅስ መሠረት አድርገን “የጌታን ስም ስለ ጠራን ብቻ እንድናለን” ብለን ብናስብ ከሚከተለው ጥቅስ ጋር እንጋጫለን፤ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ዂሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” (ማቴ. ፯፥፳፩)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡